Print this page
Saturday, 15 December 2018 14:38

ስፖርታዊ ጨዋነት፣ የተመልካቾች ረብሻ፣ ሁከት እና ብጥብጥ በኢትዮጵያ ወቅታዊ እግር ኳስ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የጥናቱ ዳራ እና የችግርቹ ማብራሪያ
በስፖርት ሜዳዎች ላይ የሚስተዋሉ ረብሻ፣ ብጥብጥ እና ሁከት ረዥም እድሜን ያቆጠሩ እና በተለያዩ ሀገራት በተለያየ መንገድ ሲቀርቡ ይስተዋላል፡፡ በተለይም እንደ እግር ኳስ ያሉ እና ንክኪ የሚበዛባቸው ስፖርቶች ለመሰል ባህሪያት ተጋላጭ በመኆን በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡     
የተመልካቾች ብጥብጥ እና ሁከት እጅግ በጣም ውስብስብ፣ ተለዋዋጭ እና ቅልቅል ከመሆኑ የተነሳ የየሀገራት ነባራዊ ሁኔታ፣ ታሪካዊ ዳራ፣ ማህበረሰባዊ እሴት፣ ፖለቲካዊ ይዘት፣ ባህላዊ ትውፊት እና መሰል ሁኔታዎች ለብጥብጡ መንስኤ በመሆን በመጠነ ማክሮ ደረጃ ሲጠቀሱ በመጠነ ደቂቅ በኩል ደግሞ የሜዳ ውስጥ እንቅስቃሴዎች ለምሳሌ የተጨዋቾች ሽኩቻ፣ ያልተገባ ጨዋታ፣ የአሰልጣኞች የአካል እንቅስቃሴ ተጠቃሽ ይሆናሉ፡፡ ከዚህ በመነሳት የተመልካቾች ብጥብጥን መንስኤን እና አቀጣጣይ ነገሮችን ለመረዳት በእነዚህ ሁለት ፅንፎች (በማክሮ እና በደቂቅ) ውስጥ የሚገኙ አጠቃላይ እንቅስቀሴዎችን መረዳት ይጠይቃል፡፡ ይህንንም ለማድረግ በኮን... ሞዴልን መሰረት በማድረግ   
የጥናቱ ዓላማ
የዚህ ጥናት አላማ
በኢትዮጵያ እግር ኳስ የተመልካቾች ብጥብጥ ያለበትን ደረጃ በመለየት አሁን ያለበትን ተጨባጭ ሁኔታ መተንተን፤
በኢትዮጵያ እግር ኳስ የተመልካቾች ብጥብጥ መንስኤዎቹን እና አቀጣጣዮችን በመለየት ያላቸውን ትስስር ለመረዳት፤
በኢትዮጵያ እግር ኳስ የተመልካቾች ብጥብጥ የሚያመጣውን ሁለንተናዊ ቀውስ ለመዳሰስ፤
በኢትዮጵያ እግር ኳስ የተመልካቾች ብጥብጥን ለመቀነስ ብሎም ለማጥፋት የአሰራር ስልቶችን መቀየስ፡፡  
የምርምሩ ዘዴ
ይህ ጥናት ገቢራዊ ያደረገው የጥናት አተገባበር ‹‹የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ›› (Stakeholders approach) የሚለውን መንገድ ሲሆን ለየትኛውም ችግሮች እና ለማንኛውም መፍትሄ  የእግር ኳሱ ባለድርሻ አካላት ሚና የጎላ መሆኑን መነሻ የሚያደርግ ነው፡፡ በዚህም አቀራረብ የጥናቱ አካላይ ተደርጎ የተወሰደው ከመንግስት እና ከአጠቃላይ የሀገሪቷ ነባራዊ ሁኔታ ጀምሮ እስከ ሜዳ ላይ እስከሚሳተፉ ባለሙያዎች ድረስ ለተመልካቾች ረብሻ ምክንያት በመሆን ተቀምጠዋል፡፡ ይህንንም ለማከናወን የምርምሩ ተሳታፊዎች ወይም ቀዳሚ መረጃ ሰጪዎች ተደርገው በዋነኝነት የተወሰዱት ተጨዋቾች፣ አሰልጣኞች፣ ዳኞች፣ የክለብ አመራር፣ የሚዲያ ባለሙያዎች፣ የደጋፊ ማህበራት፣ የፀጥታ አስከባሪዎች እና ተያያዥ ባለድርሻ አካላት ናቸው፡፡ ከእነዚህ ባለድርሻ አካላት መረጃዎችን በቡድን ውይይት እና በቃለ መጠይቅ ለማግኘት የተቻለ ሲሆን ተያያዥ የአለም አቀፍ ሰነዶችን፣ የአካዳሚክ ጥናቶችን እንዲሁም የሀገር ውስጥ ምርምሮችን ለማካተት ተሞክሯል፡፡    
