Saturday, 15 December 2018 14:54

“ኢትዮጵያ ልትጠብ ትችላለች እንጂ መቼም አትጠፋም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 ከ30 ዓመት በኋላ ለአገሩ የበቃው የራዲዮ ጋዜጠኛው

     የተወለደው አዲስ አበባ ነው፡፡ ከዚያም ነፃ የትምህርት እድል በማግኘት ወደ ሶቪየት ህብረት አምርቶ፣ ጐርኪ የስነጽሑፍ ኢንስቲቲዩትን ተቀላቀለ፡፡ እስካሁን በታዋቂው ጐርኪ የስነጽሑፍ ኢንስቲቲዩት የተማሩ ኢትዮጵያውያን ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሣና የዛሬው እንግዳችን ናቸው፡፡ ሩሲያኛ አቀላጥፎ ይናገራል፣ ያነባል፣ ይጽፋል፡፡ የፑሽኪን ድርሰቶችን ከሩሲያኛ ወደ አማርኛ መልሷል፡፡ ለህትመት ባይበቃም፡፡ ከ32 አመታት በኋላ ሰሞኑን ወደ ሀገሩ የተመለሰው አንጋፋው የዩኒቨርስቲ መምህርና ጋዜጠኛ ደምስ በለጠ፤ ለረዥም ዓመታት የኖረው በአሜሪካ ነው፡፡ በእነዚህ የስደት ዓመታት፣ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በነበረው የፖለቲካ ልዩነት ሳቢያ በሞት የተለዩትን ወንድሞቹን እንኳ በአካል ተገኝቶ መቅበር እንዳልቻለ ያስታውሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት የ“አማራ ድምጽ ራዲዮ” ዋና አዘጋጅ ሲሆን የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የኢንተርኔት ራዲዮ ባለቤትም ነበር፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ ጋዜጠኛ ደምስ በለጠን አግኝቶ፣ በአማራ የህልውና ጥያቄዎችና በሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ አነጋግሮታል፡፡


    ከ32 ዓመታት በኋላ ወደ ሀገር ቤት መመለስ ምን ስሜት ይፈጥራል?
አሁን የሚሠማኝን ለመግለጽ ይቸግረኛል፤ ምክንያቱም ብዙ ለውጦች አሉ፡፡ የለውጦቹን መሠረታዊ ነገር ገና አልተረዳሁም፡፡ ከመጣሁ ገና ሣምንቴ ነው፡፡ ያለውን ጊዜ ከቤተሰቤ ጋር ነው ለማሳለፍ የሞከርኩት፡፡ እግዚአብሔር ለእናቴ ረጅም እድሜ ሰጥቶ እግዚአብሔር ስላቆያት፣ ከሷ ጋር ትንሽ ጊዜ ላሳልፍ ብዬ ነው ያልተንቀሳቀስኩት፡፡ በእርግጥ ሀገር ውስጥ እኔ ከ30 አመት በፊት ከማውቃቸው ብዙ የተለዩ ነገሮች እንዳሉ ተረድቻለሁ፡፡ ሌላውን ደግሞ በቀጣይ ጊዜያት ለማየት እሞክራለሁ፡፡
አዲስ አበባንስ እንዴት አገኘሃት?
ብዙ ለውጥ አለ፡፡ በጣም የገረመኝ ግን የሰው ቁጥር መብዛቱ ነው፡፡ ያልጠበቅሁት ነው፡፡ ከሚገመተው በላይ የሰው ቁጥር በዝቷል፡፡ የትራፊክ ፍሰቱም “የቀደመ ይግባ” አይነት ነው፡፡ ህግና ስርዓት የለም። በሌላ በኩል ሰዎች ስራ መስራት ጀምረዋል፡፡ የስራ ትጋቱ ጨምሯል፡፡
ለትምህርት ሶቭየት ህብረት ሳለህ፣ ተማሪዎችን አሳምፃችሁ ነበር ይባላል፡፡ ስለሱ ብታጫውተን?
