Monday, 03 December 2018 00:00

“ጥልቅ ተሐድሶ” በሚድሮክ መንደር!!

Written by  ኩርኩራ ዋፎ - ከለገጣፎ
Rate this item
(10 votes)


    እንደሚታወቀው ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ፤ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት የጀመሩት ከደርግ ውድቀት በኋላ ነው፡፡ “ሚድሮክ ኢትዮጵያ” የተባለው ኩባንያ ከመቋቋሙ በፊት ሼህ ሙሐመድ ከአቶ ታደለ ይድነቃቸው ተሰማ ጋር “አል-ታድ ኢትዮጵያ” የሚል ኩባንያ አቋቁመው በኮንስትራክሽን ዘርፍ ተሰማርተው እንደነበርም ይታወሳል፡፡
ከዚያ በኋላ የመንግስት የልማት ድርጅቶች፤ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ተቋቁሞ፣ በደርግ መንግስት ይዞታ ስር የነበሩ የልማት ድርጅቶችን መሸጥ ሲጀምር፣ ሼህ ሙሐመድ አክሳሪና ሊዘጉ የተቃረቡ ተቋማትን በመግዛት በርካታ ኢትዮጵያውያንን ከስራ አጥነትና ከበረንዳ አዳሪነት አድነዋል፡፡ ተጨማሪ አዳዲስ ኩባንያዎችንም በማቋቋም ኢንቨስትመንታቸውን አስፋፍተዋል፡፡ የሥራ እድል ፈጥረዋል፡፡ “የሼህ ሙሐመድ ኢንቨስትመንት በትርፍ ላይ የተመሰረተ ኢንቨስትመንት አይደለም፡፡ ዓላማቸው ወገንን መርዳት ነው” የሚባለውም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡
ሰሞኑን መገናኛ ብዙሃንን ካጨናነቁ ጉዳዮች አንዱ በሚድሮክ ኩባንያዎች ስም ለዓመታት ታጥረው በተቀመጡ የመሬት ይዞታዎች ላይ የተጀመረው ሕግን የማስከበር ዕርምጃ ነው፡፡ “ሚድሮክ” የሚለው የኩባንያ ስም አንድ ባለሀብትን ኢንቨስትመንት የሚያመለክት ነው፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ጥቅል ስም ዣንጥላ (Umbrella) ስር ወደ 76 የሚጠጉ ኩባንያዎች የሚገኙ ሲሆን እነዚህም 76 ኩባንያዎች በተለያዩ ዘርፎች ተከፋፍለው በተለያዩ ግለሰቦች በኃላፊነት የሚመሩ ናቸው፡፡
በዚህም መሰረት ሃያ ስድስቱ ኩባንያዎች በአንድ ላይ “ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ” በሚል ቡድናዊ ስያሜ አንድ ላይ ተጣምረው በዶ/ር አረጋ ይርዳው የሚመሩ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ ሃምሳ ያህል ኩባንያዎች ደግሞ፤ “ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ” በሚል ቡድናዊ ስም የተደራጁ በእነ አቶ አብነት ገ/መስቀል የሚመሩ፣ “አግሪ ሴፍት” በሚል ቡድናዊ ስም የተካተቱ በአቶ ጀማል የሚመሩ እና “ሚድሮክ ደርባ” በሚል ቡድናዊ ስም የተደራጁ ወደ አራት የሚጠጉ ኩባንያዎች ደግሞ በአቶ ኃይሌ አሰግዴ የሚመሩ ናቸው፡፡ ሌሎች እንደ ሸራተን አዲስ ሆቴል፣ ዳሸን ባንክ፣… የመሳሰሉት ደግሞ በተናጠል በቦርድና በሌሎች አግባቦች የሚተዳደሩ ናቸው፡፡
