Saturday, 24 November 2018 12:28

ሁለት ፓትርያርኮች በአንድ መንበር?

Written by 
Rate this item
(2 votes)


   በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተፈጥሮ የቆየውን የልዩነት ዘመን ለመቋጨት በቅርቡ በተፈጸመው ውሕደትና አንድነት ብዙ ሰው ቢደሰትም፣ የፓትርያርኮቹ ሁለት መሆን ግን አንዳንዶችን ሲያሳስብ፣ አንዳንዶችን ደግሞ ሲያደናግር ይታያል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱን በመተቸት እንደ መመጻደቅም ያደርጋቸዋል፡፡ ለአንዳንዶች በፍትሐ ነገሥታችን ላይ ያለውን “ይህች ሹመት  በአንድ ዘመን በአንድ ሀገር ለሁለት ሰዎች ልትሆን አይገባም፡፡ ይህ በአንድ ሀገር ከተደረገ ግን አስቀድሞ ለተሾመው ትጽና” /ፍት. መን 4፤ 76 -78/ የሚለውን ይዘው፣ በዚያ መንገድ እየተፈጸመ አይደለም የሚለው ያሳስባቸዋል፡፡ እንዲህ ያለው ችግር፤ ሌሎቹን አብያተ ክርስቲያንም በተለያዩ ዘመናት ገጥሟቸው ሲፈቱት ኖረዋል፤ ያልተፈቱም አሉ፡፡  ለእኛ ግን እንኳን ችግሩ መንበሩም ገና አዲስ ስለሆነ በጉዳዩ ላይ ያለን ግንዛቤ ውሱን መሆኑ፣ ይህን መሰል ችግር ፈጥሮብን ይሆናል፡፡ ወይም ደግሞ ስለ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ሊኖረን የሚገባው ዕውቀት አናሳነትና ችግሩ የሚቀርብበት ፖለቲካዊ ትርጉም ወይም ክስተቱ የፈጠረው ያለመሸናነፍ ስሜትም ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህም ጋር በጉዳዩ ላይ የተሻለ ዕወቀትና ግንዛቤ ያላቸው ሰዎች ቢኖሩም ምናልባት በአካዳሚው እንደለመዱት ዐይነት ሙያን መሠረት ያደረገ ውይይት  እንዳይኖር ስድብና ጥላቻን መሠረት ያደረገውን ትችት በማየት፣ ውዝግቡን  መፍራት ዝም አሰኝቷቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ የእነርሱ ዝምታ ማብዛት ደግሞ ብዙዎቻችን የተለያየ ሀሳብ እያመጣን እንድንታወክ ማድረጉ አልቀረም፡፡ ውዝግቡ ካልቀረ ደግሞ ቀስ ብለንም ቢሆን ወደ ትክክለኛው ዕውቀት ሊያደርስ የሚችል ውይይት ብንጀምር ሳይሻል አይቀርም በሚል ይህችን የውይይት መነሻ አቅርቤያለሁ፡፡
ለዚህ ጽሑፍ መነሻነት በቀዳሚነት የተጠቀምኩት ደግሞ በቅርብ ጊዜ በድጋሚ የታተመውን የብላታ መርስዔ ኀዘንን መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ መጀመሪያ በ1956 ዓ.ም. ከታተመ  በኋላ 55 ዐመታት ያህል  ቆይቶ ለሁለተኛ ጊዜ በያዝነው በ2011 ዓ.ም. ታትሞ በሥርጭት ላይ የዋለው “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያው ፓትርያርክ፤ 1951 ዓ.ም.” የሚለው ነው፡፡ የመጽሐፉ አዘጋጅ የሆኑት ቢያንስ ለእኛ ትውልድ ታላቅ ባለውለታ የሆኑት ታላቁ ሊቅ ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ የሚያቀርቡልን ታሪክ ደግሞ ይህንንም ጉዳይ ጭምር የሚሞግት እንደሆነ ይሰማኛል፡፡
ይህ የብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ መጽሐፍ፣ በገጽ ብዛቱ ትልቅ የሚባል አልነበረም፡፡ በይዘቱ ጠቀሜታ ከታየ ግን እያንዳንዷ ጉዳይ እጅግ አስተማሪና ጠቃሚ በመሆኑ አሰር ወይም ገለባ የለሽ ምርት ሊባል የሚችል አስደናቂ መጽሐፍ ነው፡፡ በርግጥ በአሁኑ በድጋሚ ኅትመቱ አሰናጅው፣ ልጃቸው አቶ አምሃ መርስዔ ኀዘን እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆኑ ብዙ አባሪዎችን ስላካተቱበት፣ የገጽ ብዛቱ ራሱ ከ220 ገጽ በላይ ሆኗል፡፡ ለዛሬው በመጽሐፉ ካስደነቁኝና ርእሳችንን ለማየት ይጠቅማሉ ብዬ ከማስባቸው ነጥቦች ጥቂቶቹን ከማከፈል ልጀምር፡፡
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከተካተቱት ሂደታዊ ታሪኮች፣ የኢትዮጵያው የአባ ሰላማ የሊቀ ጵጵስና መንበር ወደ ፕትርክና እንዲያድግ ከግብጻውያን አባቶች ጋር  የተደረሰበትን ስምምነት የሚያስረዳውን ሰነድ (ከገጽ 38 ጀምሮ ያለውን) የሚመለከተው ከሁሉም በላይ በጣም አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ብላታ ሂደቱን እንደገለጹልን፤ ሰነዱን ግብጻውያ አባቶች አርቅቀው ካዘጋጁት በኋላ በኢትዮጵያ ተወካዮች በኩል ጥያቄዎች እየተነሡ የተደረጉትን ውይይቶችና ነጥብ በነጥብ፣ በረቂቅ ሰነዱ ላይ የተደረሰበትን ስምምነት ይገልጻል። እኔም ማቅረብ የፈለግሁት፤ ከእነዚህ ውስጥ የእኔን ትኩረት የሳቡትን ነው፡፡ እነሆ፡-