የዚያን ጊዜ የደርግ መንግስት የፓርቲ ሰዎች በትምህርት ቤት ውስጥ ነበሩ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እኛ “ነፃ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ህብረት” ብለን በህቡዕ ተቋቁመን ነበር፡፡ እዚያው እያለን የመንግስት ለውጥ መጣ፡፡ ለዚያ ለውጥ ደግሞ የኛም አስተዋጽኦ ነበረበት። የረሃብ አድማ አድርገን በደርግ ላይ ያለንን ተቃውሞ አሰምተናል፡፡ ያንን የረሃብ አድማ ያስተባበርኩት ደግሞ እኔ ነበርኩ፡፡ በወቅቱ ብዙዎቻችን የሀገር መገንጠልን አንደግፍም ነበር፡፡ የኤርትራ መገንጠልን ጉዳይ በሰፊው እንቃወም ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ በወቅቱ በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ከነበሩት ካሣ ገ/ህይወት ጋር ተጋጭተናል፡፡ የኛ ተቃውሞና አድማ በሞስኮ ሬዲዮ ይዘገብ ነበር፡፡ አድማውን ያደረግነው የራሳችን ግዛት በነበረው የኤምባሲ ቅጥር ግቢ ውስጥ ስለነበር፣ የሞስኮ ፖሊሶች እኛን መንካት አይችሉም ነበር፡፡
በኋላ ግን ቅጣት ተጥሎባችሁ ነበር አይደል?
አዎ፤ ከአድማው በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ተማሪዎች፣ የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባቸዋል፡፡ ትምህርታቸውን ጨርሰው ወደ ሀገር ቤት ለመግባት የፈለጉ፣ ያው በኢህአዴግን ሰዎች የቅጣት ገንዘብ ከፍለው እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ ምን ያህል እንደነበረ ባላውቅም፣ ወደ አገር ቤት የተመለሱ ተማሪዎች፤ ይህ መፈፀሙን ነግረውኛል፡፡ እኔ ወደ ሀገር ቤት ስላልተመለስኩ፤ስለ አከፋፈሉ ብዙ አላውቅም፡፡
እዚያው ሞስኮ ቀረህ ማለት ነው?
አዎ፤የሞስኮ ራዲዮ ላይ መስራት ጀመርኩ፡፡ የስነጽሑፍ ተማሪ ስለነበርኩ፣ በአማርኛው ክፍል ጊዜ ተቀጥሬ፣ እ.ኤ.አ እስከ 1996 ዓ.ም ድረስ ሠርቻለሁ። በንጉሡ ዘመን የተጀመረውንና ታሪካዊውን የሞስኮ ራዲዮ የአማርኛ ፕሮግራም ዘግቼ የወጣሁትም እኔ ነበርኩ ማለት ይቻላል፡፡
የሞስኮ ራዲዮ የአማርኛ ፕሮግራም የተከፈተበት ዓላማ ምን ነበር?
ያው የአሜሪካ ድምጽና የጀርመን ድምጽ አይነት ነው፡፡ ሶቪየት ህብረት አላማዋን የምታሠርጽበት ጣቢያ ነበር፡፡ በኋላ አማርኛ ቋንቋና ሌሎች በርካታ ቋንቋዎች የተቀነሱት በሩሲያ መንግስት ውሣኔ ነው። እሱ ሊዘጋ እኔ ወደ አሜሪካ አቀናሁ፡፡ አሜሪካም እንግዲህ በጋዜጠኝነት ስራ ነው የቀጠልኩት፡፡ “አንድ ኢትዮጵያ” የተባለ የማህበረሰብ ራዲዮ ላይ ነው መስራት የጀመርኩት፡፡ በኋላ “ሃገር ፍቅር ራዲዮ” ላይም ሰርቻለሁ፡፡ ከዚያም “ንጋት ራዲዮን” አቋቋምኩ። “ንጋት ራዲዮ” የኢንተርኔት ራዲዮ ነው፡፡ በመላው አለም የሚሠማ  ነበር፡፡ የመጀመሪያው በአማርኛ የሚተላለፍ የኢንተርኔት ራዲዮ ነበር፡፡ ዓላማው ደግሞ  የህዝብ ልሣን ለመሆን ነው፡፡ በእርግጥም በዓላማው ብዙ ሠርቷል፡፡
የንጋት ራዲዮ አሁን ለምን ተቋረጠ?