የተጠኑ ተለዋዋጮች
የእግር ኳስ ተመልካቾች ረብሻን ለመረዳት፣ መንስኤውን እና መፍትሄውን ከሁሉም አቅጣጫ ለማስቀመጥ ሲባል የጥናቱ ተለዋዋጮች ተደርገው Soccer Fan Violence: A Holistic Approach በሚል በ Ramón Spaaij and Alastair Anderson (2009) የቀረበው ንድፈ ሀሳብ ከጥናቱ ተሳታፊዎች በተገኙ መረጃዎች ዳብሮ እና ተሻሽሎ የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ከግንዛቤ በከተተ መልኩ ቀርቧል፡፡ (አባሪ-1)    
የምርምሩ ውጤቶች፣ ማብራሪያ እና ትርጓሜ
ከዚህ አኀፅሮተ ፅሁፍ ጋር በአባሪነት የቀረበው ሁሉን አቀፍ የተቀናጀ ንድፈ ሀሳብ እንደሚያሳየው ከሆነ እጅግ ዘርፈ ብዙ፣ በቁጥር ከፍ ያሉ ባለድርሻ አካላት እና ተለዋዋጭ ባህሪያቶች ለተመልካቾች ረብሻ መንስኤ ተደርገው ቀርበዋል፡፡ ተለዋዋጮቹንም ምቹ ሁኔታዎች፣ መንስኤዎች እና አቀጣጣዮች በሚል በሶስት መሰረታዊ ክፍሎች ለመክፈል ተችሏል፡፡
ምቹ ሁኔታዎች
ለተመልካቾች ረብሻ ምቹ ሁኔታዎች በሚል የተቀመጡት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበረሰባዊ እና ባህላዊ ሁኔታዎች ሲሆኑ ወቅታዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ የተመልካቾችን ረብሻ፣ ሁከት እና ብጥብጥ ለመቀስቀስ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተለይቷል፡፡ ከፖለቲካ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጥያቄዎች በሀገሪቷ ውስጥ መበራከታቸው፣ የወሰን አለመግባባቶች በተለያዩ ቦታዎች መከሰታቸው፣ የብሄር ጥያቄዎች ጎልተው መውጣታቸው፣ እና ተያያዥ ጉዳዮች መነሳታቸው ስቴዲየም ውስጥ ሊኖር የሚችል ረብሻን የመወሰን እድሉ የሰፋ ነው፡፡ ስፖርታዊ መድረኮች እነዚህን ፖለቲካዊ ጉዳዮች ለመግለፅ እንዲሁም በሀላፊዎች ዘንዳ ታውቆ መልስ እንዲሰጥበት የማድረጊያ መድረክ ነው፡፡ (Conflict Theory Marx and Engel 1840/1947)
ሌላው ለረብሻ ምቹ ሁኔታ ተደርጎ የተወሰደው ወቅታዊው የኢኮኖሚ ሁኔታ ሲሆን የኑሮ ውድነት፣ ሰፊ የገቢ ልዩነት፣ የስራ አጥነት እና ተመሳሳይ ጉዳዮች አንኳር የብጥብጥ መንስኤዎች ሆነው ቀርበዋል፡፡ ስፖርታዊ ረብሻ ከተመልካቾች የኑሮ ሁኔታ እና ከማህበረሰብ ምንነት ጋር ተዛማጅነት እንዳለው የሚጠቀስ ሲሆን በአብዛኛው ወጣት፣ ወንዶች እና ከዝቅተኛው የማህበረሰብ ክፍል የሚመጡ ተመልካቾች የሚበዛበት የስፖርት ሜዳ ለሁከት እና ብጥብጥ የመጋለጡ እድል ከፍተኛ ነው፡፡ (Dunnig et al 1986) በነዋሪዎች መሀከል ያለ ሰፊ የገቢ ልዩነት እና የኑሮ ደረጃ መራራቅ አንዱ የስፖርት ሜዳ ረብሻ ምክንያት ሲሆን ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች በአካባቢው ላይ ማህበረሰባዊ ቁጥጥር እንዳላቸው የሚያሳዩበት አጋጣሚ ነው (Dunnig et al 1986):: ይህም ባህሪ በኢትዮጵያ የስፖርት ስቴዲየሞች የጨዋታ ፍፃሜ በኋላ የሚስተዋል ነው፡፡
