Monday, 03 December 2018 00:00

ከልጅነት እስከ ዕውቀት - ከኢህአፓ ጋር!

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

· የቀኑ መንግሥት ይገነባል፤ የማታው መንግሥት ያፈርሳል”
· “አዛውንት ፖለቲከኞች ወደ ማማከር ሥራ ቢገቡ እመርጣለሁ”
· “እኔ ብቻ ነኝ ትክክለኛ የሚለው ግትርነታችን ይቆጨኛል”

የ60ዎቹ ትውልድ አባል ናቸው፡፡ በአገራችን ከተቋቋሙ የመጀመርያዎቹ ፓርቲዎች አንዱን ከመሰረቱት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ የኢህአፓ ሁለተኛው ሰው ነበሩ፡፡ ፓርቲውን በህቡዕ መርተዋል - አቶ ክፍሉ ታደሰ፡፡ በርካታ መፅሐፍትም ለንባብ አብቅተዋል፡- “ያ ትውልድ” -( ከቅፅ 1 እስከ 3)፤ “ዘ ጀኔሬሽን” (ቅፅ 1 እና 2)፣ “ግንቦት 7” እንዲሁም “ኢትዮጵያ ሆይ” (ቅፅ 1 እና 2) በድምሩ ስድስት ፖለቲካ-ነክ መፅሐፍትን ለአንባቢያን አድርሰዋል፡፡ ብዙዎች በዝና የሚያውቋቸው አቶ ክፍሉ፤በ1997 የቅንጅት አባል ሆነው ሲንቀሳቀሱ፣ የእስር ትዕዛዝ ከወጣባቸው ፖለቲከኞች አንዱ ነበሩ፡፡ ቀድመው ከሃገር በመውጣታቸው ግን ከእስር ተርፈዋል፡፡ በደርግ ዘመን በህቡዕ በሚያደርጉት የፖለቲካ እንቅስቃሴ፣ ወደተለያዩ ሃገራት ተጉዘዋል፡፡ ከሃገራቸው አምርረው የቀሩት ግን ከ97 ምርጫ በኋላ ነው፡፡
 አሁን የመንግሥትን ጥሪ ተከትሎ ወደ አገር ቤት ከገቡ ፖለቲከኞች አንዱ መሆናቸውን ጠቁመው ፤በፖለቲካአማካሪነት እየሠሩ እንደሚገኙም አስታውቀዋል፡፡ ኑሯቸውን በአሜሪካ ያደረጉት አቶ ክፍሉ፤ ባለትዳር ቢሆኑም ልጅ አላፈሩም፡፡ በቅርቡ ወደ ሃገራቸው ጠቅለው ለመመለስ ማቀዳቸውንም ተናግራዋል፡፡ የ71 ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ አቶ ክፍሉ ታደሰ፤በደርግ ዘመን ትውልዱን በፈጀው የ”ቀይ ሽብር ነጭ ሽብር” ጉዳይ፣ ገና
ከማለዳ ከኢህአፓ ጋር ስለፈጠሩት ቁርኝት፣በወቅታዊ ፖለቲካ ዙሪያና በሌሎችም--ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ-ምልልስ አድርገዋል፡፡ እነሆ፡-ወደ ፖለቲካ የገቡበት አጋጣሚ ምን ይመስላል?
በ1953 መፈንቅለ መንግስት ሲካሄድ፣ እኔ ልጅ ነበርኩ፡፡ የ6ኛ ወይም የ7ኛ ክፍል ተማሪ ብሆን ነው፡፡ በወቅቱ እኛ አፄ ኃይሥላሴን የምንከተል ሰዎች ነበርን። አፄ ኃይለሥላሴ ይሙት ብለን ነበር የምንምለው፡፡ በወቅቱ በእሳቸው ላይ እንዲህ ያለ ነገር ሲነሳ፣ ሊገባን አልቻለም፡፡ አባቴ የፈረንሳይ ተማሪ ነበር፣ አስተማሪም ነበር፡፡ የአፄ ኃይለሥላሴ መንግስት ደግሞ የመፈንቅለ መንግስቱን ሙከራ ይቃወማል፡፡ በዚህ ግር ይለኝ ነበር፡፡ በዚያው ወቅት ሦስት ሰዎች ተሰቀሉ ተባለና፣ እነሱን ለማየት ወደተሰቀሉበት ሥፍራ አመራን፡፡ የተሰቀሉት ግርማሜ ነዋይ፣ ግርማሜ ወንዳፍራሽና ሻምበል ጥላሁን ባየህ ናቸው፡፡ ሦስቱም ሰውነታቸው ቆስሏል፤ ተቦዳድሷል፡፡ እኔና ጓደኞቼ እዚያ ደርሰን የተሰቀሉትን ገርሞን እያየን እያለ፣ የሆኑ ግለሰቦች የተሰቀሉትን ሰዎች ቁስል በእንጨት ይወጋሉ፡፡
ያኔ እድሜዎ ስንት ይሆናል?
