Monday, 03 December 2018 00:00

የፓርቲዎች የውህደት ጉዞ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ሰባት የፖለቲካ ድርጅቶች ለመዋሃድ ተስማሙ

ኢራፓን ጨምሮ በሃገር ውስጥና በውጪ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 7 የፖለቲካ ድርጅቶች ለመዋሃድ መስማማታቸው ታውቋል፡፡ ሰሞኑን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጋር በተወያዩበት ወቅት፤ በውይይቱ ላይ 70 ፓርቲዎች መገኘታቸውን የጠቀሱት ዶ/ር ዐቢይ፤ በሃሳብ ተሰባስበው 4 ወይም 5 እንዲሆኑ ምክረ ሃሳብ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡
 ሰሞኑን ውህደት ለመፈፀም የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረሙት በሀገር ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ)፣ የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ህብረት እና በቅርቡ ወደ አገር ቤት የተመለሱ  አምስት የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው፡፡
በወ/ሮ ጽጌረዳ ሙሉጌታና በፕ/ር አቻሜለህ ዲባባ የሚመራው “የኢትዮጵያ መድህን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (መድህን)”፣ በአቶ ስለሺ ጥላሁን የሚመራው “የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ም/ቤት (ሽግግር)”፣ በዶ/ር አክሎግ ቢራራ የሚመራው “ብሩህ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብሩህ)”፣ በአቶ በርገና ባሣ የሚመራው “ቱሣ የኢትዮጵያ ትንሣኤ ዲሞክራሲያዊ ድርጅቱ (ቱሣ)” እና በአቶ ነሲቡ ስብሃት የሚመራው “ኢትዮጵያችን ንቅናቄ” የውህደቱ አካል ናቸው ተብሏል፡፡
ድርጅቶቹ ለመዋሃድ የተስማሙት ላለፉት 6 ወራት ሠፊ የመጠናናት ውይይት ካደረጉ በኋላ መሆኑን ለአዲስ አድማስ የገለፁት የኢራፓ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ፤ ህዳር 15 ቀን 2011 ለመዋሃድ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመው፣ ቀሪ የአፈፃፀም ጉዳዮች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
ፓርቲዎቹ በሀገሪቱ የተጀመረውን ሪፎርም ተከትሎ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከህዝባቸው እየቀረበ ያለውን ጥሪ በመቀበል፣ ወደ ውህደት ማምራታቸውን አቶ ተሻለ አስታውቀዋል፡፡
በተመሳሳይ ሰሞኑን በአንጋፋዎቹ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር መስራቾችና በኋላም የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባርን በመመስረት በውጭ ሀገር የፖለቲካ ትግል ሲያደርጉ የቆዩት አቶ ሌንጨ ለታ፣ ዶ/ር ዲማ ነገዎ፣ አቶ ሌንጮ ባቲን ጨምሮ በርካታ አንጋፋ ፖለቲከኞች ያሉበት ፓርቲ ከኦሮሚያ ክልል ገዥ ፓርቲ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ጋር ውህደት ፈጽመዋል፡፡
በተመሳሳይ የአማራ ገዥ ፓርቲ የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እና በትጥቅ ሲንቀሳቀስ የነበረው የአማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ከሶስት ሣምንታት በፊት ውህደት መፈፀማቸው ይታወሳል፡፡

Read 7665 times