አሁን አሁን በኢትዮጵያ ስቴዲየሞች የሚስተዋሉት የተጨዋቾች ረብሻ ከኢትዮጵያ ባህል እና እሴት ያፈነገጠ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች ሊወክሉ እንደማይችሉ በቡድን ተወያዮች የተገለፀ ቢሆንም የእግር ኳሱ ባህል በራሱ ግን አሉታዊ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡ በተለይም እግር ኳስ ሜዳን የአጉል ባህሪያት መገለጫ አድርጎ መውሰድ የተለመደ ከመሆኑ አንፃር ኳስ መጫወትን እና መመልከትን ከረብሻ እና ሁከት ጋር አዛምዶ ማየት የተለመደ ነው፡፡  
መንስኤዎች
ለተመልካቾች ረብሻ መንስኤ በሚል በጥናቱ ከተለዩት ነጥቦች መሀከል እግር ኳሳዊ ሙስና ‹‹ጥፋት፣ በተለይም የመንፈስ መበከል›› (ዮሀንስ አድማሱ፣ 1990)፣ የብሄርተኛ ክለቦች መበራከት እና በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ እምነት ማጣት የሚሉት በዋነኝነት ተቀምጠዋል፡፡
እግር ኳሳዊ ሙስና
እግር ኳሳዊ ሙስና በአልተገባ መልኩ በባለድርሻ አካላት መሀከል የሚፈጠር የጥቅም ግኑኝነት ሲሆን ጨዋታን መሸጥ፣ ዝውውርን ማወክ እና አስተዳደራዊ ኢ-ፍትሀዊነትን ማስፈን በሚል  (Ellis Cashmore and Jamie Cleland, 2014) Football’s Dark Side በሚል መፅሀፋቸው አስቀምጠውታል፡፡ በዚህም ሂደት ውስጥ አጅግ ዘርፈ ብዙ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ የሚሆኑ ሲሆን ለግንኙነታቸውም ይረዳቸው ዘንድ ተቋማዊ ባልሆነ መልኩ የሚንቀሳቀሱ የዘርፉ አካላትም ሆኑ ሌሎች ግለሰቦች በተባባሪነት አብረዋቸው ይሰራሉ፡፡ መሰል እንቅስቃሴዎች በአለም አቀፉ እግር ኳስ ውስጥ የሚታዩ ሲሆን በአፍሪካም ለዘርፉ ከፍተኛ አደጋ ከፈጠሩ ተግዳሮቶች መሀከል እንደሆነ በብዙ ፀሀፍት ተለይቷል። በእግር ኳስ ውስጥ የሙስና መስፋፋት የስፖርቱ ተመልካች በተጨዋቾች፣ አሰልጣኞች፣ ዳኞች፣ ክለቦች እንዲሁም በብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ያላቸውን እምነት የሚሸረሽር መሆኑን ተከትሎ በስቴዲየም ውስጥ ያልተገቡ ባህሪያት እንዲበረክቱ ያደርጋል፡፡
እንደ ማርክሲስት አተያይ (Marxist account, Ian Taylor’s 1969, 1971) የእግር ኳስ ረብሻ ምክንያት ወጣቱ እና የታችኛው ማህበረሰበ ክፍል ከስፖርቱ ጥቅም እየተገለለ መምጣቱ እና እግር ኳስን ለማዘመን ከሚወጣው ወጪ ተቋዳሽ አለመሆኑን (Social Marginalization) እንደ አንድ ምክንያት ያስቀምጣል፡፡ ይህ ፍልስፍና አሁን ባለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በጉልህ የሚታይ ሲሆን ከፍተኛ የገንዘብ እንቅስቃሴ በእግር ኳሱ ውስጥ እየተከናወነ ቢሆንም በማህበረሰብ እና ዘላቂነት ባለው መልኩ የአካባቢ ነዋሪዎች በቀጥተኛ መንገድ ተጠቃሚ ሲሆኑ አይታይም፡፡
የብሄርተኛ ክለቦች መበራከት
