Sunday, 02 December 2018 00:00

ሳምሰንግ፤ ቴክኖሎጂውን ለቻይና የሸጡበት ሰራተኞቹን ከሰሰ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ግዙፉ የአለማችን የኤሌክትሮኒክስ አምራች ኩባንያ የደቡብ ኮርያው ሳምሰንግ፤ “የጋላክሲ ስማርት ሞባይል ስልኮቼን የማመርትበትን ቴክኖሎጂ በህገወጥ መንገድ መንትፈው፣ ለቻይና ኩባንያዎች በመሸጥ፣ 13.8 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገንዘብ አግኝተዋል” በሚል በ8 ሰራተኞቹና ፈጠራዎቹን ገዝተዋል በተባሉት ሁለት የቻይና ኩባንያዎች ላይ ክስ መስርቷል፡፡
ኩባንያው ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ ብሉምበርግ እንደዘገበው፤ ሳምሰንግ በ8ቱ ሰራተኞቹ ላይ ክስ የመሰረተው፣ የጋላክሲ የሞባይል ስልኮቹን ስክሪን የሚሰራበትንና 1333.5 ሚሊዮን ዶላር ያህል ወጪ ያደረገበትን ኦርጋኒክ ላይት ኢሚቲንግ ዳዮድ የተሰኘውን የቴክኖሎጂ ፈጠራውን መንትፈው፣ ለሁለት የቻይና ኩባንያዎች ሸጠውብኛል በሚል ነው፡፡
በአለማችን የስማርት ፎን ገበያ ቀዳሚነቱን የያዘው የደቡብ ኮርያው ሳምሰንግ፤ “የቻይና ኩባንያዎች በራሳቸው ፈጠራ በገበያ ላይ መወዳደር ሲያቅታቸው፣የቴክኖሎጂ ፈጠራዎቼን መዝረፍ ጀምረዋል” በሚል በኩባንያዎቹ ላይም ክስ መመስረቱን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የቻይና ኩባንያዎች በአገሪቱ መንግስት የተደገፈ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ምንተፋ ላይ በስፋት ተሰማርተዋል በሚል አሜሪካም በተደጋጋሚ ቻይናን ስትወነጅል እንደቆየች ያስታወሰው ዘገባው፤ የተለያዩ የአሜሪካ ኩባንያዎችም የፈጠራ መብቶች ጥሰት ፈጽመዋል በሚል በተለያዩ የቻይና ኩባንያዎችና በሃላፊዎቻቸው ላይ ክስ መመስረታቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1207 times