Monday, 10 December 2018 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)

 “ሰው ኑሮውን ሳይሆን ሃሳቡን ይመስላል”
            
     አንድ ወንድም አለኝ፤ በዘር ፖለቲካ የናወዘ። ሞቅ ሲለው፤ “ይኸ መሬት የኛ፣ ያ ደግሞ የእነ እንትና፣ የወዲያኛው ምናምን---” እያለ በተረት ብዕር ያካልላል፡፡ አሁን ከሙያው ፖለቲካው በልጦበት፣ አንድ በዘር የተደራጀ ፓርቲ አፈ-ቀላጤ ሆኗል፡፡…
አንድ ቀን ማታ በጠና ታመመ፡፡ ከባለቤቱና ከልጁ ጋር ሆነን ሆስፒታል ወሰድነው፡፡ ባስቸኳይ ደም ካልተሰጠው ተስፋ እንደማይኖረው ተረዳን። ከሱ የደም ዓይነት ጋር የሚመሳሰል ደም በሆስፒታሉ አልተገኘም፡፡ የኔም፣ የሚስቱም፣ የልጁም ቢመረመር አልሆነም፡፡ ጉድ ፈላ!! ግራ ገባን፡፡ የምንይዝ፣ የምንጨብጠው ጠፍቶን ለሰዓታት ስንዋከብ፣ ዋናው ሃኪም በደም የተሞላ ላስቲክ አንጠልጥሎ ከች አለ፡፡ ትረፍ ሲለው!!
ህክምናውን እንደጨረሰ ሃኪሙ ከኛ የበለጠ ስለሱ መጨነቁንና ህይወቱን ለማትረፍ እንደታገለ ነገርነው፡፡ ወደ ቤት መሄጃችን ሲቃረብ፣ ዶክተሩን እናመስግን ብሎኝ ወደ ቢሮው ሄድን፡፡ ሃኪሙን እንዳገኘነው፣ እጁን ጨብጦ ምስጋናውን ሲያዥጐደጉድ ሃኪሙ ከልቡ ይስቅ ጀመር። ወንድሜ በመገረም ሃኪሙን ትኩር ብሎ ሲያየው፤ በልጅነት አብሮ የተማረ ጓደኛው ነበር። ደነገጠ፡፡…
“ውይ! አንተ ነህ እንዴ?” ብሎ ስሙን ጠራው። ተቃቀፉ፡፡ እስኪጠጋገቡ ድረስ ተሳሳሙ፡፡ ስለ ስራ፣ ቤተሰብና አንዳንድ ነገር ሲጨዋወቱ ቆይተው፤“ለካ አንተ ሆነህ ነው ህይወቴ የተረፈው! ቁም ነገረኛ ወጥቶሃልና፡፡ ድሮኮ ቀልድህና ቁም ነገርህን መለየት ያስቸግር ነበር” አለ ወንድሜ፡፡
“አንተም ባትሆን ማንንም ያለ ልዩነት የማገልገል ቃል (Hippocrates’oath) አለብኝ” አለ ጓደኛው። እኔም በተራዬ፤ “ዶክተር! በዛ ሌሊት ያንን ደም ከየት አገኘኸው?”  ብዬ ጠየኩት፡፡
“እ…እሱንማ…” ብሎ ሃኪሙ በጣም ሳቀ፤ “እሱንማ ከሪሰርች አጋሬ ነው የቀዳሁት”  
“እውነትክን ነው? እሱንም ማመስገን እፈልጋለሁ፤ የት ነው እማገኘው?” ጠየቀ ወንድሜ፡፡
“ምንም አያስፈልግም፡፡ ምስጋና ምን እንደሆነ አታውቅም” መለሰ ሃኪሙ፡፡
“ሴት ናት እንዴ? እሷንማ ሳላያት አልሄድም” አለ ወንድሜ፤ሳቁን እያጀበው፡፡
“ምስጋና አታውቅም አልኩህ’ኮ”
“የራሷ ጉዳይ ነው”
ሃኪሙም “እሺ ኑ” ብሎ እየመራን ወደ አንድ ግቢ ወሰደን። በሩን ሳይከፍት ወደ ውስጥ በእጁ እያመላከተ፤“ታያታለህ ያቺ ፈንጠር ብላ የቆመችው፣ ጥቁሯ--- እሷ ናት የለገሰችህ” አለው፤ እኔን ባይኑ እየጠቀሰኝ፡፡ ሳቄን ለቀቅሁት። ወንድሜ ግን “ምን?!” ከማለት ሌላ ቃል ሳይጨምር ራሱን ይዞ ተዘረፈጠ፡፡ …ማን ትሆን?
