Saturday, 15 December 2018 14:26

ሼክ አል አሙዲ በሙስና ፍ/ቤት እንደሚቀርቡ ተነገረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከታሰሩ በኋላ ሃብታቸው በ6 በመቶ ጨምሯል ተብሏል
 
በሳዑዲ አረቢያ መንግስት በቁጥጥር ስር የዋሉትና ከአንድ አመት በላይ በቁም እስር ላይ የሚገኙት ሼክ መሃመድ አል አሙዲ በሙስና ወንጀል ክስ እንደተመሰረተባቸውና ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ አንድ የአገሪቱ ባለስልጣን ከትናንት በስቲያ ማስታወቃቸውን ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
በሳዑዲ አረቢያ ባለሃብቶች አካባቢ ሼክ አል አሙዲ በህይወት የሉም በሚል በስፋት ሲናፈስ የነበረው አሉባልታ ፍጹም ሃሰት መሆኑን የገለጹት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት ባለስልጣኑ፣ አል አሙዲ በህይወት እንዳሉና አሁንም ድረስ በእስር ላይ እንደሚገኙ ማረጋገጫ የሰጡ ሲሆን፣ በተከሰሱበት የሙስና ወንጀል ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ቢያረጋግጡም የችሎቱ ትክክለኛ ቀን ግን ገና አለመወወሰኑን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የሼክ አል አሙዲ ቃል አቀባይ ቲም ፔንድሪ በበኩላቸው ባለሃብቱ በምንም አይነት የወንጀል ድርጊት በይፋ ክስ እንዳልተመሰረተባቸው ከመግለጽ ውጭ በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር አስተያየት ለመስጠት አለመፍቀዳቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡
አል አሙዲን በቁጥጥር ስር ከዋሉበት ጊዜ አንስቶ ባሉት ጊዚያት የተጣራ የሃብት መጠናቸው በ6 በመቶ እድገት በማሳየት 8.3 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን የጠቆመው ብሉምበርግ፣ ባለሃብቱ በእስር ላይ ቢገኙም አለማቀፍ ቢዝነሳቸው ትርፋማ ሆኖ መቀጠሉንና በስዊድን ትልቁ የነዳጅ ኩባንያ የሆነው ፕሪም ኤቢ የተሰኘው ኩባንያቸው ሽያጭ ከ30 በመቶ በላይ ማደጉን አመልክቷል፡፡
ሳዑዲ አረቢያ ባለፈው አመት ህዳር ወር ላይ ባካሄደችው የጸረ-ሙስና ዘመቻ አል አሙዲን ጨምሮ ልዑላንን፣ ሚኒስትሮችን፣ የቀድሞ ሹማምንትንና ባለሃብቶችን በሪያድ በሚገኘው ሪትዝ ካርልተን ሆቴል ውስጥ በቁጥጥር ስር ማዋሏና የተወሰኑትንም በድርድር መፍታቷ ይታወሳል፡፡

Read 2928 times