Saturday, 24 November 2018 12:49

የቅድመ ወሊድ ክትትል ተጽዕኖዎቹና ተጓዳኝ ሁኔታዎች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)


  የኢትጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ጆርናል የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ባለሙያዎች ከስነተዋልዶ ጤና ጋር በተያያዘ በስራ ላይ የገጠሙዋቸውን እውነታዎች እንዲሁም በታካ ሚዎች ዘንድ የሚኖሩ የስነተዋልዶ ጤናን የሚመለከቱ ሁኔታዎችን በምርምር ለህትመት ያበቃሉ፡፡
በዚህ እትም ለንባብ ያልነው ከአሁን ቀደም የእርግዝና ክትትልን በሚመለከት በኢትዮጵያ ለምን ያስፈልጋል ጠቀሜታውስ ምንድነው እናቶች ከእርግዝና በሁዋላ ክትትሉን የማያደርጉት በምን ምክንያት ነው የሚለውንና መደረግ የሚገባውን ይህ እትም ወደአማርኛ በመመለስ እነሆ ለአንባቢ ብሎአል፡፡ የተለያዩ የምርምር ውጤቶችን በመዳሰስ ቮልዩም 10/ቁጥር 3/ ለሆነው ጆርናል ያቀረቡት ዶ/ር ወንድሙ ጉዱ ከቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ናቸው፡፡ ወደ ጥናቶቹ ክለሳ ከመሄድ በፊት አንድ ያነጋገርናቸው እናት ልምዳቸውን እንደሚከተለው ገልጸዋል።
‹‹…እኔ ዛሬ የ58/አመት ሴት ነኝ፡፡ የተዳርኩት ግን በልጅነቴ ነው፡፡ እናም ገና ሀያ አምስት አመት ሳይሞላኝ በሁለት አመት ልዩነት ሶስት ልጆችን ወለድኩ። የምወልደውም በአንድ ሆስፒታል ስለነበር ነርሶቹ …ድሬሰሮቹ ሁሉ ያውቁኛል፡፡ ታዲያ ሶስተኛዋን ልጄን ስወልድ አንዱዋ ድሬሰር እንዲህ አለችኝ፡፡…አንቺ ግን በየአመቱ ነው እንዴ ልጅ የምትወልጂው? ለእራስሽስ ቢሆን አታስቢም እንዴ? አለችኝ፡፡ እኔም….በቃ ከዚህ በሁዋላማ አልወልድም፡፡ የፈለገ ቢሆን ልጅ አልወልድም…አልኩ፡፡ ታዲያ ሶስተኛውን ልጅ በወለድኩ ገና ሰባት ወር እንደሆነኝ አራተኛው ልጅ ተረገዘ። ይህንንማ እግዚሀር ሲቆጣኝ የሰጠኝ ነው በማለት ሀኪም ቤት ሳልሄድ ቀረሁ፡፡ ዘጠንኛ ወሬን ሳጋምስ ደግሞ ፈራሁና ቀድሞ ወደማልሄድበት ወደሌላ ሆስፒታል ምርመራ ላደ ርግ ሄድኩ። ቢቆጡኝም ምርመራዬን ቀጠልኩና መውለጃዬ ሲደርስ ያረገዝሽው መንታ ነው አሉኝ። የምወልደውም በኦፕራሲዮን መሆኑ ተነገረኝ፡፡ እኔም የዚህ የዚህ እማ እዚያው የለመ ድኩበት ልሂድና ያረጉኝን ያርጉኝ ብዬ ምርመራ ጀመርኩ፡፡ የነበረው ቁጣና ስድብ አይጣል ያሰኛል፡፡ እኔም ጥፋቴ በመሆኑ የሚሉኝን ሁሉ ችዬ ምርመራ አደረኩኝ፡፡ በሶስተኛው ቀን ምጥ መጣና ልጅ ሲወለድ መንታ የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ እስከዛሬ ድረስ የሚቆጨኝ እርጉዝ ስሆን በት ክክል ክትትል አለማድረጌ ያመጣብኝን ጭንቀት የማልረሳው በመሆኑ ነው፡፡››
አቻምየለሽ ተፈራ/ቦሌ