የእስክንድርያው ፓፓ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ሊኖረው የሚገባውን መብት በተመለከተ
በሀገራችን በኢትዮጵያ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን” በሚል የተለየ መንበር እንዲኖራት የተደረገው፣ ቤተ ክርስቲያናችን ከዚያ በፊት በመንበረ ማርቆስ የተሰየመው አባት ፓትርያርኳ ሆኖ መኖሩ የታመነ ነው፡፡ በግብጽ ቢኖርም ፕትርክናው ብሔራዊ ሆኖ፣ ለግብጽ ብቻ የተወሰነ አልነበረምና፡፡ ብሔራዊ መባልም ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን የሚገባ ስላልሆነ፣ ሊሆንም ስለማይችል፣ ከ1951 በፊት ፓትርያርክ እንዳልነበረን የሚያስቡ ሰዎች ብዥታቸው የሚመነጨው ምናልባት መንበርንም ሆነ ርእሰ መንበርን ከዚሁ ከብሔራዊነት ጋር ስለሚያገናኙት ሊሆን ይችላል፡፡ ሌላው ቀርቶ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትገነጠል ወዲያው የራሷ ፓትርያርክ በጓዳ ተጣድፎ እንዲኖራት የተደረገው ይኸው “የብሔራዊነት” ጽንሰ አሳብ ሥር የሰደደ ስለነበር ይመስለኛል፡፡ የሆነው ሆኖ፣ የብላታ መጽሐፍ ስምምነቱን አስመልክቶ ሲነግረን የሚጀምረው ግን ይህን የሚመለከት አንቀጽ በማጽደቅ ነበር፡፡ ሁለት ፓትርያርክ በአንድ ዘመን ይቻላል ወይ? የሚለውንም ከዚሁ ጉዳይ ተነሥተን ስለምንመለከተው ወደ ስምምነት አንቀጹ እናምራ፡፡
ይህን ጉዳይ በተመለከተ በሰነዱ ቀርቦ የነበረው ረቂቅ፤ “የእስክንድርያ ፓፓና ፓትርያርክ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ አለቃ ነው” (ገጽ. 41) የሚል እንደነበር የሚገልጹት ብላታ፤ የኢትዮጵያ ተወካዮች ባነሡት ጥያቄና በካሔዱት ክርክር ምክንያት “ከፍተኛ አለቃ ነው” የሚለውን “ከፍተኛ መንፈሳዊ አባት ነው” ወደሚል እንዳስቀየሩት ይነግሩናል፡፡ ስለዚህም  ከላይ በርእሳችን ላነሳነው መሠረታዊ ጉዳይ ያለው ጠቀሜታ ላይ በማተኮር፣ የስምምነቱ ዋና ጉዳይ ምን እንደሆነ እንመልከት፡፡
በተለያዩ አጋጣሚዎች ሌሎች አብያተ ክርስቲያን ራሳቸውን ችለው ስለወጡባቸው ሁኔታዎች ባነበብኩት ውሱን ንባብ መሠረት ከሆነ፤ ብዙ ጊዜ ሂደቱን የሚፈቅዱባቸውን ውሳኔዎች በሦስት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ በብዙዎች ዘንድ የተሻለ ይታወቃሉ የሚል ግምት አለኝ፡፡ በዚህ ሰነድ ረቂቅነት ቀርቦ የነበረው ግን ሦስተኛ ነገር ጨምሬ ማቅረብ እንዳለብኝ አሳስቦኛል፡፡
በአብዛኛዎቹ የሚታወቁት ሙሉ በሙሉ ራስን ችሎ መውጣት(Autocephalous) ወይም ደግሞ በሲኖዶስና በመንፈሳዊ ነገሩ አንድነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በአስተዳደሩ ብቻ ራስን መቻል (Autonomous) የሚባለው ዐይነት ውሳኔ ነበር፡፡ በዚህ በግብጻውያን በቀረበው ረቂቅ ሰነድ “ከፍተኛ አለቃ ነው” በሚለው ላይ ስምምነት ተደርሶ ቢሆን ግን ሁለቱንም ልናገኝ አንችልም ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም “ከፍተኛ አለቃ” የሚለው አገላለጽ፣ በአስተዳደሩ ላይ ሳይቀር ቦታ ስለሚሰጠው በአስተዳደር ጉዳዮች እንኳ አስፈላጊ ሲሆን ጣልቃ የመግባትን ዕድል ያገኝ ስለነበር፣ የተሰጠን ዕድል ከፊል የአስተዳደር ነጻነት (Semi-autonomous) ብቻ ይሆን ነበር ማለት ነው። አዲስ የሚያሰገኝልን ነገር ቢኖር በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ብቻ ለዋናው ፖፕ አጋዥ የሆነ ወይም አሁንም በኢትዮጵያ ላይ ብቻ የተወሰነ የምክትልነት የሚመስል መዐርግ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ አባትና በሥሩ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሊቃነ ጳጳሳት ብቻ ይሆን ነበር ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ተወካዮች ግን ይህንን ጉዳይ በአግባቡ ተረድተውት ስለነበር አልተቀበሉትም፡፡ ሆኖም አስቀይረው የደረሱበት ስምምነት ራሱ ደግሞ እንደገና ሌላ ወሳኝ መሠረታዊ መልእክት ወይም መርሕ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡
