Print this page
Monday, 10 December 2018 00:00

የምርጫ ዋዜማ ድርድር - በተፎካካሪዎች እይታ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

• ፓርቲዎቹ የጀመሩት ውይይት ትልቋን ኢትዮጵያ ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት
 • ያለን ምርጫ መሰባሰብ አሊያም ተበታትኖ ዲሞክራሲን ማጨለም ነው


    በሃገር ውስጥም የነበሩ፣ ከውጪም የተመለሱ ከ80 በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች የሃገሪቱን ፖለቲካዊ ሁኔታ ማሻሻል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከመንግስት ጋር ይፋዊ ውይት ጀምረዋል፡፡ ከሰሞኑም ሊወያዩባቸው የሚሿቸውን ጉዳዮች አወያ ለሆነው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በፅሁፍ እያስገቡ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ለመሆኑ አሁን ከመንግስት ጋር ተቃዋሚዎች የሚያደርጉት ውይይትና ድርድር ባለፉት 27 ዓመታት ምርጫ በመጣ ቁጥር ሲካሄዱ ከነበሩ ውይይቶች በምን ይለያል? ምን ውጤት ሊኖረው ይችላል? ቀጣዩ ምርጫስ ምን መልክ ሊኖው ይችላል? አሁን በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ አለመረጋጋቶች እና ግጭቶች ለምርጫው እንቅፋት የመሆን እድላቸው ምን ያህል ነው? ችግሮቹ እንዴት ይፈቱ? ተቃዋሚዎችስ ወደ 3 እና 4 ውህድ ፓርቲነት መሰባሰቡ ይሳካላቸው ይሆን?
በእዚህና ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ አንጋፋዎቹን ፖለቲከኞች አቶ አስራት ጣሴ (የቀድሞ ቅንጅት እና አንድነት ፓርቲ አመራር) እና ዶ/ር አረጋዊ በርሄ (የቀድሞ የህውሓት መስራች እና ታጋይ አሁን የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ትብብር ሊቀመንበር) የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንደሚከተለው አነጋግሯቸዋል፡፡


           ዶ/ር ዐቢይ እየተከተለ ያለው መንገድ የፅናት መንገድ ነው”
              አቶ አስራት ጣሴ (አንጋፋ ፖለቲከኛ)


    ከዚህ ቀደም በኢህአዴግ እና በተቃዋሚዎች መካከል በምርጫ ዋዜማ ላይ የሚደረጉ ድርድሮችና ውይይቶች ነበሩ፡፡ በቀድሞዎቹና በአሁኑ ውይይት መካከል ያለው መሰረታዊ ልዩነት ምንድን ነው?
በጣም ከፍተኛ ልዩነት ነው ያለው፡፡ ምክንያቱም እኔ በበኩሌ፤ ከጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በፊት የነበረውን ስርአት የህውሓት/ኢህአዴግ ስርአት አድርጌ ነው የማስበው የማምነው፡፡ ኢህአዴግም አልነበረም፤ የህወሓት አምባገነናዊ ስርአት ነው የነበረው፡፡ አሁን የሚካሄደው ውይይትና ድርድር በእኔ እይታ ህወሓት/ኢህአዴግ የሌለበት ነው፡፡ ይሄ አንዱ ልዩነት ነው። ህወሓት/ኢህአዴግ ብቻ አይደለም፤ ኢህአዴግም ቢሆን በቅርፅ እንጂ በአካል የለም ብዬ ነው የማምነው። የአሁኑ ድርድር የሚካሄደው አብዮታዊ ዲሞክራሲ በስም እንጂ በተግባር በሌለበት ሁኔታ ነው፡፡
አብዮታዊ ዲሞክራሲ በሌለበት ሁኔታ ሲሉ ምን ማለትዎ ነው---ቢያብራሩልን?
