Monday, 03 December 2018 00:00

ያልተገኘው ሰይጣን

Written by  መሐመድ ኢድሪስ
Rate this item
(7 votes)

 በአንድ በውል በማይታወቅ ጊዜ ነግሶ የነበረው የኢትዮጵያ ንጉስ አራተኛ፤ በቤተ መንግስቱ ውስጥ መኳንንቱንና የጦር አዛዦቹን ሰብስቦ፣ ትልቅ የእራት ግብዣ ደግሶ ነበር፡፡ ምግቡ ተትረፍርፎ፣ መጠጡም በገፍ ይቀርብ ነበር፡፡ እጅግ በጣም ውድ የሆነ ወይን ጠጅ እየተንቆረቆረ ሲቀዳ፣ ደናግል ወጣት ልጃገረዶች፣ በወርቅና በአልማዝ አጊጠው ልዩ በሆነ ጣዕመ ዜማ፣ ዳንሳቸውን ያስነኩታል፡፡ ሞቅታው ጨምሮ ሰው ወደ ስካር መግባት ሲጀምር፣ ጭፈራው ገብ አለና፤ የከተማይቱ አሉ የተባሉ ፈላስፋዎች፣ በስካር መንፈስ ክርክራቸውን ጀመሩ፡፡
“በግሪኮችና በትሮዮች መካከል ከተደረገው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሞቱበት ጦርነት ምን እንማራለን?” ሲል ጠየቀ፤ ዳርዮስ የተባለው ፈላስፋ፤ ወይን የሞላ ዋንጫውን ይዞ እየተንጎራደደ፡፡
“ፓሪስ፣ ሄለንን መስረቅ አልነበረበትም!” አለ፤ አንድ በስካር የተያያዘ ምላስ፡፡
“አራቱ ሰይጣኖች እያሉ ምን ሰላምና ደስታ አለ?” አለ፤ ኦርዮን የተባለው የስነ መለኮት መምህር፡፡
“ማናቸው አራቱ ሰይጣኖች?” ጠየቀ፤ ንጉስ ኢልዮን፡፡
“በዚህ ምድር ላይ ላለው ጦርነት፣ ደም መፋሰስና ግጭት፤ መንስኤ የሆኑ አራት ሰይጣኖች ናቸው--” መለሰ አርዮን፡፡
“የት ነው ያሉት?” ጠየቀ ኢልዮን በቁጣ፡፡
“የት እንዳሉና ማን እንደሆኑ ማንም አያውቅም፡፡ ከአንድ ባህታዊ በስተቀር፡፡
ንጉሱ በነጋታው፣ ባህታዊውን ፍለጋ ፈረሱን ጭኖ፣ ወደ ተባለው ጫካ አመራ፡፡ ራሱን ቀይሮና ተራ ሰው መስሎ፣ ጥቂት የወርቅ ሳንቲሞችን ይዞ፣ ባህታዊው አለበት ወደተባለው ዋሻ በእግሩ መጓዝ ጀመረ፡፡ ባህታዊው፤ ዋሻው ውስጥ እግሮቹን አጣምሮ በተመስጦ ላይ ነበር፡፡
“ሰላም ለእርሶ ይሁን” አለ ንጉሱ፣ ከባህታዊው ፊት ቆሞ፡፡
“ሰላም ለእርሶ ማናት?!”
“እውቀት ለመማር ወደ እርሶ የመጣሁ ነኝ”
“እኔ ምንም የማውቀው ነገር የለኝም፡፡ አላስታውስም” መለሱ ባህታዊው፡፡
“መቀመጥ እችላለሁ?” ጠየቀ ንጉሱ፡፡
ባህታዊው ምንም እንደማያስታውስና፣ የማስታወስ ችሎታው፣ ጭንቅላቱ ሲመታ እንደሚመጣ፣ የሰማውን አስታውሶ፡፡ እስኪመሽ ድረስ አብረው ሳይነጋገሩ ከተቀመጡ በኋላ ባህታዊው ከተቀመጠበት ተነስቶ፣ ጥቆት የባቄላ ንፍሮ ለንጉሱ ሰጠው፡፡
“ከዚህ የተሻለ ምግብ መብላት እንችላለን---ምግብ የሚሸጥበት ቦታ ብንሄድ” አለ ንጉሱ፡፡
“ጥቂት ምዕራፎችን መጓዝ ያስፈልጋል፤ በዚያ ላይ ገንዘብ የለም”
“እኔ ጋ አለ” አለ ንጉሱ፡፡
 ጀምበር ማዘቅዘቅ ጀምራለች፡፡ ወደ ሁለት ሰዓት ያህል ከተጓዙ በኋላ አንድ ትንሽ የገጠር ገበያ ጋ ደረሱ። ንጉሱ፤ አንድ የወርቅ ፍራክ ለአንድ የፍራፍሬ ሻጭ ኮበሌ ሰጠና፤
 “ለእራት የሚሆን ነገር ስጠን” አለው፡፡ ሰውየው ሚዛኑን አስተካከለና የሮማን፣ የኮክ፣ የአናናስና የብርቱካን ፍሬዎችን መዝኖ ሰጠው፡፡
“መልስ ስጠን” አለ ባህታዊው፡፡
“ችሏል” አለ፤ ብልጣብልጡ ኮበሌ፡፡
ንጉሱ አልባሌ ልብስ ቢለብስም፣ ተራ ሰው እንዳልሆነ ገብቶታል፡፡
የሰጠንህ ገንዘብ፣ የሰጠኸንን ሸቀጥ አስር እጥፍ ነው” አለ ባህታዊው፡፡
“አጭበርባሪ ነህ እያልከኝ ነው?”