13 ዓመቴ ነው፡፡ ያንን ቁስል በእንጨት እየወጋጉ ስንመለከት፣ እኔና ጓደኞቼ ደንግጠን ጮህን። ሰዎቹ፤ “ዘመዶቻቸው ስለሆኑ ነው የጪሁት” እያሉ ሊደበድቡን መጡ፡፡ እኛም ወደ ፖሊስ ሮጠን አመለጥን፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ሶስታችንም ጓደኛሞች፤ ወደ ተማሪ ንቅናቄ ውስጥ የገባነው፡፡ ያ ያየሁት ነገር ዛሬም ከህሊናዬ አይጠፋም፡፡ ያ የመፈንቅለ መንግስቱ ሙከራን ተከትሎ የመጣው የጀነራል መንግስቱ ንዋይ የፍርድ ሂደት፤ ለተማሪው እንቅስቃሴ ትልቅ ጅማሮ ነው፡፡ እኔና ጓደኞቼም በዚያ ነው ወደ ተማሪ ትግሉ የገባነው፡፡ እኔ ደግሞ ትውልድና እድገቴ፣ ተፈሪ መኮንን ት/ቤት አካባቢ ነው፡፡ በተማሪዎች የሚካሄደውን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ እከታተል ነበር፡፡ ተማሪዎች ሲያምፁ እመለከት ነበር፡፡ በተፈሪ መኮንን ት/ቤት፣ በአንድ ወቅት የአዳሪ ተማሪዎች ተቃውሞ ተፈጥሮ ነበር፡፡ በዚያ ተቃውሞ ውስጥ ሁለት ሰውነታቸው ፈርጣማ ግብፃውያን ነበሩ፡፡
የአመፁ መሪዎች ነበሩ?
ይባላል፤ እኛ ግን ያኔ አናውቅም፡፡ እነዚህ ግብፃውያን የሙስሊም ብራዘርሁድ አባላት ናቸው፤ በኋላ እንዳወቅሁት፡፡ በግብፅ እንደሚታወቀው፤ ጋማል አብዱል ናስር ንጉሡን ከስልጣን ሲያስወግዱ፣ የሙስሊም ብራዘርሁድና የኮሚኒስት ፓርቲው አግዟቸው ነበር፡፡ በኋላ ግን ጋማል አብዱልናስር፤ የሙስሊም ወንድማማቾች ላይም ሆነ ኮሚኒስት ፓርቲው ላይ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ እነዚህ ሁለት ግብፃውያንም በዚህ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ ሳይመጡ እንዳልቀረ እገምታለሁ፡፡ ግብፆቹ በአመፁ ምን ሚና እንዳላቸው በውል ባላውቅም፣ በወቅቱ እንደነበሩ ግን ዛሬም ድረስ የማስታውሰው ነው፡፡ በኋላ በእድሜም እየጨመርን ስንመጣ፣ የተለያዩ መፃህፍትን እናነብ ነበር፡፡ በዚህም ራሳችንን እያጎለበትን ወደ ትግሉ ገባን ማለት ነው፡፡
ኢህአፓ እንዴት ነው የተመሰረተው?
ኢህአፓ በዚህ ቀን ተመሰረተ የሚባል አይደለም፤ በሂደት የመጣ ነው፡፡ ኢህአፓ ከመመስረቱ 10 ዓመት በፊት ተማሪው የተለያየ ጥያቄ ሲያነሳ ቆይቷል፡፡ ይሄ አንዱ ሂደት ነው፡፡ የተማሪ ንቅናቄው ለኢህአፓ መመስረት ትልቅ አስተዋፅኦ አለው፡፡ እኛ በወቅቱ መደራጀት ምን እንደሆነ አናውቅም፡፡ ስለ ሰብአዊ መብት የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ይሄኛው የእናንተ ትውልድ፤እነዚህን ነገሮች ያውቃል፤ እድለኛ ነው፡፡  በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ የነበሩ ወጣቶች፤ለመደራጀትና ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር፣ በየአቅጣጫው ወደ ውጪ ሃገር  ወጡ፡፡ ሶማሌ፣ አውሮፓ --- በተለይ በአልጀሪያ የተለያዩ ቡድኖች ተደራጁ፡፡ በዚህ የንቅናቄ ሂደት ውስጥ ጉልህ ቦታ የነበራቸው እነ ብርሃነ መስቀል ረዳ ናቸው፡፡ አውሮፕላን ጠልፈው አልጀሪያ ገብተው፣ ትልቁን ቡድን አደራጁ፡፡ ብርሃነ መስቀል ረዳ በተለይ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ጉልህ ሚና አለው፡፡ በዚህ ሁኔታ የእርስ በእርስ ውይይት ሲደረግ ቆይቶ፣ በሚያዚያ 1964 ዓ.ም የመጀመሪያው ስብሰባ፣ በርሊን ላይ ተደርጎ ፓርቲው ተመሰረተ፡፡
ኢህአፓ በሃገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያው የፖለቲካ ፓርቲ ነው ማለት ይቻላል?
