Saturday, 24 November 2018 12:42

ሄሎ . . . ይሰማል ?

Written by  ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(5 votes)


1 - ሽብር - “Reign of Terror”
በፈረንሳይ አብዮት ጊዜ፤ በዳቦ ዋጋ ንረትና ሀገሪቱን ዳር እስከ ዳር የተዛመተባት ጽኑ ረሀብ ባመጣው ክፉ ጠኔ ተደቁሶ፣ እሚልስ እሚቀምሰው ያጣው ሰፊው ሕዝብ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ፣ ያገሩን ንግሥት ፊት ለፊት ለማግኘት ጠየቀ፡፡ ሜሪ አንቶይኔት (Marie Antoinette) ወደ ቤተ መንግሥቱ የሚተምመውን በረሀብ ያበደ የሕዝብ ጎርፍ በሩቁ አሻግራ እያስተዋለች ስትርበደበድ፤ ታማኝ ደንገጡሮቿ ጥለዋት ከጎኗ እብስ አሉ። በእንጨት ስራና በንባብ ተጠምዶ እሚውለው ንጉሡ ባሏ፤ የሚያነብበውን መጽሐፍ አስቀምጦ ቤተ መንግሥቱ በረንዳ ላይ ቆሞ፣ ለሕዝቡ የተማጽኖ ንግግር ቢያደርግም፤ ሕዝቡ ራሷ ትቅረብ አለ፡፡ ከልጆቿ ጋር መጥታ ታየች፡፡ ሕዝብ ልጆቿ ወደ ውስጥ ይግቡ አለ፡፡ እንዳለውም ሆነ። ምክንያቱም ልጆቿ በአባታቸው ፈረንሳዊያን ናቸውና፡፡ እርሷ ግን በትውልድ ኦስትሪያዊት ናት፡፡ ክሷም፤ የፈረንሳይን ሀብት በዝብዛ ላገሯ ኦስትሪያ በድብቅ ስታግዝ፤ እሷም በአልማዝ ስትንቆጠቆጥ ኖራለች የሚል ነበር። ቅጽል ስሟ ‹‹እመቤት አባካኝ›› (“Madame Deficit”) የሚል ነበር፡፡ ንግሥቲቱ ሜሪ አንቶኔት፤ ‹‹ሕዝቡ ለምን ይራባል፤ ለምን ኬክ አይበሉም!›› ብላለችም ብለው ይወርፏታል፡፡ እሷ ግን ይህን ብትልም ወድዳ አልነበረም፡፡ ለብቻዋ ቸኮሌት እሚሰሩላት አሽከሮች ሁሉ ነበራትና፡፡ እናም ያን ቀን በቁጣ የነደደውን ሕዝብ ብቻዋን ትፋጠጥ ዘንድ ግድ ሆነ፡፡ መቸም አማላጅ አይጥፋ፤ ካሁን አሁን ሲጥ አደረጓት ሲባል፤ በፍርሀት ጸሎት ስታጉተመትም፤ያገሪቱ ጀብደኛ ጀግና የነበረው  Marquis de Lafayette በርከክ ብሎ፣ እጇን ስሞ፣ በዚያች ቀን ከሞት አዳናት፡፡
ውሎ አድሮ ‹‹አብዮቱ ልጆቹን መብላት›› ሲጀምር፤ ንግሥት ሜሪ አንቶኔትና ንጉሡ ባሏ ሉዊስ (King Lois XVI) ከልጆቻቸው ጋር በጨለማ በድብቅ፣ ካገር ለመጥፋት ሲሞክሩ፣ ጠረፍ ላይ ተይዘው ወህኒ ተወረወሩ፡፡ ከችሎት በኋላም፤ አንድ ቀን ጠዋት፤ አብዮቱ ከእርሱ ጋር ያልሆኑትን ሁሉ አንገት በሚቀረጥፍበት መግደያ (guillotine) አንገቷ ተቀልቶ ከመሞት አልዳነችም፡፡ ንጉሡ ባሏም እንዲሁ፡፡ ነገ ጠዋት እንደምትገደል ያወቀች ምሽት፣ ሌሊቱን ጠጉሯ ሸብቶ ማደሩም ይነገራል፡፡ እናም የፈረንሳዩ አብዮት የሕዝብ ማዕበል በጠባዩ፤ ‹‹ከኛ ሀሳብ ጋር  የማይስማማ ማንም ቢኖር ይገደላል›› ብሎ ባወጀው “Reign of Terror” ትእዛዙ፣ እስከ መጨረሻው ዘልቆበታል፡፡ ይህም ሦስተኛ ሀሳብን ለማስተናገድ ፍጹም ዝግጁ ስላልነበረ፤ የአብዮቱን አቋም ከ‹‹ሕብር›› ወደ ሽብር ያጋደለ ያደርገዋል የሚሉ በርካታ አሰላሳዮችን አፍርቶ አልፏል፡፡