ለምሳሌ ህወሓት/ኢህአዴግ ምን ነበረ ዋናው ቋንቋቸው? የተቃዋሚ ፓርቲዎች እግር እስኪያወጡ እንጠብቃቸዋለን፤ እግር ሲያወጡ እንቆርጣቸዋለን ይሉ ነበር፡፡ አሁን አይደለም እግር መቁረጥ ይቅርና፤ ተቃዋሚ የሚለው አጠራር፣ ወደ ተፎካካሪ ተለውጦ ነው ለመቀራረብ የተሞከረው፡፡ በፊት ተቃዋሚዎች ጠላት፣ የሻዕቢያ ተላላኪዎች፣ ሃገር አጥፊዎች ስንባል ነው የከረምነው፡፡ ዛሬ እንኳን የሻዕቢያ ተላላኪ ልንባል ቀርቶ ከኤርትራ ጋር ያለው ችግር በእርቅ ተቋጭቶ፣ ኤርትራን የኢትዮጵያ አጋር አድርጓታል፡፡
ሌላ ህወሓት/ኢህአዴግ፤ ተቃዋሚዎችን ሽብርተኞችና የሽብርተኞች ጉዳይ አስፈፃሚዎች ይለን ነበር፡፡ ዛሬ ሽብርተኞች ተብለው ተፈርጀው የነበሩት ኦነግ፣ ኦብነግ፣ አርበኞች ግንቦት 7 ሃገር ውስጥ ናቸው፡፡ የኦሮሞ ሚዲያ ኔት ወርክ ሃገር ውስጥ አለ፤ ኢሳት ሃገር ውስጥ ነው ያለው፡፡ የሽብርተኝነት አዋጁ እየተሻሻለ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አሁን ያለው መንግስት ከህወሓት/ኢህአዴግ ባህሪና ጠባይ ጋር ሊቀራረብ  አይችልም፡፡ ስለዚህ ህወሃት/ኢህአዴግ በሌለበት፣ አብዮታዊ ዲሞክራሲ በቅርፅ እንጂ በተግባር በሌለበት አውድ የሚካሄድ ውይይት ስለሆነ ከቀድሞ የተለየ ያደርገዋል፡፡
በዚህ የውይይት ጅማሮ ላይ እንደተለመደው የእርስ በእርስ መፈራረጅና መወቃቀስ አልተሰማም፡፡ ማነው የተሻለ ሆኖ የቀረበው? ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወይስ መንግስት?
ይሄን ጊዜው ለወደፊት ያሳየናል፡፡ ማን ትልቅ ሆኖ እንደወጣ፣ ማን ትልቅ ሆኖ እንደቀረበ ሂደቱ ነው የሚያሳየን፡፡ አሁን ሁለቱንም ለመለካት የማይመች ሰአት ላይ ነው ያለነው፡፡
በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ሃገር ቤት ከገቡ በኋላ የሚያደርጓቸውን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች እርስዎ እንዴት ይመለከቷቸዋል?
በእነ አቶ ሌንጮ ለታ የሚመራው የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር በእነ ዶ/ር ዐቢይ ከሚመራው የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ጋር የውህደት ንግግር መጀመራቸው፣ የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ከአማራ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ጋር ውህደት መፍጠራቸው፣ አረናም ከእነ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ትብብር ጋር ለመዋሃድ መንገድ መጀመራቸው አንድ ጥሩ እርምጃ ነው፡፡ የአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ጉዞ በአንድ እርምጃ ይጀመራል አንደሚባለው፣ አሁን ያለው ጅምር ጥሩ ነው፡፡ እንደኔ እሳቤ፤ የአማራ ፓርቲ ከኦሮሞ ፓርቲ ጋር፣ የኦሮሞ ፓርቲ ከትግራይ ፓርቲ ጋር፣ የትግራይ ፓርቲ ከአማራ ፓርቲ ጋር፣ የአማራ ፓርቲ ከደቡብ ክልል፣ ከጋምቤላ፣ ከቤኒሻንጉል፣ ከሱማሌና ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር እየተደባለቁ ውህደት ቢጀምሩ ነው የምመርጠው። በየብሔሩ የተደራጀ የፓርቲ ስርአት ምንም እንኳ መብት ቢሆንም ለከፍተኛው ትግል፣ ለኢትዮጵያ መዳን፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት ሲባል ከዚህ ከክልላዊ ፓርቲነት መውጣት አለብን፡፡ የመውጫ በሩም አሁን መከፈት አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ወደፊት ልትሆነው ከምትፈልገው ቁመና ጋር የሚመጣጠን የፓርቲ አደረጃጀት ያስፈልገናል፡፡ የምርጫው ጊዜ ተራዝሞም ቢሆን በአገራችን ላይ በብሔር የተደራጁ ኃይሎች፣ በውህደት ወደ ህብረ ብሔራዊነት መለወጥ አለባቸው፡፡ በየብሔሩ መቆማቸው አደገኛ ነው፡፡ ከብሔር አልፎ ህብረ ብሔራዊ ቅርፅ ካልያዙ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚሯሯጡ ኃይሎችን የሚያግዝ ነው የሚሆነው፡፡ በዚህ ረገድ ስጋት አለኝ፡፡
ሌላው ምናልባት በቀጣዩ ምርጫ አንድ ፓርቲ ብቻውን ማሸነፍ ካልቻለ፣ የምንሄደው ወደ ጥምር መንግስት ነው፡፡ ጥምር መንግስት ደግሞ አሁን ነገሮች ባልተረጋጉበት ሁኔታ አመቺ አይደለም፤ ከፍተኛ ጉዳትም ሊያስከትል ይችላል፡፡ ስለዚህ ይህ የቤት ስራና ቅድመ ዝግጅት ከወዲሁ በጥንቃቄ መሰራት አለበት፡፡ ለዚህ ፓርቲዎቹ የጀመሩት ውይይት ትልቋን ኢትዮጵያ ታሳቢ ያደረገ፣ በሰጥቶ መቀበል ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ህዝብ የማዳን አላማ ይዞ በቅንነት መካሄድ አለበት፡፡ ከድርድሩ ለግሌ ምን አገኛለሁ የሚለውን ትተን፣ ኢትዮጵያ ምን ታገኛለች፣ ህዝብ ምን ያገኛል የሚለውን እሳቤ መሰረት ካደረገ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥሩ ውጤቶችን ማስመዝገብ ይቻላል፡፡
አሁን የተጀመረው ውይይትና ድርድር ምን ላይ ቢያተኩር ይመከራሉ? ምንስ ውጤት ይጠብቃሉ?
