Saturday, 22 December 2018 08:03

በሳምንቱ ውስጥ በግጭትና በጥቃት 23 ሰዎች ተገድለዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

•    መከላከያ ሰራዊት የተጠናከረ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስታውቋል
 
በሞያሌ በቤኒሻንጉልና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች በግጭትና በጥቃት በሳምንት ውስጥ ከ23 በላይ ዜጎች የሞቱ ሲሆን የሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ ህግ ለማስከበር አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስታውቋል፡፡
ከኬንያ ጋር አዋሳኝ በሆነችውና በተደጋጋሚ የቀውስ ቀጠና ሆና የዘለቀችው ሞያሌ ከተማ ባለፈው ማክሰኞ በበቀለ ሞላ ሆቴል  በስብሰባ ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ በተከፈተ ተኩስ ቢያንስ 13 ያህል መገደላቸውን ምንጮች ያመለከቱ ሲሆን በርካቶች ወደ ጎረቤት ኬንያ እንደተሰደዱም ተጠቁሟል፡፡
ከጥቃቱ በኋላ የመከላከያ ሰራዊት ከተማዋን መቆጣጠሩን የሚገልፁት የአካባቢው ምንጮች፤ አሁንም አለመረጋጋቱ እንደቀጠለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከጥቂት ሳምንት በፊት በአካባቢው በተፈጠረ የእርስ በእርስ ግጭት 21 ሰዎች መገደላቸውና 61 የሚሆኑት በፅኑ መቁሰላቸውንም ምንጮች አስታውሰዋል፡፡
ለ “አፍሪካን ሞኒተር” አስተያየታቸውን የሰጡ አንድ የአካባቢው ነዋሪ፤ በሞያሌ ያለው ሁኔታ ከእለት ወደ እለት አስጊ እየሆነ ነው፤ የፌደራል መንግስት የመጨረሻ የሚለውን እልባት መስጠት አለበት ብለዋል፡፡
ባለፉት 10 ወራት ውስጥ በሞያሌ ከተማ ካጋጠሙ ተመሳሳይ ጥቃትና ግጭቶች ጋር በተያያዘ ከአካባቢው ተሰድደው ኬንያ የሚገኙ ስደተኞች ቁጥር ከ5 ሺህ መላቁን ሪፖርቶች አመልክተዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል አዋሳኝ፣ ልዩ ስሙ ቶንጎ ጉሬ በተባለ አካባቢ ተሳፋሪዎች ጭኖ ሲጓዝ በነበረ ሚኒባስ ላይ መንገድ ላይ የተቀበረ ፈንጅ ፈንድቶ የ10 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተዘግቧል፡፡ አደጋ ያደረሰው ፈንጂ በማን እና ለምን እንደተቀበረ የፀጥታ ኃይሎች በማጣራት ላይ መሆናቸውም ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከተፈጠሩ ቀውሶች ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ በኦሮሚያ ምዕራብ ወለጋና ቤኒሻንጉል አካባቢ የተፈናቀሉትን ጨምሮ በአማራ ክልል ተጠልለው የሚገኙ ዜጎች ቁጥር 37 ሺህ መድረሱን የክልሉ መንግስት አስታውቋል፡፡
የክልሉ መንግስት 28 ሚሊዮን ብር የፌደራሉ መንግስት 8 ሚሊዮን ብር በድምሩ 36 ሚሊዮን ብር ለተረጂዎች ተመድቦ፣ የእለት ደራሽና የህክምና እርዳታ እየተደረገ መሆኑም ታውቋል፡፡
በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በዚህ መልኩ የሰው ህይወት እየቀጠፉ ያሉ እና ሺዎችን ከቀያቸው የሚያፈናቅሉ ግጭቶችንና ጥቃቶችን ለማስቆም የሃገር መከላከያ ሰራዊት ከረቡዕ ታህሳስ 10 ቀን 2011 ጀምሮ ችግሮቹ በተከሰቱባቸው አካባቢዎች በማያዳግም መልኩ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስታውቋል፡፡
ሃገሪቱ እየተከተለች ባለው ሁሉን አቀፍ ሃገራዊ ለውጥ በትጥቅ ሲታገሉ የነበሩ ኃይሎች ለውጡን ተከትሎ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ ሃገር ውስጥ መግባታቸውን ያስታወሰው የሃገር መከላከያ መግለጫ፤ “ይሁን እንጂ መንግስት የዲሞክራሲውን ምህዳር ለማስፋት በሚያደርገው ሆደ ሰፊነትና ታጋሽነት፣ አንዳንዶች መንግስት አልባ እየመሰላቸው አንዳንዶች ደግሞ ተመልሶ ወደ ስልጣን ለመውጣት በሚያደርጉት ህገ ወጥ እንቅስቃሴ የዜጎች ሰላም እየደፈረሰ፣ አላስፈላጊ መስዋዕትነት እየተከፈለ ነው” ብሏል፡፡
“ይህን ስርአት አልበኝነት መንግስት ከእንግዲህ በቀላሉ አያየውም” ያለው መግለጫው፤ “መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ከምንግዜውም በበለጠ በቁርጠኝነት እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል” ብሏል፡፡ ይህ እርምጃም ከረቡዕ ጀምሮ እየተወሰደ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል፡፡  


Read 2688 times