ከኛ በፊት መኢሶን፤ ጀርመን ሃምቡርግ ውስጥ ተመስርቶ ነበር፡፡ ግን መኢሶን በጣም ህቡዕ ስለነበር ስለ መቋቋሙ ማንም አያውቅም፡፡
ኢህአፓ ያኔ የመረጠው የትግል ስልት ምን ነበር?
በሰላማዊ መንገድ አይቻልም በሚል፣ ሁኔታውን ገምግመን፣ በትጥቅ ነበር የጀመርነው፡፡ በ1965 ዓ.ም ከ20 እስከ 30 የሚደርሱ ሰዎች ተመልምለውና ስልጠና ወስደው፣ ወደ በረሃ እንዲገቡ ተደርጎ ነበር፡፡
ኢህአፓ እንዴት በደርግ ተቀደመ?
ኢህአፓ በተለይ ዲሞክራሲያ በተባለው ልሳኑ፣ የሚችላቸውን ጥያቄዎች በማንሳት፣ አቅጣጫ ለማስያዝ ሞክሯል፡፡ ለወጣቱም ለሌላውም የህብረተሰብ ክፍል እንዲሁም ለራሱም ለደርግ፡፡ ይሄ እስከ 1967 መጀመሪያ ድረስ ቀጥሏል፡፡ አብዮታዊ ንቅቄው ታህሳስ 1966 ከተነሳ በኋላ እስከ መስከረም 1967 ድረስ በነፃነት ነበር ሲካሄድ የነበረው፡፡ ደርግ ስልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ ወዲያው የመናገር፣ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትን የሚደፈጥጥ እርምጃ ወሰደ፡፡ ይሄን ኢህአፓም መኢሶንም ይቃወመው ነበር፡፡ ደርግም ህዝባዊ መንግስት አስመስርቼ፣ ወደ ካምፕ እገባለሁ ሲል ነበር የከረመው፡፡ ከደርግ ጋር የነበረን መሠረታዊ ልዩነት የሚጀምረው ከመስከረም 2 አዋጅ በኋላ ነው፡፡  
ኢህአፓን ተወቃሽ የሚያደርገው አንዱ የነጭ ሽብር ጉዳይ ነው …
ይሄን በተመለከተ ሂደቱን ባስረዳ እመርጣለሁ። ደርግ አፋኙን አዋጅ በ1967 ዓ.ም ነበር ያወጀው። አዋጁ ከታወጀ ጀምሮ ኢህአፓ (ከ1967 - 1969) ሁለቱን ዓመት ወደ መሳሪያ እንቅስቃሴ አልገባም። በዚህ ጊዜ ሁሉ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች እያነሳ ነበር ኢህአፓ የቆየው። ወደ መሳሪያ ምናምን አልገባም። ዲሞክራሲያዊ መብቶች፣ የመፃፍና የመደረጃት መብት እንዲፈቀድ፣ የብዙሃን ማህበራት የመደራጀት መብታቸው እንዲጠበቅ---በሚሉት ላይ ትግል ይካሄድ ነበር፡፡ በሌላ በኩል፤ አንዱ ትልቁ ጥያቄ የነበረው የኤርትራና የብሔር ብሔረሰብ ጥያቄ ነው። በተለይ ደግሞ የኤርትራ ጥያቄ ላይ የኢህአፓ አቋም የነበረው፣ ከመብት ባሻገር በሰላማዊና ዲሞክራሲዊ መንገድ እልባት ያግኝ የሚል ነበር፡፡ ይሄን ጥያቄ በኃይል መፍትሄ ለማበጀት መሞከር ከባድ ነው፤ አይቻልም የሚል ነበር፡፡ የደርግ ርዕሰ ብሔር የነበሩት ጀነራል አማን አምዶም፤ ለኛ ብዙም ፍቅር አልነበራቸውም። ግን በአስተሳሰብ ደረጃ እሳቸውም የኤርትራን ጉዳይ በሰላም ለመፍታት ነበር የሚያስቡት። በተለይ የኤርትራ ህዝብ ፌዴሬሽኑ ከተመለሰለት ጥያቄውን ሊያረግብ ይችላል የሚል አቋም ነበራቸው፡፡ ግን ያው መንግስቱ ኃይለማርያም ገደላቸው፡፡
