Monday, 10 December 2018 00:00

የአመቱ ከፍተኛ ተከፋይ ሙዚቀኞች ይፋ ተደረጉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  የ7 አመቱ ህጻን በ12 ወራት 22 ሚ. ዶላር በማግኘት በዩቲዩብ ገቢ አለምን ይመራል


    ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት የ2018 የፈረንጆች አመት የአለማችን ከፍተኛ ተከፋይ ሙዚቀኞችን ዝርዝር በሳምንቱ መጀመሪያ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ የአየርላንዱ የሙዚቃ ቡድን ዩቱ በ316 ሚሊዮን ዶላር አጠቃላይ ገቢ ቀዳሚነቱን መያዙ ታውቋል፡፡
ኮልድፕሌይ የተባለው ታዋቂ የሙዚቃ ቡድን በ115.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የሁለተኛነት ደረጃን ሲይዝ፣ የ27 አመቱ ድምጻዊ ኤድ ሼራን በ110 ሚሊዮን ዶላር በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ ታዋቂው ድምጻዊ ቡርኖ ማርስ በ100 ሚሊዮን ዶላር አመታዊ ገቢ የአራተኛነት ደረጃውን ሲይዝ፣ ኬቲ ፔሪ በ83 ሚሊዮን ዶላር አምስተኛ፣ ቴለር ስዊፍት በ80 ሚሊዮን ዶላር ስድስተኛ፣ ጄይ ዚ በ76.5 ሚሊዮን ዶላር ሰባተኛ፣ ጋንስ ኤን ሮዝስ በ71 ሚሊዮን ዶላር ስምንተኛ፣ ሮጀር ዋተርስ በ68 ሚሊዮን ዶላር ዘጠነኛ፣ ዲዲ በ64 ሚሊዮን ዶላር አስረኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
የአመቱ የፎርብስ ምርጥ አስር የአለማችን ከፍተኛ ተከፋይ ሙዚቀኞች ባለፉት አስራ ሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ በድምሩ 886 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘታቸው ተነግሯል፡፡
በተያያዘ ዜና በአመቱ በዩቲዩብ በለቀቋቸው የተለያዩ ቪዲዮዎች ከፍተኛ ገቢ ያገኙ ሰዎች ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ 22 ሚሊዮን ዶላር በማግኘት በአንደኛነት ደረጃ ላይ የተቀመጠው የሰባት አመቱ አሜሪካዊ ብላቴና ራያን ነው፡፡ የህጻናት አሻንጉሊቶችን የተመለከቱ አዳዲስና አዝናኝ መረጃዎችን በዩቲዩብ የሚያሰራጨው ራያን፣ ከፍተኛ ተወዳጅነት ያተረፈ ሲሆን  የራያን የዩቲዩብ ገጽ 17 ሚሊዮን ያህል ተከታዮች እንዳሉት ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
በዩቲዩብ ገቢ ሁለተኛ ደረጃን የያዘው ጃክ ፖል የተባለ አሜሪካዊ ሲሆን፣ የሚለቃቸው የራፕ ሙዚቃዎችና የሽወዳ ትርኢቶች ከ3.5 ቢሊዮን በላይ ጊዜ ታይተውለት፣ 21.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱ ተነግሯል፡፡
በዩቲዩብ በአመቱ ከፍተኛ ገቢ ያገኙት ቀዳሚዎቹ አስር ግለሰቦችና ቡድኖች ባለፉት አስራ ሁለት ወራት በድምሩ 180 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘታቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

Read 2458 times