እኔ ወደ ኤርትራ ሄድኩ፡፡ ራዲዮውን የሚመራ አልነበረም፤ ስለዚህ ተቋርጧል፡፡
አሁን በአሜሪካ ምን እየሰራህ ነው?
የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ነኝ፡፡ ከዚያ ጐን ለጐን ደግሞ “የአማራ ድምጽ ራዲዮ” ላይ በዋና አዘጋጅነት እየሠራሁ እገኛለሁ፡፡ “የአማራ ድምጽ ራዲዮ” የተቋቋመው፣ ለአማራ ተቆርቋሪ በሆነው “ሞረሽ ወገኔ” የአማራ ድርጅት ነው፡፡ እኔ “የሞረሽ” አባል አይደለሁም፡፡ ግን የራዲዮውን አላማ ተቀብዬ፣ የጋዜጠኝነት ሙያ ነፃነቴን ጠብቄ ነው የምሠራው፡፡
ራዲዮው በባህሪው የአማራውን ጉዳይ እየተከታተለ ይዘግባል፡፡ የአማራው ጥያቄ የህልውና ጥያቄ ነው፡፡ በፖለቲካ ትግል ማኒፌስቶው፣ አማራውን ጠላት አድርጐ ፈርጆ ሲንቀሳቀስ የነበረው፣ በኋላም ማኒፌስቶውን በህገ መንግስቱ አጽንቶ፣ ሀገር ሲመራ የነበረው መንግስት፤ በአማራው ላይ መጠነ ሰፊ የማጥፋት ዘመቻ ፈጽሟል፡፡ ከዚህ አንፃር ነው የአማራው ትግል የመኖርና ያለመኖር፣ የህልውና ጥያቄ የሚሆነው፡፡ ራዲዮውም በዚህ አላማ ነው የሚሠራው።
በአማራው ላይ ደርሷል ለሚባለው መጠነ ሰፊ ጥቃት ማስረጃው ምንድን ነው?
ብዙ ማስረጃ አለ፡፡ በገሃድ ግልጽ ማፈናቀል ሲፈፀምበት ነበር፡፡ ይሄ የታቀደ፣ የተቀነባበረ ማፈናቀልና ግድያ ነው፡፡ ዘሩን እንዳይተካ በመርፌ ተወግቷል፡፡
ተጨባጭ ማስረጃዎችን ልትጠቅስልኝ ትችላለህ?