በሌላ በኩል፤ መኢሶን ከደርግ ጋር ግንኙነት ከመፍጠሩ በፊት በተለይ እኔ ነበርኩ ከመኢሶን ጋር አወያይ የነበረው፡፡ እኔና አንዳርጋቸው አሰግድ በአንድ በኩል እንዲሁም ተስፋዬ ደበሳይና ኃይሌ ፊዳ በሌላ ደረጃ እንወያይ ነበር፡፡ በውይይታችን ሁለታችንም የነበረን አቋም፣ ኤርትራ ውስጥ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ነበር፡፡ ምክንያቱም ከተቀሰቀሰ በቀላሉ ጦርነቱን ማሸነፍ ስለማይቻል፣ ሃገሪቱ ቀውስ ውስጥ ትገባለች፤ ስለዚህ ሰላማዊ በሆነ መልኩ ነው መፈታት ያለበት የሚል አቋም ነበረን፡፡ ሁለታችንም በዚህ በኩል የምንችለውን ሁሉ እናድርግ ነበር፤ አቋማችን። እኛና መኢሶን የተስማማነው፤ ጦርነቱ እንዳይነሳ በተመሳሳይም የመሬት አዋጁ እንዲታወጅ ነበር፡፡ ደርግ ቀድሞ ሁለቱንም አወጀ፡፡ ጦርነቱንም የመሬት አዋጁንም አወጀ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ እያለን ደርግ በከተማ በተለይም በሰራተኛ ውስጥ ያለውን እንቅስቃሴ መቆጣጠር እያቃተው መጣ፡፡ የሰራተኛው ጥያቄ አንድ ብቻ ነበር፤ እሱም የመደራጀት መብታችን ይከበር የሚል ነው፡፡ ይሄ እየከረረ ሲሄድ፤ደርግ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበርን ዘጋ፡፡ ሲዘጋ በየቦታው ተቃውሞ ተጀመረ፡፡ ደርግ ይሄን መቋቋም ሲያቅተው ደግሞ እንደገና ከፈተ፡፡ የሰራተኛው ጥያቄም በስፋት መቅረብ ጀመረ፡፡ ምላሽ ካልተሰጣቸው የስራ ማቆም አድማ ለማድረግ እንደሚገደዱ አስታወቁ። ይሄን መልዕክት የያዘ ወረቀት፣ በአየር መንገድ ውስጥ ሲያሰራጩ የነበሩ ስድስት ሰዎች፣ መስከረም 1968 ተገደሉ። ከየክፍለ ሃገሩ የመጡ ሰራተኞችም እየተለቀሙ ወደ እስር ቤት ተወሰዱ፡፡ 600 ሰው ታሰረ፡፡ እኔ “የሰራተኛው ድምፅ” የሚባለውን ጋዜጣ አዘጋጅ ነበር። በወቅቱ እኔም አንደር ግራውንድ (ህቡዕ) ገባሁኝ፡፡ በዚያው “አንደርግራውንድ” የሰራተኞች ንቅናቄ ተጀመረ። እኛ ስናደራጀው ነበር፡፡ የታሰሩ መሪዎችን (6 መቶዎቹንም) ሁሉም ሰራተኞች፣ እስር ቤት እየሄደ እንዲጠይቅ፤የታሰሩ ሰዎችን ቤተሰብ ለመርዳት፣ እያንዳንዱ ሰራተኛ በወር 5 ሳንቲም እንዲያዋጣ ተወስኖ ትልቅ ንቅናቄ ተፈጠረ፡፡ በኋላ ጥር ላይ “ኢላማ” (የኢትዮጵያ ላብአደሮች ማህበር) የሚባል ንቅናቄ ተጀመረ፡፡ በድብቅ ነበር የተመሰረተው፡፡ የ“ኢላማ” ስብሰባ የተካሄደው ዳሮ ነጋሽ በምትባል፣ የብርሃንና ሰላም ሰራተኞች ማህበር መሪ የነበረች ቤት ውስጥ ነው፡፡ በዚህ እንደገና የሰራተኛው እንቅስቃሴ ለደርግ ራስምታት መሆን ጀመረ፡፡ በየፋብሪካው መሪዎቻችን ሳይፈቱ ሌላ ማህበር አይመሰረትም የሚል እንቅስቃሴ ተጀመረ፡፡ ይህ የሆነው ደርግ በመኢሶን መሪነት ስድስት መቶዎቹን ካሰረ በኋላ፣በአጠቃላይ ኢሠአማን ተክቶ የሚሰራ ማህበር ለመመስረት እየተዘጋጀ ነበር፡፡ ሆኖም መሪዎቻችን ሳይፈቱ ሌላ ማህበር አንመሰርትም የሚለውን እንቅስቃሴ፣ ደርግ ምንም ማድረግ አልቻለም፡፡ የታሰሩትን ፈታ፡፡