በኢትጵጵያ የእናቶች ሞት ትልቅ የህብረተሰብ ጤና ችግር ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከ100‚000/ በሕይወት ከሚወለዱ /412/አራት መቶ አስራ ሁለት/ እናቶችን በሞት ማጣት በአ ለም ከፍተኛ ከሚባለው የሞት መጠን የሚመደብ ነው፡፡ ስለሆነም በእርግዝና ጊዜ ተገቢውን ክትትል ማድረግ የእናቶችን የስነተዋልዶ ጤንነት ለማሻሻል ከሚረዱ ዋነኛ ተግባራት አንዱ ነው፡፡ በተለይም የማህጸንና ጽንስ ጤና ጉዳይ አስቸጋሪ እና ውስብስብ በሆነባቸው ታዳጊ አገ ራት ቅድመ ወሊድ ክትትል በሽታን ለመከላከልና ጤናን ለመጠበቅ ቁልፍ ሚና የሚጫወት የመሆኑ ምስጢር አገልግሎቱን የሚፈልጉ የህብረተሰብ ክፍሎች በትክክል ወይም በጊዜው ወደ ህክምና ተቋማቱ የማይሄዱ መሆኑን ጨምሮ የጤና ተቋማቱም የተሟላ አገልግሎት ለመስ ጠት ተሟልተው የማይገኙ መሆኑ እንደዋነኛ ነጥብ የሚቆጠር ነው፡፡
በተለያዩ ታዳጊ በሁኑ አገራት እናቶች በእርግዝና ጊዜ ክትትል እንዳያደርጉ ምክንያት የሚሆ ኑት ነገሮች በተለያዩ ጥናቶች የተለያዩ ምክንያቶች ተጠቁመዋል፡፡ ቢሆንም ግን እነዚህ ውጤ ቶች በአገር ደረጃ የስነተዋልዶ ጤናን በማሻሻል ረገድ እና የእናቶችንና ጨቅላ ሕጻናቶችን ጤና በመጠበቅና ሞትን በመቀነስ ረገድ ለሚዘጋጁ ፖሊሲዎች እና ፕሮግራሞች ጠቃሚ እንደሚሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን የጥናቶቹ ውጤቶች ሲገመገሙ በተለይም በኢትዮጵያ የእርግዝና ክትትል ማድረግ የሚፈልጉ እናቶች ቢኖሩም ግን በተለያዩ ምክንያቶች ፍላጎታቸው አለመሳካቱ ተጠቁሞአል፡፡ በኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ ማለትም በ2016/ የወጣው EDHS እንደሚ ያሳየው የእርግዝና ክትትል 62% ያህል መሆኑን ነው፡፡
በኢትዮጵያ የእርግዝና ክትትልን እንዳይካሄድ ሊያደርጉ ይችላሉ ተብለው በተለያዩ ጥናቶች የተጠቆሙት ነጥቦች የተለያዩ ናቸው፡፡
አንዳንድ ጥናቶች ሁኔታውን በዘር በመለየት ይኼኛው ከዚህኛው በተሻለ ክትትል ያደርጋል በሚል ጥቆማ ሲያደርግ በሌላው ጥናት ሲደገፍ አይታይም፡፡
ሌሎች ጥናቶች ደግሞ ሁኔታውን በሀይማኖት ይለዩታል፡፡ ለምሳሌም በ/2000/ የወጣው EDHS እንደሚገልጸው በገጠር አካባቢ የሙስሊም እምነት ተከታዮች ከክርስትና እምነት ተከታዮች በተሻለ ክትትል እንደሚያደርጉ ተጠቁሞአል፡፡
ሌሎች ጥናቶች ደግሞ የቤተሰብ ቁጥር መብዛት እንደ አንድ አገልግሎቱን ያለመጠቀም ምክንያት የተወሰደባቸውም ይገኛሉ፡፡
እናቶች በባህላዊ መንገድ እምነታቸውን የሚያካሂዱ ከሌሎች እምነት ተከታዮች ባነሰ የእርግዝና ክትትል እንደሚያደርጉ የጠቆሙ ጥናቶችም አሉ፡፡
የሴቶች የውሳኔ ሰጪነት አቋም ሌላው በእርግዝና ጊዜ ለሚያስፈልገው ክትትል ድርጊት እንደ አንድ ወሳኝ ኩነት የታየበት ጥናትም አለ፡፡
የኢኮኖሚ ጉዳይ ማለትም በየወሩ የሚገኝ ገቢ እና የአኑዋኑዋር ደረጃ ሌላው ክትትል ለማድረግ ወይም አለማድረግ እንዲሁም በጊዜው ወደ አገልግሎት መስጫው ተቋም መሄድ አለመሄድን ለመወሰን በምክንያትነት የተወሰደባቸው ጥናቶችም አሉ፡፡ በሁሉም ጥናቶች ወርሀዊ ገቢያቸው ከ/500-1000/ብር የሚሆንና ኑሮአቸው ዝቅተኛ የሆኑ ቤተሰቦች ወደሕክምና ተቋም ሄደው የእርግዝና ክትትል ለማድረግ ፈቃደኛ የማይሆኑባቸው ምክንያቶች እንደሆኑ ተጠቁሞአል፡፡