ተጨባጭ ማስረጃዎች አሉን፡፡ የአማራ የህክምና ባለሙያዎች ማህበር ያደረገው ጥናት አለ፡፡ ያ የጥናት ሰነድ በእጃችን ላይ ነው፡፡ “ሞረሽም” ያስጠናው ጥናት አለ፡፡ ዝም ብለን በባዶ የምንናገረው አይደለም፡፡ በቂ ተጨባጭ ማስረጃ አለን፡፡ ራሱ በመንግስት ፓርላማ ውስጥ 2.4 ሚሊዮን ህዝብ መጥፋቱ ተገልጿል። አማራዎች በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ክፍለ ሀገሮች፣ከሌሎች ወንድሞቻቸው ጋር ተጋብተው ይኖራሉ፡፡ ግን በፌደራል መንግስቱ የውክልና መብት የላቸውም፡፡ ይሄ የህልውና ጥያቄ ነው። ክልል ተብሎ በተሰጣቸው ቦታ እንኳ የራሣቸው ተወካይ የላቸውም። በሌላው ክልል የራሱ ተወላጅ እንዲያስተዳድር ነው የተወሰነው፡፡ ወደ አማራ ክልል ስንመጣ፣ የወረዳ ሊቀመንበር አማራ ላይሆን ይችላል፡፡ በሌላው ክልል ግን አማራ እንኳን ስልጣን ሊኖረው፣ ህልውናው በስጋት የተሞላ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሁሉንም ክልል ህገ መንግስቶች መመልከት በቂ ነው፡፡ የትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል፣ ደቡብ ክልልና የአማራ ክልልን ህገመንግስት በአንድ ጠረጴዛ ላይ አስቀምጠን እንመልከታቸው፡፡ የኦሮሚያ ክልል፤ መምራት የሚችሉት የኦሮሞ ተወላጆች ብቻ ናቸው ይላል፡፡ የትግራይም ለትግራይ ተወላጆች ብቻ ነው የሚለው፡፡ ወደ አማራ ክልል ሲመጣ ግን ጉዳዩ ሌላ ነው፡፡ የሁሉም ተወካይ እንዲመራ ነው የተመቻቸው፡፡ ይሄን መመልከቱ በቂ ነው፡፡
“የአማራ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ” ዋነኛ አላማና ግቡ ምንድን ነው?
የአማራው ብሔርተኝነት ማለት ይቸግረናል፡፡ ጉዳዩ የአማራው የህልውና ትግል ነው፡፡ ብሔርተኛ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ሲቋቋሙ ያለውን አንድምታ፣ ከዚህ አንፃር ማየት አለብን፡፡ ህወኃት ሲቋቋም ትግራይን ከኢትዮጵያ እገነጥላለሁ ብሎ ነው፡፡ ኦነግ ሲቋቋም የኦሮሞን ህዝብ ከኢትዮጵያ ነፃ አወጣለሁ ብሎ ነው፡፡ ኦብነግ ሲቋቋም የሶማሌን ህዝብ ከኢትዮጵያ ነፃ አወጣለሁ ብሎ ነው፡፡ ወደ አማራው ስንመጣ ግን ጥያቄው በዚህ ደረጃ የሚቀመጥ አይደለም፡፡ የአማራ፣ ጥያቄ የህልውና ጥያቄ ብቻ ነው። ከኢትዮጵያ የመገንጠል ጥያቄ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ እና አማራ፣ አማራ እና ኢትዮጵያዊነት፤አንድ አይነት ገጽታዎች ናቸው፡፡ ማንም አማራ በኢትዮጵያዊነቱ ጥርጣሬ የለውም፡፡ ስለዚህ ጥያቄው የህልውና ነው። ሌሎቹ ብሔርተኛ ድርጅቶች መነሻ አላማቸው ሌላ ነው፡፡ አማራው ግን የሚገባውን ቁመና አላገኘም፡፡ መብቱ አልተከበረም፡፡ ዘሩ እንዲጠፋ ተደርጓል፡፡ ይሄ መብቱ እስኪከበር፣ አማራ የህልውና ትግል ያደርጋል፡፡
የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙት እንዴት ነው?
መብትን ማክበር ነው፡፡ ህገ መንግሥቱ ላይ መሰራት አለበት፡፡ ህገ መንግስቱ ላይ ተሰርቶ መብትን ማክበር ከተጀመረ፣ የህዝቡ ጥያቄ በአንዴም ባይሆን በሂደት ምላሽ ያገኛል፡፡ ጊዜውን ጠብቆ ይፈታል፤ የሚል እምነት አለኝ፡፡
ክልሉን ለ27 ዓመት ሲመራ የቆየው ብአዴን፣ ስያሜውን ወደ አዴፓ ቀይሮ፣ በለውጥ ሂደት ውስጥ መሆኑን አስታውቋል፡፡ አዴፓ የአማራ ህዝብ ጥያቄዎችን ምላሽ የመስጠት ብቃት አለው ብለህ ታምናለህ?