በእነዚህ ኩባንያዎችም በአጠቃላይ እስከ 100 ሺህ የሚደርሱ ቋሚ፣ ጊዜአዊና የኮንትራት ቅጥር ሠራተኞች የሥራ እድል አግኝተዋል ተብሎ ይገመታል፡፡ ይህም የሰው ኃይል ሼህ ሙሐመድን ከመንግስት ቀጥሎ ብዙ የሥራ እድል የፈጠሩ ባለሃብት ያደርጋቸዋል፡፡
ሰሞኑን በመገናኛ ብዙሃን እየተስተጋባ ያለው የመሬት ማስመለስ ጉዳይ፣በየትኛው የሚድሮክ ቡድን ውስጥ ያለውን መሬት የሚመለከት ነው? ለሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ግልጽ የሆነ ምላሽ ካልተገኘ፣በስመ ሚድሮክ በህግና በስርዓት ስራቸውን እያከናወኑ ያሉ ኩባንያዎች ላይ፣ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳይፈጠር በማሰብ ነው ይህቺን ማስታወሻ ለመጻፍ የተነሳሁት። ይህንን ጽሁፍ ያዘጋጀሁበት ሁለተኛው ምክንያቴ ደግሞ በተለይ በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች ውስጥ የሚስተዋሉ ድክመቶችን በማንሳት የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማመላከት ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፒያሣ አካባቢ ሰሞኑን የወሰደው የሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ይዞታ የሆነ መሬት፣ እነ አቶ አብነት ገ/መስቀል በሚመሩት በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ውስጥ የነበረ ነው፡፡ ግንባታውም በሚድሮክ ኮንስትራክሽን ድርጅት አማካይነት ይካሄድ እንደነበር ይነገራል፡፡ ይህ ፒያሳ አካባቢ የነበረ መሬት መጠኑ 3.3 ሔክታር ሲሆን፤ ለሲቲ ሴንተር የሚሆን መንታ ሕንፃ ለመገንባት የታሰበ ነበር፡፡
ሼህ ሙሐመድ ይህንን መሬት በ1990 ዓ.ም ነበር የተረከቡት፡፡ በዚህ መሬት ላይ 44 ፎቆችን ለመገንባት መታቀዱ በወቅቱ ሲገለጽ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እስከ አሁን ድረስ አራት ጊዜ የዲዛይን ለውጥ መደረጉ ታውቋል፡፡ በመጨረሻም፤ (የዛሬ ሦስት አራት ዓመት ገደማ) በተሰራው ዲዛይን፣ 40 ፎቅ ተብሎ የነበረው ህንፃ ወደ 4 ፎቅ ዝቅ እንዲል መደረጉ፣በወቅቱ በመገናኛ ብዙሃን ጭምር እንደተነገረ አስታውሳለሁ፡፡
በዚህ ስፍራ ላይ ህንፃው እስከ አሁን ለምን እንዳልተሰራ የተለያዩ መላምቶች (ምክንያቶች) ቢገለጹም፣ “ገንዘቡ ቀድሞ ተበልቶ አልቋል” በሚለው ሃሳብ ላይ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ የዛሬ 20 ዓመት የነበረው የግንባታ ዋጋ መጨመርም በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡
ሼክ መሐመድ ራሳቸውን መከላከል በማይችሉበት ሁኔታ ላይ እያሉ ዕርምጃው መወሰዱ አግባብ እንዳልሆነ አንዳንድ ሰዎች ቢናገሩም፤ በበኩሌ መሬቱ ለህዝብ አገልግሎት እንዲሰጥ መደረጉ አግባብ ነው እላለሁ። ህንፃ የመገንባት አቅሙ እስካለ ድረስ ሌላ መሬት የማግኘት እድሉም የተዘጋ ሊሆን እንደማይችልም አስባለሁ፡፡  
አንዳንድ ነጥቦች ስለ ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ
የዛሬ 20 ዓመት ገደማ ጀምረው ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕን በማቋቋም፣ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት/ ፕሬዝዳንትነት እየመሩ ያሉት ዶ/ር አረጋ ይርዳው ናቸው፡፡ ዶ/ር አረጋ ይርዳው፤ ይህንን ኃላፊነት ሲረከቡ በቴክኖሎጂ ግሩፑ ውስጥ 5 ደካማ ኩባንያዎች ብቻ ነበሩ፡፡ ከአምስቱ ውስጥ የተሻለ ሕይወት አለው ሊባል የሚችለው ሚድሮክ ጎልድ ኃ. የተ. የግል ኩባንያ ብቻ ነበር፡፡ እሱም ቢሆን በ35 ፈረንጆች “የተወረረ” እና ከገቢው ይልቅ ወጪው የሚያመዝን ኩባንያ ነበር፡፡
ዛሬ በቴክኖሎጂ ግሩፑ ስር ያሉት ኩባንያዎች ብዛት 26 ደርሷል፡፡ እንደ ትረስት፣ ኩዊንስ ማርኬት፣ አውቶ ሜይንቴናንስ ወዘተ. የመሳሰሉት ኩባንያዎች ዶ/ር አረጋ ራሳቸው “ሀ” ብለው ያቋቋሟቸው ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ለምሣሌ፤ ኢትዮ-ድሪም፣ ጂቱ እና አንሊሚትድ ፓኬጂንግ፣… የመሳሰሉት ደግሞ በአሰራር ድክመት ከስረው ሊዘጉ ሲያጣጥሩ ሼህ ሙሐመድ ለዶ/ር አረጋ እየሰጧቸው፣ የአሰራር ስርዓታቸው እንዲሻሻልና እንዲያገግሙ የተደረጉ ናቸው፡፡
ዶ/ር አረጋ፤ የሼህ ሙሐመድን አደራ በአግባቡ እየተወጡ መሆኑ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ ሰውየው ጊዜአቸውንም፣ እውቀታቸውንም፣ ጉልበታቸውንም መስዋእት አድርገው እየሰሩ ነው፡፡ ዶ/ር አረጋ በሙያቸው “አንቱ” የተባሉ፣ ስመ-ጥር መሀንዲስ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ለረዥም ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በውጪ ሀገርም በአቬሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ መስራታቸው ይነገራል፡፡ የእውቀትም የልምድም ችግር የለባቸውም፡፡
ዶ/ር አረጋ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ በርካታ ቁም ነገሮችን ያከናወኑ በመሆኑ፣ ያን ሁሉ እዘረዝራለሁ ብሎ መነሳት ጊዜና ጉልበት ማባከን በመሆኑ፣ እዚያ ላይ ማተኮር አልሻም፡፡ ይሁን እንጂ፤ ዶ/ር አረጋ ሰው በመሆናቸው እንደ ሰው የሚታዩባቸውን ጎላ ብለው የሚስተዋሉ ጉድለቶችን ለማንሳት እወዳለሁ፡፡
እነዚህን ጉድለቶች ለመጠቆም የተነሳሁት ከእርሳቸው የላቀ እውቀት ያለኝ መሆኑን ለማሳየት ሳይሆን፤ የራሷ መላጣ እንደማይታያት እንስሳ፣ ዶ/ር አረጋም የሚፈጽሟቸው ስህተቶች “አልታያቸውም” የሚል እምነት ስላደረብኝ ነው፡፡ በዚህም መሰረት፤ በእርሳቸውና በሚመሯቸው ኩባንያዎች ያስተዋልኳቸውን የአሰራር ክፍተቶች እንደሚከተለው ለመጠቃቀስ እሞክራለሁ፡፡
የዶ/ር አረጋ ድክመቶች - “Double Standard”