***
እንደ ዓይንና አፍንጫችን፣ እንደ እጅና እግራችን የምናውቀውን እውነት ከሌሎች ስንሰማ እንበሽቃለን፡፡ አብሮ አደጋችን እንኳ “አንተ ሰነፍ ተማሪ ነበርክ፣ እኛ ስንዋኝ አንተ ትፈራለህ፣ ቁጭ ብለህ ታየን ነበር ወዘተ” ቢለን ቅር ይለናል፡፡ እንቀየማለን፡፡ “አያቶችህ እንደዚህ ናቸው፤አንተ ግን የዘር ድርጅት ታጫፍራለህ ወዘተ--” ዓይነት ጫን ያለ ነገር ከተናገርንማ ነገር ተበላሸ፡፡
ወዳጄ፡- እያንዳንዱ ሰው ራሱን ሆኖ የተፈጠረበት፣ ራሱን ሆኖ እሚኖርበት የተለያዩ ተፈጥሯዊ፣ ሰው ሰራሽና አካባቢያዊ እንዲሁም አለማቀፋዊ ምክንያቶች ብዙ ናቸው። እያንዳንዱ ሰው በአካልም ሆነ በአእምሮው ከሌላው ይለያል። ሁሉም የየራሱ---ሁሉም ደግሞ አንድ ላይ የሚመሳሰልበትና የሚለያይበት ስነ ልቡናዊ ባህሪ አለው፡፡ በየጊዜው የሚለዋወጠው ውስጣዊ ቅድስናና አውሬነቱ ብቻ ሳይሆን ጥበበኞቹ እንደሚሉት፤ የፊት መልኩ እንኳ ግራና ቀኙ ይለያያል፡፡ ስለዚህ ሰው ራሱን በሆነበት፣ ራሱን ባገኘበት መንገድ እንደ ተፈጥሮ ፀጋ፣ እንደ ተፈጥሮ ባህሪ ከእነ እንከኑ ቢገኝ የሱ ስህተት አይደለም። ሰው እንደ ሃሳብ ራሱን ካልሆነ ግን ችግር ነው። ሰው ከእንስሳት የሚለየው በስልጣኔውና በእውቀቱ ነወ፡፡
“ሰው ኑሮውን ይመስላል” ሲባል እያንዳንዱ ግለሰብ በመኖር ውስጥ ያለውን ቦታ የያዘው በፍላጐቱ ወይም በግዴታ ሊሆን ይችላል። ሰው በእግሩ የሚሄደው ጫማ ስላጣ ወይም በጫማ የሚራመደው ጫማ ለማድረግ ተገዶ ከሆነ፣ ጉዳዩ የመምረጥና ያለመምረጥ ሳይሆን የመገደድና አማራጭ ያለመኖር ይሆናል፡፡ ኑሮው እማይፈልገውን እንዲሆን አድርጐታል፡፡ የማይፈልገውን ሆኖ ሲኖር ደግሞ የሚፈልገውን ተገዶ ይዘነጋል፡፡ በትንሽ ቦታ ተከልሎ የኖረ፣ የሰው ጠረን የለመደ አንበሳ፤ በጫካ ከሚኖሩት ዘመዶቹ ቢቀላቅሉት አይመቸውም፤ ይሸሻል፡፡ በአንድ ወቅት ሳይፈልግ የተጫነበት ባህሪ፤ የአሁኑ እሱነቱ “ኑሮ” ሆኗል፡፡ ኑሮ ከመሆንና ካለመሆን ልማድ አልፎ የማሰብና ያለማሰብ ጉዳይ ነው፡፡
“ሰው ኑሮውን ሳይሆን ሃሳቡን ይመስላል” (a man is what he thinks) ሲባልም አንዱን ከሌላኛው መነጠል ያስቸግራል። ሐሳብን መምሰል የሚያፈነግጠው እንደ ኑሯችን ፈቅደንም ሆነ ተገደን የምንለምደው፣ ከለመድነው በኋላ የማንገላገለው መሆኑንና አለመሆኑን ስለምናረጋግጥበት ነው፡፡ መሆን ስንል በቀላሉ ማገናዘብና ምክንያታዊነት ሲሆን አለመሆን ደግሞ አለማገናዘብና ኢ-ምክንያታዊነት ይሆናል። ሁለቱ የአስተሳሰብ መንገዶች የተራራቁ መዳረሻ አላቸው፡፡ ሚሊ ሜትርና ኪሎ ሜትርን ቀላል ምሳሌ አድርገን የያንዳንዳችንን የህይወት ጉዞ በማሰብ አቅማችን ልክ እንደሚወሰን መረዳት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ኤግዚስተንሺያሊስቶች፤  “ሰው ሃሳብ ነው፣ እስኪሞት ድረስ ይለዋወጣል” ይላሉ፡፡
***
ወደ ትረካችን ስንመለስ፡- ወንድሜ ደም የለገሠችውን ካላየሁ ሞቼ እገኛለሁ በማለቱ ከቀልደኛው ሃኪም ጋር ተያይዘን ላቦራቶሪው ወደሚገኝበት ግቢ ማምራታችንን፣ እዛም እንደደረስን ሃኪሙ በአጥሩ በኩል ወደ ውስጥ እያመለከተ፤ “ያቻትና” በማለት ለጋሿን እንዳሳየን፣ እኔና ሃኪሙ ስንስቅ፣ ወንድሜ እንደወደቀ ተጨዋውተናል። በግቢው ውስጥ ያየናቸው የተለያዩ እንስሳት ነበሩ፡፡ የወንድሜ ደም የተቀዳው ከአንዲት ፍየል እንደሆነ ነበር ጓደኛው ያመላከተን። እውነቱን ይሁን ቀልዱን እስከ ዛሬ አልነገረንም፡፡
ወዳጄ፡- እኔ እንደሚገባኝ “ደም” ማለት ውሃና ምግብ ነው። በየጊዜው ቢቀዳና ቢፈስ ተመልሶ ይተካል፡፡ ወተት፣ አሳ፣ እንቁላል፣ ሥጋ የሚበላ ሰው የእንስሳ ደም የለብኝም ማለት አይችልም። በአራት ክፍል ቢመደብም በዓለም የሚኖሩ ህዝቦች ደም ተመሳሳይ ነው፡፡ የኔ ወንድም ብረት እየበላ እንደሚኖር ሰው፣ መደናገጡ ማሰብ ያለመቻሉ መገለጫ ይመስለኛል፡፡ ወዳጄ አንድ ነገር ልብ በልልኝ፤ “ኤትኒሲቲ”ን ከደም ጋር ማወራረስ ለኔ ስህተት ነው። “ኢትዮጵያውያኖች በደማቸው ውስጥ አልበገርነት አለ” ሲባል “አልበገር” የሚባል ኬሚካል ደማቸው ውስጥ ይገኛል ማለት አይደለም። ዘረኝነት ሃሳብ ነው፡፡ ሂትለር እንደሚለው፤ ሲቆሽሽ ወይም ሲያረጅ ፋሽኑ እንዳለፈበት ያረጀና የተቀደደ ልብስ ይጣላል፡፡ ካስፈለገ ደምም በህክምና ጥበብ ይቀየራል። ዘርና ደም አንድ ቢሆን ውጭ ሃገር ለህክምና እየሄዱ ደማቸውን የሚያስቀይሩ ዘመዶቻችን ምን ሊባሉ ነው ?
በነገራችን ላይ በአንዳንድ “ኋላቀር” ማህበረሰቦች፤ የእንስሳት ደም መጠጣት፣ የረጋውን ጠብሶ መብላት እንደ ዋና ምግብ ይቆጠራል፡፡ ለመሰናበቻ----
“…እኔን “እኔ” የሚያረገኝ
አለመስማማቴ’ኮ ነው
‘ሚያስማማ ነገር ከሌለኝ
ወላ ማንም ይሁን ማን
ከራሱ ከግዜርም ቢሆን” ይልሃል---ፀሐፊው፡፡
(Man for himself - Eric From)    
ሠላም!!


Read 1176 times