Sunday, 25 November 2018 00:00

ሀሳቡ ለማቋቋም በታሰበው የአማራ ሚዲያ ላይ የማነሳቸው ጥያቄዎች

Written by  አሰግደው ሽመልስ (ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ)
Rate this item
(2 votes)

    በአማራ ክልል ውስጥ ያለው እጅግ የሚልቀው ማኅበረሰብ፣ ችግርና ድህነት የኅልውና ሰረሰሩን ሊበጥሱት ታግለዋል፤ ጥለዋል፤ ወድቀውም ገልብጠዋል፡፡ ይኸ ማኅበረሰብ ሌሎች አያሌ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ የደረሰባቸው አሣር ደርሶበታል፤ የመከራ ዘመኑን በሌላ የመከራ ዘመን ተሸጋግሯል፡፡ ከክልሉ ውጪ በመላው ኢትዮጵያ ውስጥ ተበትኖ ኑሮውን በመምራት፣ አገሩን በማቅናት ደፋ ቀና ይላል፡፡ በርግጥ ከክልሉ ውጪ የሚኖረው አማራ እንዲሁ በተድላ ላለመኖሩ እልፍ ማሳያና ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ነገር ግን የሆነው ሁሉ በእውነተኛው የአካባቢው ማኅበረሰብ ፍላጎት ሳይሆን በእንጭጭ የፖለቲካ ኃላፊዎችና የስልጣን ካዳሚዎች ሴራ እንደሆነ አይደበቅም፡፡ ከዚህ የንዑሳን ፖለቲከኞች ትርክት በዘለለ በዚያው ከሚገኙት ማኅበረሰቦች ጋር በዘር በጎሳ መንደርና ወንዝ ሳይቆርር፣ በጋራ ተስማምቶ ኖሯል፤ እየኖረም ነው፡፡ ይሁንና ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር በጋራ አገር ስለ ማቅናትና ኅብር ስለ መፍጠር፣ ቢቸገር ችግሩን፣ ቢራብ የአንጀቱን መሟሸሽ፣ ቢበደል የእንባውን ሸንተረር፣ ቢደላው ሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹን የሚረዳበትና ልደፍጥጥህ የሚለው ጽንፍ ቢመጣ እራሱን የሚከላከልበት የራሱ አንደበት ያስፈልገዋል፡፡ እንደ ኅብረተሰብ፣ ማኅበራዊ ስነ-ልቦናውን በታዳጊ ልጆቹ የልቦና እርሻ የሚዘራበትና የሚያዘምርበት የተግባቦት ተቋም ቅንጦቱ ሳይሆን የነገ እጣ-ፈንታውንም የሚወስን ይሆናል:: አሁን መታሰቡ፣ ወደ ተግባር መገባቱም  መልካም ነው፡፡
አካሄዱና አመሠራረቱ
ሚዲያውን ለማቋቋም ዓለም አቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ ሥራዎች መጀመራቸውን  ተመልክቻለሁ። አመሠራረቱ ላይ ግን ጥያቄ አነሳለሁ፡፡ መቼም የሚቋቋመው የሕዝብ ሚዲያ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም (በሕዝብ ስም ገንዘብ ተሰብስቦ ለንግድ ማድረግ አይቻልምና)፡፡ የሕዝብ ከሆነ ደግሞ ኅብረተሰቡ በሥሙ ስለሚከፈተው ሚዲያ የማወቅ መብት አለው፡፡ የማቋቋሙን ኃላፊነት የወሰደው አካል፣ ስለ አመሠራረቱ መረጃ መስጠትና ማሳወቅ እንዳለበት ሊረዳ ይገባዋል፡፡ ሕዝቡም የራሱ በሆኑ አደረጃጀቶች የማወቅና የመምከር መብቱን ሊነፈግ አይገባም። የሕዝብ ሚዲያ መሠረታዊ ሀሳቡ፤ የዚያው ሕዝብ ይሁንታና ሚዲያው ከተቋቋመ በኋላ ለሚቀርበው ተረክ ኃላፊነቱን የሚወስድ መሆን ይኖርበታል፤ ይዘቱንም የመወሰን ያልተገደበ ድርሻ አለው፡፡
አስፈላጊው የኤዲቶሪያል ጉዳይ
