Saturday, 24 November 2018 12:50

ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ “ሊያከብሩት በሚገባቸው መገፋቱና ከሚያገለግላቸው መሸሹ ያሳዝናል”

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)


ክቡር ዶክተር ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ  አስተዳደር ከውስጥና ከውጪ ደርሰውብኛል በሚላቸው አጓጉል  ተፅዕኖዎች ከፌዴሬሽን የፕሬዚዳንት ስልጣን ለመልቀቅ መወሰኑ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያስደሰተ አይደለም፡፡ ያለፉትን ሁለት ዓመታት የአትሌቲክስ ፌደሬሽኑን በብቃት ለመምራት  ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን የገለፀው ኃይሌ፤ አትሌቶችና አሰልጣኞች የልምምድ እና የስልጠና መሰረተልማት አልተሟላንም፤ በፌደሬሽኑ አመራር ተገቢ ትኩረት አልተሰጠንም በሚል ተቃውሟቸውን በይፋ መግለፃቸው መምራት የምችልበትን ሞራል አሳጥቶኛል ብሏል፡፡ የፕሬዝዳንት ስልጣኑን ከተረከበ ጀምሮ ለማከናወን ካቀዳቸው ተግባራት 30 በመቶውን ብቻ መፈፀሙ ያላረካው ኃይሌ በፌደሬሽኑ አስተዳደር ውስጥ ሲንከባለሉ የቆዩ  ችግሮች ላይ ስርነቀል ለውጥ ለመፍጠር የማይቻልበት ደረጃ ፤ በዓለም አቀፎቹ የአትሌቲክስ እና የስፖርት ተቋማት መመሪያና ደንቦች መሰረት ስፖርቱን በማስተዳደር፤ በማስፈፀምና በማጠናከር ለመስራት  እንዳዳገተውም አብራርቷል፡፡
ከወር በፊት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 22ኛ መደበኛ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔውን ሲያካሂድ  ‹‹ክለቦች የጠቅላላ ጉባዔ አባል መሆን አለባቸው የለባቸውም›› በሚለው አጀንዳ   ላይ ባለድርሻ አካላት የነበራቸው አለመግባባት ቀውሱ እንደፈጠረው  እየተነገረ ነው፡፡  በ22ኛ መደበኛ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ክለቦች የጠቅላላ ጉባዔ አባል መሆን የሚችሉባቸው ቅድመ ሁኔታዎች በሙያተኞች ጥናት ከተሰራበት በኋላ በሚቀጥለው ጉባዔ ውሳኔ እንደሚያገኝ በአብላጫ ድምፅ ቢወሰንም ማለት ነው፡፡ በተለይ ‹ክለቦች የጠቅላላ ጉባዔ አባል በሚሆኑበት  አካሄድ ላይ የኦሮሚያ ክልል አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፅኑ ተቃውሞው ነበረው፡፡  ባለፈው የውድድር ዓመት ያስመዘገበውን ውጤት መነሻ በማድረግ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የ240 ሺሕ ብር ተሸላሚ ቢያደርገውም ክልሉ ይህን ሽልማት ‹‹አይመጥነንም›› በሚል ምክንያት ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆነውም ከዚሁ ጋር ተያይዞ ነው፡፡  ከዚህ በኋላም ፌዴሬሽኑ ባለፈው እሑድ ኅዳር 2 ቀን 2011 ዓ.