Wednesday, 12 December 2018 00:00

ባለፈው አመት በሽብር ጥቃቶች የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ቀንሷል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

አይሲስ አሁንም ቀንደኛው የሽብር ቡድን ነው


    በመላው አለም ከሽብር ጥቃቶች ጋር በተያያዘ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ላለፉት ሶስት ተከታታይ አመታት እየቀነሰ መምጣቱንና ባለፈው የፈረንጆች አመት በከፍተኛ ደረጃ የቀነሰው በኢራቅና በሶርያ መሆኑን አንድ አለማቀፍ ሪፖርት አመልክቷል፡፡
ኢንስቲቲዩት ፎር ኢኮኖሚክስ ኤንድ ፒስ የተባለው ተቋም ባለፈው ረቡዕ ይፋ ባደረገው አለማቀፍ የሽብርተኝነት ሁኔታ አመላካች ሪፖርት እንዳለው፣ በ2017 የፈረንጆች አመት በሽብር ጥቃቶች ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር በ27 በመቶ መቀነስ  አሳይቷል፡፡
በአመቱ በኢራቅና በሶርያ እንዲሁም በአውሮፓ አገራት ከሽብር ጥቃቶች ጋር በተያያዘ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ለመቀነሱ በምክንያትነት የተጠቀሰው አሸባሪው ቡድን አይሲስ በተወሰዱበት ወታደራዊ እርምጃዎች መሸነፉና መዳከሙ ነው፡፡
አይሲስ በፈጸማቸው የሽብር ጥቃቶች የሞቱ ሰዎች ቁጥር በ2017 የ52 በመቶ መቀነስ ማሳየቱ የተነገረ ሲሆን፣ ያም ሆኖ ግን የሽብር ቡድኑ ብዙዎችን ለሞትና ለመቁሰል አደጋ በመዳረግ አሁንም ቀንደኛው የአለማችን አሸባሪ ቡድን ሆኖ እንደቀጠለ ተገልጧል፡፡  
በ2017 በሽብር ጥቃቶች የሞቱ ሰዎች በከፍተኛ መጠን የቀነሰው በአውሮፓ አገራት መሆኑን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ የመቀነሱ መጠን 75 በመቶ ያህል እንደሚደርስም አመልክቷል፡፡
ጥናቱ ከዳሰሳቸው 163 የአለማችን አገራት መካከል በ96ቱ በሽብር ጥቃቶች ለሞት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር መቀነስ ማሳየቱን፤ በ46 አገራት ደግሞ መጨመር ማሳየቱን የዘገበው ሲኤንኤን፤ በአለማችን 67 አገራት ውስጥ በአመቱ ቢያንስ አንድ ሰው በሽብር ጥቃት ለሞት መዳረጉንም አክሎ ገልጧል።

Read 1809 times