Monday, 10 December 2018 00:00

ሴቶችን የማብቃት ፋይዳው!

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

 ከዘጠነኛ ክፍል ትምህርቷን አቋርጣ በግለሰብ ት/ቤት ውስጥ በፅዳት ሰራተኛነት ተቀጥራ ስትሰራ አመታትን ላስቆጠረችው ወ/ሮ ትዕግስት እጅጉ፤ የምትመራው ህይወት ከፈጣሪ ተሰፍሮ የተሰጣት፣ በእሷ አቅምና ችሎታ ሊሻሻል የማይችል አድርጋ የቀተበለችው ነበር፡፡ ከምትሰራበት ት/ቤት በሚከፈላት 400 ብር ወርሃዊ ደመወዟ በግንበኝነት የቀን ስራ አነስተኛ ገቢ የሚያገኘውን ባሏን በገቢ በማገዝ፣ ሶስት ልጆቿን ለማሳደግ ለዓመታት ታትራለች፡፡ ኑሮዋ ከእጅ ወደ አፍ ሆኖባት፣ ልጆቿን እንኳን አጥግባ ማብላት በተሳናትና ተስፋ በቆረጠችበት ሰዓት ነው የሴቶች ራስ አገዝ ቡድን ወደምትኖርበት አዳማ ከተማ መምጣቱን የሰማችው፡፡
ቡድኑ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶችን በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ ኑሮና በአመለካከታቸው እድገት እንዲያመጡና ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ብሎም ማህበረሰቡን እንዲጠቅሙ ለማድረግ የሚያስችል የአቅምና የስልጠና ድጋፍ ያደርጋል። ይህንን ጉዳይ የሰማችው ወ/ሮ ትዕግስት፤ በቡድኑ ውስጥ ታቅፋ አመታትን ከኖረችበት የድህነት ህይወት ለመላቀቅ፣ ራሷን የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስና ልጆቿን ለማስተማር የሚያስችላትን እገዛ ለማግኘት ተመኘች፡፡ የቡድኑ አባል ለመሆን ተመዘገበች፡፡ ትዕግስት ከሴቶች ራስ አገዝ ቡድን በመጀመሪያ ያገኘችው ነገር ራሷን መለወጥ እንደምትችል የሚያሳያትን የአመለካከት ለውጥ ነበር፡፡
“መቻልን የተማርኩት ከሴቶች ራስ አገዝ ነው፤ ውስጤ የነበረውን አቅም እንዳወጣ አድርጎኛል፤ የፈለኩትን መስራት እንደምችል ራስ አገዝ አንቅቶኛል” ትላለች - ወ/ሮ ትዕግስት፡፡ በራስ አገዝ ቡድን ያገኘችው ስልጠናና ድጋፍ ከራሷ አልፋ የሌሎች ችግርና ጥቃት እንዲሰማትና እነሱን ለማገዝ እንድትነሳሳ አቅም ሰጥቷታል፡፡ ዛሬ ወ/ሮ ትዕግስት የራሷን የመኖርያ ቤት ሰርታ፣ ህመምተኛ ባሏን በመደገፍ፣ ልጆቿን በአግባቡ ለማሳደግ የምትችል ሴት ሆናለች፡፡ ከኢኮኖሚያዊ ለውጧ ባሻገር በቤት አስተዳደር፣ በትዳር ጉዳዮችና በልጆች አስተዳደግ ላይ ያላት አመለካከት ተቀይሯል - እንኳን ለራሴ ለሰው እተርፋለሁ ትላለች፡፡
እንደ ወ/ሮ ትዕግስት እጅጉ ሁሉ በሴቶች ራስ አገዝ ቡድኖች እየታቀፉ ኑሮአቸውን የለወጡ፣ ራሳቸውን የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ የቻሉ በርካታ ሴቶችን በአገር አቀፍ ሴቶች ራስ አገዝ ቡድኖች በዓል ላይ አግኝቻቸው ነበር፡፡ በዓሉ በአገራችን ለስድስተኛ ጊዜ ባለፈው አርብና ቅዳሜ የደቡብ ክልል ዋና ከተማ በሆነችው ሃዋሳ ከተማ ላይ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡
በአዲስ አበባ፣ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ነዋሪ የሆነችውና በሴቶች ራስ አገዝ ቡድን ውስጥ ታቅፋ በኑሮዋ አስገራሚ ለውጥ እንዳገኘች የነገረችኝ ወ/ሮ ጠይባ ያሲን፤ በዚህ ቡድን ውስጥ በቆየችባቸው ዓመታት ከትንሽ ቁጠባ ተነስቶ ራስን መለወጥና ኑሮና ማሻሻል እንደሚቻል መማሯንና በህይወቷም ከፍተኛ መሻሻል መምጣት መቻሏን ገልፃልኛለች፡፡ የራስ አገዝ ሴቶች ቡድኑ ከኢኮኖሚያዊ መሻሻል በተጨማሪ በአካባቢው ህብረተሰብ ህይወትና ኑሮ ላይ ሴቶች የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ አስችሏቸዋል፡፡