ድርድሩ በዋናነት በምርጫው ህግና ስርአት እንዲሁም በምርጫ ቦርድ መሻሻል ላይ ማተኮር ቢችል ጥሩ ነው። ምክንያቱም ለረጅም ጊዜ ምርጫዎችን በሙሉ ዋጋ ቢስ ያደረገው በአብዛኛው የምርጫ ቦርድ ጉዳይ ነው። ዲሞክራሲያዊ ነፃነትን ያፈኑ የፀረ ሽብር፣ የሚዲያ፣ የመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አዋጆችን ማሻሻል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በጥልቀት መወያየት ያስፈልጋል። ይሄን ማድረግ ከባድ አይደለም፡፡ የቴክኒክ ጉዳይ ነው፤ ብዙ ጭቅጭቅ የሚፈልጉም አይደሉም፡፡ በአብዛኛው በባለሙያዎችና በኮሚቴዎች ሊሰራ የሚችል ነው፡፡ አብዛኛውን ጉዳይ ለባለሙያዎች መስጠት ጠቃሚ ነው፡፡
ከምርጫው በፊት ብሔራዊ መግባባትና እርቅ መቅደም አለበት የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ የእርስዎ አቋም ምንድን ነው?
በእርግጥም እርቅና ብሔራዊ መግባባት መቅደም አለበት፡፡ አሁን ይሄ ሳይካሄድ ምርጫ ይደረግ ቢባል ለግጭት ሁኔታዎችን ሆን ብሎ እንደማመቻቸት ነው የሚቆጠረው፡፡ ለረብሻና ለግርግር በር መክፈት ነው። ለለውጡ አደናቃፊዎች ምቹ ሜዳ መስጠት ማለት ነው፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት በጣም የተበላሸ የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳ ነው ያለው፡፡ ያንን ለማስተካከል በጣም ከባድ ነው። ያ ስርአት እኮ ሰው ሳይቀር ነው ያበላሸብን፣ የሰዎችን ስነ ምግባር እኮ ነው ያበላሸብን። ይሄ ሁሉ መስተካከል አለበት፡፡ ምርጫ ደግሞ መካሄድ ያለበት ፈፅሞ መረጋጋት፣ ስርአት፣ የህግ የበላይነት፣ በህዝቦች መሃል መተማመንን፣ ከእኔ ይልቅ ሃገሬ የሚለው አመለካከት መስፈኑን ካረጋገጥን በኋላ ነው። ምርጫ የውጤት ጉዳይ አይደለም፤ ዋናው ሂደቱ ነው፡፡ ሂደቱ ውጤታማ ከሆነ፣ ውጤቱ አስጨናቂ አይሆንም፡፡ ይሄን ማድረግ ለኢትዮጵያዊያን ልሂቃንና ባለሙያዎች የማይቻል አይደለም፡፡ በዚህ መንገድ ከተሰራ በእውነቱ ውጤታማ የማንሆንበት ምክንያት አይታየኝም፡፡
በኛ ሃገር የፓርቲ ፖለቲካ ባህል ውስጥ የሊቀ መንበርነት ቦታ ትልቅ ግምት ይሰጠዋል። ከዚህ አንፃር አሁን ያሉት ከ70 በላይ ፓርቲዎች እንደተባለው ተዋህደው ወደ ሶስትና አራት የሚሰባሰቡ ይመስልዎታል?