2 - መለያ ምልክት - Stigma
በአይሁዳዊያን ላይ የተሰራጨውን ሀሰተኛ የሽብር አሉባልታ ተከትሎ፤ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት በአውሮጳ የሚኖሩ አይሁዳዊያን ሁሉ በናዚ የተላለፈውን ትእዛዝ ለመፈጸም ተገድደው ነበር፡፡ በእጃቸው ላይ ቢጫ የዳዊት ኮከብ እንዲያስሩ፡፡ በዚህም አይሁዳዊያኑን በቀላሉ ለመለየትና ለማግለል ተቻለ፤ ለመያዝ፤ ለመግደል፤ ለማጎር፤ ለማሰቃየት ...ወዘተ.፡፡ የዴንማርክ ንጉሥ የነበረው King Christian ግን፤ አዋጁ በታወጀ ማግስት እርሱ ራሱ ቢጫውን ኮከብ በእጁ ላይ አስሮ አደባባይ ወጣ፤ የዴንማርክ ሕዝብም ሁሉ እሱን ተከተለ፡፡ በዚህም ምክንያት አይሁዳዊያኑን ከዴንማርክ ሕዝብ መለየት አልተቻለም፡፡ አይሁዳዊያኑ በአሳ ማጥመጃ ጀልባዎች እየተጫኑ ከዴንማርክ ምድር ወጥተው እስኪያበቁም ትብብሩ ቀጠለ፡፡
ይህን ታሪካዊ ኩነት 75ኛ አመቱን ለመዘከር ባሳለፍነው ጥቅምት ወር የእስራኤል ፕሬዚደንት Reuven Rivilin በኮፐንሀገን ተገኝተው፣ ለከተማዋ ከንቲባ ፍራንክ ጄንሰን እንዲህ ሲሉ ተናገሩ...‹‹ The courage, the bravery, the humanity and the solidarity of the Danish people and the Danish resistance stood as a firm wall between Denmark and the Nazi death machine.” jpost 10/11/18.  ገጣሚው እንዲል ፤ ‹‹ትዝታ ነው ኗሪው›› . . .
ስሜት ሟች ነው
በቃ ተቀበረ
ማን በማን ይፈርዳል፤
ፍቅር ግን ህያው ነው
በይቅርታ አብቦ
አዲስ ቀን ይወልዳል፡፡
3 - አባ ውቃው - Hellooooo!
የሽብር ወሬ አዲስ አበባን የናጣት ቀን፤ መርሥኤ ሐዘን ወልደ ቂርቆስ በታሪክ ማስታወሻቸው ላይ እንደገለጡት፤ ጳጉሜ 1 ቀን 1920 ዓ.ም ዘውዲቱ፣ ምኒልክና ተፈሪ መኮንን በአባ-ውቃው ጉዳይ ከጠዋቱ ሦስት ሰአት ጀምሮ አንድ ጊዜም ሳያቋርጡ፣ እስከ ማታው አስራ አንድ ሰአት ሲነጋገሩበት ውለዋል፡፡  
ውሳኔውም ሁለት ትእዛዝ አወጣ፤ 1ኛ. አድማውን ሊያስነሱ ነው ተብሎ የተወራባቸው ቤተ መንግሥቱ ሊጋባ ወዳጄ ውቤም በአፈ ንጉስ አረጋይ እጅ ተይዘው እንዲቆዩ፡፡ 2ኛ. የአድማውን ወሬ ሰማሁ ብለው ንግሥት ዘንድ ቀርበው የተናገሩት የዘበኞች አለቃ ደጃዝማች አባ-ውቃው፤ በአጋፋሪ ወልደ ማርያም እጅ ታስረው እንዲጠበቁ፤ ተወስኖ ንግሥትም ወደ እልፍኛቸው፤አልጋ ወራሽም ወደ ማረፊያቸው ተመለሱ- ይላል የዘውዴ ረታ ‹‹ተፈሪ መኮንን - ረዥሙ የሥልጣን ጉዞ›› መጽሐፍ  . . .