በአካባቢያቸው በተለያዩ መንገዶች ጥቃት የሚደርስባቸውን ህፃናትና ሴቶች ለመታደግ የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ ስፍራው በርካታ ህገ ወጥ ተግባራት የሚፈፀምበት እንደመሆኑ መጠን በሴቶች ራስ አገዝ ቡድን ውስጥ የታቀፉት ሴቶች እነዚህን ህገ ወጥ ተግባራት በመከላከልና ልጆች ወደነዚህ ተግባራት እንዳይሄዱ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸውም ነግረውኛል፡፡
በበዓሉ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ሱካሬ ሹዳ እንደገለፁት፤ የሴቶችን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመቅረፍ፣ ሴቶችን በራስ አገዝ ቡድን በማደራጀት እራሳቸውን ብሎም ቤተሰባቸውን እንዲሁም አካባቢያቸውን ለመቀየር እንዲችሉ ማገዝ የሁሉም ዜጋ ግዴታ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የራስ አገዝ ቡድን አሰራር ድርጅቶች (Cosap) የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሙሉጌታ ገብሩ በበኩላቸው እንዳሉት፤ 28 የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በ Cosap ውስጥ አባል ሆነው በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ,፣ በቤኒሻንጉል,፣ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባና በድሬዳዋ መስተዳደሮች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶችን በራስ አገዝ ቡድን በማደራጀት፣ ራሳቸውንና ማህበረሰቡን እንዲጠቅሙ በማድረግ ሂደት ላይ ይገኛል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ እስከ አሁን 230 ሺህ ሴቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ እነዚህ ሴቶች ከገቢያቸው ላይ በመቆጠብ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ይዘዋል። በዚህ ሳቢያም 526 ሺህ የሚሆኑ ልጆቻቸውን ህይወት ለመለወጥ ችለዋል ብለዋል፡፡
የራስ አገዝ ቡድን ድርጅቶች ህብረት (ኮሳፕ) ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ አካሉ፤ ሴቶች ራሳቸውን እንዲያበቁ በማገዝ፣ የሴቶችንና ህፃናትን ህይወት እንዲለወጥ በማድረጉ ረገድ እያከናወኑ ያሉት ተግባር ውጤታማ መሆኑን ጠቁመው፤ ከ230 ሺህ በላይ ሴቶች በቡድን ተደራጅተው፤ ከገቢያቸው በመቆጠብ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል እንዲኖራቸው ማድረግ ተችሏል፡፡ በተገኘው ለውጥ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸውና የሴቶችን ህይወት ለመለወጥ የሚደረገውን ጥረት ይበልጥ በማስፋፋትና በማጠናከር በርካታ ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ዕቅድ እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡ ሴቶችን ማብቃት ህብረተሰብን ማብቃት ነው ይባል የለ!

Read 601 times