የፓርቲዎች ወደ ሶስትና አራት መሰባሰቡ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ አለበለዚያ የምንፈልገውን የዲሞክራሲ ስርአት ምስረታ እንደገና እናዘገየዋለን፡፡ በዘገየ ቁጥር ደግሞ ዲሞክራሲ እንዲጠፋም እድል እንሰጠዋለን። ያለን ምርጫ መሰባሰብ አሊያም ተበታትኖ ዲሞክራሲን ማጨለም ነው። እዚህ ሃገር ውስጥ አዲስ ሰው የለም ሁሉም ይተዋወቃል፤ ራሳቸውንም ያውቃሉ፤ እኔ አበክሬ የምለምነው “እባካችሁ እንተዋወቃለን፤ እናንተም ራሳችሁን ታውቃላችሁ፤ ለንስሃ ጊዜ ወስዳችሁ ሰርተፍኬታችሁን መልሱና እንደ ግለሰብ ወደምትፈልጉት ፓርቲ እየሄዳችሁ አባል በመሆን፣ በጋራ ጠንካራ ፓርቲ ፍጠሩ ነው የምለው፡፡ ከዚህ በኋላ በድጎማ ቀለብ እየተሰፈረላቸው የትም መሄድ አይቻልም፡፡ እነዚህ ሰዎችን አምርረን ሳንወቅስ፣ ሰርተፍኬታቸውን እየመለሱ የፓርቲ ቁጥርን በመቀነስ አስተዋፅኦ ማበርከት አለባቸው። ይሄ ካልሆነ ምርጫ ቦርድ የፓርቲ ማቋቋሚያ ህጉን መሰረት አድርጎ፣ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ በርካቶቹ ይሄ ህግ ያስቀመጣቸውን ለምሳሌ ጠቅላላ ጉባኤ በየሁለት አመቱ ማድረግ የመሳሰለውን አያሟሉም፤ ከዚህ አንፃር ለምርጫ ቦርድ አስቸጋሪ አይሆንም፤ ነገር ግን ምርጫ ቦርድ እዚህ ተግባር ውስጥ ከመግባቱ በፊት እነሱ በራሳቸው መንገድ በሰለጠነ አኳኋን ሰርተፍኬታቸውን ቢመልሱ ለለውጡ አስተዋፅኦ እንዳደረጉ ይቆጠራል፡፡ ፓርቲ በማፍረስ ብዙ የበደሉንና ዲሞክራሲን ለጉዳት የዳረጉ ሰዎች አሉ፡፡ አሁን ጊዜው እነሱን የምንወቅስበት ጊዜ ሊሆን አይገባም። ብዙ መከራና ፈተና የከፈሉ ወገኖቼ፤ ሌሎችን ማውገዝ ትተን፣ የወደፊቱን እጃችን ላይ ያለውን ግዙፍ ስራ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ እነዚያም ወደ ህሊናቸው ተመልሰው ጉዳዩን ውስብስብ ሳያደርጉት፣ አስተዋፅኦዋቸውን ቢያበረክቱ መልካም ነው፡፡ ይሄ ከሆነ ቀሪዎቹ  ፓርቲዎች ለመዋሃድ መነጋገር መወያየት ነው የሚያስፈልጋቸው፡፡ ሃገርን አስቀድመው ከተወያዩ፣ ውህደት የመፍጠሩ ጉዳይ ይሳካል የሚል እምነት አለኝ፡፡
አሁን የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ተደርገው የተሾሙት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ቦርዱን በማሻሻሉ ረገድ የሚሳካላቸው ይመስልዎታል?
ከወ/ት ብርቱካን ጋር አብረን ሰርተናል፡፡ አብሮ እንደሰራ ሰው ስለ እርሷ መናገር የምችለው በጣም ጠንካራ የመርህ ሰው፣ ላመነችበት ነገር ጥግ ድረስ የምትገፋ ሴት መሆኗን ነው፡፡ በእውቀት ደረጃ ጥንቁቅ የህግ ምሁር፣ አሁን ደግሞ ከእውቁ ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ድግሪዋን በህዝብ አስተዳደር ጨምራበት የነበራትን ከፍተኛ እውቀትና አቅም የበለጠ አሳድጋለች፡፡ በዚህ እውቀቷና ብቃቷ ምርጫ ቦርድን እንደምታሻሽለው ሙሉ እምነት አለኝ፡፡ እርግጥ ነው ወ/ት ብርቱካን ብቻዋን መስራት አትችልም፤ ድጋፍ ያስፈልጋታል። አብሯት የሚሰራ ቡድንን የማዋቀሩ ጉዳይ ወሳኝ ነው፡፡ በተረፈ ግን የአንድነት ፓርቲ ሊቀ መንበር ስትሆን በልምድና በእድሜ የሚበልጧት ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነገር ግን የእርሷን ብርታትና ብቃት ስላየን ነው እንድትመራን የመረጥናት፡፡ ያንን እምቅ አቅምና የመሪነት ችሎታ ለመጠቀም ነበር ያኔ የመረጥናት። ዛሬም በበለጠ አቅም ኃላፊነቷን ትወጣለች የሚል ሙሉ እምነት አለኝ፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በአገራችን ታሪክ የመጀመሪያውን ነፃና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ የጓጉ ይመስላሉ። የሚሳካላቸው ይመስልዎታል?
አሁን ዶ/ር ዐቢይ እየተከተሉ ያሉት መንገድ የፅናት መንገድ ነው፡፡ በእውነት እኔ በዶ/ር ዐቢይ ውስጥ ያየሁበት ሙሉ በጎነት ነው፤ የተቀናነሰ ነገር የለውም፡፡ ሙሉ የሃገር ፍቅር ነው ያላቸው፡፡ እኛ እንኳ ሃገራችንን እንወዳለን እያልን ብዙ እንናገር ነበር፤አሁን ግን የሚበልጠን ነው የመጣው፡፡ ሃገርን በመውደድ፣ ለእውነት በመቆም፣ ለሃቅ በመቆም ከኛ የሚበልጥ መጥቷል፡፡ ሃገር ወዳድነትን በዚህ ደረጃ ሳየው ክብር እሰጣለሁ፡፡ ሃገሩን የሚወድ መሪ ደግሞ ይሳካለታል። የሚሳካለት የኛ ሙሉ አጋዥነት ስለሚጨመርበት ነው። የሁሉም አጋዥነት ከተጨመረበት ይሳካል። ሁሉም ሰው ቀና በማሰብ ብቻ ከገዛ ይሳካል፡፡ መጥፎ ነገሮችን ባለማናፈስ፣ ጥቃቅን ስህተቶችን ባለማጉላት በትብብር ከተሰራ ስኬታማነቱ ጥርጥር የለውም። በስህተት ተገፍቶ የወደቀ፣ በስህተት የታሰረ ካለ በቀናነት ነገሮችን እያየ እንዲስተካከሉ ማድረግ ነው አጋዥ የሚሆነው፡፡ በሌላ በኩል፤ ሁሉም ጉዳይ በአንድ ጀምበር ይፈፅሙ እያሉ ጥያቄ ማንጋጋትና ምላሽ መጠበቅ አያስፈልግም፡፡ አሁን ያለንበትን ሁኔታ ከሁለትና አንድ አመት በፊት ከነበርንበት ሁኔታ አንፃር ነው መመልከት ያለብን፡፡ በዚህ በኩል እኛ ካገዝነው፣ ዶ/ር ዐቢይ የፅናት መሪ እንደመሆኑ፣ የፈጣሪ ድጋፍ የሁላችንም አቅም ተጨምሮበት ይሳካል፡፡ አለመሳካት ማለት እኮ ሁላችንም ተያይዘን ጠፋን ማለት ነው፡፡ ለሁላችንም ውድመት ነው፡፡ ይሄ ጉዳይ አማራጭም ሊሰጠው አይገባም፡፡ መቶ በመቶ መሳካት አለበት ብለን ነው፣ ለአጨናጋፊ ተግባሮች የ1 በመቶ እድል እንኳ መከልከል ያለብን፡፡ ይሳካል፤መሳካቱም አማራጭ የለውም፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ እያለን ዛሬም በግጭቶች የሰው ህይወት እየጠፋ ነው፡፡ ይሄ ሁኔታ ስጋት አይፈጥርም?
ስጋት ምንጊዜም ይኖራል፡፡ ስጋት የሌለበት ህይወት የለም፡፡ ነገር ግን በስጋት ውስጥ ስኬታማ መሆን ይቻላል፡፡
እንዴት?
አንደኛ፤ በተለይ ለጠረፍ አካባቢ ክልሎች ልዩ ትኩረት መስጠት ነው፡፡ በቤኒሻንጉልና አፋር ልክ በሶማሌ ክልል እንደተደረገው፣ ወደ ጥሩ ሁኔታ እንዲመጣ ከወዲሁ መስራት ያስፈልጋል፡፡ እኔ ዶ/ር ዐቢይ ያለበትን አጣብቂኝ እረዳዋለሁ። በሁለት መንገድ ነው አጣብቂኝ ውስጥ የገባው። ዝም ቢባል፣ ሌቦችንና በዳዮችን ለህግ አላቀረበም ይባላል፤ በሌላ በኩል ህግ ላስከብር ብሎ ሲንቀሳቀስ ደግሞ በህዝብ መሃል ውዥንብር እየተነዛ ብሔር ተጠቃ ይባላል። ይሄ ከባድ አጣብቂኝ ነው፡፡ አሁን ጠ/ሚኒስትሩ የያዘውን የትዕግስት መንገድ ማድነቅ ነው ያለብን፡፡ የህዝብ ግጭት እንዳይፈጠር ትዕግስት ያስፈልጋል፡፡ ለኔ የተያዘበት የትዕግስት መንገድ፣ አንዱ የትግሉ ስልት ነው፡፡ በተቻለ መጠን በቀላሉ የግጭት መግቢያ የጓሮ በር የሆኑ አካባቢዎች ላይ ትኩረት ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን በችኮላ ሳይሆን አሁን በተያዘው የትዕግስት መንገድ ነው መኬድ ያለበት፡፡ ዶ/ር ዐቢይ እንዳለው፤ አብዮት ማካሄድ ቀላል ነው፣ ሪፎርም ማካሄድ ግን አንዱ ከባድ ገፅታው አሁን ያለው ጉዳይ ነው፡፡ የትዕግስትና የፅናት መንገድ ደግሞ በጣም አድካሚ ነው፤ ውጤቱ ግን በረከት ነው፡፡ የሰው ደም ዛሬም መፍሰሱ በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ ነገር ግን ሁሉም በትዕግስት ነው መያዝ ያለበት፡፡ ክፉ ሰዎችም ባሉበት ምድር ነው የምንኖረው፡፡ ትዕግስቱና ፅናቱ ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው፡፡  


---------


                  “አሁን የለውጥ ሃይሎችና እኛ መሃል ላይ ተገናኝተናል”
                       ዶ/ር አረጋዊ በርሄ (አንጋፋ ፖለቲከኛ)


     እርስዎም ተሳታፊ የሆኑበት የተፎካካሪ ፓርቲዎችና የኢህአዴግ ውይይትና ድርድር ተጀምሯል፡፡ ጅማሮውን እንዴት አገኙት?