በወቅቱ በመኢሶን በኩል የተጀመረው የሰራተኞች ማህበርን ማደራጀት ብዙ ርቀት ሄዶ ስለነበር፣ከእስር የተፈቱትን ለማካተት አስቸጋሪ ነበር፡፡ በዚህ እንደገና በድብቅ አመራሩ በኩል ተቃውሞ አሰማ። የአመራር ምርጫው መራዘም አለበት የሚል ጥያቄ ቀረበ። ትልቅ ተቃውሞ ተነሳ፡፡ ምርጫውን ማካሄድ እንደማይቻልና ሰራተኛውን መቆጣጠር እንደማይችሉ ሲረዱ፣ የማህበሩን አመራሮች ምርጫ ላልተወሰነ ጊዜ አስተላልፈነዋል አሉ፡፡ በዚህም የሰራተኛው እንቅሰቀሴ ቆመ፡፡ በዚህ መሃል ነው ደርግ የጦርነት አዋጅ ያዘጋጀው፡፡ “ማንኛውም የኢህአፓ አባል በተገኘበት ይገደል” የሚለውን ጦርነት፣ በ1969 መስከረም 2 አወጀ፡፡ ያኔ ነው፣ ኢህአፓ ራሱን ወደ መከላከል የገባው፡፡
ግድያ 1 (የመጀመሪያው)፤ የ60ዎቹ ነው፤ ጅማ ላይ ሚያዚያ 1968 ደርግ፣ በርካታ አባሎችን ገድሎብናል። ከዚያ በፊትም ግድያ ፈፅሟል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ኢህአፓ ምንም አይነት የኃይል እንቅስቃሴ አልጀመረም፡፡ ኢህአፓ ጀመረው የሚባለው ነገር ከዚህ አንጻር ውድቅ ነው፡፡ ቀይ ሽብር ነው የተጀመረው፡፡ እነሱ ያንን የጦርነት አዋጅ ካወጡ በኋላ ነው ኢህአፓ የጀመረው፡፡
በወቅቱ ደርግ፣ መኢሶንና ኢህኣፓ ሊደማመጡ አለመቻላቸው፣ ሃገሪቱ አሁን ድረስ ላልወጣችበት የቀውስ አረንቋ  ዳርጓታል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ይስማማሉ?
እሱ እውነት ነው፡፡ ያለመደማመጥ ብሎ ማስቀመጥ ያስቸግራል፡፡ ጉዳዩ መብትን ያለማክበር ነው። አሁን ያሉት ወጣቶች የሚጠይቁት መብት ነው፤ ያኔም የመብት መከበር ጥያቄ ነበር፡፡ “ለመደማመጥ የሚያስችለንን ሁኔታ ገድበሃል፤ ለመደማመጥ እድል ይሰጠን” ነው ጥያቄው የነበረው፡፡ ደርግ የህዝቡን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት በህግ ነው የገደበው። ታዲያ እንዴት ለመደማመጥ የሚያስችል ሁኔታ ይፈጠር? በወቅቱ እኮ ዛሬ ካሉ የመብት ጥያቄዎች ያነሰ የመብት ጥያቄ ነበር ስናቀርብ የነበረው፡፡ የኛ ጥያቄ፤ የመብት መረገጥ ነው፡፡ እነዚያ ያኔ በትንሹ የምናነሳቸው ጥያቄዎች ናቸው፤ ዛሬ ሰፍተው የወጣቱ ጥያቄ የሆኑት፡፡
ኢህአፓ ለዚህ ሃገር ፖለቲካ አበርክቶታል የሚሉት አስተዋፅኦ ምንድን ነው?
