Saturday, 15 December 2018 16:28

የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ አረፉ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

*የቀብር ሥነሥርዓታቸው የፊታችን ረቡዕ  ይከናወናል
ከቀዳማዊ ንጉስ ሃይለሥላሴ ዘመን ጀምሮ ረዥም ዕድሜያቸውን በተለያዩ የመንግስት ሃላፊነት ያገለገሉትና በአሁኑ የኢህአዴግ መንግስት ለ12 ዓመታት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት መቶ አለቃ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፤ባደረባቸው ህመም በጦር ሃይሎች ሆስፒታል  ህክምና ሲከታተሉ ቆይተው፣ በ94 ዓመት ዕድሜያቸው ትላንት ሌሊት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው የፊታችን ረቡዕ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤ/ክርስቲያን የሚፈጸም ሲሆን የአንድ ቀን ሃዘን እንደሚታወጅም ታውቋል፡፡   
በንጉሱ ዘመን፣ በኤርትራ የሲቪል አቬሽን ሃላፊ በመሆን የመንግስት ሥራቸውን የጀመሩት መቶ አለቃ ግርማ፤ ከ3 ዓመት በኋላም የኢትዮጵያ ሲቪል አቬሽን ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሾመዋል፡፡ ለሁለት ዓመትም የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዋና ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል፡፡ የፓርላማ አባልም ነበሩ፡፡ የደርግ መንግስት ከወደቀ በኋላ ሥልጣን በተቆጣጠረው ኢህአዴግ  መንግስት ለመመስረትና አዲስ ህገመንግስት ለመቅረጽ በተደረገ ስብሰባ ላይ ተጋብዘው ነበር፡፡
 በ77 ዓመት ዕድሜያቸው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙት መቶ አለቃ ግርማ፤ለሁለት የሥልጣን ዘመን - ለ12 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ቀጥተኛና ግልጽ ባህርያቸው እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋችነታቸው በህዝብ ዘንድ ተወዳጅነትን እንዳተረፈላቸው  የሚነገርላቸው የእድሜ ባለጸጋው፤ እ.ኤ.አ በ1991 ዓ.ም ለም ኢትዮጵያ የተባለ የአካባቢ ጥበቃ ማህበር አቋቁመው፣ በደን ልማትና በረሃነትን በመከላከል ዘመቻ ላይ በንቃት ተሳትፈዋል፡፡
መቶ አለቃ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ፤ ለ20 ዓመት ገደማ በግጭትና በጦርነት የዘለቁትን ኢትዮጵያና ኤርትራን ለማስታረቅ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን ህልማቸው ከጥቂት ወራት በፊት በጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግስት፣ እውን ሆኖ በዓይናቸው ለመመልከት ታድለዋል፡፡ የቀድሞው ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ፤ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት ነበሩ፡፡  


Read 7253 times