Monday, 10 December 2018 00:00

“አር ዩ ስቲል ኢን ዋን ፒስ?”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
“አር ዩ ስቲል ኢን ዋን ፒስ?” ይላል ፈረንጅ። አለ አይደል… በየቦታው ሜዳና ተራራ ለመቆራረስ የሚሞከርበትና በትልቅነቱ ‘ከአፍሪካም፣ ከዓለምም አንደኛ’ የሆነ መቀስ ለመሥራት  እየተሞከረ ስለመሰለን … እዚህም ማዶ፣ እዛም ማዶ ላላችሁ ሁሉ… “አር ዩ ስቲል ኢን ዋን ፒስ?” እንላለን፡፡ ከሆናችሁ፣ እንደዛው ያቆያችሁማ!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ ጥያቄ አለኝ፡፡
አንድዬ፡- ጭራሽ! እንደው ለአፍህ እንኳን “እንዴት ከረምክ?” ሳትለኝ ዘለህ ጥያቄ አለኝ ትላለህ!
ምስኪን ሀበሻ፡- ይቅርታ አንድዬ፣ ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ ስለሆነብኝ ነው፡፡ ጨርቄን አስጥሎኝ ሊያስኬደኝ ጫፍ ስለደረሰ ነው፡፡
አንድዬ፡- ስንቴ ነው ጨርቅህን የምትጥለው? ከዚህ በፊትም ጨርቄን ልጥል ነው ስትለኝ አልነበረም እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ የከዚህ በፊቱ ከልቤ ሳይሆን የአንተን ሆድ ለማራራት የምለው ነበር። የአሁኑ ግን መመለሻ የሌለው የምር ነው፡፡
አንድዬ፡- እሺ በል ጥያቄ ያልከውን ጠይቀኝ። ደግሞ መልሱን ብስት “ደጅ ሄደህ ሳማ ቀጥፈህ አምጣ፣” እንዳትለኝ! መቸም ዘንድሮ “እኔም አንድ ሰሞን እንዲህ አድርጎኝ ነበር” የሚለውን ተረት ረስታችሁታል፡፡ ወደ ጥያቄህ…
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ከአንተ መዝገብ ቤት የምንፈልጋቸው አጣዳፊና አንገብጋቢ ሰነዶች አሉ፡፡
አንድዬ፡- ሰነዶች ነው ያልከኝ?
ምስኪን ሀበሻ፡- አዎ አንድዬ፣ ሰነዶች ነው ያልኩት። አንተ ዘንድ ያሉትንና መሬቱን እየከፋፈልክ ሊዝ የሰጠህባቸውን ሰነዶች  በሙሉ እንፈልጋለን፡፡
አንድዬ፡- ዛሬ ደግሞ ጭራሽ ለየላችሁ ማለት ነው! ለነገሩ ድሮም ይቺ ቀን እንደምትመጣ እጠረጥር ነበር።
ምስኪን ሀበሻ፡- ምኑን ነው የጠረጠርከው አንድዬ?
አንድዬ፡- አንድ ቀን ለይቶላችሁ የእኔንም ፈጣሪነት ሁሉ ረስታችሁ የምታደርጉትን እንደሚያሳጣችሁ አውቄው ነበር፡፡ ግን እንዲህ ፈጥናችሁ እዛ ደረጃ ላይ ትደርሳላችሁ አላልኩም ነበር፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ምን ብልህ ነው ይሄን ያህል የተበሳጨኸው!
አንድዬ፡- ጭራሽ የሊዝ ሰነዶች አምጣ ትሉኛላችሁ!  አንደኛችሁን አውርዳችሁ፣ አውርዳችሁ የጠጅ ጓደኛችሁ አደረጋችሁኝ!
ምስኪን ሀበሻ፡- ይህን ያህል ካበሳጨሁህ ይቅር። አንድዬ፣ ግን እኛስ ምን እናድርግ? ግራ ገባን እኮ! ያም ይነሳና መስመር አስምሮ “ከዚሀ ወዲህ የኔ ነው” ይላል፤ ያኛውም ይነሳና “ይሄኛው የኔ ነው” ይለናል፡፡ አንድዬ ግራ ግብት ነው ያለን፡፡
አንድዬ፡- መስመር ማስመር አሁን አልተጀመረ፣ ነገሩ የተበላሸው እኮ ያኔ ፈረንጅ ሸንሽኖ የሠጣችሁን የተቀባላችሁ ጊዜ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- ቆይ አንድዬ፣ መሬት ያንተ አይደለም እንዴ?
አንድዬ፡- ዓለም የእናንተ ነው። እኔንማ ቆመጥ ይዛችሁ አባሩኝ እንጂ!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እንደ ዘንድሮ አያያዛችን ምንም ብናደርግ አትገረም። ራሳችንን ማወቅ ያቃተን እየበዛን ነውና!
አንድዬ፡- እሱ ቆየ እኮ! በእናንተ መገረም ከተውኩኝ ከረመ እኮ! ቆይ በተራዬ እኔ ደግሞ ልጠይቅ… እናንተ ትናንት እዚች ምድር ላይ ነበራችሁ?
ምስኪን ሀበሻ፡- ኧረ አልነበርንም!
አንድዬ፡- ነገስ እዚች ምድር ላይ ትኖራላችሁ?
ምስኪን ሀበሻ፡- አንኖርም፣ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡- ታዲያ እናንተ ምን ቤት ናችሁና ነው መሬት ላይ እያሰመራችሁ ሌላውን “ከዚህ አትለፍ፣” “ከዚህ ውልፍት እንዳትይ!” እየተባባላችሁ፣ በእኔ ግዛት ፈላጭ፣ ቆራጭ ያደረጋችሁ! እዛ አፈር ስር አኮ በየዘመናቱ በዚች ዓለም ላይ መጥተው የሄዱ የብዙ ትውልዶች ታሪኮች አሉ! እዛ አፈር ስር መስመር እንዳይሰመር፣ አገር ድፎ ዳቦ እንዳትሆን ህይወታቸውን የገበሩ ትውልዶች አጽም እኮ ተከምሮበታል! ከምድር በላይ ያለውን ብትንቁ እንኳን ከምድር በታች ያሉትን አጽሞች ጡር አትፈሩም?
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እኔም እኮ የብዙዎችን ብሶት ይዤ አመጣጤ፣ አንዱም ይሄ ነገር ግራ ስለገባን ነው። ምን ጉድ መጣብን? “ከድንበር ወዲህም፣ ከድንበር ወዲያም ከስር ሆነው የሚቆሰቁሱ ረጃጅም እጆች አሉ ወይ?” እያልን ነው፡፡ አንድዬ፤ እውነቱን ልንገርህና ግማሾቻችን ዱላና ቆንጨራ እየወዘወዝን፣ ስንት ዘመን አብሮን የኖረውን ስናሳድድና ድራሽህ ይጥፋ ስንል፣ ገሚሶቻችን ደግሞ ሆድ እየባሰን ነው፡፡ አንድዬ፤ በጣም ሆድ እየባሰን ነው፡፡ እንቅቡም፣ ሰፌዱም እየነካካን፣ የእኛም ሆድ ሊጠይም ምንም አልቀረው፡፡
አንድዬ፡- በባዶ ሆዳችሁ ነው ሆድ የሚብሳችሁ…
ምስኪን ሀበሻ፡- በባዶ ሆዳችን አንድዬ፣ በባዶ ሆዳችን፡፡ እንደውም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሆድ እያስባሱን ያሉት ሆዳቸውና የባንክ ሂሳባቸው ሞልቶ የፈሰሰባቸው ናቸው እያልን ነው፡፡
አንድዬ፡- ለሀሜትማ ማን ብሏችሁ፡፡ “ብለምነው፣ ብለምነው አልሰማ አለኝ፣” እያላችሁ እኔን ሳይቀር የምታሙኝን እኮ እሰማለሁ፡፡ ቆይ እስቲ… አንድ ያልገባኝ ነገር… ያ፣ ያ ማን ነው ጢሙን እንኳን በቅጡ ሳይቆረጥ፣ ህዝብና ህዝብን ሲያቆራርጥ የኖረው…
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ብስቅ ትቆጣኛለህ?