ም. በሱሉልታ ባዘጋጀው አገር አቋራጭ ውድድር ላይም የኦሮሚያ ክልል አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከአስተዳደሩ ጋር የነበረውን ቁርሾ ያንፀባረቀ ሲሆን በወቅቱ በርካታ አትሌቶች ፌዴሬሽኑን በመቃወም የተለያዩ መፈክሮችን በመያዝ አደባባይ ሲወጡ፤ በስፖርት ማዘውተሪያ ዕጦች ችግር ላይ የወደቁበትን ሁኔታ ፌዴሬሽኑ በትኩረት ተመልክቶ መፍትሄ እንዲሰጥና ትጥቅና መሰል ቁሳቁሶች እንዲሟሉላቸው ጠይቀዋል፡፡ ሻለቃ ኃይሌንና በርካታ የስፖርት ቤተሰብን ያሳዘነው ግን ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተቃውሞ የተሳተፉት አትሌቶች ተምሳሌት የነበሯቸውን የአትሌቲክስ ጀግኖችን ክብር መንሳታቸው  ነው፡፡  ከአትሌቲክስ ውጭ በሚነሱ ጉዳዮች የአመራርነት ሚናውን የሚያምሱ ግለሰቦች መኖራቸው አበሳጭቶኛል ያለው ኃይሌ፤ በዚያ ምክንያት ፌደሬሽኑ መጎዳት የለበትም በሚል አቋም መፅናቱና ከሃላፊነቱ በገዛ ፈቃዱ ለመልቀቅ የወሰነውም ከዚሁ ጋር ተያይዞ ነው፡፡  የዓለማችን የምንግዜም ምርጥ አትሌት የሆነው ሻለቃ ኃይሌ በፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንትነት ማገልግል የሚችልባቸውን ተጨማሪ ሁለት ዓመታት መታገስ የተሳናቸው አትሌቶች እና አሰልጣኞች ከሃላፊነቱ እንዲነሳ መግፋታቸው፤ እሱም  ችግሮችን ተጋፍጦ በቀረው የስራ ዘመን ሊፈጥር የሚችለውን ለውጥ በመሸሽ ለመልቀቅ መወሰኑ ያሳዝናል፡፡ በአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ሊኖር የሚገባውን ሕግና ሥርዓት ለማስከበር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ከባለድርሻ አካላቱ ተቀባይነት አለማግኘታቸውም የሚያሳስብ ነው፡፡  በኃይሌ አመራርነት በአትሌቲክስ ስፖርት ድርሻ የነበራቸውን አሰልጣኞች የማሰባሰብ፣ በጋራ የመስራት እና የመተባባር ስሜት እንዲፈጠር ተሞክሯል፡፡ የክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች፣ የስልጠና ማዕከላት እና የአትሌቲክስ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍና ለማበረታታት የበጀት ድጋፍ ተሰጥቷል። ለአሰልጣኞች ማህበር፤ ለዳኞች ማህበር እና ለአትሌቶች ማህበር ማጠናከርያ ድጋፎች ተደርገዋል። የሀገር ውስጥ ስልጠናዎችንና ውድድሮችን በብቃት ለመምራት እንዲቻል የአሰልጣኞችንና የዳኞችን ስልጠናዎችም  ተካሂደዋል፡፡ በቀሪዎቹ ሁለት ዓመታት የተሻሉ ስኬቶች ሊኖሩ እንደሚችሉም ይጠበቅ ነበር፡፡
በተያያዘ ባለፈው ሰሞን በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ  ያደረገው የፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ፤ ኃይሌ የመልቀቅ ውሳኔውን በድጋሚ እንዲያጤነውና ወደ ሃላፊነቱ እንዲመለስ ሙከራ ቢያደርግም አልተሳካለትም። ከዚያ ስብሰባ በፊት ኃይሌ ውሳኔውን ልትቀለብስ ትችላለህ ተብሎ ከጋዜጠኛ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥ‹‹ ወደ ኋላ አልመለስም፤ ከፌደሬሽኑ ሃላፊነት ብለቅም ስፖርቱን መደገፍና መርዳቱን አልተውም። ለሚቀጥሉት 2 ዓመታት በስራ አስፈፃሚው አባል ሆኖ በመቀጠል ድጋፍ እሰጣለሁ፡፡››  ብሎ ነበር፡፡ የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ  የፌደሬሽኑን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ኮለኔል