“አዎን ነህ!”
የፍራፍሬ ሻጩ ግብረአበሮች፤ ንጉሱንና ባህታዊውን ከበው ማዋከብ ጀመሩ፡፡ ሌሎቹን የወርቅ ፍራንኮች ለመዝረፍ አሰፍስፈዋል፡፡ “እንዲያውም አንተ ሌባ ነህ፡፡ የንጉስ ኢልዮን ማህተም ያለበትን የወርቅ ፍራክ ከየት አመጣህ?” አለ ፍራፍሬ ሻጩ፤ንጉሱን አንገት አንቆ፡፡
“ምክንያቱም እኔ ንጉስ ኢልዮን ስለሆንኩ!”
ሁሉም በእግራቸው መሬቱን እየደበደቡ በሳቅ ፈነዱ፡፡
“በል ቀልዱን ተውና ቀሪዎቹን ፍራንኮች አምጣ!” አለ ኮበሌው፤ የንጉሱን አንገት በኃይል አንቆ፡፡
እድሜውን ሙሉ የፈረስ ጉግስ፣ ትግልና አሰቃቂ የግድያ ስልት ሲማር ያደገውን ንጉስ ኢልዮን፤ የኮበሌውን እጅ ከአንገቱ አላቆ በአንድ ምት አፈር ላይ ደባለቀው፡፡ ገበያው ተተረማመሰ፡፡ አንዱ ጫኝ አውራጅ ተንደርድሮ፣ ወደ ንጉሱ መጣ፡፡ በጉልበቱ ጭኑን መታው፡፡ ሰውየው ራሱን ሳተ፡፡ እንዲህ ዓይት ነገር አይተው የማያውቁት የዚያ ቦታ ሰዎች፤ ህይወታቸውን ለማትረፍ የያዙትን ይዘው መፈርጠጥ ጀመሩ፡፡ ንጉሱ ዞሮ ወደ ባህታዊው ተመለከተ፡፡ በግርግሩ መሃል ተመትተው ወድቀዋል፡፡ አጠገቡ በርከክ ብሎ ቀና አደረገው፡፡ ባህታዊው፤ አናቱን ሲመታ ነው፣ የማስታወስ ኃይሉ የሚመለሰው፡፡
“አንደኛው ሰይጣን፤ ከገንዘብ ጋር የተገናኘው ስስት ነው” አለው ፈገግ ብሎ፡፡
የያዙትን ይዘው ማደርያ ፍለጋ፣ ወደ ቅርቢቱ መንደር አመሩ፡፡
“ማደርያ ይኖራል?” ሲል ጠየቀ ንጉሱ፤ አንድ ሰፊ ዛኒጋባ ቤት ውስጥ የተደረደሩ አልጋዎችን እየተመለከተ፡፡
አከራይዋ፤ ይህ ቀረሽ የማትባል ቆንጆ ነበረች፡፡ ውብ ዓይኖችዋን እያስለመለመች፤
“አንደኛ ማዕረግ ያለው አንድ አልጋ ብቻ ነው፡፡” አለችው፡፡
ሰውየው፤ ተራ ሰው እንዳልሆነ አውቃለች፡፡
“ይያዝልን” አለና፤ አንድ የወርቅ ፍራንክ ሰጣት። አይንዋንም አፍንጫዋንም ከፍታ፤ “ዝርዝር የለዎትም?” አለችው፡፡
“ያዥው!” አላትና ከባህታዊው ጋር ወይን ጠጅ ለመቀማመስ ተያይዘው፣ ጫጫታና ሁካታ ወዳለበት ቀጣዩ ዛኒጋባ አመሩ፡፡ ርካሽ ወይን ጠጅ ሲጠጡ አመሹ፡፡ እኩለ ሌሊት ገደማ አዳራሹ ውስጥ የነበረው ጠጪ ሁሉ እየተንጋጋ፣ በሩ ላይ ተኮልኩሎ፣ ወደ ውጭ መመልከት ጀመረ፡፡
“ምንድነው?” ሲል ጠየቀ ንጉሱ፡፡
“አገር ገዢውና ጠባቂዎቹ ናቸው!” አለ፤ ፊቱ የወየበ ሽማግሌ፣ አፉ እየተሳሰረ፣ ዋንጫውን ወደ አፉ አስጠግቶ፡፡
“ምን ያደርጋል እዚህ?”
