Saturday, 01 December 2018 16:32

ስለማህጸን በር ካንሰር እውቀት፤ ግንዛቤና፤ የመከላከል ተግባር

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

 ሴቶች እድሜያቸው ከሰላሳ አመት በላይ ከሆነ ቢቻል በአንድ አመት ካልተቻለ በሶስት አመት ወይንም በአምስት አመት አንዴ የህክምና ምርመራ በማድረግ ጤንነታቸውን መከታተል ይገባቸዋል፡፡
ዶ/ር ካሳሁን ኪሮስ
የማህጸን በር ካንሰር በሴቶች ላይ የሚከሰት አስከፊው የካንሰር አይነት እና በአጠቃላይም በገዳይነት ደረጃው ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጠው ነው፡፡ በ2018 እንደተመዘገበው መረጃ በየአመቱ በአለም አቀፍ ደረጃ 500‚000 አዲስ ህሙማን ተገኝተዋል፡፡ በአብዛኛው ሁሉም የማህጸን በር ካንሰር ሕመሞች Human Papilloma Virus (HPV)ከሚባለው የቫይረስ አይነት ጋር የሚገናኙ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ቫይረስ ያለባቸው አብዛኞቹ ሴቶች የማህጸን በር ካንሰር ችግር ላይገጥማቸው እንደሚችልም በሕክምናው ዘርፍ ታይቶአል፡፡ የማህጸን በር ካንሰር የሚይዛቸው ሴቶች ከሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ ኢንፌክሽን ጋር በተያያዘ ወይንም በሌሎች የአኑዋኑዋር ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ ሊከሰት እንደሚችል ይገመታል፡፡
Human Papilloma Virus (HPV) ስለሚባለው ቫይረስ ማወቅ ከሚያስፈልገው ነገር የሚከተለው ይገኝበታል፡፡
የግብረስጋ ግንኙነት ከተለያዩ ወንዶች ጋር የምታደርግ ሴት በአንድ አጋጣሚ በHuman Papilloma Virus (HPV) ልትያዝ ትችላለች፡፡ ነገር ግን ወደ 90% በላይ የሚሆኑት በቫይረሱ ቢያዙም እንኩዋን ኢንፌክሽኑ ከ1-2 አመት ከቆየ በሁዋላ በራሱ ጊዜ ምንም ዘላቂ ሕመም ሳይኖረው ሊድን ይችላል፡፡
በወሲብ ግንኙነት ጊዜ ኮንዶምን መጠቀም ከቫይረሱ እራስን ለመከላል ሊያግዝ ይችላል፡፡
ሴቶች ከብዙ ወንድ ጋር ሳይሆን ከአንድ ወንድ ጋር ብቻም የወሲብ ግንኙነት ቢፈጽ ሙም በቫይረሱ አይያዙም ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህም በተወሰነ ጊዜ በሕክምና ምር መራ እያደረጉ እራስን ማወቅ ተገቢ ይሆናል፡፡
ከማህጸን በር ካንሰር ጋር በተያያዘ ብዙ የሚነሱ ነጥቦች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ በህመሙ ዙሪያ ያለው እውቀት፤ ግንዛቤ እና እራስን ከሕመሙ ለመከላከል የሚደረገው ጥንቃቄ ምን ይመስላል? የሚለውን ከአንድ ጥናት የተወሰደ እውነታ ለንባብ ብለናል፡፡ ጥናቱን ይፋ ያደረጉት ይታገሱ ሀብታሙ አወቀ፤ ሳሙኤል ዮሀንስ አያንቶ እና ታሪኩ ላላጎ ኤርሳዶ ናቸው፡፡ ጥናት የተደረገውም በኢትዮጵያ በደቡብ አካባቢ በሆሳእና እና ሀዲያ ዞን ነው፡፡ ለጥናቱ የተመረጡት ሴትችም ጡት በማጥባት እድሜ ያሉ ናቸው፡፡