ደራርቱ ቱሉን በሽግግር ፕሬዝዳንትነት የሰየማት ሲሆን ከ2 ወር በኋላ በሚያካሂደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤም የመጨረሻ ውሳኔውን እንደሚያሳልፍና በቀሪዎቹ ሁለት ዓመታ በፕሬዝዳንትነት የሚሰራውን እንደሚመርጥ አስታውቋል፡፡በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በሽግግር ፕሬዝዳንትነት የምትመራው ክብርት ዶክተር /ኮለኔል/ አትሌት ደራርቱ ቱሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ሰራ አስፈፃሚ አባል እንደሆነች ይታወቃል። በሩጫ ዘመኗ በረጅም ርቀት ሩጫ በትራክ፣ በአገር አቋራጭ፣ በጎዳና ላይ ሩጫ እንዲሁም በማራቶን ፈርቀዳጅ እና ወርቃማ ታሪኮችን ያስመዝገበች ስትሆን ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ በረጅም ርቀት የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ በኦሎምፒክ ያገኘች ሆና ስሟ በታሪክ መዝገብ ሰፍሯል፡፡ ከ74 በላይ ዓለም አቀፍ ውድደሮች ያሸነፈች ስትሆን  4 ኦሎምፒኮች 4 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች በመሳተፍ ከ10 በላይ የወርቅ ሜዳልያዎች ተጎናፅፋለች። 2 የኦሎምፒክ የወርቅና 1 የነሐስ ሜዳሊያዎች በ10ሺ ሜትር ያገኘች ሲሆን በአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የወርቅና የነሐስ ሜዳሊያዎች በ10ሺ ሜትር፣  በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ፣ በ5ሺ ሜትር የጎልደን ሊግ አሸናፊ ፣ በዓለም የአትሌቲክስ ፍፃሜ በ5ሺ ሜትር የብር ሜዳልያ ፣ በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በ10ሺ ሜትርና በ3ሺ ሜተር ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች ፣ በዓለም ኮንትኔንታል ካፕ በ10ሺ ሜትርና በ3ኺ ሜተር ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች፣ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች እንዲሁም 3 ታላላቅ ማራቶኖች በለንደን፣ በቶኪዮና በኒውዮርክ ከተሞች ድል ያደረገች ናት። ከደቡብ አፍሪካው ዌስተርን ኬፕታውን ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ እንደተቀበለችም ይታወቃል። ኮለኔል ደራርቱ ቱሉ ሃላፊነቱን ከተረከበች በኋላ  ፌደሬሽኑን በፕሬዝዳንትነት ቋሚ ሆና እየመራች ለመቀጠል ፍላጎት እንደሌላት ተናግራለች፡፡ የመጀመርያ ስራዋ የሆነው ባለፈው ሰሞን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና በኦሮሚያ ክልል የለገጣፎ ከተማ አስተዳደር ይዞታ የሚገኘውን የማዘውተሪያ ቦታ የአሸዋ ትራክና ጥርጊያ በጋራ አልምቶ ለመጠቀም ስምምንት መፈራረም ነው፡፡ ስምምነቱ አትሌቶች የስልጠና ማቴርያል እና ጂምናዝየም ለመጠቀም የሚኖርባቸውን ወጭ እንደሚያስቀር ተነግሯል፡፡