“አልጋ አከራይዋ ውሽማው ናት፡፡”
ንጉሱ ወይን ጠጁን ተጎነጨ፤ሞቅታው ሲጨምር፣ ሰካራሞቹ እየተንገዳገዱ፣ አንዴ ቅጥ የለሽ ዳንስ የወለሉ አቧራ እስኪቦን መደነስ፣ ሲሻቸው ደግሞ ዋንጫ እየተወራወሩ መሰዳደብ ጀመሩ፡፡ ልብሳቸውን እያወለቁ ከወገብ በላይ እራቁታቸውን ሆነው፤ “ና ወንድ ከሆንክ አንገጫግጭሃለሁ!” እየተባባሉ ቢሰዳደቡም፣ ማንም የተደባደበ ሰው የለም፡፡
ነገሩ ያላማረው ንጉስ ኢዮኤል፤ የሰከረውን ባህታዊ ደግፎ ከአዳራሹ ወጣ፡፡ ወደ ማደሪያቸው ሲደርሱ፣ ሻማ በርቶ፣ በሩ ገርበብ ብሎ ነበር፡፡ አልጋ አከራይዋ፤ በአንድ በጥንቃቄ የተላጨ ሪዝ ያለው ጎራዴውን በወገቡ ላይ የታጠቀ፣ የወርቅ ማዕረግ ትከሻው ላይ ያለው ረጅም ሰው ጭን ላይ ተቀምጣ ወይን እየጠጣች ነበር፡፡ ብድግ ብላ ተነስታ ወደ ንጉሱ ተንደርድራ መጣችና፤ “መጣችሁ! እንኳን መጣችሁ! የቀራችሁ መስሎኝ አልጋውን አከራየሁት፡፡ ከሱ የተሻለ ሁለተኛ ማዕረግ ውስጥ አልጋ እሰጣችኋለሁ፤ ኑ ተከተሉኝ” አለችና፤ ፊቷን አዙራ መራመድ ጀመረች፡፡
“አንደኛ ማዕረግ ነው የምፈልገው!”
አከራይዋ ፊትዋ ቀልቶ፣ ከንፈርዋ ተንቀጠቀጠ፡፡ አንዴ የወርቅ ማዕረግ ትከሻው ላይ ያደረገውን ረጅም ሰውዬ፣ አንዴ አልባሌ ለብሶ፣ ፊት ለፊትዋ የቆመውን፣ ሰው ቀርቶ ሰይጣን የማይፈራውን ሰው፣ አፈራርቃ እየተመለከተች፤ “የተከራዮት እኮ እሳቸው ናቸው፡፡ አገር ገዢው” አለች፡፡
“አያገባኝም!”
“ምን አልክ?” አለ ረጅሙ ሰው፣ ከመንበሩ ተነስቶ።
ንጉሱ አልመለሰም፡፡ ሻሞላውን መዘዘና ወደ ንጉሱ አንገት አወናጨፈ፡፡ ንጉሱ ዝቅ ብሎ አሳለፈና በእግሩ ብልቱን መታው፡፡ አገር ገዥው ተንበረከከና በኃይል ጮኸ፡፡ አራቱ ጠባቂዎች ከውስጠኛው ክፍል እየተንጋጉ መጡ፡፡ ዛኒጋባው ድብልቅልቁ ወጣ። አራቱም ጠባቂዎች ከድብደባው አላመለጡም፡፡ ንጉሱ፤ መሬት ላይ የተዘረረውን ባህታዊ ተመለከተ፡፡
“ሁለተኛው ሰይጣን፤ ከክብር ጋር የተገናኘ ትዕቢት ነው” አለው፡፡
አገር ገዢውና ጠባቂዎቹ ሁለተኛ ማዕረግ፣ ንጉሱና ባህታዊው አንደኛ ማዕረግ የተያዘላቸው አልጋ ላይ ተኙ፡፡ እኩለ ሌሊት አልፎ ምንግያ ላይ ንጉሱ ሸለብ አደረገው፡፡ ግን ብዙ አልቆየም፤ ለስላሳ እጅ ፊቱን ዳሰስ ሲያደርገው ታወቀው፡፡ አይኑን ከፈት ሲያደርግ፣ አከራይዋ ስስ ውስጥ ልብስ ለብሳ፣ ፊት ለፊቱ ቆማለች፡፡ ሰፊው አልጋ ላይ በግርጌ የተኛው ባህታዊ ያንኮራፋል፡፡
“አልጋዬ ተያዘብኝ፣ ይበቃናል?” አለች ፈገግ ብላ፡፡
