Tuesday, 04 December 2018 11:54

ከመሰላል አውርዶ ‘ዘጭ’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
“ስማ... ልጅቷን አየሀት አይደል!”
“አዎ፣ አየኋት፡፡ እና…በዓይኔ ስላየኋት የሚለውን ዘፈን ልምረጥላት!”
“እና…ቆንጆ አይደለችም! እኮ በላ፣ የሀበሻ ሞናሊዛ አይደለችም!”
“ቆንጆ ነገር ነች… ግን…”
“ግን ምን? ቆንጆ አይደለችም ልትል ነው?”
“አላልኩም፡፡ ግን ምን መሰለህ…ዳሌዋ አካባቢ…”
“ዳሌዋ! ደግሞ ለዳሌዋ ምን ልታወጣለት ነው! ሰዉ ሁሉ እየፈዘዘ የሚያየውን ዳሌዋን ምን ልታወጣለት ነው?”
“ምን መሰለህ…ግን ቅር እንዳይልህ…”
“አቦ…ንገረኝ”
“ዳሌ ይህን ያህል ሲሰፋ ምን ያደርጋል ብዬ ነው…”
“ቢሰፋስ ምን አለበት! እንደፈለገ ቢሰፋስ የሌላ ሰው ስጋ ቆርሳ አልወሰደች!”
“ቆይ አትቆጣ…በትርፍነት የተያዘ ብለው እንደሰሞኑ…ይህ የቆርቆሮ አጥር የሚያፈርሱት ነገር…”
“ምን!… እሷ ለአንተ ቆርቆሮ ነች ማለት ነው? እሷ የምትፈርስ አጥር ነች ማለት ነው!”
“አንተ እኔ ለጨዋታ ብዬ ነው… ምንድነው እንዲህ የምታካብደው!”
“ቆይ አንተ ማነህና ነው ሰዉን ሁሉ አፉን የምታስከፍተውን ቆንጆ፤ ዳሌዋ ምናምን እያልክ አቃቂር የምታወጣው!”
“አንተ ማነህና ነው…” ማለት ሲጀመር ነገር ተበላሸ ማለት ነው፡፡ የምር አስቸጋሪ ነው። ዘንድሮ በትንሹም መቀለድ አስቸጋሪ ነው። ከዓመታት በፊት አንድ ወዳጃችን ‘ጆክ’ የምንለውን መናገር እንዴት አስቸጋሪ እንደሆነ ተናግሮ “ሳቃችንን ነጠቁን…” ብሎ ነበር፡፡ ምክንያቱም ለቀልድ ብለን የተናገርነው ነገር፣ በሆነ ልዩ የ‘ትራንስሌሽን ሶፍትዌር’ ወይ ከዘር፣ ወይ ከእምነት፣ ወይ ከመሰል ያልታሰበ ነገር ጋር ይያያዝና ችግር ነው፡፡ ከወራት በፊት የሆነ መዝናኛ ስፍራ በራሳቸው ጊዜ ሲቀላለዱ የነበሩ ጓደኛሞች አጠገብ የነበሩ ሌላ ‘የማያገባቸው’ ሰዎች፤ የ‘እርጎ ዝንብ’ ሆነው ትርምስ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ቀልዶቹን የ‘እርጎ ዝንቦቹ’ ከዘር ጋር አያይዘውት አረፉላችሁ፡፡
ለምሳሌ የሆነ ቋንቋ ተናጋሪ ያልሆነ ሰው፤ ቋንቋውን በራሱ ቅላጼ ሲናገር መሳሳቅና መቀላለድ የተለመደ ነበር። አሁን እንደዛ አይነት ‘ቀልድ’ ጦስ ይዞ ይመጣል፡፡ የምር ግን አይገርማችሁም… በድንገት ሳሩም ቅጠሉም በአንድ ጊዜ የቼ ጉቬራና የማኦ ዜዱንግ ቅልቅል የሆነበት ዘመን!