የፖለቲካ ፓርቲ ባህል እንዲኖር ማድረጉ ትልቁ አስተዋፅኦ ይመስለኛል፡፡ ዛሬ ድረስ ህዝቡ ለመብቱ የመታገል ባህሉም ከዚያ የመጣ ነው፡፡ በፅናት የመታገል ፍላጎት በኢህአፓ በኩል የሰረፀ ይመስለኛል፡፡ የህዝባዊ ስርአት ምስረታ፣ የእኩልነት ጥያቄ እንዲሁም የመሬት ጥያቄ በማንሳት፣ ለአርሶ አደሮች የመሬት ጥያቄ መጠናከር ኢህአፓ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡
አሁን በአቶ መርሻ ዮሴፍ የሚመራው ኢህአፓ፣ ሃገር ውስጥ ገብቷል፡፡ እርስዎ ከነሱ ጋር ያለዎት ግንኙነት ምንድን ነው?
እተባበራቸዋለሁ፡፡ በሚያደርጉት ሁሉ አግዛቸዋለሁ፡፡ የሚያነሱት የህዝብ እኩልነትን፣ ዲሞክራሲን ነው፣ ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ፀንታ እንድትቆም፤ አሁንም ያ ፍላጎት አለ፡፡ እነሱ ይሄን ነው እያደረጉ ያሉት፡፡ በታሪካችንም የጋራ ታሪክ ነው ያለን፤ በዚያ እጋራቸዋለሁ፡፡ አብረንም በዚህ ጉዳይ እንሰራለን፡፡ ዛሬም ነገም በዚያ እተባበራቸዋለሁ፡፡ ግን በድርጅቱ ውስጥ ራሴ በወሰድኩት አቋም ተሳታፊ አይደለሁም፡፡ ኢህአፓ አሁን ምን ያህል ጥንካሬ አለው የሚለው ሊያከራክር ይችላል፤ ግን አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ የተሻለ ቁመና አላቸው ከሚባሉት ፓርቲዎች አንዱ  ነው፡፡
ኢህአፓ በፖለቲካ ልዩነት ምክንያት እርስበርሱ ለተጠፋፋው ትውልድ  ኃላፊነት ይወስዳል?
የቀይ ሽብር ነጭ ሽብር ጉዳይ፣ ከዲሞክራሲ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የመብት መከበር ጥያቄ ነው። የህዝቡን መብት ማክበር ካልተቻለ፣ ውጤቱ ያው ነው የሚሆነው፡፡ የቄሮ፣ የፋኖ-- ንቅናቄ ለምን ተነሳ? የ97 ምርጫ ለምን እንዲያ ተጠናቀቀ? የመብት ጥያቄ አይደለም? ያ ግድያ ለምን ተፈፀመ? የመብት ጥያቄን ተከትሎ እንዲህ ያለው ነገር ይከሰታል፡፡ የትግሉ አንዱ መራር እውነት ነው፡፡ መብትን የመገደብ መጨረሻው ይሄው ነው፡፡ ቀይ ሽብር በተለይም ሰራተኛው፣ የራሴ ማህበር ይኑረኝ ብሎ ሲታገል፣ በመብት ጥያቄ ላይ የታወጀ የሞት አዋጅ ነው፡፡ መብት ሲገደብ አመፅ ይወለዳል፡፡ አመፅ ደግሞ ወደዚህ አይነት መጠፋፋት ይወስዳል፡፡ ቀይ ሽብርም የዚህ ባህሪ አካል ነው፡፡
ጥያቄው ኃላፊነቱን ማነው የሚወስደው ነው?
ሙሉ ለሙሉ ደርግ ይወስዳል ማለት አይቻልም። በደርግ ውስጥም የነበሩ እነ ሻምበል ሞገስ ወ/ሚካኤል፣ እነ መቶ አለቃ አለማየሁ ኃይሌ፣ እነ ጀነራል ተፈሪ በንቲ-- የጦርነቱን አዋጅ ሁኔታ ለመቀየር በተለይ ከነሐሴ 1968 ጀምሮ ደርግን ሪፎርም ለማድረግ፣ በቀጥታ ህዝባዊ መንግስት ለመመስረት፣ የተቃዋሚ ኃይሎች በዚህ ሂደት ውስጥ እንዲሳተፉ ጥረት አድርገው ነበር፡፡ በወቅቱ እነ ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማርያም፤ በረቀቀ ደባ ነው እነዚህን ኃይሎች አጥፍተው፣ የቀይ ሽብርን በዚያ ደረጃ ሊያፋፍሙ የቻሉት፡፡ በዚህ ምክንያት በአጠቃላይ የጥፋቱ ባለቤት ደርግ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ከደርግ አባላት አብዛኞቹ ድርጊቱን አንፈልግም ብለው ነበር። የኮሎኔል መንግስቱ፣ በከፊልም የመኢሶን ቡድን ነው፣ ይሄ ነገር ሥራ ላይ እንዲውል ያደረገው፡፡ ደርግ በጅምላ መፈረጅ የለበትም፡፡
መስቀል አደባባይ የቆመው “የቀይ ሽብር ሰማዕታት ሃውልት” ለእርስዎ ምን ትርጉም ይሰጥዎታል?