ዶ/ር አረጋ፤ ሼህ ሙሐመድ የሰጧቸውን ኃላፊነት ተረክበው ስራ እንደጀመሩ፣ ያጋጠማቸውን ሁኔታ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገልጹ ነበር፡፡ በዚያ ወቅት ሚድሮክ ጎልድን የሚመሩ ወደ 35 ገደማ ፈረንጆች እንደነበሩና እነዚያ የውጭ አገር ሰዎች ትልቅ ደመወዝ እየተከፈላቸው፣ አዲስ አበባ ተቀምጠው ገንዘብ እንደሚያባክኑ የተረዱት ዶ/ር አረጋ፤ ሰዎቹን ቀስ በቀስ በማሰናበት እነሱ ይሰሩት የነበረውን ስራ ኢትዮጵያውያን ተተክተው እንዲሰሩ ማድረጋቸውንና በዚህም ተቋሙን ውጤታማ ማድረጋቸውን ከራሳቸው አንደበት ሰምቻለሁ፡፡
እንዲህ ያለው እርምጃ ተገቢና ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ነገር፣ ዛሬ ዛሬ ዶ/ር አረጋ “ፈረንጅ አምላኪ” የሚያስመስላቸውን ተግባር ሲፈጽሙ እያየን መሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ፤ በኤልፎራ ብቻ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያውያን ሊሰሩት የሚችሉትን ስራ እየሰሩ፣ ከፍተኛ ደመወዝ እየተከፈላቸው የሚሰሩ ስድስት የደቡብ አፍሪካ “ፈረንጆች” አሉ፡፡ (አንዳንዶቹ አእምሯቸው የተነካ፣ አልፎ አልፎ የሚያጓሩ ወፈፌ ብጤ ናቸው)
እንደኔ እንደኔ፣ እንዲህ ያለው ፈረንጅ አባሮ፣ ፈረንጅ የማምጣት አባዜ፣ ለአንድ ጉዳይ ሁለት መስፈርት (Double Standard) መጠቀም ነው፡፡ 85 በመቶ በግብርና ላይ የተሰማራ ህዝብ ባለበት ሀገር፣ ከሁሉም በላይ ከረዥም ዓመታት በፊት በዓለም ማያ፥ በጂማና በአምቦ የእርሻ ኮሌጆችን ባቋቋመች ሀገር፣ የእርሻ ባለሙያ ታጥቶ ነው ከደቡብ አፍሪካ ገበሬ አምጥተው የቀጠሩት? ሊሆን አይችልም! 35 ፈረንጅ ሲያባርሩ፤ የማዕድን ባለሙያ ያላጡትን፣ የእርሻ ባለሙያ አጣሁ ማለት የማይመስል ነገር ነው፡፡
የኢኮኖሚ ባለሙያ ሊቃውንት እንደሚሉት፤ አንድ የንግድ ድርጅት አትራፊ መሆን ከፈለገ በቅድሚያ ወጪዎቹን መቀነስ፣ ርካሽ ጉልበት መጠቀም… ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ የኢኮኖሚክስ መርህ አኳያ ከደቡብ አፍሪካ ለመጡት “ገበሬዎች” የሚከፈለውን ደመወዝና ጥቅማጥቅም ስናየው፣ ዶ/ር አረጋ እየሄዱበት ያለው አሰራር ምን ያህል አትራፊ እንዳልሆነ መገንዘብ አያዳግትም፡፡
ይህንን ሁኔታ በትንሽ ስሌት ላሳይ፡፡ ለምሳሌ፡- ከደቡብ አፍሪካ የመጣ የአንድ የእርሻ ባለሙያ፤ ጥቅማ ጥቅሞቹን ጨምሮ ወርሃዊ ደመወዙ እስከ 330 ሺህ ብር ይደርሳል፡፡ በአንፃሩ፤ የኤልፎራ ዋና ሥራ አስኪያጅ የአንድ ዓመት ደመወዝ ከእነ ጥቅማጥቅሙ ከ350 ሺህ ብር አይበልጥም፡፡ ልዩነቱን እዩት! የአንድ ፈረንጅ የአንድ ዓመት ደመወዝ፣ የሥራ አስኪያጁ የ12 ዓመት ደመወዝ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ወይም አንድን ደቡብ አፍሪካዊ ለአንድ ዓመት የምንቀጥርበትን ገንዘብ ቢያንስ ቢያንስ 24 ኢትዮጵያውያንን ለአንድ ዓመት ልንቀጥርበት እንችላለን ማለት ነው፡፡ ኤልፎራን “ብር መቋጠር የማይችል ቀዳዳ ከረጢት” (በእርሳቸው አባባል ‘Black hole’) ያደረገው፣ እንዲህ ያለው ሁኔታ መሆኑን፣ ዶ/ር አረጋ ልብ ሊሉት ይገባል!