ብሄርተኛ ክለቦች በአንድ ብሄር፣ ብሄረሰብ፣ ጎሳ እና ዘር ተለይቶ እንዲታወቅ ብሎም እንዲደገፍ ተደርጎ የሚመሰረት የእግር ኳስ ክለብ ሲሆን በዘመነ ቅኝ ግዛት በተለይም በአፍሪካ ተስፋፍቶ የነበረ የክለብ አደረጃጀት ነው፡፡ ቅኝ ገዢዎች ስፖርትን በተለይም ደግሞ እግር ኳስን በመጠቀም የዘር እና የባህል ልዩነቶች በአፍሪካውያን ላይ እንዲሰርፁ ለማስቻል በነገድ ላይ የሚያጠነጥኑ ቡድኖችን በስራ ቦታዎች (በፋብሪካ፣ ማእድን ቁፋሮ) ላይ ያቋቁሙ ነበር (Peter Alegi፣ 2009 )፡፡ መሰል ክለቦች የቅኝ ግዛት ትውፊቶች (Colonial Legacy) በመባል በተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎች ላይ ተጠቅሰዋል፡፡   
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በተለይም ከ2009 ዓ.ም በኋላ በስፋት እየተስተዋለ ለመጣው የደጋፊዎች ረብሻ እና ስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ትልቁን ሚና የሚጫወተው ወቅታዊው የኢትዮጵያ የብሄር ፖለቲካ እንደሆነ በብዙ የጥናቱ ተሳታፊዎች ተገልጧል፡፡ ለዚህም በዋነኝነት እንደ ምክንያት የቀረበው ክለቦች ከእግር ኳስ ክለብነት እና የእግር ኳስ እንቅስቃሴን ከሚያራምድ ተቋምነት በዘለለ የብሄር መገለጫዎች እየሆኑ መምጣታቸው ነው። እንደ ማሳያም ቁጥራቸው ትንሽ የማይባል ክለቦች ስያሜ፣ ቅፅል ስም፣ አርማ፣ ዜማ ከተፈጥሯዊ አሰፋፈር ጋር ተዳብሎ በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ከብሄር /ፖለቲካ ጋር ተያያዥነት ኖሮት እንዲቀርብ መደረጉ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በተጨማሪም ከፖለቲካ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ምስሎችን በአልባሳቶቻቸው እና በሌሎች ስፖርታዊ መድረኮች ላይ ሲጠቀሙበት ይታያል። ይህ ፍፁም ከአለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሰራር የራቀ ሲሆን በጨዋታ ህጎች አንቀፅ 4 የተጨዋቾች ቁሳቁስ (Players’ Equipment) በሚለው ስር ‹‹ከውጭም ሆነ ከውስጥ የሚለበሱ የተጨዋቾች ትጥቅ፤ ከማንኛውም አይነት የፖለቲካ፣ የሀይማኖት ምልክቶች ወይም የግለሰቦች መፈክር፣ አባባል እና ምስል የፀዳ መሆን አለበት።›› ይላል፡፡
በፌዴሬሽኑ እምነት ማጣት
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ለረዥም አመታት ስሙ እየጎደፈ መምጣቱ በባለ ድርሻ አካላት በኩል ተቀባይነት እንዳያገኝ አድርጎታል፡፡ በተለይም የስቴዲየም ታዳሚዎች የቡድናቸውን ውጤት ማጣት ከፌዴሬሽኑ ስህተት፣ አቅም ማነስ፣ ተንኮል እና ወንጀል ጋር ማያያዛቸው አንዱ ለስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል እና ለረብሻ መንስኤ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድኑ የውጤት እጦት ጋር ስሙ ተያይዞ የሚነሳው ፌዴሬሽኑ በምርጫ ወቅት በሚነሱ አላስፈላጊ ውዝግቦች ጋር ተዳምሮ ከፍተኛ የሆነ የምስል ውድቀት ውስጥ ሊገባ ችሏል፡፡
ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለው የላላ ግንኙነት፣ በስፖርቱ ቤተሰቦች ያተረፈው ኢ-ተአማኒነት እንዲሁም ማህበረሰብ አቀፍ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚያደርገው ውስን የሆነ ተሳትፎ በተመልካቾች ዘንዳ የእኔነት ስሜት እንዳይፈጥር አድርጎታል፡፡ ይህ የአንድ ተቋም የእምነት ማጣት ደግሞ የአልታዘዝ ባይነትን በመፍጠር የግጭት መንስኤ እነደሆነ በተለያዩ መስኮች የተደረጉ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡
አቀጣጣዮች
የእግር ኳስ ቤተሰቡ ወደ ስቴዲየም አካባቢ ከመጣ እና በጨዋታው ከታደመ በኋላ የሚከሰቱ ቅፅበቶች፣ ድርጊቶች እና ሁኔታዎች ለተመልካቾች ረብሻ አቀጣጣይ ነገሮች ተደርገው የተወሰዱ ሲሆን የሜዳ ውጭ ተግባራት እና የሜዳ ውስጥ ተግባራት በሚል ለሁለት ተከፍለው ተቀምጠዋል፡፡
የሜዳ ውስጥ ተግባራት
ለተመልካቾች ረብሻ መቀጣጠል አንዱ እና ዋንኛው የሜዳ ውስጥ ተግባራት ሲሆኑ ከእነዚህም መሀከል ዳኝነት፣ የተጨዋቾች ስነ ምግባር፣ የአሰልጣኞች እንቅስቃሴ፣ የቡድን መሪ እና የተቀያሪ ተጨዋቾች ስነ ስርአት ከጨዋታው ጥራት እና ደረጃ ጋር እንዲሁም ቀልብ ያዢነት ጋር በመሆን ይወሰዳሉ፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ዳኝነት እና የዳኝነት አስተዳደር ለስቴዲየም ረብሻ፣ ሁከት እና ብጥብጥ መንስኤ እንደሆነ በጥናቱ ከተገኙ አንኳር ነጥቦች ለመረዳት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹ገለልተኛ ዳኛ የለም፤ ከምደባ ጀምሮ በገንዘብ የማይሰራ ነገር የለም፣ እከሌ እና እከሌ ሲጫወቱ እከሌ ማሸነፍ አለበት››  እና የመሳሰሉት የሚሉ ቅሬታዎች ከጥናቱ ተሳታፊዎች በስፋት ተነስተዋል፡፡ ከዳኞች ከቅም፣ አመዳደብ እና ግልፀኝነት ከጎደለው አሰራር በተጨማሪ የኮሚሽነሮች እና የዳኞች ግኑኝነት፣ የጨዋታ ሪፖርቶች አቀራረብ፣ የዳኞች ገለልተኝነት  ሌላው ቅሬታን የሚያስነሳ አሰራር እና ለስነ ምግባር መጓደል መንስኤ ተደርጎ ቀርቧል፡፡ ዳኞች አንዳንዴም በጥቅማ ጥቅም እና በመደለያ በመያዝ ሌላ ጊዜም ከባለሜዳ ከደጋፊዎች እና ሰራተኞች በሚደርስባቸው ከፍተኛ ጫና ምክንያት ያልተገባ ጥቅም ለቡድኖች መስጠታቸው በተመልካቹ ዘንድ ቅቡልነት እያጡ እንዲሄዱ አድርጓቸዋል፡፡
ሜዳ ውስጥ ከዳኞች በተጨማሪ በእንቅስቃሴ ተሳታፊ የሆኑት ተጨዋቾች፣ አሰልጣኞች፣ ቡድን መሪዎች እና የተቀያሪ ወንበር አባላት ለረብሻ እና ሁከት መንስኤ ሲሆኑ በሰፊው ይስተዋላል፡፡ የዳኛን ውሳኔ በፀጋ አለመቀበል፣ ነገሮችን ማግነን፣ ዳኛን መክበብ፣ ማዋከብ፣ ዳኛን ማመናጨቅ፣ ዳኛን መማታት፣ ተጋጣሚን መማታት፣ ወደ ሜዳ መግባት ፣ የውጭ ተጨዋቾች ባህላችንን አለማወቅ፣ ደጋፊን ማነሳሳት፣ ደጋፊን መሳደብ፣ ከጨዋታ በኋላ አለመጨባበጥ እና ተመሳሳይ ባህሪያት ፀብ አቀጣጣይ ተደርገው ተወስደዋል፡፡ እነዚህ ባለድርሻ አካላት የስፖርቱ የመጀመሪያ ተጠቃሚ ከሞሆናቸው አንፃር ከሌሎቹ በተለየ መልኩ በህግ እና በስርአት በቀላሉ ሊታረሙ እና ክትትል ሊደረግባቸው የሚችሉ ናቸው፡፡  