ሁላችንም እንደምናውቀው በፊት የነበረው የኢህአዴግ አመራር አምባገነንነት የሠፈነበት፣ የግሉን አስተሳሰብ በህዝባችን ላይ መጫን እንጂ የህዝቡ ሃሳብ ምን እንደሆነ እንኳ የማይታወቅበት፣ ህዝቡ የሚፈልገውን ነገር እንዲያደርግ የሚፈቅድ አልነበረም፡፡ አሁን ግን ከለውጡ ወዲህ ሃሳቦች በነፃነት እንዲንሸራሸሩ እድል ተከፍቷል፡፡ ይሄ እድል ደግሞ በትግል የመጣ ነው፡፡ የለውጥ አራማጆቹ ከፊት ሆነው ይምሩት እንጂ የመጣው ለውጥ ከህዝብ ግፊት ነው። አሁን የመንግስትነትን ቦታ የያዙት ሰዎች ኢህአዴግ ናቸው ለማለትም ከባድ ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን ራሣቸው ኢህአዴግ ነን ስለሚሉ፤ ኢህአዴግ ናቸው፡፡ ነገር ግን ኢህአዴግ እንዳልሆኑ ሁኔታውን ለሚከታተል ሰው ያስታውቃል፡፡ ከኢህአዴግ ፕሮግራም አንፃር የእነሱ የተለየ ነው፡፡ ኢህአዴግ ከተቃዋሚዎች ጋር የነበረውን የመፈረጅ ግንኙነት አሽቀንጥረው ጥለው በሀገራችን ጉዳይ ሁላችንም እኩል መደራደር እንችላለን ማለታቸው የተለየ ያደርገዋል፡፡ ለምሣሌ በምርጫ ቦርድ አወቃቀርና ህግ ላይ የሁላችንም ግብአት እንዲኖር ተነጋግረናል፡፡
ሁላችንም ያመንንባት ወ/ት ብርቱካንም ቦርዱን እንድትመራ ተሹማለች፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ለዚህ ሹመት ሲያጭዋት እኛን አማክረውናል፡፡ እነዚህ ለውጦች ከዚህ ቀደም ከነበረው በእጅጉ የተለዩ ናቸው፡፡ በርካታ በውጭ የነበርን ፓርቲዎችም ወደ ሀገር ውስጥ ገብተን የመንቀሳቀስ እድል አግኝተናል፡፡
በውይይቱ ጅማሮ  ማነው የተሻለ ሆኖ የቀረበው? ተቃዋሚዎች ወይስ መንግስት?
እውነት ለመናገር ኢህአዴግ ውስጥ የነበሩና ለውጡን የመሩ ሰዎች፤ የተሻለ አቋም ይዘው መጥተዋል፡፡ እኛ ውጪ ሆነን ስንጮህለት የነበረውን አቋም ተግባር ላይ ማዋል አልቻልንም ነበር፡፡ እነዚያ ስንጮህላቸው የነበሩ አቋሞች ግን እነዚህ የመንግስት ሰዎች አራምደው፣ ወደፊት ገስግሰው መጡ፡፡ ከዚያ መሃል ላይ ተገናኘን ማለት ነው፡፡ አሁን በአቋሞቹ ላይ ተገናኝተናል፡፡ ለእነዚህ አቋሞች ሁሉም የበኩሉን ትግል አድርጓል፡፡ በዚህ ሂደት መንገድ ላይ የተገናኘን ይመስለኛል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ “በሀገሪቱ የበሰለ ፖለቲከኛም ፖለቲካም የለም፤ ቢኖር ኖሮ ፍሬው ህዝቡ ላይ ይታይ ነበር” ብለዋል፡፡ እርስዎ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
የፖለቲካ ነፃነት በሌለበት ሁኔታ ህዝብ የአፈና አገዛዝ ውስጥ ነው የሚሆነው፡፡ ሃሳቡን ሊገልጽና ሊደራጅ፣ በአስተሳሰብ ሊበለጽግ አይችልም። ካልተወያየ፣ የሚበጀውን ሃሳብ ነጥሮ እንዲወጣ ካልተደረገ እንዴት ታዲያ የበሰለ ፖለቲካ መፍጠር ይቻላል?  