ሌላው የዶ/ር አረጋን ለአንድ ጉዳይ ሁለት መስፈርት (Double Standard) የመጠቀም ድክመት ላንሳ፡፡ ዶ/ር አረጋ፤ ጥሩ እውቀት ያላቸው ምሁር ብቻ ሳይሆኑ፤ እውቀት ሀገርንም ተቋምንም ሊለውጥ እንደሚችል የጠራ ግንዛቤም አላቸው፡፡ ለዚህም ነው ዩኒቲ ዩኒቨርስቲን እንዲመሩ ኃላፊነት ሲሰጣቸው፣ ዩኒቨርስቲ ገብተው ስለ ስነ-ትምህርት (Education) ተምረው፣ ሌላ የዶክትሬት ዲግሪ የያዙት፡፡ ይህንን ያደረጉት በእውቀት ላይ የተመሰረተ አመራር ለመስጠት መሆኑንም ደጋግመው ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ ይሄ ትክክለኛ አስተሳሰብ፣ ጠቃሚ መርህ ነው፡፡
ታዲያ ዶክተር አረጋ ይህንን መርህ ተከትለው እየሰሩ ነው? አይደለም! በቅርብ ጊዜ በኤልፎራ የፈጸሙት ተግባር ይህንን የሚጻረር ነው፡፡ ሰሞኑን ኤልፎራ የተባለውን ኩባንያ ውስጣዊ አደረጃጀት (ማኔጅመንቱ ሳይመክርበት፣ በጥናት ሳይደገፍ) በስሜት ተነሳስተው ከለወጡ በኋላ፣ የዶሮ ልማት ዘርፉን እንዲመራ “ማኔጂንግ ዳይሬክተር” አድርገው የ“ሾሙት” ሰው፣ 12ኛ ክፍልን በአግባቡ ያጠናቀቀ እንኳ አይደለም፡፡ ይህ ታክሲ ነጂ የነበረ ሰው፤ እንኳን በእውቀት ላይ የተመሰረት አመራር ሊሰጥ ቀርቶ ከሰው ጋር የእግዜር ሰላምታ ለመለዋወጥ የሚያስችል ባህሪ የሌለው፣ ተግባብቶ መስራት የጎደለው፣ ከካቦነት የዘለለ ስራ መስራት የማይችል መሆኑን ሁሉም ሰው ያውቃል።
ዶ/ር አረጋ፤ ይህንን ሰው መድበው ዝም ቢሉ ጥሩ ነበር፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት፤ “የኢህአዴግን ፕሮግራም ከተቀበለ ዘበኛንም ቢሆን ሚኒስትር ማድረግ” እንደሚቻል ከተናገሩት ጋር በተመሳሳይ ሁኔታ ዶ/ር አረጋ፤ ሾፌራቸው የነበረን ግለሰብ ሥራ አስኪያጅ አድርገው ከሾሙ በኋላ የኩባንያውን የበላይ ኃላፊዎች ሰብስበው፤ “ይህ ሰው ዲግሪ የለውም፤ ግን እናንተ ካላችሁ አራት ዲግሪ ይበልጣል” ማለታቸውን አንድ ወዳጄ ሹክ ብሎኛል፡፡ እንዲህ ያለው ለአንድ ጉዳይ ሁለት መስፈርት (Double Standard) የመጠቀም አባዜ፤ሚድሮክን ወደ አደገኛ አዘቅት እያንደረደረው መሆኑ ይታየኛል፡፡
የመሪ (Leader) ባህሪ መጥፋት በሚድሮክ
እንደ ዶ/ር አረጋ ያለ በCEO ደረጃ ኃላፊነት ይዞ በርካታ የንግድ ተቋማትን የሚመራ ሰው፤ ቀዳሚ ስራው መሆን ያለበት፣ እርሱን የሚተኩ መሪዎችን ማፍራት መሆኑን በዘርፉ የተመራመሩ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ በዚህ ረገድም ዶ/ር አረጋ፤ የተሳካ ስራ ሰርተዋል ለማለት የሚቻል አይመስለኝም፡፡
በርግጥ በእርሳቸው ዙሪያ አስር ምክትሎችን በስም ደረጃ ኮልኩለዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች እያንዳንዳቸው ከሁለት በላይ ኩባንያዎችን ስራ እየተከታተሉ ነው ቢባልም፣ አንዳቸውም እዚህ ግባ የሚባል ፍሬ ያለው ስራ ሊሰሩ ባለመቻሉ፣ ዶ/ር አረጋ፤ ጧት ማታ ከመማረር አልፈው በአደባባይ ድክመታቸውን በመናገር ሲተቹ ይስተዋላሉ፡፡ የኩባንያ ሥራ አስኪያጆች፤ በራስ በመተማመን ስሜት ስራቸውን መስራት ትተው፣ በየእለቱ ወደ ዶ/ር አረጋ ቢሮ በመሄድ ከእርሳቸው የሚሰጥን ቡራኬ መሰል መመሪያ አንጠልጥለው በመምጣት፣ ያልገባቸውን ስራ ለመስራት ላይ ታች በማለት ሲመናተሉ ይታያሉ፡፡