“ከፍተኛ መንፈሳዊ አባት ነው” በሚል የተተካውንና ከዚያ ቀጥሎ በግብጾች የቀረቡትን ረቂቆችና በእኛም ተወካዮች ስምምነት የተደረሰባቸውን ስናይ ግን በዚህ ቃል ላይ የተደረሰው ስምምነት፣ በሁለቱ አካላት ላይ የነበረው መረዳት አንድ ዐይነት አይመስለኝም፡፡ በእኔ እምነት ግብጾች ይህን ቃል የተቀበሉት፤ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለመጨረሻ ሊፈቅዱ ያሰቡት፣ የመጨረሻው ከእነርሱ የመውጣት ወሰን አሁንም  ሙሉ በሙሉ ራሳችንን የቻልን (Autocephalous) መሆናችን ሳይሆን በአስተዳደር ብቻ ራሰን  የቻሉ (Autonomous) መሆንን ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በእኛ ዘንድ የነበረው ግንዛቤ ግን ራስን ሙሉ በሙሉ መቻል መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ የግብጾች ግንዛቤ ይህ መሆኑን የሚደግፉልኝ ሌሎች ሦስት ጉዳዮች በዚህ የስምምነት ሰነድ ላይ ይገኛሉ፡፡
በዚሁ ሰነድ ላይ ከተስማሙባቸው ጉዳዮች አንዱ፤ አዲሱ ለኢትዮጵያ የሚሾመው አባት “ፓትርያርክ ካቶሊኮስ” እንዲባል ግብጾች ያቀረቡት ሀሳብ ነው፡፡ ይህ ሀሳብ በእኛ ሊቃውንት ዘንድ ካቶሊኮስ የሚለውንና ከካቶሊክ ጋር ግንኙነት እንዳለን የሚያስመስለውን ቃሉን ለማስለወጥ ከመጣራቸው በቀር መሠረተ ሀሳቡን ለማስለወጥ ግን (እንደ ሰነዱ) አልሞከሩም። ምክንያታቸው ግን አለመረዳት ብቻ ሳይሆን ለውጥ አያመጣብንም ብለው አስበውም ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያታቸው ምንም ሆነ ምን ካቶሊኮስ የሚለውን ቃል “ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት” በሚል በማስቀየር ስምምነቱ እንደተጠናቀቀ፣ ከዚህ ከብላታ መጽሐፍ ላይ እንረዳለን፡፡ ይህም ማለት የኢትዮጵያው ፓትርያርክ ይህንኑ መዐርግ የሚይዘው በመልክአ ምድር ኢትዮጵያ በምትባለው ብሔራዊት ሀገር ብቻ የተወሰነ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ምከንያቱም መዐርጉ “ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት” ዘኢትዮጵያ ማለት፤የክህነቱ ክትትል ለተገኘበት ለመንበረ ማርቆስ በኢትዮጵያ ላይ ለሚሾሙት ሊቃነ ጳጳሳት ብቻ እንጂ በሁሉም (በግብጽና ከእስክንድርያው ፓፓ ተሹመው በዝርዎት ያለውን ሕዝብ ለማገልገል በመላው ዐለም የተበተኑት ላይ)  የበላይ ርእስነትን ሊያስገኝለት አይችልምና።  ስለዚህ ራስነቱ (ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት የሆነው) በኢትዮጵያ ለሚኖሩ ሊቃነ ጳጳሳት ብቻ ነበር፡፡  በዚህም ምክንያት ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ስለመሆኑ “ፓትርያርክ” የሚል ቅጽል ተሰጠው እንጂ ሙሉ ፓትርያርክ ገና ያልሆነ (እንደ ስምምነቱ) ነበር ማለት ነው፡፡ ይህም ልክ በአካዳሚያው እንደ ተባባሪ ፕሮፌሰር (በሥሩ ብዙ ረዳት ፕሮፌሰሮችን፣ ዶክተሮችን፣… እያማከረ) ዋና ፕሮፌሰር እንዳልሆነው ወይም በጦሩ ዐለም ለሙሉ ጀነራልነት እንዳልደረሰ እንደ ሊቱናንት ጄነራል ዐይነት ማለት ነው፡፡ በግብጾች በኩል ለማሳመኛነት የቀረበው አንደኛ “የባግዳድ ጳጳስ መጠሪያው ይህ ነው” የሚልና ዳግመኛም በአንድ መንበረ ማርቆስ ላይ ሁለት አባቶች ሲቀመጡ ለመለየት ነው የሚል እንደነበር ብላታ በጽሑፋቸው አስፍረዋል፡፡ እንግዲህ ልብ በሉ! ያ ሒደት ውጤቱ  ሁለት አባቶችን በአንድ ቅዱስ መንበር ማስቀመጥ ነው ማለት ነው፡፡ በሌላም ቋንቋ እስከዚህ ዘመን ይህን ዕድል የተከለከልነው፣ በዚሁ መሠረታዊ ቀኖናዊ ምክንያት እንደሆነም እየተነገረን ነው፡፡  ይህም ማለት ለመንበረ ማርቆስ በእኩል መዐርግና ሥልጣን የሚጠሩ ነገር ግን በሁለት ቦታ የሚቀመጡ ሁለት ወራሲዎች ሊኖረው አይችልም ወይም አይገባም እንደ ማለት ነውና፡፡ ሊሆን የሚችለው