አይቻልም፡፡ ኳሱ እኮ የሃሳብ ነፃነት ነው፡፡ አለምን እየለወጠ ያለውስ የሃሳብ ነፃነት ነው፡፡ ሃሳብ ነው ለምን የሚመራው፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ሃሳብ ስንት ሚሊዮኖችን እያንቀሳቀሰ ነው፣ የማርክስ ሃሳብ ሚሊዮኖችን ያንቀሳቅሳል፡፡ ዛሬ እነዚህ ሰዎች የሉም፤ ሃሳባቸው ግን ሚሊዮኖችን እየመራ ነው፡፡ ስለዚህ እስካሁን ድረስ ገዥው ፓርቲ ሲያደርግ የነበረው ሃሳብ በነጻነት እንዳይንሸራሸር ማፈን ነበር፤ አሁን ተፈትቷል፡፡ ስለተፈታ መንቀሳቀስ ተጀምሯል፤ ህዝቡም ትንሽ ሃሳብ እያገኘ ነው፡፡ ሁሉንም ችግሮች ለመቅረፍ ግን ትንሽ ጊዜ ይጠይቃል፡፡ ሃሣብን በማንሸራሸር ደግሞ ሚዲያ ትልቅ ሚና ነው የሚጫወተው፡፡ ለዚህ የሚበጅ ስርአት መፍጠር አለብን፡፡ ይሄ አለመኖሩ ነው ችግር ውስጥ ያቆየን፡፡ አሁን ጥሩ ፖለቲከኛና በፖለቲካ የበሰለ ማህበረሰብ የመፍጠሩ ጉዞ የተጀመረ ይመስለኛል፡፡
ፓርቲዎች ወደ ሶስትና አራት ተሰባሰቡ እየተባለ ነው፡፡ ከኛ ሀገር የፓርቲ ፖለቲካ ባህል አንጻር ይሄ የሚሳካ ይመስልዎታል?
ይሄ ከባድ ስራ ነው፡፡ በቀላሉ መሰባሰብ አይቻልም። ነገሩ ቀላል አይደለም፡፡ ስር የሰደደ የእኔነት፣ የግልን ሃሳብ የማራመድ ባህል ነው ገንኖ የቆየው፡፡ በአንፃሩ ሀገራዊ አጀንዳን በጋራ የማራመድ ባህል አልዳበረም፡፡ ነገር ግን የሃሳብ ፖለቲካን የሚያወቁ ሰዎች እየተሰባሰቡ፣ የመስጠትና መቀበል መርህን አራምደው፣ ለሁላችንም የሚጠቅም ስርአት ሊመሠርቱ ይችላሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ የሰጥቶ መቀበል አመለካከት ያላቸው አካላት ተሰባስበው መስራት ከጀመሩ ለግላችን ብቻ እንቆማለን የሚሉ ሃይሎች እየከሰሙ ይሄዳሉ፡፡ ህዝቡም የሚፈልገው ወጣቱም የሚፈልገው ይሄ ስለሆነ ተሰባሳቢ ሃይሎች የበለጠውን ድጋፍ ያገኛሉ፡፡ በዚህ መንገድ ከግቡ መድረስ ይቻላል።
ከዚህ በፊት በአንድነት የመሰባሰቡ ባህል ባልዳበረበት ሁኔታ ምርጫው አንድ አመት ከ6 ወር በቀረው ሁኔታ ምን ያህል መጓዝ ይቻላል?
በቁርጠኝነት ለመናገር ይከብደኛል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይሄ ነገር እውን ይሆናል አይሆንም ለማለት ይቸግረኛል፡፡ ነገር ግን ምሁሩ ወገን እያወቀው ስለሄደ በጽናት ከተንቀሳቀሰ መንግስትም አዎንታዊ ግፊት ካደረገ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውህደቶች እውን ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለሀገሪቱ መረጋጋትና እድገት ቀና አመለካከት ያላቸው ወገኖች በሙሉ እንዲሰባሰቡና አብረው እንዲሠሩ ከተደረገ ውጤት ይመጣል፡፡ ከዚህ ውጪ ሌላ አማራጭ የለንም፡፡ ያለው አማራጭ ተያይዞ መጥፋት ብቻ ነው፡፡ ይሄ እንዳይመጣ አሁን ያለውን እድል በቀናነት መጠቀም ያስፈልገናል፡፡
በተለያዩ መድረኮች በአማራና በትግራይ የፖለቲካ ልሂቃን መካከል ያለውን መካረር እንዴት ያዩታል?
ልክ ነው መካረሩ አለ፡፡ በስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች የሚያካርሩት ነገር እንዳለ አውቃለሁ፡፡ ለምንድነው የሚያካርሩት? የህዝቡን ስሜት በመቀስቀስ ጽኑ መሠረት የሌለው ድጋፍ ለማሰባሰብ ይመስለኛል። ይሄ አደገኛ አካሄድ ነው፡፡ ለማንም አይጠቅምም። በእርግጥ ይህ ሁኔታ ቀደም ብሎ ካበበው መጥፎ የፖለቲካ ባህላችን ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የጥቅም ጉዳይም አለበት፡፡ በጣም ውስብስብ ጉዳይ ነው፡፡
ይሄ ችግር እንዴት ነው ሊቀረፍና ሊስተካከል የሚችለው?