አንድዬ፡- በእኔው!
ምስኪን ሀበሻ፡- ኧረ አይደለም፣ አንድዬ። ‘ይሄ ጢሙን ሳይቆረጥ ህዝብ የሚያቆራርጠው’  ያልከው እንዴት እንደተመቸኝ አልነግርህም፡፡
አንድዬ፡- አትንገረኝ፣ ባትነግረኝም አውቀዋለሁ። ሌላውን ከፍ፣ ከፍ የሚያደርግ ነገር ሳይሆን ሌላውን የሚሸነቁጥ ነገር ስትሰሙ ደስታችሁ ጣራ እንደሚነካ አውቃለሁ፡፡ የማልሰማችሁ እንዳይመስልህ፡፡ ሁሏንም ነገራችሁን እሰማችኋለሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እስቲ ለወደፊቱ እንድንጠነቀቅ ከሰማህብን ነገሮች ትንሽ ንገረን፡፡
አንድዬ፡- እናንተ ናችሁ የምትጠነቀቁት! እናንተ እኮ አልሳካ እያላችሁ እንጂ “ወይ ፍረድ፣ ወይ ውረድ!” እያላችሁ እያስፈራራችሁኝ፣ እኔ ላይ መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ ስንት ጊዜ ሞክራችሁ ነበር፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ እንደሱ የምንለው እኮ ተስፋ ስንቆርጥ ነው፡፡
አንድዬ፡- እኮ፣ እኔስ ምን አልኩ! እናንተ ተስፋ በቆረጣችሁ ቁጥር የእኔን ዙፋን ለመቁረጥ ያምራችኋል።
ምስኪን ሀበሻ፡- ኧረ አንድዬ፣ ይሄን ያህልም አትቆጣ…
አንድዬ፡- መቆጣቴ አይደለም… ደግ ደጉን ከመስማት ይልቅ ክፉ ክፉውን መስማት ትወዳላችሁ። የወደቀው ተነስቶ ቆመ ከምትባሉ፣ የቆመው ወድቆ ከመሬት ተደባለቀ ሲሏችሁ ነው የምትወዱት! ይሄን ትክዳላችሁ?
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እንደዛ የምንለው እኮ ለክፉ ሰዎች ነው...
አንድዬ፡- አይደለም፣ ለክፉ ሰዎች ብቻ አይደለም። ጓደኛችሁም ቢሆን፣ ዘመዳችሁም ቢሆን፣ የእናታችሁ ልጅም ቢሆን በኑሮ ከእናንተ ሻል ካለ፣ ትንሽ ያማረበት ከመሰላችሁ… እኔ በራፍ ላይ ቆማችሁ “የእሱን ጉድ ካላሳየኸኝማ!”  “እሷን ካላስለቀስክልኛማ!” እያላችሁ የወንጀል ተባባሪ ልታደርጉኝ ትሞክሩ የለ እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ ልብ ስጠና!…ደግ ደጉን የሚሠራ ልብ ስጠና!
አንድዬ፡- እኔማ ለሁላችሁም እኩል ንጹህ ልብ ሰጥቼ ነበር፡፡ ይሄ ምንድነው በምትሉት… በቫይረስ ያበላሻችሁት እናንተው ናችሁ። ቅድም ልጠይቅህ የነበረውን፤ ያ ጢሙን ሳይቆርጥ ህዝብ እያቆራረጠ ያጨራረሰው...
ምስኪን ሀበሻ፡- ማርክስ ማለትህ ነው አንድዬ?
አንድዬ፡- አዎ! እሱ ሰውዬ እናንተ ዘንድ ገብቶ እንደሁ አጣርተህ መልሱን ይዘህ እንድትመጣ፡፡ በል ደህና ሁን፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አሜን አንድዬ፣ አሜን!
“አር ዩ ስቲል ኢን ዋን ፒስ?”
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1568 times