ማንም ሰው ከኦህዴድ የለውጥ ኃይሉ ዶ/ር ዐቢይ ይወጣል ብሎ አስቦ አያውቅም፡፡ ስለዚህ ከኢዴፓ ጠንካራ የለውጥ ኃይል አይወጣም ማለት አይቻልም፡፡ ከእነሱ ውስጥ ምናልባት የነበረውን ስርአት ሲያገለግሉ የነበሩ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ግን ድርጅቱ ከጊዜው አንፃር ራሱን እያስተካከለ፣የህዝቡን ጥያቄ ሊመልስ የሚችልበት እድል አለ፡፡ አሁን ባለው ሀኔታ እገሌ ይችላል አይችልም ከሚለው ወጥተን፣ በጋራ መቆምና መታገል የሚገባበት ጊዜ ነው፡፡
ህወሓት በሚያስተዳድረው የትግራይ ክልል፣ህገ መንግስቱ ይከበር የሚሉ ሰላማዊ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው፡፡ በዚህ ላይ  አስተያየትህ ምንድን ነው?
ራሴን ምሳሌ አድርጌ አንድ ነገር ልናገር፡፡ በደርግ ጊዜ እኔ ተማሪ ነበርኩ፡፡ በወቅቱ በቀበሌ በኩል ሰልፍ እንድትወጣ ትገደዳለህ፡፡ በቀበሌ ሰልፍ ካልወጣህ፣ ከቀበሌ የምታገኛቸውን ራሽን እንዳታገኝ ትደረጋለህ፡፡ ይሄን ታሪክ ስለማውቅ፣ ህውሓት ከዚህ የተለየ ያደርጋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ፣ የትግራይ ህዝብ፣ ለኢትዮጵያ አንድነት ተሟግቷል፣ ለዳር ድንበሯ መከበር ተዋድቋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን የትግራይ ህዝብ በህውሓት ታፍኖ ነው ያለው፡፡ ቀጣዩን ሂደት ግን ብዙ ሳንርቅ የምናየው ይሆናል፡፡ የመገንጠል እሳቤ ሲቀነቀን እንሰማለን፡፡ እባብ ያየ በልጥ ይደናበራል እንደሚባለው፣ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተገንጥላ፣ዛሬ ያለችበትን ሁኔታ  በአይኔ አይቻለሁ፡፡ በትግራይ መገንጠል ቢኖር ከዚያ በባሰ ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል ጥርጥር የለኝም፡፡ ይሄን ማስተዋል የሚችሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
በአማራና በትግራይ ክልሎች የፖለቲካ ልሂቃን መካከል ያለው መካረር እንዴት ሊረግብ ይችላል?
እኔ በሁለቱም በኩል ያለውን ነገር በእኩል ሚዛን አልመለከተውም፡፡ “የትግራይ ህልውና በአማራ መቃብር ላይ ነው የሚሆነው” የሚል ማኒፌስቶ ቀርፆ የተነሳ ድርጅትና ትግራይን እንደ ጠላት የማያይ እንቅስቃሴ፣ በአንድ ዐይን ማየት ስህተት ነው፡፡ በአማራው ውስጥ አሁንም ያለው የአንድነት መንፈስ ነው፡፡ ከፖለቲካ ልሂቃኑ ባሻገር በጉዳዩ ላይ እስካሁን የህዝቡን ድምፅ መች ሰማነው? የኢትዮጵያ ህዝብ በታሪኩ የተደመጠበት ጊዜ የለም፡፡ ያ ሁሉ በአማራና በኦሮሞ መካከል ሲነዛ በነበረ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ላይ ህዝቡ መች ሃሳብ ተጠየቀ? መች ድምፁን አሰማ፡፡ ነገር ግን ያ ማህበረሰብ በአጭር ጊዜ ውስጥ አንድነቱን ሲያፀና አይተነዋል፡፡ የተወሰኑ ሰዎች አላማና ግባቸውን ስለሚያራግቡ እንጂ ህዝቡ መች ተደምጦ ያውቃል? ህዝቢ ሲደመጥና ጉዳዩ ለህዝብ ሲተው፣ አሁን ያለው ችግር ተፈትቶ፣ መልካም ነገር እንደሚመጣ አልጠራጠርም፡፡
