Monday, 10 December 2018 00:00

የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ ማሻሻያ ሊደረግበት ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

የማሻሻያ አዋጁ ለውይይት ቀርቧል

    በመከላከያ ሠራዊት አዋጅ ቁጥር 809/2006 ላይ በተመለከቱ ከ28 በላይ የአዋጁ አንቀፆች ላይ ማሻሻያ ሊደረግ ነው፡፡ በአዲሱ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ በወታደራዊ ካምፖች፣ ቢሮዎች ወይም በግል የሠራዊት መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ጊዜ የማይሰጥና አደገኛ ወንጀል ወይም የፀጥታ መደፍረስ ሲከሰት ወይም ይከሰታል የሚል በቂ ጥርጣሬ ሲኖር በየደረጃው ያለ አዛዥ እስር ወይም ብርበራ ማካሄድ ይችላል ይላል፡፡
ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ፣ ለውጭ ግንኙነትና ሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተመራው ይኸው ረቂቅ የማሻሻያ አዋጅ፤ የወንጀል ድርጊት ተፈጽሟል ተብሎ በሚታመንበት ጊዜ ምርመራውን የማስጀመርና የመጀመር ኃላፊነትን ለጦር አዛዥና ለወንጀል መርማሪው ሰጥቷል፡፡ በወንጀል መርማሪውና በአዛዥ መካከል ምርመራን ስለመጀመር ወይም ስለማቋረጥ ልዩነት ከተፈጠረ አንድ ደረጃ ከፍ ብሎ ያለ አዛዥ ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡ አዛዥ ምርመራን ለማቋረጥ የሰጠው ትዕዛዝ ህገወጥ ሆኖ ከተገኘ ተጠያቂ ይሆናል።
ረቂቅ የማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 2/2011 ሆኖ ለውይይት በቀረበው በዚሁ የማሻሻያ አዋጅ ላይ እንደተገለፀው፤ በሚኒስትሩና በጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ አቅራቢነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገራዊ ጥቅምና ደህንነትን ለመከላከል ሲባል እጅግ ጥብቅ ሚስጢር ብሎ የሚሰይማቸውን የጦር መሳሪያና የውጊያ ቁሳቁስ የግዥ የሂሣብ መዛግብትና ሰነዶች፣ ለመረጃ የወጡ የክፍያ ማስረጃዎች እንዳይገለፁ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ማሻሻያ አዋጁ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ፣ የሚኒስትሩና የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙን ሥልጣንና ተግባር በተመለከተ ዝርዝር መመሪያ እንደሚወጣ አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ መከላከያ ሰራዊት በምድር ኃይል፣ በአየር ሃይል፣ በባህር ሃይልና በልዩ ዘመቻዎች ኃይል የሚደራጅ መሆኑን የሚጠቁመው አዲሱ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ፤ የመከላከያ ሰራዊቱ እንደ አስፈላጊነቱ የስፔስና የሳይበር ሃይሎችን ሊያካትት እንደሚችል አመልክቷል፡፡ እያንዳንዱ ሃይልም እንደአስፈላጊነቱ ተጠባባቂ ሃይል እንደሚኖረውም የማሻሻያ አዋጁ ላይ ተጠቅሷል፡፡
ረቂቅ የማሻሻያ አዋጁ ላይ እንደተመለከተው፤ አዋጁ በማንኛውም የመከላከያ ሰራዊት አባል ላይ እንዲሁም እንደ አግባብነቱ በሲቪሎች ላይም ተፈፃሚ ይሆናል፡፡  

Read 4329 times