ሻለቃ ኃይሌ ከፌደሬሽን አመራርነት እንዲለቅቅ በአትሌቲክሱ ባለድርሻ አካላት መገፋቱ እና ደርሰውብኛል በሚላቸው ጫናዎች ከሃላፊነቱ መሸሹ የስፖርት ቤተሰቡን አደናግጦታል፡፡ በርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አደጋ ላይ መውደቁን በሚያመለክቱ ዘገባዎች ሽፋን የሰጡት ሲሆን እውቅ የስፖርት ባለሙያዎችና ጋዜጠኞችንም ያሳዘነ ክስተት መሆኑን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡   ኃይሌ ከስልጣን መልቀቅ ሊወስን መገደዱ በፌዴሬሽኑ የውስጥ እና የውጭ አስተዳደር መግባባትና መደማመጥ መጥፋቱን ያመለክታል የሚሉ የአትሌቲክሱ ባለድርሻ አካላት ጥቂት አይደሉም፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ የውድድር መድረኮች የኢትዮጵያ ውጤት መዳከሙ፤ በትልልቅ የማራቶን ውድድሮች በሁለቱም ፆታዎች በኬንያውያን ከፍተኛ ብልጫ መወሰዱ፤ የዓለም ማራቶን ሪከርድን የመስበር ትጋት ከኢትዮጵያ ጠፍቶ በኬንያ የበላይነት መቀጠሉ፤ በዓለም አትሌቲክስ የኮከብ አትሌቶች ምርጫ ከመጨረሻ እጩዎች ተርታ የሚገባ ኢትዮጵያዊ አትሌት መጥፋቱ እንዲሁም  በፌደሬሽኑ አስተዳደር ክልሎች፤ አሰልጣኞች፤ ማናጀሮች እና አትሌቶች በተለያዩ ውዝግቦች መጠመዳቸው ለብዙዎች ስጋት ሆኖባቸዋል፡፡ ትልቁ የስልጣን አካል ሃላፊነት የሰጠው ጠቅላላ ጉባዔ በመሆኑ የውዝግቡን የመጨረሻ ውሳኔ ከ2 ወራት በኋላ በሚያደርገው አስቸኳይ ጉባዔ  እንደሚወስን ቢጠበቅም፤ በፌደሬሽኑ አስተዳደር ከፕሬዝዳንቱ መንበር ውጭ የተድበሰበሱት እና የሚያጋጩት አወዛጋቢ አጀንዳዎች በዚያን ወቅት ሊያገረሹ እንደሚችሉ ያሰጋል፡፡በተለይ በፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ የአባላት ጥንቅርና የክለቦች ተሳትፎ ጉዳይ ላይ ባለፉት ጉባዔዎች የተደረጉ ውይይቶች በከፍተኛ ደረጃ ማከራከራቸውና መፍትሄ አለማግኘታቸው የሚያስጨንቅም ነው፡፡  
በኬንያው ኔሽን ሚዲያ ግሩፕ በሚታተመው ታዋቂው ዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ ላይ በአዘጋጅነት የሚሰራው በርናባስ ኮሪር በፃፈው ሃተታ በላቀ የአትሌቲክስ ስኬት ለአፍሪካና ለመላው ዓለም ተምሳሌት የምትሆነው ኢትዮጵያ በስፖርት የአስተዳደር ቀውስ መታመሷን አሳፋሪ ብሎታል፡፡ ኃይሌ ከዓለማችን የምንግዜም ምርጥ አትሌቶች ተርታ በግንባርቀደምነት ከሚያሰልፈው ስኬታማ የሩጫ ዘመኑ በኋላ ወደ ስፖርቱ አመራር ሲመጣ የዓለም አትሌቲክስ ማህበረሰብ   ልዩ ጉጉት ማሳደሩን ያወሳው በርናባስ ኮሪር፤ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውስጥ ብዙ እንደሚሰራ ተስፋ እየተደረገ፤ በድንገተኛ የፖለቲካ አጀንዳዎች ከስልጣኑ የሚለቅበትን አጓጉል ግፊት ፕሮፌሽናል አሰልጣኞች፤ አትሌቶች እና የስፖርት አመራሮች መፍጠራቸውን የሚወገዝ ነው ብሏል። ተመሳሳይ ሁኔታም በኬንያ አትሌቲክስ እንደበሽታ መዛመቱንም አስገንዝቧል፡፡ ኃይሌ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ላይ የሚያልመውን ለውጥ ለማምጣት በቂ ጊዜ ያስፈልገው እንደነበር የጠቀሰው ፀሃፊው፤ ከሃላፊነቱ ለመልቀቅ ያሳለፈውን ውሳኔ ከመስዕዋትነት መቁጠሩ አስገርሞኛል ብሏል፡፡
ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ከሁለት ዓመት በፊት ‹‹ባልመረጥም እመረጣለሁ›› በሚል ርእስ ከአዲስ አድማስ ጋር ቃለምልልስ አድርጎ ነበር፡፡ በወቅቱ ከፕሬዝዳንትነት ምርጫው  በፊት ምን እንደሚሰማው ተጠይቆ ‹‹ተመረጥኩም አልተመረጥኩም የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን አሸናፊ ሆኖ በትክክለኛ መስመር እስኪገባ ድረስ ጥረት ማድረጌን አላቋርጥም፡፡ በርግጥ ብዙዎች ኃይሌ የሚያስተዳድራቸውን ኢንቨስትመንቶች እና በርካታ የግል ስራዎቹን ትቶ እንዴት ፌዴሬሽኑን በሙሉ ትኩረት ሊመራ ይችላል ብለው ስኬታማ ልሆን እንደማልችል ጥርጣሬ ሊገባቸው ይችላል… ግን እኔ በምሰማራበት የኃላፊነት መስክ ሁሉ ከ95 በመቶ በላይ ስኬታማ መሆን እንደምችል በእርግጠኛነት ነው የምናገረው፡፡ ሁሉንም ስራዎቼ እኮ የፈጠራቸው ሩጫው ነው፡፡ ሁሌም ቅድሚያ ትኩረት የምሰጠው ለአትሌቲክሱ ስፖርት ነው፡፡ ለስፖርት ቅድሚያ የምሰጠው ለ100 ሚሊዮን ህዝብ ስኬታማ ሆኜ መስራት የምፈልገው ሃላፊነት ስለሆነ ነው፡፡ በአጠቃላይ ለሁሉም አደራ የምለው የኢትዮጵያን አትሌቲክስን እንታደገው ነው፡፡ ስፖርቱን ወደነበረበት ቦታ ለመመለስ በ1 እና በሁለት ዓመት ከፍተኛ ለውጥ እናመጣለን ብዬ የምገባው ቃል የለም፡፡ በጣም የወረደውን አትሌቲክስ ወደ ነበረበት ቦታ ለመመለስ ከ3 እና ከ4 ዓመታት በላይ ተባብረን መስራት ይኖርብናል፡፡ ምናልባትም ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የምናገኛቸው ድጋፎች የተጠናከሩ ከሆነ ከዚያም በፈጠነ ጊዜ የምንፈልገውን ለውጥ ማስመዝገብ እንደምንችል ነው የማምነው፡፡›› የሚል ምላሽ ሰጥቶ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን  ከ70 ዓመታት በፊት እንደተመሰረተ የታሪክ መዛግብቶች ያወሳሉ።  በፌደሬሽኑ ድረገፅ የተቀመጠው ታሪካዊ ዳራ እንደሚያወሳው ፌዴሬሽኑ በተቋቋመበት ወቅት የነበረውን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ኮሎኔል ጌታሁን ተክለማርያም በበላይነት ይመሩና ያገለግሉ እንደነበር፤  በመቀጠል ደግሞ አቶ ተስፋዬ ሽፈራው ተተክተው የአትሌቲክስ ስፖርቱን መምራታቸውን፤ ከእኝህ ሰው በኋላ ደግሞ ኮሎኔል በቀለ ይግዛው፣ ኮሎኔል ዘለቀ እርገጤ፣ አቶ አክሊሉ ይምታቱ፣ አቶ አሥራት ኃ/ጊዮርጊስ፣ አቶ ተፈራ ዋሲሁን፣ ሻምበል ኃለፎም ምሩፅ፣ አቶ ሙሉጌታ ኃ/ማርያም በተከታታይ ተተካክተው የአትሌቲክስ ስፖርቱን ይመሩ እንደነበር ይነገራል፡፡ የተለያዩ አማተር አገልጋዮች ከሠራዊቱ ቤትና ከልዩ ልዩ ተቋማት ፌዴሬሽኑን በበጎ ፈቃደኝነት መርተውታል። በፌደሬሽኑ የአመራር ታሪክ አበይት ምዕራፍ ሆኖ የሚጠቀሰው ከ1994 ዓ. ም. በኋላ እስከ 2004 ዓ. ም. ማብቂያ ድረስ  ያገለገሉ ብቸኛዋ ሴት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ብሥራት ጋሻውጠና ነበሩ፡፡ እርሳቸውን ተክተው እስከ 2008 ዓ. ም በመምራት ላይ የነበሩት ደግሞ የተከበሩ አቶ አለባቸው ንጉሴ  ነበሩ። ፌዴሬሽኑ በተቋቋመበት ወቅት የነበረውን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሌ/ኮሎኔል ብርሃነ ተፈራ በበላይነት ይመሩና ያገለግሉ እንደነበር፣ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ከዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር፣ ከአዲዳስ ኩባንያ፣ ከአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን፣ ከምስራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ሪጅንና ከአቻ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ተቋማት ጋር መልካም የሚባልና በአርዓያነት ሊጠቀስ የሚችል ግንኙነት እንደሚያደርግ የሚያወሳው ታሪካዊ ዳራ ፌዴሬሽኑ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (IAAF) አባል እንደሆነም ይጠቅሳል፡፡  በአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን (CAA) እና በምሥራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ሪጅን (EAAR) ውስጥ ከካውንስል አባልነት ባለፈ በአመራርነት የሚያገለግልም ነው፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በየአመቱ በሚያካሂዳቸው ከ10 በላይ የሃገር ውስጥ ውድድሮች ላይ የመላ ሃገሪቱ ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ክለቦች እንዲሳተፉ የሚያደርግ ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ አትሌቶች ከሚያገኙት የቡድን ሽልማት ፣ ከአትሌት ማናጀሮች ዓመታዊ ክፍያ፣ ከዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማሕበር፣ ከሕንፃ ኪራይ እና ከአዲዳስ ኩባንያ በድምሩ በየዓመቱ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ሲኖረው፤ በሌላ በኩል በየውድድር ዘመኑ ውስጥ በፌደሬሽኑ ስር ለተካሄዱት ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች፣ በተለያዩ የመሰረተልማት ስራዎች፤ ለፌዴሬሽኑ ሰራተኞችና አሰልጣኞች ደመወዝና ስራ ማስኬጃ፣ ለትምህርትና ስልጠና፣ ለብሔራዊ ቡድን አትሌቶች ድጎማ፣ ለማርኬቲንግና ኮሚዩኒኬሽን፣ ለስፖርት ዕቃዎች ግዢ፣ ለሜዳና ለሕንፃ ጥገና፣ ለድጋፍ ለማበረታቻ እና ሽልማት እንዲሁም ሌሎች ለታቀዱ ስራዎች ማስፈፀሚያ እስከ 43 ሚሊዮን ብር ወጭ የሚያስመዘግብም ነው፡፡ አቶ ሙሉጌታ ኃይለማርያምን ተክተው ወ/ሮ ብሥራት ጋሻውጠና ከ1994 ዓ. ም. በኋላ እስከ 2004 ዓ. ም. ማብቂያ ድረስ  ያገለገሉ ብቸኛዋ ሴት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ነበሩ፤ እርሳቸውን ተክተው እስከ 2009 ዓ. ም. መጀመሪያ ድረስ አቶ አለባቸው ንጉሴ ፌዴሬሽኑን የመሩ ሲሆን ከመንግስት ተቋማት ከሚመጡት ወኪሎች ይዘውት የነበሩትን የፕሬዝዳንትነትን ኃላፊነት ወደ ስመ ጥርና ታዋቂ አትሌቶች ያዛወረ ክስተት በተፈጠረበት የ2009 ዓ. ም. ምርጫ ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ ፕሬዝዳንት ሆኖ ፌዴሬሽኑን ሲመራ ቆይቷል፡፡

Read 1436 times