ይሄን ችግር ለመቅረፍ በጐ አመለካከት ያላቸው ወገኖች በሙሉ አብሮ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ አንዱ በአንዱ ላይ ጣት መቀሠር አያዋጣም፡፡ ጣት በመቀሳሰር አሸናፊ የሚሆን የለም፡፡ ተያይዞ መጥፋት ነው፡፡ ሁቱና ቱትሲ ሲጨፋጨፉ ሁለቱም ወገኖች ናቸው የሞቱት፡፡ እርግጠኛ ነኝ ወደዚህ አንገባም፤ ነገር ግን ሁኔታውን ከወዲሁ ልንቆጣጠረው ይገባል። ምክንያቱም የሚጐዳው ሁሉም ህዝባችን ነው። ስለዚህ ችግሮች ካሉ በሰከነ መንገድ ተቀምጦ በመወያየት መፍታት እንጂ እዚህና እዚያ ሆኖ ለከንቱ የፖለቲካ ጥቅም ማጋበሻነት የህዝብን ስሜት መጠቀም ተገቢ አይሆንም፡፡ ይሄን ለማድረግ ደግሞ አሁን ችሎታውም በእጃችን ነው ያለው፤ ያንን መጠቀም አለብን፡፡ ስለዚህ ችግሩን በውይይትና በንግግር በቀላሉ መፍታት ይቻላል፡፡
በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎችም የሰው ህይወት እየቀጠፉ ያሉ ግጭቶች እየተከሰቱ ነው፡፡ እነዚህ ግጭቶች እንዴት ነው ሊቆሙ የሚችሉት?
በየአካባቢው ግጭት አለ፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች ባስ ብለውም ወደ አውዳሚነት እየተሸጋገሩ ነው፡፡ ግጭቶቹ ለምን? ከምን? እንደተነሱ እናውቃቸዋለን፡፡ ከአያያዝ ጉድለት ባለፉት 27 ዓመታት የነበረው ስርአት የፈጠራቸውም ናቸው፡፡ ተገቢ ያልሆነ የአስተዳደር፣ የግንኙነት ፖሊሲ፣ ልዩነትን በማጉላት ለአገዛዝ እድሜ ማራዘሚያ የተጠቀሙባቸው ስልቶች ናቸው፤ ዛሬም ችግር እየፈጠሩ ያለው፡፡ ይሄን ትርክት የሚያፈርስ ፖሊሲ፣ አስተዳደርና ትምህርት በመቅረጽ፣ ህዝቡን በደንብ ለማስረዳት ከተንቀሳቀስን፣ በዘላቂነትን ችግሩን መፍታት እንችላለን፡፡ በንግግር የማይፈታ ችግር የለም፡፡ ይሄንንም ብዙ ስር ሳይሰድ ከወዲሁ ትኩረት ሰጥቶ መፍታት ይቻላል፡፡ ከኛ በጣም ትልቅ የሆኑ አገራት እንኳን ይሄን ችግር መፍታት ችለዋል፡፡ እነ ህንድና ቻይና ከኛ የህዝብ ቁጥርም ጂኦግራፊያዊ ስፋትም የላቁ ናቸው፡፡ ግን ለህዝባቸው በሣል ፖሊሲ በመንደፍ ነው ችግሮችን የሚሻገሩት፡፡ አሁን በተጀመረው መንገድ ህዝብን በበሳል አመለካከት መምራት ከዚህ ችግር ያወጣናል፡፡
በእነዚህ ችግሮች ውስጥ ሆነን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሃገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያውን ነፃና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማድረግ የጓጉ ይመስላሉ፡፡ ይሄ ህልም የሚሳካ ይመስልዎታል?
ከምርጫው በፊት ሠላምና እርቅ አስፈላጊ ነው። ሰላምና እርቅ ማለት ችግሮቻችንን በሰከነ መንገድ መፍታት ማለት ነው፤ ሌላ ትርጉም የለውም፡፡ ይሄም ሂደት ተጀምሯል፡፡ መጀመሩ ጥሩ ነው፡፡ በቀጣይም ሙሉ ለሙሉ ይከናወናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ይሄ ከተከናወነ ነገሮችን ሰከን ብለን ማየት እንችላለን ማለት ነው፡፡
በሌላ በኩል፤በምርጫ ሥርዓት ማሻሻል ሂደት ላይ ሁሉም ከተሳተፈና አሁን በተጀመረው መንገድ የሚቀጥል ከሆነ፣ ምርጫውን ውጤታማ የማድረጉ ጉዳይ ይሳካል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ችግሮች ከወዲሁ እየተቀረፉ፣ የሁላችንም ቀናነት ከታከለበት ይሳካል፡፡ የማይሳካበት ምክንያት አይኖርም፡፡

Read 1837 times