ጥናቱ እንደሚያስረዳው የማህጸን በር ካንሰር በኢትዮጵያ ሴቶችን ከሚገድሉ የካንሰር አይነቶች በሁለተኛነት ደረጃ የሚቀመጥ ሲሆን ይህን እስከ 2020 (በውጭው አቆጣጠር) ለመከላከል የሚያስችል ግብ ተቀምጦ እየተሰራበት የሚገኝ ነው፡፡ የማህጸን በር ካንሰርን ለመከላከል የሚያስችል በሀገር ደረጃ ያለ እውቀት፤ ግንዛቤና ድርጊት ምን ይመስላል ለሚለው ጥናት ወደ 583 ሴቶች የተሳተፉ ሲሆን ጥናቱ የተጠናቀቀውም June 2015 ነበር፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው በጥናቱ ከተካተቱት 583 እናቶች መካከል ወደ ሁለት መቶ ሰባ (46.3%) የሚሆኑት ሲጠየቁ የማህጸን በር ካንሰር ስለሚባለው ነገር ሙሉ የሆነ እውቀት አልነበራ ቸውም፡፡ ለጥያቄው ከቀረቡት ውስጥ ሀምሳ ስምንት (9.9%) የሚሆኑት ጥናቱ ከመጀመሩ በፊት በተሳሳተ መንገድ ሕመሙን የገለጹ ናቸው፡፡ ሁለት መቶ ሶስት (34.8 %) የሚሆኑት ጭርሱንም ስለህመሙ መረጃ የሌላቸውና የተሳሳተ ግንዛቤ ያላቸው እንዲሁም የማህጸን በር ካንሰርን መኖር አለመኖሩን አስቀድሞ ለማወቅ የህክምና ፍላጎት የሌላቸው መሆኑም ከግንዛቤ ገብቶአል፡፡ በተጨማሪም ስለማህጸን በር ሕክምናም ሆነ ስለመከላከሉ ምንም አይነት መረጃ አግኝተው የማያውቁ ነበሩ፡፡ በጥቅሉ በፍተሻው የተገኘው በማህጸን በር ካንሰር ዙሪያ ያላቸው እውቀት የደከመ እና መከላከሉንም እንደማያውቁት ነው፡፡ የእውቀት መድከም ደግሞ ከግንዛቤ እና ዝንባሌ መድከም ጋር እንደሚያያዝ እሙን ነው፡፡ ይህ እውነታ ሕመሙን እንዳይከሰት ለማድረግ የማያስችል መሆኑን የጥናቱ አቅራቢዎች ይገልጻሉ፡፡
የካንሰር ሕመም ባደጉትም ይሁን በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት በየጊዜው መጠኑ እየጨመረ እና አስከፊ እየሆነ እንዲሁም ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ትልቅ የጤና ችግር እየሆነ በመጣ በት ዘመን ላይ እንገኛለን፡፡ የካንሰር ሕመም ታማሚዎቹን ከማሰቃየት ባሻገር የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ሁኔታዎች ቀውስ ነው፡፡ ምንም እንኩዋን ጉዳዩ አለም አቀፍ ቢሆንም በተለይም በታዳጊ እና በመካከለኛው አገሮች ሕመሙን ለመመርመርም ይሁን ሕክምናውን ለመስጠት ያለው ሀብት ውስን በመሆኑ በፍጥነት ሕመሙ እየጨመረ እና ብዙዎችን ተጎጂ እያደረገ ነው፡፡  
ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት በየአመቱ ከ100.000 ሴቶች 34.8 የሚሆኑ ሴቶች አዳዲስ በካንሰሩ የተያዙ ስለሆኑ ምርመራውን ያደርጋሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ከ100.000 ውስጥ 22.5% የሚሆኑት ሴቶች በሕመሙ ምክንያት ይሞታሉ፡፡ በሰሜን አሜሪካ ከሚኖረው በካንሰሩ የመ ሞት እድል ጋር ሲነጻጸር እጅግ ከፍተኛ ነው። በሰሜን አሜሪካ ከ100.000 እናቶች በጡት ካንሰር ምክንያት 6.6% በማህጸን በር ካንሰር ምክንያት ደግሞ 2.5% ሴቶች ሊሞቱ እንደሚችሉ መረጃዎች ጠቁማሉ፡፡