ዋናዉ ፓፓ ወፓትርያርክ የግብጹ ሆኖ፣ የኢትዮጵያው ግን “ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ” ተብሎ በተወሰነ ቦታ ላይ ብቻ በዋናው ሥር የሚቀመጥ ለኢትዮጵያውያን ከእስክንድርያው ፓፓ ቀጥሎ ያለ ሁለተኛ ፓትርያርክ ለማለት ይመስለኛል፡፡ ሆኖም በእኛ ሀገር ሊቃውንት ዘንድ የነበረው ግንዛቤ ግን ይህ የነበረ አይመስለኝም፡፡ ግብጽ ወርደው የሚደራደሩት ግን ቢያንስ በሀገር ውስጥ ይነገር ከነበረው ለየት ያለ ግንዛቤ  እንደ ነበራቸው፣ አሁንም ከሌሎቹ የስምምነት ነጥቦች መረዳት ይቻላል፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ወክለው ሲደራደሩ የነበሩት ሊቃውንት የነበራቸውን ግንዛቤ ለየት ያለ እንደነበር ለመረዳት ይቻለን ዘንድም የተወሰኑ ነጥቦችን ላክል፡፡ በረቂቅ ሰነዱ መሠረት ከሆነ የኢትዮጵያው አዲሱ አባት በኢትዮጵያ ጳጳሳትን የመሾም ፈቃድ ቢያገኝም የሚሾማቸውን ከእነ ሕይወት ታሪካቸው አስቀድሞ ለግብጹ ፓፓ እንዲያሳወቅ ግዳጅ ይጥልበት ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ሊቃውንት በቀረበው ክርክር ግን የግብጹም ፓፓ በግብጽ ሲሾም ለኢትዮጵያው ያሳውቅ የሚል ተጨማሪ ሀሳብ አቅርበው በጉዳዩ ላይ ይስማማሉ፡፡ በእኔ እምነት የዚህ ስምምነት ዐላማ ወይም ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ሥልጣን ግልጽ አይደለም፡፡ በግብጾች በኩል የቀረበው ሀሳብ ግልጽ ነው፡፡ ዋናው ትልቁ አባት የመንበረ እስክንድርያው ነው የሚል ነበር፤  ለኢትዮጵያው የማሳወቅ ግዴታ የተጣለበትም በዚሁ ምክንያት ነበር፡፡ አሁን ግን የግብጹ ለኢትዮጵያው ያሳውቅ ሲባል ግብጾች የተስማሙት ለበታቹ ቢያሳውቅም ያኛው የመለወጥ ሥልጣን እስከሌለው ድረስ ምንም አይደለም የሚል ሀሳብን የያዘ ይመስለኛል፡፡ በእኛ ሊቃውንት በኩል ግን ትይዩነትን ያሳያል ብለው ይሁን ወይም ሌላ ጥቅም ታይቷቸው እንደሆነ የሚያብራራ ምክንያት አልቀረበም፡፡
ከዚህ ቀጥሎ የቀረበው  ሁለተኛው ሀሳብ ደግሞ ፓፓው እክል ቢገጥመው ሲኖዶስን መሰብሰብ የሌላ ግብጻዊ አባት ሥራ መሆን የለበትም፡፡ ይልቁንም የኢትዮጵያው አዲስ ተሿሚ ሁሉንም መምራት አለበት ብለው ኢትዮጵያውያን ያቀርባሉ፡፡ ግብጻውያን በመሠረተ አሳቡ ተስማምተው በጽሑፍ አይገለጽ፤ ሁልጊዜም ቢሆን የሚሰበስበው በመዐርግ የሚበልጠው ስለሆነ የኢትዮጵያው ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነጳጳሳት ነውና ከሁሉም ሊቃነ ጳጳሳት ስለሚበልጥ የግድ መገለጽ አያስፈልገውም ብለው ኢትዮጵያውያኑን ያሳምኗቸዋል፡፡ ስለዚህ በዚህ አንቀጽ ስምምነት መሠረት፤ የኢትዮጵያ ወኪሎች የሲኖዶሱን አንድነትና የፓፓውን የበላይነት ተቀብለው ነበር ማለት ይቻላል። እንደ እኔ እምነት ግን ይህ መሠረታዊ ጉዳይ በሌሎቹ የኢትዮጵያ ሊቃውንት ዘንድ የሚታወቅ አልነበረም፤ ወይም እስካሁንም ድረስ ግንዛቤያችን ትክክል አልነበረም ያስባለኝ ነጥብ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ተወካዮች የተለየ አቋም ያሰኘኝ ግን ከላይ የተገለጸውን እስከነ ስም አጠራሩ ከተቀበሉ በኋላ የኢትዮጵያው አዲስ ተሿሚ አባት ከኢትዮጵያ መልክአ ምድራዊ ክልል ውጭ ለሚደረግ መስፋፋት ጳጳሳትን መሾም አይችልም የሚለውን ሌላውን የስምምነት ነጥብ አንቀበልም ማለታቸው ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ከላይ  ቀድመው “ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት” ብለው የተስማሙበትን ምክንያት አላወቁትም ነበርን የሚያሰኝ ነው፡፡ እገሌ ዘእስክንድርያ፣ እገሌ ዘሮም፣ እገሌ ዘቁስጥንጥንያ በሚለው አንጻር አሁን እንዳለው “ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ” ብለን እንሔዳለን ብለው አስበው ይሆን? ወይስ ጊዜና ቦታ ይተርጉሙት ብለው? የሚሉትን ጥያቄዎች ሊያጭርም ይችላል፡፡ ይህን አስበው ከነበረ “ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት” ተብሎ ከግብጾች የተቀበልንበትን ዐላማ ከማሳካት ያለፈ ትርጉም የሚኖረው አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩ የታሠረው “ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት” የሚለው መዓርግ ላይ ነውና፡፡ በአንጻሩ ግብጾቹ ግን ለድርድር የተቀመጡት የእስክንድርያውን መንበር  የበላይነት ወይም የክትትሉ መነሻነት ለማስከበርም ጭምር ሊሆን ይችላል፤ ይህን ሁሉ የሚያደርጉት እያወቁ ነበር ማለት ይቻላል። ስለዚህ በዚህ ነጥብ ላይ መስማማት ሲያቅታቸው ወደፊት ፓፓውና የኢትዮጵያው ፓትርያርክ ጉዳዩ ሲያጋጥም ተወያይተው በተስማሙበት መሠረት ይሁን በሚል ይስማማሉ። ብላታ ይህን ስምምነት አስመልክተው የራሳቸውን አሳብ ሲገልጹ ወደፊት ሁኔታው ሲያጋጥምና ፓፓውና ፓትርያርኩ ሲወያዩ ባይስማሙ፤ የኢትዮጵያው አባት በውጭ ሀገር ለሚፈጠር ሀገረ ስብከት ጳጳሳትን እንዳይሾሙ ቀድሞ ከሚከለክል ቅድመ ሁኔታ ተርፈናል ይላሉ። በዚሁ መንገድ ግብጾችም ምናልባት ወደፊት ኢትዮጵያውያን ሲጠይቁን እንከለክላለን፤ አሁን ምን አዳረቀን ብለው ወስደውታል ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ ጉዳዩ ግን የግብጾች አቋም ወጥነት ያለውና ዋናው ፕትርክና ያልተፈቀደ መሆኑን የሚያመለክት ሲሆን ኢትዮጵያውያን ወኪሎች ደግሞ ለግብጾች እንደ ሀሳባቸው የሚሔዱ እየመሰሉ ራስን የመቻልን ነገር በውስጠ ታዋቂ ብቻ እየጎተቱ ይመስላል፡፡ የተለየ የምለውም ይህንኑ ነው፡፡  
ከአቡነ ባስልዮስ በኋላ ሊሾሙ የሚገባቸውን ፓትርያርኮች በተመለከተ
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ካስገረሙኝ ስምምነቶች አንዱ ይህ ጉዳይ ነው፡፡ ብላታ በመጽሐፋቸው ገጽ 41 ላይ እንዲህ ይላሉ፡-
“ለፓትርያርክነት የሚመረጠው ሰው ከቆሞስነት መዓርግ በላይ ካልሆኑት መነኮሳት መካከል እንዲሆን የሚል በስምምነቱ ላይ እንዲገለጽ ሲሉ ሀሳብ አቀረቡ። ይኸውም ሕግ በግብጽ ፓትርያርክ ላይ ጭምር ለወደፊት የሚጸና መሆኑን ኮፕቱ ስላረጋገጡልን በስምምነቱ ውስጥ ተገልጾ ተጽፎአል፡፡ ይህ ግን ለወደፊት እንጂ ባሁኑ ላለው ሹመት የማይሠራበት ስለመሆኑ የሁለቱ ወገን መልእክተኞች በቃል ንግግር አድርገው ከተግባቡበት በኋላ አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ የሚሆኑት ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ መሆናቸውና በግርማዊ ንጉሠ ነገሥት መመረጣቸው በግርማዊነታቸው ወረቀት ሲረጋገጥ፣ ፓፓና ፓትርያርኩም በዚሁ መስማማታቸውን በጽሑፍ አረጋግጠው መልስ እንዲሰጡ ሆኖ በቃል ስምምነት ተወሰነ፡፡ ይህ ሁሉ በጽሑፍ ተረጋግጦ ተፈጽሟል፡፡”
በዚህ ከላይ በጠቀስኩት መረጃ መሠረት፤ ለኢትዮጵያ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት የሚሆነው አባት ሊሾም የሚገባው ቀጥታ ከምንኩስና ሕይወት መጥቶ፣ በሆነ ሀገረ ስብከት ላይ ሊቀ ጳጳስነትን ይዞ “ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ” ሊሆን ፈርመን ነበር ማለት ነው፡፡ ሆኖም ሰነዱ አንድ ነገር ግልጽ ሳያደርግ አልፏል፡፡ ይህ ከምንኩስና መጥቶ “ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ”  ሆኖ የሚሾምልን አባት፤ በሊቀ ጵጵስና የሚሾምበትን ሀገረ ስብከት ግልጽ አላደረገም፡፡ ለምሳሌ የግብጽ ፓፓ ሆኖ የሚሾመው ሰው ሀገረ ስበከቱ እስክንድርያ ናት።  ይህም ማለት የግብጹ ፓፓ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ ሆኖ እንጂ ሌላ ሀገረ ስብከት ላይ ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ለፖፕነት እንደማይሾመው ማለት ነው፡፡ የእኛን አሁን ያለንን  ስናየው፣ ቅርብ ጊዜ በተሻሻለው ሕገ ቤተ ክርስቲያን፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን ሊቀ ጳጳስነት ይሰጠዋል፡፡ በመዓርግ ሲጠራ ግን እንደገና “ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም” ይባላል፡፡ ይህ ሁሉ የፕትርክናችንን ነገር እንድናስብበትና እንድናጠናው፤ የበለጠ ግልጽነት ባለው ሕግ እንድናስቀምጠው የሚገፋ ይመስለኛል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ይህንን ጉዳይያ ያካተትኩበት ዋናው ምክንያት ግን ለግብጾች ከገባነው ስምምነት ያለ ምንም ሕጋዊ ማሻሻያ መውጣታችን ለችግራችን አስተዋጽኦ ይኖረው ይሆን ለማለትም ነው፡፡ ምክንያቱም ግብጾቹ እንዲፈጸም ይጠብቁ የነበሩ መሆኑን ከሚከተለው ታሪክም መረዳት ይቻላልና፡፡  