የሚቋቋመው ሚዲያ በግለሰቦች አስተባባሪነት ይመራ እንጂ፣ አጠቃላይ የኤዲቶሪያል ሥራው በግለሰቦች የሚዘወር መሆን የለበትም፡፡ ከመቋቋሙም በፊት እያንዳንዱ  የኤዲቶሪያል ጉዳይ የተገራና በጥናት የተደገፈ ሊሆን ያሻል። የሕዝብ ሚዲያ ስለሆነ የኤዲቶሪያል ጉዳዩን በበላይነት የሚወስን፣ የሚያዘጋጅ፣ የሚመራና የሚቆጣጠር አካል (የኅብረተሰቡ ትክክለኛ ውክልና የተረጋገጠበት) ያስፈልገዋል፡፡ የኤዲቶሪያል ጉዳይ የሚዲያውን የመቋቋም ምክንያት፣ ዓላማና ግብ ከኅብረተሰቡ የተኖረ ሕይወት፣ ከዛሬ ማኅበረ-ፖለቲካ-ኢኮኖሚያዊ ዕውነታና የነገ መንገዱን ከማመላከት የሚመነጭ እንጂ ዛሬ ላይ ባለው ሁኔታ ላይ ብቻ የተመሠረተም ሊሆን እንደማይገባ መታወስ አለበት። የሚተዳደርበት ገቢ ምንጩ፣ ዘዴው፣ መንገዱ፣ የሐብት አስተዳደሩ፣ የይዘትና የቅርፅ ምልከታውን መወሰን ያስፈልገዋል፡፡ ለዚህም ባለቤቱ ሕዝቡ ቀዳሚ ሊሆን ይገባል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ስያሜው፤ የኅብረተሰቡን ስነ-ልቦና መነሻ ያደረገ የኤዲቶሪያል ውሳኔ፣ የኅብረተሰብ ፍላጎት ካልተንፀባረቀበት ተግባሩ መንገታገቱ አይቀሬ ይሆናል፡፡
ዘለቄታውስ፡ በግለሰቦች በጎ አድራጎት፣ በዳያስፖራው መዋጮ ወይስ በኅብረተሰቡ ሐብት?
ይህን ትልቅ ሥራ ሊደጉም/ሊረዳ የሚችል እልፍ ባለሀብትና የመንግስት ጭፍራ እንደሚኖር ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን የሕዝብ ሚዲያ የሚቋቋመውም ሆነ የሚደገፈው በራሱ ፍላጎት ባሳየው ማኅበረሰብ መሆን አለበት፡፡ ለዚህም መሠረታዊ ሀሳቡ፣ የሚዲያው ሥራ፣ አመራርና  ፍላጎት በደጓሚው ፍላጎት እንዳይጠመዘዝ ስለሚፈራ ነው፡፡ በመሆኑም እያንዳንዱ የአማራ አርሶ አደር፣ የራሱ ሚዲያ ሲቋቋም የማወቅ መብት እንዳለው ሁሉ፣ በሳንቲምም የመደገፍ መብቱ ሊከበር ይገባዋል፡፡ ድህነቱን ሰበብ ተደርጎ በማያውቀው የፋይናንስ ምንጭ ቢቋቋምለት፣ ነገ ለሚጠይቃቸው ድርብ ጥያቄዎች መልስ አይኖርም፡፡ የሕዝብ ሚዲያ ምናልባትም ከመንግስትና ጡንቻው፣ ከፈረጠመ ባለሐብት ምፅዋት ወጥቶ፣ የሕዝቡ አንደበትና የሀሳብ ማንሸራሸሪያ ማማ እንዲሆን የሕዝብ መሠረት ይያዝ፤ እያንዳንዱ ግለሰብ ጎጆ ውስጥ አብሮ እንዲኖር ይደረግ፡፡
መሠረታዊ ፍልስፍናው
ፍልስፍና ያስፈልገዋል፡፡ የአማራን ኅልውና እና እንደ ሕዝብ የመለወጥ ፍላጎትና የጉዞ ፍጥነት ወደፊት ማጓን እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ከሌሎች የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች ጋር ስለሚኖረው መስተጋብር የጠራ ፍልስፍና ይፈልጋል፡፡ በተጓዳኝ ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ወይም ፖለቲከኞች ርዕዮት የራቀ መሆንም አለበት። ያለፈው፣ ዛሬ ላይ የቆመበትና የነገ ጎዳናው ትርክት፤ አሁን እንደሚስተዋሉት የጎጥ አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ሚዲያዎች መበላላትንና መጠፋፋትን የሚያወግዝና አብሮ መኖርን የሚያራምድ መሆን ይኖርበታል፡፡ ሚዲያው ፋፍቶና ጎልብቶ መቀጠል የሚችለው፣ የፍልስፍና ማጠንጠኛው አብሮ መኖር ሲሆን ብቻ ነው፡፡

Read 846 times