የቀይ ሽብር ሰማዕታት እንዲቋቋም የተወሰነ አስተዋፅኦ አድርጌያለሁ፡፡ ስለዚህ እደግፋለሁ ማለት ነው፡፡ የሰማዕታቱ መታወሻ መኖር ነበረበት፡፡ በምን መልኩ? አሁን ባለው መልኩ ይሻላል አይሻልም? የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚያ ሰማዕታት የወደቁት ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ፀንታ እንድትቆም ካላቸው አላማ ነው፡፡ የለማች ኢትዮጵያ እንድትኖር ነው መስዋዕት የሆኑት፡፡ ወጣቶቹ ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው ብቻ ቢያስቡ በዘመኑ የተማሩ፣ ለራሳቸው መኖር የሚችሉ ነበሩ፤ ግን ለኢትዮጵያ ብለው ነው የወደቁት፡፡ የካቲት 12 ሃውልት፤ ለጣሊያን የግፍ ሰለባዎች እንደቆመው ሁሉ፣ እነዚህም መስዋዕትነት የከፈሉ ወጣቶች፣ የሰማዕታት ሃውልት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሃገራቸው አንድነቷ የተጠበቀ፣ ነፃነት ያላት ሀገር እንድትሆን ነው የተዋደቁት፡፡
በነጭ ሽብር ለወደቁትም እኩል መታሰቢያ ያስፈልግ ነበር የሚሉ ወገኖች አሉ ----
በዚህ ላይ እኔ አንድ ጥያቄ ላንሳ፡፡ የካቲት 12 መታሰቢያ ሃውልት የማን ነው?
በጣሊያን የተጨፈጨፉ ሰዎች መታሰቢያ …
ታዲያ እዚያ ላይ ለጣሊያን ወታደሮች ወይም ጨፍጫፊዎች መታሰቢያ መካተት ነበረበት?
ይሔኛው በወንድማማቾች መካከል የተፈጸመ፣ የእርስ በእርስ እልቂት ነው ብለው ይከራከራሉ…      
እዚህ ጋ አንድ ነገር ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ማንም መሞት አልነበረበትም፡፡ መሞት የሚወደስ ነገር አይደለም፡፡ ሁለተኛ በነጭ ሽብርም በቀይ ሽብርም አንድ ሰው ሲሞት የሚጎዳ ወገን አለ፡፡ ሚስቱ፣ ልጆቹ፣ ወንድሞቹ፣ እናትና አባቱ ይጎዳሉ፡፡ አሳዛኝ ነገር ነው። ግን ስረ መሰረቱ ለመብት በሚደረግ ጥረት ነው ይሄ የሚከሰተው፡፡ በመብት ነፋጊና መብት ጠያቂ መካከል ነው ድርጊቱ የተፈፀመው፡፡ አሁን እነ ዶ/ር ዐቢይ መጥተው ነገሮች ባይስተካከሉ ኖሮ እኮ፣ ዛሬም ወደዚያው ችግር ነበር የምንገባው፡፡ እንዲያውም ሃገራችንም ትበታተን ነበር፡፡ ያኔ በነበረው ሁኔታ ከገዳዮችም መካከል ሟቾች ነበሩ፡፡ ፈጅተው ፈጅተው፣ ኢህአፓም ሌላውም በወሰደባቸው እርምጃ የሞቱ አሉ፡፡ ታዲያ እነዚያም ሰማዕታት ሊባሉ ነው? እኔ አይመስለኝም፡፡ ጣልያን ሲወረን የሞተ ጣልያናዊ ሰማዕት ይባል ከሆነ፣ ይሄ ለኔ አይገባኝም፡፡ ጣልያን ሲወረን፣ የሞተ ጣልያናዊ፣ ሰማዕት ይባል ከሆነ ይሄ ለኔ አይገባኝም፡፡
በኢህአፓ ታሪክና ድርጊቶች ውስጥ እርስዎን አሁን የሚቆጭዎት ነገር አለ?