ንጉሱ ከመመለሱ በፊት ረጅሙ አገር ገዢ፣ በሩን በርግዶ ገባና፤ አከራይዋን በጥፊ ሲያጮላት፣ መሬት ላይ ተዘረረች፡፡ ወዲያው ዘለለና ንጉሱ ላይ ተከመረ። ሁለቱም ተያይዘው፣ ከአልጋው መሬት ላይ ወደቁ። ባህታዊው በርግጎ ተነሳና፣ ንጉሱን ለማስጣል አገር ገዢውን ከኋላ አነቀው፡፡ አገር ገዢው፤ ንጉሱን ለቆ ተነሳና፣ አንገቱን ከባህታዊው እጅ አላቆ ባህታዊውን ሲወረውረው፣ የባህታዊው አናት ከዛኒጋባው ምሰሶ ጋር ተላተመ፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው፤ አገር ገዢው በራሱ ሻዋላ፣ በንጉሱ ተወጋና፣ ተዝለፍልፎ መሬት ላይ ተዘረጋ፡፡
“ስልጣንህን ተነጥቀሃል!” አለው የዘቦቹ አለቃ፤ ጎራዴውን የንጉሱ አንገት ላይ ደግኖ፡፡
ንጉሱ፤ የባህታዊውን ጭንቅላት ቀና አድርጎ አነሳው፡፡
“ሶስተኛው ሰይጣን፣ ከሴት ጋር የተገናኘው ቅናት ነው፡፡” አለው፡፡
ንጉሱ፤ እነዚህ ሶስት ሰይጣኖች፣ ከሶስት ጥሩ ነገሮች ጋር የተገናኙ፣ ለሁሉም ደም መፋሰስና ብጥብጥ ምክንያት መሆናቸውን ተረዳ፡፡ በነጋታው ፈረሱን ጫነና ባህታዊውን እንዲህ አለው፤ “ወደኔ መኖርያ ልወስድህ እችላለሁ፡፡ የፈለግከው ነገር ሁሉ ይሟላልሃል፡፡ እዚህ ጫካ ውስጥ ብቻህን የምትኖርበት ምክንያት አይታየኝም” አለው፡፡
ባህታዊው ተስማማና ፈረሶቻቸውን ይዘው መጋለብ ጀመሩ፡፡ የተወሰነ ምዕራፍ ከጋለቡ በኋላ ሰፊው የንጉሱ በግንብ የታጠረ ከተማ ደረሱ፡፡ የከተማው ሰፊ በር ግን እንደ ወትሮው ክፍት አልነበረም፡፡ ይባስ ብሎ ከሃምሳ የማያንሱ ብረት ለበስ ዘቦች፣ በሩ ላይ ጎራዴያቸውን ታጥቀው ተደርድረው ቆመዋል፡፡ ንጉሱ ነገሩ አላማረውም፡፡
“በሩን ክፈት” አለ ንጉሱ፤ በታላቅ ድምፅ፡፡
“ንጉሱ እንዳይከፈት አዘዋል” አለ፤ አንደኛው ዘብ፡፡
“ማነው ንጉሱ?” ጠየቀ ኢዮኤል፡፡
“ንጉስ አሎንያስ”
አሎንያስ ሁልግዜ እሱ ላይ መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ ያሴር እንደነበር ቢነገረውም፣ ማስረጃ ካላገኘሁ አልነካውም ብሎ አልፎት ነበር፡፡ ንዴቱን መቆጣጠር ያልቻለው ኢዮኤል፣ ጎራዴውን መዞ፤
“እኔ ነኝ ንጉስ ኢዮኤል” አለ፡፡
“የታለ ዘውድህ?”
በፍጥነት እየጋለበ ዘቦቹ መሃል ገባ፡፡ አራቱን ጨርግዶ ከጣላቸው በኋላ በድንገት ከጀርባው ተወጋ። መሬት ላይ ሲወድቅ፣ባህታዊው ጭንቅላቱ በደም ርሶ መሬት ላይ ተዘርሮ አየው፡፡ እየተንፏቀቀ ወደሱ ተጠጋ። “አራተኛው ሰይጣን፤ ከስልጣን ጋር የተያያዘው…” አለና ሳይጨርስ፣ ትንፋሹ ጸጥ አለ፡፡ አሾፈበት፡፡  
ከስልጣን ጋር የተገናኘው፣ ዋናውና  ኃይለኛው ሰይጣን፣ ማንነቱ ባይታወቅም፣ ንጉሱ ላይ ሃያ ዓመት በግዞት አስሮ ቀለደበት፡፡ ይህ ሰይጣን እስካሁን ማንነቱ አይታወቅም፡፡     

Read 3672 times