የጡት እና የማህጸን በር ካንሰር በታዳጊ አገሮች ዋናዎቹ ሴቶችን ገዳዮች የሆኑ በሽታዎች ሲሆኑ የማህጸን በር ካንሰር በአመት እስከ 882.900 የጡት ካሰር ደግሞ እስከ 444.500 የሚደርሱ አዲስ ታማሚዎች ወደሕክምናው ይቀርባሉ፡፡ በታዳጊ አገሮች በጡት ካንሰር በአመት 324.300 ሴቶች ሲሞቱ በማህጸን በር ካንሰር ደግሞ 230.400 ሴቶች በየአመቱ ለሕልፈት ይዳረጋሉ። ይህ ቁጥር በአለም አቀፍ ደረጃ እስከ 2025 ድረስ ከፍ እንደሚል የሚገመት ሲሆን በጡት ካንሰር የሚሞቱ ሴቶች 720.905 እንዲሁም በማህጸን በር ካንሰር ደግሞ 394.905 የሚሆኑ ሞቶች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ጥናቱ መረጃውን ጠቅሶ ለንባብ ብሎአል፡፡
በኢትዮጵያ በጥቅሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በተለይም የማህጸን በር ካንሰር ሕመም ድርብ ጫና የፈጠረ ሕመም ነው፡፡ ምንም እንኩዋን በኢትዮጵያ በብሔራዊ ደረጃ የተደረገ ጥናት ባይኖርም በካንሰር ላይ ጥናት የሚያደርገው አለምአቀፍ ቡድን (IARC) የማህጸን በር ካንሰር በሁለተኛ ደረጃ ገዳይ  መሆኑን አረጋግጦአል። እንደመረጃው ከሆነ በአዲስ አበባ በተደረገው ምዝገባ እንደተገ ኘው ውጤት የማህጸን በር ካንሰር ሴቶችን በሁለተኛ ደረጃ ለሞት የሚያበቃ ሕመም መሆኑን ያረጋገጠ ሲሆን ይህም ከጡት ካንሰር ቀጥሎ የተመዘገበ ነው፡፡
የማህጸን በር ካንሰርን ለመከላከል የህክምናው አቅርቦት እንዲሁም የባለሙያዎች ተሳትፎ ወሳኝ ከመሆኑ አንጻር በኢትዮጵያ በመንግስት እና በተለያዩ አጋር ድርጅቶች አማካኝነት የተለያዩ የድጋፍ እንቅስቃሴዎች በመደረግ ላይ ናቸው፡፡ Human Papilloma Virus (HPV) ለሚባለው ቫይረስ ሴቶች ከመጋለጣቸው አስቀድሞ ምርመራ እንዲያደርጉ እና እራሳቸውን እንዲከላከሉ የሚያስችላቸውን አገልግሎት በበቂ እንዲያገኙ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች በመሰራት ላይ መሆናቸውን ጥናቱ ያመለክታል፡፡
‹‹…የማህጸን በር ካንሰርን ለመከላከል ማንኛዋም ሴት አስቀድማ የህክምና ክትትል ማድረግ ይጠበቅባታል። ካንሰሩ እንደተከሰተ አስቀድሞ ለማወቅ የሚያስችሉ ሁኔታዎች በአንዳንድ የሰውነት ክፍሎች  የማያጋጥሙበት ሁኔታ አለ፡፡ ለምሳሌ በማህጽን ውስጥ በዘር ፍሬ አካባቢ የሚፈጠረውን ካንሰር አስቀድሞ ለማወቅ አስቸጋሪ የሚሆንበት ሁኔታ አለ፡፡ ነገር ግን የህክምናው ክትትል ተደርጎ ካንሰሩ በመጀመሪያው ደረጃ ላይ እያለ ሳይስፋፋ ከታወቀ ህክምና በማድረግ መፈወስ ይቻላል። ካንሰሩ በሰውነት ክፍሎች መኖር አለመኖሩን ለማወቅ ከሚቻልባቸው የሰውነት ክፍሎች የሚታዩ ምልክቶች አሉ፡፡ ፈሳሽ በብዛት በብልት በኩል ይወጣል፣ ደም በብዛት አለጊዜው ይፈሳል፣ በግብረስጋ ግንኙነት ጊዜ መድማት ይኖራል፣ በመጸዳዳት ጊዜም ደም ሊፈስ ይችላል፡፡ ነገር ግን ቫይረሱ ብዙ ከቆየና በሽታውም ወደሌላ ሰውነት ከተስፋፋ ሕክምናው ብዙ አጥጋቢ አይሆንም፡፡ ስለዚህ ሴቶች የህመሙን ምልክት አይተናል አላየንም ብለው መዘናጋት የለባቸውም፡፡››
    ዶ/ር ካሳሁን ኪሮስ
ይቀጥላል

Read 680 times