አባ ውቃው ግን የእመቤቴ ዙፋን ሊገለበጥ ነው በሚል ንዴታቸው ገንፍሎ፣ ‹‹እኔ ምኒልክ አሽከር የደረሰው ይድረስ የእመቤቴን የዘውዲቱን ክብር አላስነካም›› ብለው፤ የዳግማዊ ምኒልክን መታሰቢያ ቤት አስከፍተው፤ መትረየሳቸውን ጠምደው፣ ወታደሮቻቸውን አሰባስበው፣ ከፍተኛ ሆነ የሽለላና የፉከራ ድምጽ ማሰማት ጀመሩ። (አዲስ አበባ በስጋትና ሽብር መናጥ ጀመረች! ከአመሻሽ ጀምሮ ሌሊቱን ሙሉ ቢለመኑ አሻፈረኝ አሉ፡፡) ‹‹ይህ እብድ አባ-ውቃው ምናልባት ምክር ቢሰማ፣ ንግሥት፤ ደህና ነኝ አታስብ ብለው አንድ ሰው ቢልኩበት ይሻላል...›› ሲሉ አልጋ ወራሽ ባመለከቱት መሰረት፣ ሹማምንቱ ደጅ ቢጠኗቸውም፤ ‹‹ከራሳቸው ከንግሥት ካልሰማሁ በስተቀር እናንተ የምትሉትን አላምንም፤‹የሌሊቱ ጨለማ ወደ ብርሀን ወገግ ሲል መታኮሴ የማይቀር ነው!››  አሉ፡፡
ዛሬም እኛ (ባልተጣራ ወሬ) የማህበራዊ ሚዲያው ቴክኖሎጂን ለበጎ ዓላማ አላዋልነውም ብለን እንተዛዘባለን፡፡ በዚያች ሌሊት የእምዬ ምኒልክ ስልክ ግን ላገር ሰላም ባጀ፡፡ ... ‹‹የግርማዊት ንግሥት የእልፍኝ አሽከሮች የበላይ አለቃ የሆኑት ቀኛዝማች ኃይለ ሥላሴ መገኖ አንድ ነገር ተገለጠላቸው፡፡ ‹‹የፖስታና የቴሌፎኑ ሚኒስትር እዚሁ ስላሉ፣ አሁን ባስቸኳይ ከእልፍኙ እስከ መታሰቢያ ቤቱ ድረስ የስልክ መስመር ተዘርግቶ፣ ግርማዊት ንግሥት፣ አባ-ውቃውን ቢያነጋግሩት ይሻላል...›› አሉ፡፡ በዚህ ሀሳብ ሁሉም ስለተስማሙበት ሁለት ሰአት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ስልክ ተዘርግቶ፣ንግሥቲቱ አባ-ውቃውን ለማነጋገር ቻሉ፡፡
ንግሥት፤ ለአባቴ ለዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ይሁን ብዬ ያሰራሁትን ቤተክርስቲያን በማይረባና ባልተጣራ ወሬ ተነስተህ መታኮሻ እንዲሆን ታስደፍረው?...  
አባ-ውቃው፤ ኧረ ለመሆኑ ንግስት ደህና ነዎት ወይ?
ንግስት፤ እኔማ ደህና ነኝ-- ምን አለብኝ?
አባ-ውቃው፤ እኔ እኮ በንግስት ላይ አንድ ነገር የደረሰ መስሎኝ ነው እንጂ፤ ንግስትማ ደህና ከሆኑልኝ፣ የሚይዘኝ ሰው ይላኩልኝና እጄን እሰጣለሁ፤ ብለው ቃል ገቡ፡፡
ወዲያውም እጨጌ ገብር መንፈስ ቅዱስና ልጅ ከበደ ተሰማ (ኋላ ደጃዝማች) ተልከው፣ አባ-ውቃውን በደንቡ መሰረት በሰንሰለት አስገብተው፣ ወደ ሚታሰሩበት ቦታ ወሰዷቸው፡፡››
...እነሆ፤ ያገራችን የቅርብ ዘመን ታሪክና የከሳሽ ተከሳሽ መልክ ትውፊት ገጽ ድርሣን ይህን ይላል፤ (‹‹በስልክ አነጋግሪኝ በቀጭኑ ሽቦ››) . . . ሄሎ ... ተፈላጊ ታሳሪ ወዲያውኑ ወደ ፈላጊው - ህጋዊ አሳሪው ዘንድ ከተፍ፡፡ አዲሳባም ከሽብርና ሁከት ጸጥ እረጭ - ሀገርም ሕዝብም ሰላም፡፡ ጥይት ሳይጮህ፤ በአንዲት የስልክ ጥሪ ብቻ፡፡ አቤት? ወዴት?... ከች!!


Read 2078 times