እናላችሁ… ሰውዬው ልጅቱ ዳሌ ላይ ደስ ያላለውን ነገር ስለተናገረ “አንተ ማነህና ነው!” ተባለ፡፡ ይህች ደግሞ ዘንድሮ ‘ኮምፐልሰሪ’ መዝሙራችን ሆናለች፡፡ ብዙ ጊዜ ሻል ያለ ሀሳብ ሲቀርብ ‘የመከላከያ ሀሳብ’ ትጥቅ ስለሌለን “እሱ ማነውና ነው!” “እሷ ማነችና ነው!” ይባላል። ምን  መሰላችሁ… ዘንድሮ ‘እኔ ያደነቅሁትን ሁላችሁማ አድንቁ፣’ ‘እኛ እንዴት ነሽ ገዳዎ፣ ካልን ምንም ጥያቄ ሳያስፈልግ “አሀ ገዳዎ፣ በሉ፣” ምናምን  ነገር በዝቷል፡፡ እና ሌላው ሰብሰብ ብሎ “ሆ!” ስላለ እናንተም “ምን?” “ማን” “እንዴት?” ሳትሉ “ሆ!” እንድትሉ ይፈለጋል፡፡ ነገርዬው ተቀላቀል አይነት ነገር ነው፡፡ በዘመኑ ፖለቲካ ላይ “የእኔ አመለካከት፣” የሚለውን ሀሳብ የነቁ የበቁ ለሚባሉ ወዳጆቹ ሊናገር የሞከረ ሰው በ“አንተ ማነህና ነው!” አፉን አዘግተውታል፡፡
“ካለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል፣” ማለቱ ቀርቶ…
“እንግዲህ ነገሬን ከከንፈሬ አልለቅም
የሰው ዶሮ አለና ከአፍ ከአፍ የሚለቅም» ነው፡፡
የምር ግን...እንግዲህ ጨዋታም አይደል...አሁን ፖለቲከኖቻችን፣ ‘አክቲቪስት’ የሚባሉት ሁሉ ወይ ከዚህ ወገን ወይም ከዛኛው ወገን “እሱ ማነውና ነው!” ምናምን ነገር ሳይባሉ የቀሩ ጥቂት ይመስሉኛል፡፡
መናናቃችን ይሁን ለራሳችን የምንሰጠው ግምት ጣራ ቀዶ የወጣ ስለሆነ ይሁን…ሀሳብን የምናሸንፈው በተሻለ ሀሳብ ሳይሆን በ“እሱ ማነውና ነው!” ቅዝምዝም ዱላ ሆኗል፡፡
“ከመተባበርና ከመግባባት ይልቅ መቀናናትና መመቀኛኘት ያጠቃናል፣” ብለዋል ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት፡፡ ዘንድሮም መቀናናትና መመቀኛኘት እንደ ጉድ ነው፡፡ ፖለቲካችንን ነገሬ ብላችሁ እንደሁ ከመጋረጃ ጀርባ ከሚያምሱት ምክንያቶች መሀል መቀናናትና መመቀኛነት አይጠፉበትም፡፡
ደግሞላችሁ… “እሱ ማነውና ነው!” እንደሚባለው ነገር ደግሞ “እሱ ከማን ይበልጣልና ነው!” የምንላት ነገር አለችን፡፡ ባስ ሲል ደግሞ… አለ አይደል… “እሱ ማነውና ነው!” ከማለት ተከትሎ የምትመጣ… “እሱን አናውቀውምና ነው!” የሚሏት ነገር አለች፡፡
“ስማ… ትናንት ማታ ቲቪ አየህ?”
“አላየሁም፣ ምን አመለጠህ ልትዪኝ ነው?”
“እንትና የሚባለው ፖለቲከኛ፣ ጨዋታውን አመጣው ነው የምልህ!”
“በአቅም ማነስ ከፖለቲካ ወጥቻለሁ አለ?”
“አንተ… ስለ አገራችን ኤኮኖሚ የሰጠውን ትንተና ብትሰማ፣ እማዬ ድረሽ ነበር የምትለው!”