አሁን ለውጥ መጥቷል ብዬ አስባለሁ፡፡ ከ32 ዓመት በኋላ እዚህ መገኘቴ በራሱ ለውጥ ነው፣ በተለይ ለኔ፡፡ ዛሬ ያለምንም ፍርሃትና ስጋት፣ የማስበውን እየተናገርኩ ነው፡፡ ይሄ ሲጠየቅ የነበረ መብት ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ግን ማህበረሰቡ የጠየቃቸው ሁሉ ተመልሰዋል ወይ ከሆነ ጥያቄው፣ አልተመለሱም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከተመረጡ አንስቶ እስካሁን ያለው ጊዜ በጣም አጭር ነው፡፡ ፋታ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በእርጋታ ነው ጥያቄዎች መመለስ ያለባቸው፡፡ እኔ ወደ ሃገር ቤት ከገባሁ በኋላ በሚዲያ ማቋቋም ጉዳይ ወደ ሚመለከታቸው ቢሮዎች ባቀናሁ ጊዜ ያስተዋልኩት፣ ቀናነቱ እየመጣ መሆኑን ነው፡፡ ሌላው የቢሮክራሲ ጉዳይ በጊዜ ሂደት የሚመለስ ይሆናል፡፡ በምርጫ ቦርድ የብርቱካን ሚደቅሳ ወደ ሰብሳቢነት መምጣትን ማን ጠበቀው? ወ/ት ብርቱካን የህግ ሰው ናት፣ ዋጋ ከፍላበታለች፣ለዚህ ቦታ ከሷ የተለየ ሚዛን ኖሮት የሚቀርብ የለም፡፡ ጥሩ ምርጫ ነች፡፡ ተቋሙን ግን በሂደት ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ወ/ት ብርቱካንን እንደ መሾም ቀላል አይሆንም፡፡ በጥልቀት ጊዜ ተወስዶበት ነው መሰራት ያለበት፡፡
ከፓርቲዎቹ ብዛት፣ ከጊዜው ማጠርና ከፖለቲካዊ አለመረጋገት አንጻር፣ በቀሩት ጊዜያት ውስጥ በአገራችን ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማድረግ ይቻላል ይላሉ?
 ፓርቲዎቹ አሁን ካላቸው ቁመና አንፃር፣ በአንድ ዓመት ተኩል ውስጥ በቂ ተፎካካሪ ይሆናሉ ብዬ አላምንም፡፡ ምናልባትም የምርጫውን ጊዜ አራዝሞ እንዲጠናከሩ ማድረግ ይጠበቅ ይሆናል፡፡ በቂ መዋቅር ባለው ገዥ ፓርቲና ደካማ ተፎካካሪዎች ባሉበት፤ጥሩ ምርጫ ማድረግ ይቻላል ማለት የማይታሰብ ነው። ምርጫው ለተወሰነ ጊዜ መራዘም አለበት ብዬም አምናለሁ፡፡ ምርጫው ከተራዘመ ጥሩ ቁመና ገንብተው፣ እውነተኛ ተፎካካሪ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
የጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፣ የለውጥ እርምጃዎችን  እንዴት ታያቸዋለህ? ምንስ ተስፋ ታደርጋለህ?
