Monday, 10 December 2018 00:00

ፕ/ት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ከዓመቱ የአለማችን 100 ተጽዕኖ ፈጣሪ ሴቶች አንዷ ሆነው ተመረጡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

    በዝርዝሩ ውስጥ የተካተቱ ብቸኛዋ አፍሪካዊት ናቸው

    የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በታዋቂው ፎርብስ መጽሄት የአመቱ የአለማችን 100 ተጽዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ተብለው ከተመረጡት እውቅና ዝነኛ ሴቶች መካከል አንዷ ሆነው የተመረጡ ሲሆን፣ በዝርዝሩ ውስጥ የተካተቱ ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሆነዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ 100 የአለማችን ሴቶች በተካተቱበት የፎርብስ የአመቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ዝርዝር ውስጥ የ97ኛ ደረጃን የያዙ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ብቸኛ ሴት ፕሬዚዳንት የሆኑት ሳህለ ወርቅ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሆነው መሾማቸው በአገሪቱ የጾታ እኩልነትን በማስፈን ረገድ በጎ አንድምታ ያለው ፈር ቀዳጅ እርምጃ መሆኑን ፎርብስ ገልጧል፡፡
ፕሬዚዳንቷ በተመድ ቆይታቸው ጉልህና ውጤታማ የዲፕሎማሲ ስራ ማከናወናቸውን የጠቆመው ፎርብስ፣ በበዓለ ሲመታቸው ወቅት በአገሪቱ ሰላምና አንድነት ለማስፈን በትጋት እንደሚሰሩ ማስታወቃቸውንም አስታውሷል፡፡
የዘንድሮውን የፎርብስ 100 ተጽዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ዝርዝር በቀዳሚነት የመሩት የጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ መርኬል ሲሆኑ፣ የእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ በሁለተኛ፣ የአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክርስቲያን ላጋርድ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
በአመቱ የአለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት ሌሎች ታዋቂ ሴቶች መካከልም የእንግሊዚቷ ንግስት ኤልዛቤጥ ሁለተኛ፣ የቶክሾው አቅራቢዋ ኦፕራ ዊንፍሬይ፣ ድምጻዊቷ ቢዮንሴ ኖውልስ፣ የፕሬዚዳንት ትራምፕ ልጅ ኢቫንካ ትራምፕና የሚሊንዳና ጌትስ ፋውንዴሽን መሥራች ሚሊንዳ ጌትስ ይገኙበታል፡፡

Read 5583 times