የሜዳ ውጭ ተግባራት
ለተመልካቾች ረብሻ እንደማቀጣጠያ ከተነሱት ሜዳ ውጭ ተግባራት መሀከል አልኮል እና መጠጥ፣ የፀጥታ አካላት ብቃት እና አድሎአዊነት፣ የስፖርት ሚዲያዎች፣ የመጫወቻ ስቴዲየሞች ደረጃ እና የደጋፊዎች አቀማመጥ በተደጋጋሚ ተጠቅሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ እየታዩ ለሚገኙት የደጋፊዎች ስነ ምግር መጓደል እና ስፖርታዊ ጨዋነት መጥፋት  እንዲሁም ሁከት እና ብጥብጥ መንስኤ ተደርገው በጥናቱ ተሳታፊዎች ከተቆጠሩት መሀከል በስቴዲየም ዙሪያ ወይም በመጨዋቻ ሜዳ አካባቢ የሚገኙ መጠጥ ቤቶች፣ የሱስ አስያዥ ስፍራዎች እንዲሁም ተያያዥነት ያላቸው ቦታዎች እንደሆኑ በቡድን ውይይት ተሳታፊዎች ተጠቅሷል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ አለም አቀፍ ጥናቶች ውስን የሆነ አጠቃላይ መደምደሚያ ላይ ባይደርሱም የአለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፊፋ፤ የእግር ኳስ ውድድሮችን በሰላም እና ያለምንም እረብሽ ለማከናወን ይረዳ ዘንድ ባዘጋጀው መመሪያ ላይ (FIFA Stadium Safety and Security Regulation) እንዳስቀመጠው ከሆነ የአልኮል እና መጠጥ አጠቃቀም በእግር ኳስ ሜዳዎች አካባቢ በጥንቃቄ ሊያዝ ይገባል፡፡
ማስፈፀሚያ ስልቶች
ከላይ በቀረበው ሁሉን አቀፍ የተቀናጀ ንድፈ ሀሳብ የተዘረዘሩትን የተመልካቾች ረብሻ ምቹ ሁኔታዎች፣ መንስኤዎች እና ማቀጣጠያዎችን ለመቀነስ ብሎም ለማጥፋት ይረዳ ዘንድ በሌሎች ሀገራት ተሞክረው ውጤታማ የሆኑ አሰራሮችን፣ በሰነድ ምክረ ሀሳብ ተደርገው የቀረቡ ስትቴጂዎችን፣ ሳይንሳዊ የባህ ማረቂያ መንገዶችን እንዲሁም ከተሳታፊ ባለድርሻ አካላት የቀረቡ የመፍትሄ ሀሳቦችን እ የማስፈፀሚያ ስልቶች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡
እግር ኳሳዊ ሙስናን ለመዋጋት እና የስፖርቱን ህልውና ለመጠበቅ በቅርቡ ከተቋቋመው እና የወንጀል መከላከል እና ምርመራ ተቋማትን በስሩ ካደረገው የሰላም ሚኒስቴር ጋር የፌዴሬሽኑ የስነ ምግባር ኮሚቴ በኩል በጋራ መስራት፤
የተማሪዎች፣ የወጣት እና የጎልማሶች እግርኳሶች በየአካባቢው እንዲዘወተሩ በማድረግ የስፖርታዊ ጨዋነትን ማስተማር፣ የማህበረሰቡን የሞራል እሴት መገንባት፤
እንደ አስፈላጊነቱ የስፖርት ህግ እና የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች ስነ ምግባር አዋጅ ማውጣት፤
የዲሲፕሊን ህጉን ከወንጀለኛ መቅጫ ህግ ጋር እንዲገናኝ ማድረግ፤
ክለቦች ከክለብም በላይ በመሆን ከስሜት ቆስቋሽ ነገሮች እራሳቸውን አርቀው ማህበረሰብ ግንባታ ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ በልማት ረገድ የአካባቢያቸው ፈርጥ እንዲሆኑ ማስቻል፤
ፌዴሬሽኑ ለምስል ግንባታ የሚረዱ የማህበረሰብ ተኮር እንቅስቃሴዎች ውስጥ መግባት፤
