Print this page
Monday, 26 November 2018 00:00

የአለማችን የስኳር በሽተኞች ቁጥር 420 ሚሊዮን ደርሷል ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)


  በኮንጎ ኢቦላ 177 ሰዎችን፣ ኮሌራ 857 ሰዎችን ገድሏል
በአለማችን የስኳር በሽተኞች ቁጥር ቁጥር ባለፉት ሶስት አስርት አመታት በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉንና በአሁኑ ወቅት የስኳር በሽተኞች ቁጥር 420 ሚሊዮን ያህል መድረሱንና የስኳር በሽታ በየአመቱ 1.6 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ለህልፈተ ህይወት እንዲዳረጉ ምክንያት ይሆናል ተብሎ እንደሚገመት የአለም የጤና ድርጅት አስታወቀ፡፡
የስኳር በሽታ ለአይነ ስውርነት፣ ለኩላሊት ከጥቅም ውጭ መሆንና ለልብ ድካም በሽታ በማጋለጥ ረገድ ቀዳሚነቱን እንደሚይዝ  ድርጅቱ ከትናንት በስቲያ ባወጣው አለማቀፍ ሪፖርት የጠቆመው ድርጅቱ፣ ሰዎች የስኳር በሽታን ለመከላከል ጤናማ አመጋገብ እንዲከተሉ፣ የሰውነት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉና ከመጠን በላይ የክብደት መጨመር እንዳይከሰትባቸው መጠንቀቅ እንዳለባቸውም መክሯል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ባለፈው ሃምሌ የተቀሰቀሰው የኢቦላ ወረርሽኝ 303 የአገሪቱ ዜጎችን ማጥቃቱንና በቫይረሱ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች 177 መድረሱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ የጤና ሚኒስቴር ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በአገሪቱ የተቀሰቀሰው የኦቦላ ቫይረስ የከፋ ጥፋት እንዳያደርስ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ሲሆን፣ ከ30 ሺህ በላይ ሰዎች የጸረ-ኢቦላ ቫይረስ ክትባት እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡
በተያያዘ ዜናም የኮሌራ ወረርሺኝ በዚህ አመት ብቻ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 857 በናይጀሪያ ደግሞ 1 ሺህ 110 ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት መዳረጉ ተዘግቧል፡፡
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በ2018 የፈረንጆች አመት የተቀሰቀሰው የኮሌራ ወረርሽኝ 25 ሺህ 170 ያህል የአገሪቱ ዜጎችን ማጥቃቱንና ከእነዚህም መካከል 857 ሰዎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን የዘገበው አናዶሉ ኒውስ ኤጀንሲ፣ ባለፈው አመት በአገሪቱ የተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ 55 ሺህ ሰዎችን ማጥቃቱንና 190 ያህሉ ለሞት መዳረጋቸውንም አስታውሷል፡፡
በዘንድሮው አመት ከ36ቱ የናይጀሪያ ግዛቶች በ29 ያህሉ ውስጥ የተቀሰቀሰውና 1 ሺህ 110 ሰዎችን የገደለው ኮሌራ ለህልፈተ ህይወት የዳረጋቸው ሰዎች ቁጥር ከአንድ አመት በፊት ከነበረው የ84 ሰዎች ሞት በእጅጉ ጭማሪ ማሳየቱንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ኮሌራ በመላው አለም በየአመቱ 2.8 ሚሊዮን ያህል ሰዎችን እንደሚያጠቃና 91 ሺህ ያህል ሰዎችም ከኮሌራ ጋር በተያያዘ ለሞት እንደሚዳረጉም ዘገባው ገልጧል፡፡

Read 1803 times
Administrator

Latest from Administrator