የእያንዳንዱ ኩባንያ ዋና ስራ አስኪያጆችም ሆኑ፤ “Principal Operation Officer” የሚል ማዕረግ የተሰጣቸው የዶር አረጋ ምክትሎች፣ የመሪነት ሚናቸውን በአግባቡ መወጣት ባለመቻላቸው፣ የእያንዳንዱን ኩባንያ እቅድ የሚያቅዱት፣ ሰራተኛ የሚቀጥሩና የሚያሰናብቱት፣ አቅጣጫ የሚሰጡት፣ ስለ እያንዳንዱ ነገር ውሳኔ የሚወስኑት… ራሳቸው ዶ/ር አረጋ ናቸው፡፡
ከዚህ አልፈው የእያንዳንዱን ኩባንያ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ራሳቸው ወደ መከታተል ወርደዋል። እናም ተኪን የማፍራቱ ስራ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ካለበለዚያ (ከመለስ ዜናዊ በኋላ ኢትዮጵያን እንደገጠማት መሰነካከል) እርሳቸው ከሌሉ፣ ሁሉም ነገር ተረት ሆኖ ይቀራል የሚል ስጋት አድሮብኛል፡፡
ዶ/ር አረጋ፤ ባለፉት 20 ዓመታት የተሰጣቸውን 5 ኩባንያዎች ወደ 26 ከፍ አድርገዋል፡፡ (በርግጥ ብዙዎቹ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች እንጂ ከአምስቱ ኩባንያዎች የተገኘውን ገቢ በማሳደግ የተፈጠሩ አይደሉም) ለእነዚህ ኩባንያዎች የአሰራር ስርዓትም ዘርግተዋል፡፡ ኩባንያዎቹን የሚመሩ ዋና ሥራ አስኪያጆችንም ሾመዋል፡፡ ይሁን እንጂ “ዋና ሥራ አስኪያጅ” ተብለው የተቀመጡት ሰዎች (አንዳንዶቹ) በስማቸው የንግድ ፈቃድ ከማውጣት የዘለለ የመወሰን ስልጣን የላቸውም፡፡ (ስልጣን ብቻ ሳይሆን አቅምም ስለሌላቸው በማኔጅመንት አባላት የሚነሱ ሃሳቦችን በመፍራት ሌላው ቀርቶ የማኔጅመንት ስብሰባ በአግባቡ አያካሂዱም፡፡ ለምሳሌ፡- በኤልፎራ ባለፉት 11 ወራት አንድም የማኔጅመንት ስብሰባ ተደርጎ አያውቅም)
በየዓመቱ የሚቀርበውን የኩባንያዎቹን የአፈጻጸም ሪፖርት ስንመለከት፤ ከሃያ ስድስቱ ኩባንያዎች ብዙዎቹ መዘጋት የሚገባቸው አክሳሪዎች ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ በሚሊዮን የሚቆጠር የባንክ ብድር እንዳለባቸውም ይነገራል፡፡ ዶ/ር አረጋ የሚመሯቸው እነዚህ 26 ኩባንያዎች፣ አንዱ ከሌላው ጋር በገበያ ትስስር የተቆራኙም ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት አንዱ ኩባንያ ባይኖር የሌላውም ህልውና አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ሳይታለም የተፈታ ሆኗል፡፡
ኩባንያዎቹ ለሚያመርቷቸው ምርቶች ገበያ ፈልገው፣ ሸጠው፣ ተወዳዳሪና አትራፊ ሆነው የሚሰሩበት አግባብ እስከ አሁን በግልጽ አይታይም። በዚህም ምክንያት ብቃት ያለው፣ መወሰን የሚችል የኩባንያ መሪ ባልተፈጠረበት ሁኔታ፣ ዶ/ር አረጋ ከሌሉ ስንቱ ኩባንያ እንደሚዘጋና ምን ያህል ሰራተኛ እንደሚበተን፣ የሰይጣን ጆሮ አይስማ ብሎ ማለፍን እመርጣለሁ፡፡