በፌዴሬሽኑ አደረጃጀት ውስጥ ያሉ ተግባራት ወጥነት፣ አሳታፊ እና ግልፀኝነት የተሞላባቸው ማድረግ፤
ቀጣዩ የስራ አስፈፃሚዎች ምርጫ ከምንግዜውም በላቀ ቅቡል እንዲሆን ማድረግ፤
በስፖርቱም ሆነ ከስፖርቱ ውጭ በጎ ስም ያላቸውን ግለሰቦች በማቅረብ ኃላፊነት መስጠት፤
የደጋፊዎች ሽልማት መስጠት (Fan Award)፤
ከጨዋታ በፊት ወይም አጋማሽ የሚካሄዱ የደጋፊዎች ፉትሳል ውድድር መጀመር፤
ከደጋፊዎች ጋር አብሮ የሚሰራ የአደረጃጀት ንዑስ ክፍል ማቋቋም፤
የአለም አቀፍ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፊፋ የጨዋታ ህግ-4 ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ፤
በክለቦች መቋቋም ላይ ከማህበራት ማደራጃ ፈቃድ በተጨማሪ ፌዴሬሽኑ የራሱ የሆነ ደንብ እንዲኖረው ማድረግ፤
ክለቦች ብሄር ቀመስ እንቅስቃሴን፣ አደረጃጀትን፣ አስተሳሰብን በገሀድ እንዲያወግዙ ማድረግ፤
እስካሁን የተሰራ ስህተትን ለመቅረፍ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የክለብ ባለስልጣናት፣  የፖለቲካ ሙህራን፣ የእግር ኳስ ባለሙያዎች እና የስፖርቱ ማህበረሰብ በተገኙበት ተከታታይ ውይይት ማድረግ፤
የዳኞች ምደባን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ግልፅ ማድረግና ፍትሀዊነትን ማረጋገጥ፤
የዳኞች የሪፖርት ፎርማትን በማሻሻል የቡድኖችን ባህሪ፣ የፀጥታ ኃይሉን ባህሪ፣ የደጋፊውን ባህሪ እንዲገመግሙ ማድረግና በቀጣይነት ለሚወሰዱ ሽልማቶች፣ እርምጃዎች እና የውድድር መንፈሶች መረጃ መሰብሰብ፤
ሜዳ ላይ ለሚታዩ ብልሹ አድራጎቶች እና ባህያቶች የጥቁር ካርድ ስርአት መዘርጋት፤
ውበት ያላቸው ጨዋታዎች እንዲካሄዱ የቴክኒክ ክፍል እገዛ፣ ሽልማት እና ግምገማ ፤
ሜዳ ከማገድ፣ በዝግ ስቴዲየም ከማጫወት፣ ከገንዘብ እና የተጨዋች ቅጣት በተጨማሪ ህጉ ላይ ያለው የነጥብ ቅነሳዎች ተግባራዊ ቢደረጉ፤
የ‹‹አንድ ደቂቃ›› ህግ እንዲጀመር ማድረግ፤
የስፖርት ሜዳ ጥፋቶች ከወንጀል ህጉ ጋር እንዲተሳሰር ማድረግ፤
የዳኞችን ስልጠና ከተለመደው ጊዜ በተለየ ማሻሻል፣ በዳኛው እውነተኛ እንቅስቃሴ ላይ የተመሰረተ በቪዲዮ የታገዘ እራስን በራስ የመገምገም (Self Reflection) ትምህርቶችን መስጠት፤
የአልኮል አቅርቦትን መቆጣጠር፣ መቀነስ አስፈላጊም ሆኖ ሲገኝ የጨዋታ እለት ማገድ፣ ሰክረው የሚገቡ ተጨዋቾችን በትንፋሽ መመርመሪያ በመጠቀም ማገድ፤
ሚዲያን መከታተል፣ መመርመር፣ ላልተገቡ መረጃዎች ቀልጣፋ መልሶችን መስጠት አስፈላጊም ሆኖ ሲገኝ አስተማሪ እርምጃዎች በመውሰድ ለፍርድ ቤት ማቅረብ፤
የፀጥታ ኃይሉ ከስፖርት ሜዳ አጠባበቅ ጋር የተያያዘ ስልጠናዎችን እንዲያገኝ ማድረግ፤
የስቲዋርድስ አሰራር ወይም በአንዳንድ ክለቦች እንደታዩት የደጋፊዎች የፀጥታ ኃይል ማዘጋጀት ፤
የመፈተሻ ቴክሎጂዎችን፣ ካሜራዎችን መጠቀም፤
እግር ኳስ ማህበር እና በሀገሪቱ ፖሊስ ፅ/ቤት በጋራ በመሆን የተዘጋጀ የስቴዲየም አጠባበቅ መመሪያ (Policing of Football Matchs)፤