እስካሁን ያደረጓቸውን እንቅስቃሴዎች በበጎ ነው የማየው፡፡ ገና ቃለ መሃላውን ሲፈፅሙ ነው በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ መሰረት አድርገው፣ ንግግራቸውን የጀመሩት። በእርግጥ የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነቱ ላይ ጥርጣሬ የነበረው አይደለም፤ ነገር ግን ለፖለቲካ ስልጣንና ሰዎች ስልጣናቸውን ለማቆየት ሲባል የተበተቧቸው ሴራዎች ነበሩ፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ያንን ሴራ በጣጥሰው ነው የወጡት፡፡ ማዳመጥ የሚችሉ መሪ ናቸው፡፡ በእሳቸው ሁሉም ሃሳቦች ላልስማማ እችላለሁ፤ ነገር ግን አካሄዱን በበጎ ነው የማየው፡፡ የሚሰሩትን ነገሮች እያበረታታን መሄድ ነው ያለብን፡፡
ኢትዮጵያዊነት ላንተ ምንድነው?
ኢትዮጵያዊነትም ብሄርተኝነት ነው፡፡ እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ የኖርኩትም ያደግሁትም በኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ ነኝ። ኢትዮጵያዊነት ከሁሉም ነገር ይበልጣል፡፡ ነገር ግን በኔ ውስጥ የህልውና ጥያቄ አለ፡፡ ህልውናዬ ሲኖር ነው ኢትዮጵያዊነቴ የሚኖረው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ምንድን ነው ካልከኝ ግን ለኔ ሁለመናዬ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ማለት ለኔ ያሳደገኝ ማህበረሰብ፣ በዙሪያዬ ያሉ ሰዎች፣ ዛፉ፣ ወንዙ፣ ተራራው፣--ሃረር፣ ደሴ፣ አዲስ አበባ የማውቃቸው ሰዎች፣ ሃይማኖቴ፣ ባህሌ ናቸው፡፡
አሁን የሚታየው የብሔርተኝት እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያ ህልውና ስጋት ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ አንተስ ምን ትላለህ?
አዎ ስጋት አለኝ፤ ምክንያቱም ሶቭየት ህብረት ሲፈርስ በአይኔ አይቻለሁ፡፡ ሶቭየት ህብረት በሁሉም ነገር አቅም የነበረው አገር ነው፡፡ ያ ሲፈርስ አይቻለሁ። ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት አጋጣሚ ሊፈጠርባት ይችላል፡፡ ግን ህዝቡ ድምፁን ከሰጠ አትፈርስም። ኢትዮጵያ በታሪኳ ውስጥ አንዴ ስትሰፋ፣ ሌላ ጊዜ ስትጠብ ኖራለች እንጂ እንደ ሃገር ጠፍታ አታውቅም። ለወደፊትም አትጠፋም፡፡ በአለም ላይ ህልውናቸው ጠፍቶ ከማያውቅ ጥቂት ሃገራት፣ ኢትዮጵያ አንዷ ነች። ያውም በነፃነቷ ፀንታ የኖረች፣ ብቸኛ ሃገር ሆና ነው፤ ሶስት ሺህ ዓመት የኖረችው፡፡ ይህ ታሪኳ በዓለም ብቸኛ ያደርጋታል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ልትጠብ ትችላለች እንጂ መቼም አትጠፋም፡፡
ህገ መንግስቱ ብዙ ክርክሮችና ውዝግቦች ይነሱበታል፡፡ ያንተ አስተያየት ምንድን ነው?
እኔ ህገ መንግስቱ ትክክል ነው ብዬ አላምንም፡፡ ምክንያቱም አማራው በሌለበት ነው፣ ህገ መንግስቱ የተቋቋመው፡፡ አማራ፤ አንድ አማራ ተወካይ ሳይኖረው ነው ህገ መንግስቱ የወጣው፡፡ ወልቃይትን እንኳ ትግራይ ክልል ውስጥ ሲያደርጉ፣ አንድ የወልቃይት ሰው አልተጠየቀም፡፡ ራያም በተመሳሳይ፡፡ ስለዚህ አማራው በዚህ ህገ መንግስት እንዴት ነው ሊመራ የሚችለው፡፡ ባልተወያየበት፣ ራሱ ባላወጣው፣ ህገ መንግስት ለምን ይጠየቃል፡፡


Read 1461 times