ወደ ማጠቃለያ ከመሄዴ በፊት አንዲት ነጭብ ልጨምር፡፡ ይህቺን ጽሁፍ ሳዘጋጅ፣ ለረጅም ጊዜ በሚድሮክ ውስጥ ለሰራ ወዳጄ ደወልኩና፣ አስተያየት ካለው እንዲሰጠኝ ጠየቅኩት፡፡ እንዲህ አለኝ፤ “ወደ ሚድሮክ መጥቼ በመስራቴ ጥሩ “ሎሌ” መሆን እንዴት እንደሚቻል ተምሬአለሁ” ካለ በኋላ… “ከዶ/ር አረጋ ጋር መወያየት አስቸጋሪ ነው፡፡ አንድ ቃል በተናገርክ ቁጥር ከአፍህ ላይ እየቀሙ መልስ ስለሚሰጡህ ስርዓት ባለው መልኩ ሀሳብ መለዋወጥ አስቸጋሪ ነው። በዚህም ምክንያት በርካታ ሃሳቦችን ይዘህ ሄደህ፣ መናገር እንዳትችል አፍ አፍህን ሲሉህ፣ ጭንቅላትህ ተናውጦ፣ ያሰብከው ጠፍቶብህ፣ ስድብ ቀምሰህና ተዋርደህ ትመለሳለህ… እናም ጉዳይ እንኳ ቢኖረኝ ወደ እርሳቸው ከመሄድ መሸሽን መርጫለሁ፡፡ በዚህም ምክንያት ከእርሳቸው መማር የሚገባኝን እውቀት ማግኘት አልቻልኩም…” ነበር ያለኝ፡፡ እንዲህ ያለውን ሁኔታ እኔም አስተውያለሁ፡፡ እናም ይህም ሊታረም የሚገባው የአለቃና የምንዝርን ግንኙነት ውጤታማ የማያደርግ ተግባር ነው እላለሁ፡፡
ማጠቃለያ
የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በሚድሮክ ውስጥ ለረዥም ዓመታት የሰራ በመሆኑ ስለ ኩባንያዎቹ ደካማና ጠንካራ ጎኖች ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ብዙ መረጃዎችም በእጁ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ፣ ስጋትን ከመግለጽ ውጪ ሁሉም መረጃ ለጋዜጣ የሚቀርብ ባለመሆኑ፣ከዚህ በላይ መሄድን አልመረጥኩም፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለማዘጋጀት የተነሳሁትም የሚድሮክንም ሆነ የዶ/ር አረጋን ድክመት ለማጋለጥ ሳይሆን፤ ሁሉንም ነገር በይሉኝታ ይዘን በዝምታ ካለፍነው፣ የታጠረ መሬት ማስረከብ ብቻ ሳይሆን የሰራተኛ መበተን ሊፈጠር እንደሚችል ያለኝን ስጋት ገልጬ፣ ችግሮች በጊዜ እንዲፈቱ ለማሳሰብ መሆኑ እንዲታወቅ እሻለሁ፡፡
ከዓመታት በፊት ስለ ታላቁ ባለቅኔ፣ ስለ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን የሰማኋት አንዲት የሎሬቱ ንግግር በጊዜ መርዘም አልረሳኋትም፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው… በአንድ ወቅት የሎሬት ፀጋዬ ድርሰት ዝግጅት ተጠናቀቀና ለህዝብ ከመቅረቡ በፊት በባለሙያዎች ይገምገም ብለው ይጠይቁታል፡፡ ይህንን የሰማው ሎሬት ፀጋዬ፤ በንዴት ጦፎ “ፑሽኪንን ማን ገመገመውና ነው የእኔ ስራ የሚገመገመው?!” አለ ሲባል ሰምቼ ነበር፡፡
ራሳቸውን የሁሉም ነገር አዋቂ አድርገው ከፍታ ላይ ያስቀመጡት ዶ/ር አረጋ፤ ይህቺን ጽሁፍ ሲያነቡ “ፑሽኪንን ማን ተቸው?!” ዓይነት ጥያቄ እንደማያነሱ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ካነሱም ትልቁን ድክመታቸውን ከማመላከት የዘለለ ፋይዳ እንደማይኖረው አስረግጬ ልነግራቸው እወዳለሁ፡፡ በርግጥ ሰውየው ችግሮቹን ጠንቅቀው እንደሚያውቋቸው አስባለሁ፡፡ ሊገባኝ ያልቻለው ከኩባንያዎቹ ቀጣይነትና ከሰራተኛው ህልውና አንጻር አፋጣኝ ምላሽ ያልሰጡበትን ምክንያት ነው፡፡