ፍልሰተ ፓትርያርክ ወምንታዌ ሲኖዶስ
ከግብጾች ስንወጣ ጉዳዩ በዚህ መልክ የተቋጨ ቢሆንም የስምምነቱ ትርጉም ግን በተለይ ወደ እኛ ቤተ ክርስቲያን በበቂ ሁኔታ መጥቶ ነበር ለማለት የሚያስቸግር ይመስለኛል፡፡ ይህን የሚጠቁመው አቡነ ባስልዮስ አልፈው አቡነ ቴዎፍሎስ ሲተኩ በሹመቱ ላይ ያጋጠመው አለመግባባት ነበረ፡፡ የመጀመሪያው ያጋጠመው ችግር ሹመቱ መቼና የት ይፈጸም የሚለው ጉዳይ ነበረ፡፡ ግብጾች ስምምነቱ የሚያስረዳው፤ የግብጹ ፓፓ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛው መንፈሳዊ አባት ስለሆነ ሹመቱ የሚፈጸመው በግብጹ ፓፓ እንደ አቡነ ባስልዮስ ካይሮ ላይ ነው ሲሉ፤ ኢትዮጵያውያን ደግሞ አዲስ አበባ ላይ በራሳችን እጅ ነው እንጂ እንግዲህ ድጋሚ እጅ የምንነሣበት ጉዳይ አብቅቷል ይላሉ፡፡  ጊዜውን በተመለከተም በአጋጣሚ የግብጹ ፓፓ ከአቡነ ባስልዮስ ቀድመው አርፈው ስለነበረ ግብጾች ቀድሞ ፓፓው ይመረጥ ይሾምና ከዚያ እንደ ሥርዓቱ በፓፓው የኢትዮጵያው ፓትርያርክ ግብጽ መጥቶ ዋናው መንበር ያለበት ካይሮ ላይ ይሾማል ሲሉ ኢትዮጵያውያኑ ግን የፓፓውንም ሹመት አንጠብቅም፣ ቀድመን እንሾማለን ፣ ቦታውም አዲስ አበባ ነው ብለው ክርር አሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የግብጹ አቃቤ መንበር በሁኔታው ተስማሙ፡፡ መርሐ ግብሩ ሲነደፍ ግን ኢትዮጵያውያኑ ለግብጻውያኑ ልክ እንደ ሌሎቹ ተጋባዥ አብያተ ክርስቲያን  የ5 ደቂቃ ብቻ የጸሎት መርሐ ግብር መያዛቸውን እንጂ የተለየ ፕሮግራም እንዳልተያዘላቸው አሳወቁ፡፡ ግብጾቹ ይህን ሲያውቁ በነገሩ ተናድደው ይህማ ከሆነ አንገኝም አሉ፤ በዚህ ጊዜ ንጉሠ ነገሠቱ ሽምግልና ገብተው የጸሎት ጊዜውን 30 ደቂቃ ያስደርጉላቸውና ለመገኘት ይስማማሉ፡፡ ጊዜው ይርዘም የሚለው ዋናው መልእክት ግን ሹመቱን የምንሰጠው እኛ ነን፤ ሙሉ በሙሉ ራሳችሁን እንድትችሉ አልተስማማንም ለማለት እንደነበር ከላይ ቀድመን ከገለጽነው ለመረዳት ይቻላል፡፡ በሹመቱ ሰዐትም ራሱን የቻለ ውዝግብ ይከሰታል፡፡ ብቻ ነገሩ እንደሆነው ሆኖ ይፈጸማል፡፡ ከዚያ ወዲህም በአቡነ ቴዎፍሎስ መገደል ምክንያት እንደተለያየን ቀረን፤ የስምምነቱ ይዘትም ተረሣ። ስማችን ግን እንደዚያው “ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ” በሚለው ብሔራዊነት ያነገበ  መልክአ - ምድራዊ መገለጫ ይዞ እንደጸና ቀረ፡፡ ሊቃነ ጳጳሳትን ከኢትዮጵያ ውጭ መሾሙን ግን ከካሪቢያን እስከ አውስትራሊያ፣ ከእንግሊዝ እስከ ደቡብ አፍሪካ ቀጠልንበት፡፡ ስማችን ግን አሁንም ያው “ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳ ዘኢትዮጵያ” ብቻ መሆኑ አንድ ነገር እየጠቆመ ተቀምጧል፤ ሲያስቡት ያስገርማል፡፡   
በአንድ ሀገር በአንድ ዘመን፣ ባለ ሁለት ፓትርያርክ የመሆን ነገር
ከዚሁ አስቀጥለንም (ባለፈው ጊዜ ሲኖዶሳችን የቀኖና ጥሰት ተፈጽሟል ሲል እንደገለጸው) የአቡነ ቴዎፍሎስ ዕረፍት ሳይረጋገጥና ሳይታወጅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ተሾሙ፡፡ እርሳቸው ሲያርፉ ደግሞ አቡነ መርቆሬዎስ፡፡ በንጉሠ ነገሥቱ ምርጫና ፈቃድ ግብጻዊ ፖፑ አጽድቆት በመሾም የተጀመረው የኢትዮጵያ ፕትርክና፤ በደርግ ዘመንም በእርሱ ፈቃድ በራሳችን መርጠን ወደ መሾም መጣን፡፡ ሆኖም የመንግሥትን ተጽእኖናና ጣልቃገብነት በሕግም በአሠራርም በመንፈስም ሳንቃወመውም ሳንገራውም ቀጠለ። የመንግሥት ለውጥ ሲከሰትም እንደገና ሌላ ችግር ጨምሮ መጣና አዲስና ያልተለመደ ችግርን ይዞ ብቅ አለ፡፡ ነባሩን ፓትርያርክ አሰድዶ አዲስ አስሾመ። በዚህ ምክንያት ሁለት ፓትርያርክና ሁለት ሲኖዶስ ተፈጠረና ስንወዛገብ ቆየን፡፡ ይህም በእግዚአብሔር ቸርነት ባለፈው ዐመት በዕርቅና በስምምነት ተቋጨ። ስምምነቱም ሁለቱንም በፓትርያርክነት ተቀብሎ ቀድመው ለተሰየሙት የመዐርግ ቅድምናውን ሰጥቶ ሁለተኛውን አስከተለ፡፡ ጥያቄው የሚጀመረው እዚህ ጉዳይ ላይ ነው ማለት ነው። ከላይ ያነሳነው ጥያቄም ከዚሁ አጭርና በደንብ ያልተጠና ልምዳችን ተወለደ። ወደፊት ሊፈጥር የሚችለውንም ችግር መናቅ ደግሞ አግባብ መስሎ አልተሰማኝም፡፡ ስለዚህም ቀደም ብሎ መወያየቱ ሳይሻል አይቀርም አልኩና አነሣሁት። ጥያቄው ግልጽ ነው፤ እንዴት በአንድ መንበር ሁለት አባት በአንድ ጊዜ ሊኖረን ይችላል የሚል ነውና፡፡ በርግጥም ነገሩ ሊያስጠይቅ የሚችል ነው፡፡
