Saturday, 22 December 2018 08:03

በትምባሆና በአልኮል መጠጦች ማስታወቂያ ላይ ገደብ ላይ ገደብ ሊጣል ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

-    የሺሻ ምርትን ማምረትት ማስመጣት፣ መሸጥ፣ ማስጨስ የተከለከለ ነው
-    ቢራን ጨምሮ ማንኛውንም የአልኮል መጠጥ ማስታወቂያዎች ማስተዋወቅ የሚቻለው ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ድረስ ብቻ ነው
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትምባሆና በአልኮል መጠጦች ማስታወቂያዎች ላይ ገደቦችን ለመጣል በወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ እየመከረ ነው፡፡
ምክር ቤቱ ሰሞኑን ለውይይት ባቀረበውና የምክር ቤቱ አባላት በስፋት እየተወያዩበት በሚገኘው በዚሁ ረቂቅ አዋጅ ላይ እንደተገለፀው፤ ማንኛውንም የአልኮል መጠጥ በህዝብ መሰብሰቢያና መገልገያ ቦታ፣ በስፖርት ማዘውተሪያ፣ በአውራ ጐዳና ላይ፣ በጋራ የመኖሪያ ቤቶችና በመሰል ቦታዎች ላይ ማስተዋወቅ አይቻልም፡፡
ማንኛውም የአልኮል ይዘቱ ከ10% በላይ የሆነ አልኮል አምራች፣ አስመጪ ወይም አከፋፋይ የህዝብና የመንግስት በዓላትና ስብሰባዎችን፣ የንግድ ትርኢቶችን፣ የስፖርት ውድድሮችን፣ የትምህርት ቤት ዝግጅቶችን እንዲሁም ወጣቶች የሚሳተፉባቸውን ፕሮግራሞች በቀጥታ ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ስፖንሰር ማድረግ አይችሉም፡፡
ቢራን ጨምሮ የአልኮል ይዘቱ ከ10%  በታች የሆነ አልኮል በብሮድካስት አማካኝነት ማስተዋወቅ የሚቻለው ከምሽቱ 3 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ እንደ ረቂቅ ህጉ፤ የአልኮል መጠጥ የሚተዋወቅበት ወይም ፕሮሞት የሚደረግበት ጊዜ፣ ቦታና ሁኔታን በሚመለከት፣ አዋጁን ለማስፈፀም በሚወጣው ደንብ መሰረት ተጨማሪ ገደብ ሊጣል ይችላል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰሞኑን ያፀድቀዋል ተብሎ በሚጠበቀው በዚሁ ረቂቅ አዋጅ ላይ እንደተገለፀው፤ በፋብሪካ ደረጃ ተዘጋጅቶ ለህብረተሰቡ የሚቀርብ ማንኛውም የአልኮል መጠጥ፤ የአልኮል መጠኑን በመግለጽ በተገቢ መንገድ ካልተጠቀሙት የጤና ችግር እንደሚያስከትል እንዲሁም አልኮል መጠጣት ጽንስን ሊጐዳ እንደሚችል የሚያስረዳ ገላጭ ጽሑፍ በጠርሙሱ ላይ በጉልህ በሚታይ ሁኔታ ሊሰፍር ይገባል፡፡
የመገናኛ ብዙሃን ባለቤቶች ወይንም የማስታወቂያ አሰራጭና አስነጋሪዎች፤ አዋጁ የሚያወጣውን ደንብና መመሪያ ማክበር ግዴታ ያለባቸው መሆኑን የደነገገው ረቂቅ አዋጁ፤ አዋጁን በማያከብሩ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ጥብቅና የማያዳግም እንደሆነ አመልክቷል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ ረቂቅ አዋጁ በተለያዩ የትምባሆ ምርቶች ላይ የማስታወቂያና የስፖንሰርሺፕ ገደብ ጥሏል፡፡ በዚሁ መሰረትም ማንኛውንም የትምባሆ ምርት ማስተዋወቅ፣ ስፖንሰር ማድረግና ምርቱን በተለያዩ መንገዶች ፕሮሞት ማድረግ የተከለከለ ነው፡፡ በትምባሆ ምርቶች ላይም ተጨማሪ ግብር ይጣላል፡፡
በተያያዘ ሁኔታም፤ የሺሻ ምርትን ማምረት፣ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት፣ ማከማቸት፣ ማከፋፈል፣ ለሽያጭ ማቅረብ፣ ማስጨስ በህግ የተከለከለና ምንም አይነት ፈቃድ የማይሰጠው ተግባር ነው በረቂቅ አዋጁ
፡፡አዋጁ ክልከላ የጣለባቸውን ምርቶች በተለያዩ መንገዶች ያስተዋወቀ፣ እንዲተዋወቅ ያደረገ፣ ያስነገረ የሚዲያ ተቋምና ግለሰብ የእስራትና የገንዘብ ቅጣት እንደሚጣልበትም ረቂቅ ህጉ አመልክቷል፡፡ በዚሁ ረቂቅ አዋጅ ላይ የተወካዮች ምክር ቤት እየመከረ ሲሆን ሰሞኑን ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡






Read 3568 times