በኔ እይታ የሚድሮክ ውድቀት የታላቁ ባለሀብት የሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ድክመት የወለደው ውድቀት ሳይሆን፤ በዙሪያቸው የተሰለፉና ኃላፊነት ወስደው ሚድሮክን እንመራለን ያሉ ሰዎች የፈጸሙት ስህተት ውጤት ነው፡፡ ዶ/ር አረጋ፤ ከሌሎቹ የሚድሮክ ኃላፊዎች ድክመትና ውድቀት ትምህርት ወስደው እየመሯቸው ባሉ ኩባንያዎች ውስጥ ተሸፋፍነው የተቀመጡ ድክመቶችን “በጥልቅ ተሐድሶ” ካላስተካከሉ፣ ውጤቱ አጥር አፍርሶ መሬት በማስረከብ ብቻ የሚጠናቀቅ ክስተት አይሆንም። ይልቁንም የብዙ ቤተሰብ መበተንን ሊያስከትል እንደሚችል ከወዲሁ ሊያስቡበት ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ ለዓመታት የሰሩትን በጎ ነገር ሁሉ በዜሮ ማባዛት ብቻ ሳይሆን በታሪክ ፊት ተጠያቂ መሆንም ነው፡፡
ዶ/ር አረጋ ባለፉት 20 ዓመታት ገደማ ያቋቋሟቸው ኩባንያዎች የሚመሩበትን የአሰራር ስርዓት በጽሁፍ አዘጋጅተው በሀገሪቱ በሞዴልነት የሚታይ ዘመናዊ የንግድ ሥራ አሰራር እውን እንዲሆን ጥረት አድርገዋል። በቀጣይ ጊዜአት ተጨማሪ ኩባንያ ከማቋቋም ወይም ሌላ የማስፋፊያ ስራ ከመስራት ታቅበው፣ ያቋቋሟቸው ድርጅቶች ቀጣይ ህልውና እንዲኖራቸው የማድረግ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል። ይህ አውን እንዲሆን ደግሞ የእርሳቸው ጣልቃ ገብነት ሳይኖር ኩባንያዎቹ በተመደበላቸው ኃላፊና የማኔጅመንት አባላት እንዲመሩ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ለማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡
ከዚሁ ጋር የተያያዘ አንድ ሃሳብ ልጨምር፡፡ ኩባንያን የመምራት “ስልጣን” መሰጠት ያለበት ለአቅመ ስልጣን ለደረሰ፣ በልበ ሙሉነት (with confidence) አስቦ ለሚሰራ፣ እውቀትም ልምድም፣ የመሪነት ብቃትም ላለው ሰው እንጂ የ”ተላላኪነት” ሚና ለሚጫወት ሰው፤ ኃላፊነትን ማሸከም ትርፉ ኪሳራ ነው፡፡
ሚድሮክ በውስጡ ባለ የአመራር ድክመት የተነሳ ላለፉት 15 ዓመታት ከሚድሮክ ጋር አብረው የዘለቁትን እንደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመሳሰሉ ደንበኞቹን እንዳያጣ እሰጋለሁ፡፡ ይህ ፍፁም መሆን የሌለበት ነው፡፡ መፍትሄው ደግሞ “ጥልቅ ተሐድሶ” ማድረግና የኩባንዎቹን አሰራር ማስተካከል፣ ፈረንጅ ተኮር አሰራርን ማስቀረት፣ ብዙ ጊዜ ያገለገሉ እድሜ ጠገቦችን በክብር መሸኘት፣ አዳዲስ የኩባንያ መሪዎችን መድቦ ሁሉንም የመወሰን ስልጣን መስጠት፣ ጣልቃ አለመግባት፣… ነው፡፡ ሚድሮክን እስካሁን በመጣንበት ከፊል ፊውዳላዊ “የሞግዚትነት” አሰራር ሳይሆን፣ በዶ/ር ዐቢይ የመደመርና የፍቅር መስመር መለወጥ ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል!
ሁላችንም ለለውጥ እንነሳ፡፡ እንደ ዶ/ር ዐቢይ ህልም ይኑረን፡፡ አንድ ቀን ህልማችን ተሳክቶ፣ ይህቺን ሃረግ  የምናስታውስበት ቀን ይመጣ ይሆናል! - ማን ያውቃል!?
ከአዘጋጁ፡- ከላይ የቀረበው ጽሁፍ ይዘት የሚያንጸባርቀው የጸሃፊውን ብቻ ነው፡፡

Read 3657 times