በእኔ መረዳት ሁለቱን አባቶች በአንድ ወቅት ፓትርያርክ ብሎ መቀበልን ስሕተትና የማይታሰብ አድርጌ አልወስደውም፡፡ ሆኖም ቢደረግ ኖሮ የምለው ተጨማሪ ነገርም ይኖረኛል፡፡ ከላይ ረዥም ትረካ ጋር የነገሩን የመነሻ ሰነድ ለመዳሰስ የፈልግሁትም ለዚህ ነውና፡፡  ነገር ግን ዕርቁ ከመፈጸሙ በፊት ለጠየቁኝ አንዳንድ አካላት ሀሳቤን ለማስረዳት እንደሞከርኩት አንድ ነገር ብቻ በኅሊና ውስጥ ከሚኖር መረዳት (Personal understanding) ይልቅ ወደ ሰነድነትና ወደ አሠራር ግልጽ ሆኖ መውጣት ነበረበት ባይ ነኝ። ለምሳሌ አሁን ያለው የቤተ ክህነቱ ዐሠራር እንዳለና እንደተጠበቀ ሆኖ  የአቡነ መርቆሬዎስ ላይ “ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ” የምትለዋን ቀንሶ መተው ወይም ደግሞ “ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ” የሚለው ላይ “ወለካልዓን ዘበሐውርት” የሚል ቢጨመር የተሻለ ግልጽ ሊሆን ይችል ነበር፤ ግራ መጋባቱንና ውዝግቡንም ሊቀንሰው ይችል ነበር ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱ ደግሞ ከላይ በሰፊው በግብጹ ፓፓና በኢትዮጵያው ፓትርያርክ ላይ ለኢትዮጵያውያን ሁለተኛ የሚደረገውን “ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት” (ዘኢትዮጵያ ከሚለው የቦታ አመልካች በራሳችን) በመጨመር አንድነቱን በምስጢር እንዳጸኑት፣ አሁንም ይህን የመሰለ ተጨማሪ ቅጽል ቢደረግ ኖሮ የበለጠ ግልጽነት ይኖረዋል ባይ ነኝ፡፡ ይልቁንም ደግሞ እንዴት ሁለት አባቶች በአንድ መንበር ላይ የሚለውን ለሚያነሱ  ሰዎች፣ ቢያንስ እነርሱ በሚያስቡት ወይም በሚገምቱት መንገድ እንዳልሆነ ግልጽ ሊያደርግላቸው ይችል ነበር፡፡
በነገራችን ላይ አርመንና ሌሎችም እንደኛ ዐይነት የቆየ ችግራቸውን የፈቱትም በዚሁ መንገድ ነበር፤ አንዱን ካቶሊኮስ ብቻ ብሎ በተወሰነ የመልክአ ምድር ላይ በመሰየም ማለት ነው፡፡  በርግጥ በአሁኑ ጊዜ የአርመን ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ መዋቅር ከእኛም የተለየ ነገር ያለው መሆኑን አስቀድሞ መገንዘብ ይገባል፡፡ በአርመን ዘንድ ከፍተኛው የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ መዐርግ ፓትርያርክ የሚለው ሳይሆን “ጠቅላይ ፓትርያርክና ካቶሊኮስ” (Supreme Patriarch and Catholicos of all Armenians) የሚለው በአንድነት ነው፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ያለው ካቶሊኮስ ብቻ የሚባለው ነው፡፡  ከዚያም ፓትርያርክ የሚባል ሦስተኛ መዐርግ ለብቻው አላቸው። ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ ከሊቀ ጳጳስ ከፍ የሚል ፕራይሜት (Primate) የሚባል መዐርግ አላቸው። ይህም ልዩነታቸውን ሲያስወግዱ ያስተካከሉበት መንገድ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በአሁኑ ጊዜ  ያሏቸው ከፍተኛ አባቶች ሁለት ካቶሊካይ (ካቶሊኮስ የሚለው በብዙ ቁጥር) ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ካረኪን ካልዐይ (Karekin 11) የመላው አርመኖች ጠቅላይ ፓትርያርከና ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት (Supreme Patriarch and Catholicos of all Armenians) ሲሆኑ ሁለተኛው ደግሞ መቀመጫቸውን በሊባኖሷ አንቴሊያስ ያደረጉት የታላቋ ኪልቅያ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት (Catholicos of the Great House of Cilicia) የሆኑት አራም ቀዳማይ  (Aram 1) ናቸው፡፡ ከእነዚህ ቀጥሎ ደግሞ ከፍተኛ ፓትርያርክ ብቻ የሚል መዐርግ ያላቸው ሌሎች ሁለት አባቶች አሏቸው፡፡ እነርሱም በቁስጥንጥንያ የአርመን ፓትርያርክና በኢየሩሳሌም የአርመን ፓትርያርክ ናቸው፡፡ ይህ ማለት ኦርቶዶክሳዊ ትውፊትን እንደጠበቁ፣ የተሻረ ቀኖና ከነበረ በዚያ ንስሐ ገብቶ አሠራርን አስተካክሎ  መዋቅርንም ጠብቆ መሔድ ይቻላል ማለት ነው፡፡    