በተለዩ ጨዋታዎች ላይ ጊዜያዊ (ተንቀሳቃሽ) የፖሊስ ምርመራ ማካሄጂያ ጣቢያዎችን ማቋቋም
የስቴዲየም አቀማመጥን ማሻሻል በተለይም በአዳዲስ ስቴዲየሞች የቤተሰብ፣ የህፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች፣ የአዛውንቶች መቀመጫዎችን መለየት፤
ክለቦች ከራሳቸው የሜዳ ይዘት፣ ማህበረሰብ፣ ባህል እና የቡድን ማንነት መሰረት በማድረግ የደህንነት እና የጥበቃ ስትራቴጂ እንዲያቀርቡ ማድረግ (ESJA, 2018)፤
የክለብ ደጋፊዎች ማህበር እንዲጠናከሩ ማድረግ እና የመግቢያ ቲኬት እንዲያገኙ ማድረግ (ESJA, 2018)፤
ጨዋታን ካርኒቫል ማስመሰል፣ እረፍት ሰአትን መዝናኛ ማድረግ፡፡
ይህ የተራዘመ አኀፅሮተ-ፅሁፍ (Extended Abstract) የስፖርት ኮሚሽን፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና የስፖርት ሚዲያ በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ በአደረጉት የውይይት መድረክ ላይ ከቀረበው የጥናት ወረቀት የተወሰደ ነው፡፡
የጥናት ቡድኑ አባላትም፡-
አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ማርኬቲንግ ማኔጅመንት ዲግሪ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በአ.አ ፌዴሬሽን የጥናት ቡድኑ ሰብሳቢ፣
ዶ/ር ተፈራ ታደሰ ፒኤች ዲ በስርአተ ትምህርት እና ማስተማር ስነ ዘዴ ተባባሪ ፕፕሮፌሰር ጅማ ዩኒቨርሲቲ
ዶ/ር አመንሲሳ ከበደ ፒኤችዲ ስፖርት ሳይንስ ረዳት ፕሮፌሰር ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ኢንስትራክተር በወጣቶች ስፖርት አካዳሚ
ዶ/ር ወገኔ ዋልተንጉስ ፒኤችዲ ስፖርት ሳይንስ ረዳት ፕሮፌሰር ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ
አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ማስተርስ ዲግሪ የህዝብ አስተዳደር እና የልማት ማኔጅመንት አዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ክለብ
አቶ ኃይለ እግዚአብሔር አድሃኖም ዲግሪ የህዝብ አስተዳደር እና የልማት ማኔጅመንት የስፖርት ሚዲያ ባለሙያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ፀሐፊ
አቶ አንበሰ መገርሳ ማስተርስ ዲግሪ ስፖርት ሳይንስ አዳማ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ዋና ሥራ አስኪያጅ
አቶ ሳመኤል ስለሺ ማስተርስ ዲግሪ በስፖርት ስነልቦና እና እግር ኳስ ሌክቸረር አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
ወ/ሮ መሰረት በላይነህ ፀሐፊ በአ.አ ፌዴሬሽን  
ተባባሪዎች
ወ/ሪት መስከረም ታደሰ - ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ጽ/ቤት
አቶ ተሾመ - ከወጣቶች ስፖርት አካዳሚ

Read 5824 times
Administrator

Latest from Administrator