ከዚህ በተረፈ በጉዳዩ ላይ የእውቀት ማነስ ፤የእርግዝናን ክትትል በማድረግ ረገድ የተሳሳተ ዝንባሌ መኖር፤ በእርግዝናው ላይ የተሳሳተ ግንዛቤ መፍጠር ፤ እና ወደሕክምና ተቋም ለመ ሄድ ጊዜ ማጣት የመሳሰሉት ምክንያቶች በተለያዩ ጥናቶች መጠቆማቸውን ይህ የጥናቶች ክለሳ ያስረዳል፡፡
ዶ/ር ወንድሙ ጉዱ ጥናቶችን በመከለስ ያገኙት ውጤት እንደሚያስረዳው የእናቶች ትምህርት፤ ገቢያቸው፤ የሚኖሩበት ቦታ፤ የባሎች ዝንባሌ እና የእርግዝናን ከትትል ማወቅ፤ የመገናኛ ብዙሀንን የመመልከት ወይንም የማድመጥ እንዲሁም የማንበብ እድል፤ እርግዝናን በእቅድና በፍላጎት መፈጸም፤የጤና ተቋማትን የማግኘት ምቹ ሁኔታ እና የተሟላ አገልግሎት ማግኘት፤ የእርግዝና ክትትሉን የማድረግ ዝንባሌን እንዲሳካ ወይንም እንዳይሳካ የሚያደርግ መሆኑን ያገኙዋቸው ጥናቶች እንደሚያሳዩ ገልጸዋል፡፡
ክለሳው እንደሚጠቁመው የግለሰብ ሁኔታዎች ሌላው መታየት ከሚገባቸው ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህም የሴቶች እድልን በራስ የመወሰን አቅም፤ ማህበራዊ ግንኙነቶች እና ባህላዊ እምነቶች እንዲሁም የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት የስራ ሰአት፤ የአገልግሎት ሰጪዎቹ ባህርይ እና አሰራር የተጠቃሚውና አገልግሎት ሰጪው ግንኙነት፤ የአገልግሎት ክፍያው፤ እንዲሁም የሚሰጠውን የህክምና አገልግሎት ጥራትና ብቃት እና የተጠቃሚውን እርካታ ለማየት የሚያስ ችል በደንብ የተጠና ጥናት አለመኖሩን ክለሳው ያሳያል፡፡
ባጠቃላይ ሴቶች ትምህርትን ቢቀስሙ እና እውቀት እንዲኖራቸው ቢደረግ እንዲሁም እርግዝና በእቅድ ቢሆን የእርግዝና ክትትልን ተግባራዊ ለማድረግ ይረዳል፡፡ የክትትል ሂደቱ እናቶቹን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን ባሎችንም እንዲያካትት ቢደረግ እናቶች ከመውለዳቸው አስቀድሞ በመጀመር የሚያስፈልገውን ትብብር እንዲያገኙ ያግዛል። በአሰራርም የሚያግዙ ፖሊሲዎች፤ ፕሮግራሞች መቀረጽ ያስፈልጋቸዋል፡፡ አገልግሎቱን የሚሰጡ ተቋማትም እርካታ በሚሰጥ መልኩ እንዲፈጽሙት ከተቋም አደረጃጀት ጀምሮ የባለሙያዎችን አሰራር ማስተካከል እንደሚ ጠቅም ጥናቶቹ ሳይጠቁሙ አላለፉም የዶ/ር ወንድሙ ጉዱ ክለሳ እንደሚያሳየው፡፡   በኢትዮጵያ ያለውን የእርግዝና ክትትል በትክክል እናቶች እንዲጠቀሙበት ምን እንደሚያውካቸውና መጠቀማቸውም የሚያመጣውን ጥቅም በሚመለከት ግን ዘርዘር ያለ እና ጥልቅ የሆነ ጥናት መደረግ እንደሚያስፈልግ የጠቆመው ክለሳ ተጠቃሚውን ህብረተሰብና አገልግሎት ሰጪውን ባማከለ መንገድ ጥናቶች ነጥቦቹን በጉልህ ቢያሳዩ እናቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ለዚህ እገዛም ባሎች እንዲሁም ቤተሰቦች ከጎናቸው ይሆናሉ፡፡ ይህን ማድረግ ከተቻለ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ይረዳል፡፡ 

Read 1546 times