በእኛም ሁኔታ ለምሳሌ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ተዘዋውረው በሚሠሩበት ሁኔታ ላይ ቢሆኑ ኖሮ፣ በእርሳቸው መዐርግ ላይ  ወይም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ መዐርግ ላይ “ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ላዕለ (በውስተ) ካልዓን በሐውርት” የሚል ዐይነት ጨምሮ ከኢትዮጵያ ውጭ በመላው ዐለም ያሉትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ጳጳሳት በሙሉ በቀዳሚነት ለብቻቸውም ሁሉ ሊሰበሰቡ ከሚያስችል አስተዳደራዊ ሥርዓት ጋር መስጠትና መንበሩንም እንደ ኢየሩሳሌም ባለው ቦታ ላይ አድርጎ መወሰን ይቻል ነበር ማለት ነው፡፡ ይህም ካልሆነ ደግሞ አሁን ባሉበት ሆነው በአጠራር የሹመት ቅደም ተከተላቸውን የተከተለ የመዐርግ አመልካች ነገር መጨመር ይቻል ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን “ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ላዕለ ኢትዮጵያ ወለኩሎን ዘበሐውርት” ብሎ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን ደግሞ እስካሁን የተለመደውን በመስጠት ቢጠሩ ነገሩን ግልጽ ያደርገው ይመስለኛል።  በነገራችን ላይ የግሪክ ኦርቶዶክስም በኢየሩሳሌም የምትሾመውን አባት አሁንም ፓትርያርክ ነው ብላ የምትጠራው፡፡ ስለዚህ ዋናው አሠራሩ፣ ምንነቱን ግልጽ የማድረግ ጉዳይ እንጂ ፈጽሞ የማይቻል የሚባል አይደለም የምለው ለዚህ ነው፡፡
ከላይ ከብላታ መጽሐፍ በመርህ ደረጃ የተመለከትነውም እኮ በኢትዮጵያና በግብጽ መካከል በተደረገው ስምምነት፤ ኢትዮጵያም ሆነ ግብጽ ሁለት ሁለት ፓትርያርኮች የነበሯቸው መሆኑን ነው፡፡ ልዩነቱ አንዱ በአዲስ አበባ ሆኖ ኢትዮጵያውንን ብቻ እንዲመራ መታሰቡ ነበር፡፡ ስለዚህ አሠራራችን ግልጽ ማድረግ ከመጠየቁ በቀር ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያኑ ይፈቅዳል ወይም አልተፋለሰም ማለት ነው፡፡  በአሁኑ ወቅት ለእኛ ነገሩን ለመረዳት ያከበደብን  በኢትዮጵያ አቡነ ባስልዮስ ሲሾሙ፣ የግብጹ ፓፓ የበላይ አባትነቱ የቀረ ስለመሰለን ነው አንጂ ሰነዱ የሚለው ግን ከፍተኛ መንፈሳዊ አባታችን የነበረ መሆኑን ነውና፡፡ አቡነ ባስልዮስን ቀብቶ የሾመውም ሆነ በኋላም ግብጾች አቡነ ቴዎፍሎስን ቀብተን የምንሾመው እኛ ነን ያሉት ስሜታቸው ወይም ስለ ስምምነቱ የነበራቸው መረዳት ይህ ስለነበረ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህ የብላታ መጽሐፍስ ለ55 ዐመታት ያህል ተደብቆና ተረስቶ ከኖረ በኋላ በፈቃደ እግዚአብሔር ዘንድሮ የታተመው፣ ይህንን ችግር ለመፍታት ወይም በዚህ ጉዳይ ላይ ያለንን ግርታ ለማጥራት ይሆን? መጽሐፉ በርግጥ ከዚህም የሚያልፉ ለምርምር የሚጋብዙ ብዙ ጉዳዮችን ይዟል፡፡
እስካሁን ከእነጉድለቱ የመጣንበት እንዳለ ሆኖ የወደፊት መንገዳችንን አቃንተንና አስተካክለን ለመሔድ ለሚደረገው ጥናትና ውይይትም የሚኖረው ጠቀሜታ እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ እስኪ አንብቡትና በሚጠቅም መንገድ እንወያይበት፡፡ በሚቀጥለው ደግሞ ከዚሁ መጽሐፍ በመነሣት ስለ ግብጾች የሚነገረውን ፖለቲካዊ አገላለጽ (በአሉታም ሆነ በአዎንታ) ለማቅረብ እመኛለሁና ጸሎታችሁ አይለየኝ፡፡ ምክንያቱም ከእነርሱ ሳንወጣ ረጂም ዘመን የቆየንበትንም ሆነ የወጣንበትን ሂደት በአብዛኛው ከምንሰማው ፖለቲካዊ አቀራረብ ጸድተን ብናየው፣ ለቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ይሰማኛል፡፡ ሰላም ተመኘሁ!!

Read 2007 times