ብዙ የሚቆጨኝ ነገር አለ፡፡ ከሚቆጩኝ ነገሮች አንዱ ስንደራጅ ጀምሮ ውይይት ስናደርግ የነበረው፣ በኃይሌ ፊዳና በብርሃነ መስቀል ረዳ መካከል ነበር። ያንን በማድረግ ፈንታ ብዙ ተሳታፊዎችን አካትተን ብንወያይ ምናልባት የነበሩንን ችግሮች ልናስወግድ እንችል ይመስለኛል፡፡ በዚያም የውይይት ባህላችንን ልናዳብር እንችል ነበር፡፡ ይሄን ለማድረግ ደግሞ ገደቦች ነበሩብን፡፡ በህቡዕ ነበር መደራጀት የሚቻለው። ያ ከፍተኛ ጫና ነበረው፡፡ ነገር ግን እንደ ምንም ውይይት ብናደርግ ኖሮ፣ ሁኔታዎች ሊለወጡ ይችሉ ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ በሌላ በኩል፤ የግራ ርዕዮት ዓለምን ብዙዎቻችን ስንቀበል፣ ርዕዮቱ ሙሉ ለሙሉ ለችግሮቻችን መፍትሄ ያመጣል ብለን እናስብ ነበር፡፡ ግን ይሄን ርዕዮት ምን ያህል ተረድቸዋለሁ፣ ምን ያህል አብላልቼዋለሁ የሚለውን ማየት ነበረብን፡፡ እኔ ብቻ ነኝ ትክክለኛ የሚለው ግትርነታችን ይቆጨኛል፡፡ ይሄ የአስተዳደጋችን ውጤት ነው፡፡ እኔ ሳድግ ክርስትና ብቸኛው ወደ ገነት የሚያስገባ ነው ተብዬ ነው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ያለው ሁለት ኃይል ነው፤ ብሄርተኛና ኢትዮጵያ የሚለው፡፡ የአሁን ፖለቲከኞች እኔ ብቻ ነኝ ትክክል ከሚለው የግትርነት ባህል ወጥተው፣ ሃሳብ መቀባበል አለባቸው፡፡
ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የታዩትን ለውጦች እንዴት አገኙት?
የእነ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ቡድን፣ ለኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ ይዞ የመጣ ነው፡፡ ሂደቱም ተስፋ ያለው ነው። ጠንክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ጉዞው የአልጋ በአልጋ አይመስለኝም፡፡ በርካታ ውጣ ውረዶችን ማለፍ አለበት፡፡
ለለውጡ ስጋት የሚሆነው ማን ይመስልዎታል?
ባለፉት 27 ዓመታት አንድ ተጠቃሚ መደብ ተፈጥሯል፡፡ ያ መደብ አሁን ጥቅሞቼን ላጣ እችላለሁ ብሎ ሰግቷል፡፡ በሚችለው መጠን ሁሉ ጥቅሙን የሚያሳጣው ሂደት እንዳይቀጥል ይፈልጋል፡፡ ሁለተኛ በበላይነት ሲመራ የነበረ የፖለቲካ ኃይል አለ። ያ ኃይልም በጥንቃቄ መያዝ ያለበት ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የቀን መንግስትና የማታ መንግስት ነው ያለው። የቀኑ መንግስት ይገነባል፤ የማታው መንግስት ሊበታትን ይጥራል፤ የቀኑ መንግስት አንድነት ይላል፤ የማታው መንግስት ሊያፈርስ ይሞክራል፡፡ የቀኑ መንግስት ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ እርምጃዎች ሊወስድ ይሞክራል፤ የማታው መንግስት ወደ ኋላ ለመጎተት ጥረት ያደርጋል፡፡ ሃገሪቱ አሁን በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለችው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሁኔታዎች በመገንዘብ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ይሄኛው የሽግግር ሂደት መክሸፍ የለበትም፡፡ እነ ዶ/ር ዐቢይ የሚወስዷቸው ጠንካራ እርምጃዎች የሚደገፉ ቢሆንም፣ ይሄ ሂደት ግን በግለሰቦች ላይ የተንጠለጠለ መሆን ዮለበትም፡፡ ከግለሰቦች ወጥቶ ተቋማዊ መሆን አለበት፡፡ ያኔ ነው አስተማማኝ ለውጥ ውስጥ የምንገባው፡፡ ይሄን ሂደት መፍጠር፣የማታውን መንግስት ሊያተጋው ይችላል፡፡ ስለዚህ ለየት ያለ አካሄድ ያስፈልጋል፡፡
አሁን እርስዎ  በምን ሁኔታ ላይ ነው ያሉት?
እኔ ከ65 ዓመት በላይ ያለ ሰው፣ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ አያስፈልግም የሚል እምነት ስላለኝ፣ ከፖለቲካ ፓርቲ ወጥቼ፣ በፖለቲካ ማማከሩ ውስጥ ነው ያለሁበት፡፡ ሌሎችም በዚህ ደረጃ ወደ ማማከሩ ቢገቡና ቦታውን ለወጣቱ ቢለቁ ደስ ይለኛል፡፡


Read 3417 times