“እማዬ የምትደርስበት ሌላ ብዙ ጉዳዮች አሏት፡፡”
“አንተ…እኔ ከምሬ ነው፡፡ እንዲሀ አይነት ትንታኔ ቢቢሲ ላይ እንኳን አትሰማም፡፡”
“እባክሽ ተዪኝ…ደግሞ እሱ ብሎ የኤኮኖሚ ተንታኝ! ይሄኔ የቤቱን የወር አስቤዛ እንኳ ማስላት አይችልም፡፡”
“ይቺ እንኳን ኮምፕሌክስ ነች!”
የምር ግን… “ለምሳሌ ከተናገራቸው ነገሮች እስቲ አንድ ሁለቱን ንገሪኝ፣” ምናምን ማለት ማንን ገደለ! …ከአገር ኤኮኖሚ ተንታኝነት አውርዶ የቤት አስቤዛ ለማስላት ‘የብቃት ማረጋገጫ’ መከልከል ምን የሚሉት ፍርድ ነው? ብዙ ጊዜ እንዲህ የምንል ሰዎች፤ “እስቲ አንተ ስለ አገራችን ኤኮኖሚ የሆነ ነገር ንገረኛ፣” ብንባል…አለ አይደል… “ገንዘቡ ሁሉ ባህር ማዶ እየተጋዘ ምን ኤኮኖሚ አለና ነው!” ብለን ባንዘጋው ነው!
“ስሚ እንትናን አወቅሻት? ያቺ እንኳን ከእናንተ ቤት በላይ የነበረችው…”
“አወቅኋት…ምን ሆነች? የዱባይ ሼክ  ጠብ አደረገች እንዳትዪኝ!”
“የራስሽን ህልም ነው የምታውሪው፡፡”
“እሺ ምን ሆነች?”
“ምን የመሰለ ሲንግል ለቃለች፡፡”
“ምን! ራስዋ ሲንግል ሆና ሲንግል ለቀቀች?”
“አላማረብሽም፡፡”
“እሺ ሲንግል ለቀቀች ነው ያልሽኝ!”
“አልሰማሁም እያልሽኝ ነው! የአገሩ ኤፍ.ኤም ቀኑን ሙሉ የእሷን ዘፈን ሲያሰማ አይደል እንዴ የሚውለው!”
“ተይ እባክሽ፣ እሷ ብሎ ዘፋኝ፤ አናውቃትምና ነው! ሰፈር ሰርግ በተደረገ ቁጥር የቤቷን ትሪና ሳፋ ከበሮ እያደረገች ሰባብራ የጨረሰች አይደለች እንዴ! እኛ እንደውም ስንት ጊዜ ጎረቤት ስለሆነች ተውናት እንጂ ዘፈንኩ እያለች ስትጮህ ቀበሌ ልንከሳት ሁሉ ነበር፡፡”
“ምን ብላችሁ ልትከሷት ነበር?”
“ከሆነ አውሬ ድምጽ የሰረቀች ስለሆነ ከየትኛው አውሬ እንደሰረቀች ይጣራልን ልንል ነበር፡፡”
“አቤት ክፋት! አንቺ ምን አድርጋሽ ነው እንዲህ የምትጠያት!”
ምንም አላደረገቻትም፡፡ ግን የሆነ የምናውቀው ሰው ትንሽ በመሰላሉ ሁለት፣ ሦስት ደረጃዎች ከፍ ያለ ሲመስለን፣ እንቅልፍ የሚነሳን የሆነ አባዜ ስላለ ነው፡፡
ልክ እኮ አንዷ የ‘ሀይ ስኩል’ ቦይፍሬንዷን “አገባ እኮ…” ሲሏት… “እሱ ብሎ ባል፣ አላውቀውምና ነው! ከእነሚሊተሪ ጫማው አይደለም እንዴ አልጋ ላይ ሲወጣ የነበረው!” እንደማለት ነው። (ያውም ከፋይ እንዲመስል በብርጭቆ ወረቀት የተፈተገ የሚሊተሪ ጫማ!  ቂ…ቂ…ቂ…) እናማ…ይሄ ሰውን ከመሰላል እያወረዱ ዘጭ ማድረግ የሚቀርበት ዘመን ይናፍቀናል።
  ደህና ሰንብቱልኛማ!

Read 5794 times