Saturday, 24 November 2018 12:15

የ”አርበኞች ግንቦት 7” ራዕይ፣ ተስፋና ፈተና

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)


    (የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊው ቃለ ምልልስ)

   • የጀርመን ህገ መንግስት፤ የፌደራል ስርአቱን ለማፍረስ መወያየት እንኳ አይፈቅድም
• ህገ መንግስታችን የሰራነውን ቤት በፈለግን ጊዜ ለማፍረስ የሚፈቅድ ነው
• የፌደራል ስርአትን እንፈልጋለን፤አሁን ያለው አይነት ግን አይደለም
• ነፃ የዲሞክራሲ ተቋማት እውን ሆኖ ማየት ትልቁ ዓላማችን ነው

አርበኞች ግንቦት 7 ወደ ሃገር ቤት ከተመለሰ በኋላ  ምን አይነት እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ነው?
የመጣነው መስከረም መጀመሪያ ላይ ነው። ከሁለት ወር በላይ ሆኖናል፡፡ እንደመጣን በአገር ውስጥ ካሉ አባሎቻችን፣ ደጋፊዎቻችን እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች ካለው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የመመካከር፣ ፕሮግራማችንን የበለጠ የማስተዋወቅ ስራ ስንሰራ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ በሚኖረን ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ያለንን እቅድ በተመለከተም ስንነጋገር ቆይተናል። እንዴት ፓርቲ እንመስርት? ፓርቲ ስንሆን ምን አይነት አደረጃጀት ይኖረናል? በሚለው ላይም ከደጋፊና አባሎቻችን ጋር ተመካክረናል። እንደሚታወቀው፤ አርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ነው እንጂ ፓርቲ አይደለም፡፡ አንድነት፣ ዲሞክራሲ፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ፍትህ በሚሉ አምስት እሴቶች ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ ነው እንጂ የፖለቲካ ፓርቲ አይደለም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ አይደለም ማለት የፖለቲካ ፕሮግራም የለውም፣ የኢኮኖሚ ፕሮግራም የለውም፣ የተፃፈ ፖሊሲ የለውም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብን አስቀድሜ በጠቀስኳቸው አምስት እሴቶች ላይ ማስተባበር ነበር ስራችን፤ ያ ተሳክቶልናል፡፡ ወደ ሃገር ቤት ከገባን በኋላ ግን የፖለቲካ ፓርቲ መሆን አለብን ብለን ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ ምስረታውን እውን ካደረግን በኋላ እንደ ማንኛውም የተቃዋሚ ፓርቲ፣ በምርጫ ቦርድ ቀርበን እንመዘገባለን ማለት ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ መሆን ነው አሁን ትልቁ ስራችን፡፡
አርበኞች ግንቦት 7 ወደ ፖለቲካ ፓርቲነት የሚለወጠው ብቻውን ነው ወይስ ከሌሎች ጋር ይዋሃዳል?
አርበኞች ግንቦት 7 ብቻውን ነው ወደ ፖለቲካ ፓርቲነት የሚለወጠው ወይስ ከሌሎች ጋር ይዋሃዳል የሚለውን እየመከርንበት ነው። በእርግጥ አርበኞች ግንቦት 7 ከዚህ በኋላ ከሌሎች ጋር ውህደት አይፈፅምም፡፡ ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ድርጅት ጋር ከዚህ በኋላ አንዋሃድም፡፡
ለምን? ምክንያታችሁ ምንድን ነው?
አርበኞች ግንቦት 7 በመዋሃድና ህብረት በመፍጠር ብዙ ልምድ አለው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ ስንሆን ወይም ስንዋሃድ፤ የሚዋሃዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራር ያዋጣሉ፡፡ የስም ውዝግብ ውስጥ ይገባሉ፤ የፕሮግራም ጭቅጭቅ ውስጥ ይገባሉ፡፡ የሚቀጥለው ትግል የሚፈልገው ግን ጠንካራ አመራር ነው፡፡ ጠንካራ ድርጅት ነው። በተለይ ጠንካራ አመራር ደግሞ በመዋጮ አይመጣም፡፡ የፓርቲው አባላት ከታች ወደ ላይ ተገንብተው ካልመጡ በስተቀር መሪዎች በመዋጮ መምጣት የለባቸውም የሚል ጠንካራ አቋም አለን። በራሳችን ከተንቀሳቀስን በምንም ሳንጨቃጨቅ፣ ከታች ወደ ላይ መምጣት እንችላለን፡፡ ከዚህ በፊት በውህደት በኩል ያየናቸው በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ስለዚህ አሁን ተመልሰን ወደዚያ ውስጥ አንገባም፡፡ አሁን አርበኞች ግንቦት 7 ከሚባለው ንቅናቄ ጋር አብሮ ፓርቲ መመስረት የሚፈልጉ ሰዎች ሊቀላቀሉን ይችላሉ፡፡ እኛ እየሰራን ያለነው ከታች ከወረዳ ጀምሮ የሚመጣ የፓርቲ መዋቅር እንጂ ከላይ ወደ ታች የሚሄድ አይደለም፡፡ የፖሊሲና የፖለቲካ ፕሮግራም እያዘጋጀን ነው። እኛ ፖሊሲያችንና የፖለቲካ ፕሮግራማችንን ማምጣት የምንፈልገውም፣ ከህዝባችን  ማህበራዊ መሰረት ነው እንጂ ዝም ብለን ሌላው የተከተለውን አንከተልም፡፡
እናንተ የምትመርጡት የፖለቲካ መንገድ የትኛው ነው?
እርግጥ ፕሮግራማችን በርዕዮተ ዓለም መቃኘት አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ማህበረሰብ ምን ይመስላል? የሚለውን ያገናዘበ መሆን አለበት፡፡ ሁሉ ሞልቶለት ተሞላቆ የሚኖር ትንሽ ማህበረሰብ አለ። በሌላ በኩል ደግሞ በድህነት የሚማቅቅ ትልቅ ማህበረሰብ አለ፡፡ በእነዚህ ሁለት የማህበረሰብ ክፍሎች መካከል ያለውን ትልቅ ልዩነት በምንድን ነው የምናጠብበው? እሱን ለማጥበብ እኛ ማስፈን አለብን ብለን የምናምነው ማህበራዊ ፍትህን ነው፡፡ በማህበራዊ ፍትህ ላይ የሚያምን ወይም ማህበራዊ ፍትህን መርሁ አድርጎ የሚከተል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ይኖረናል ማለት ነው፡፡ መንግስት የሚያወጣቸው የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲዎች በቀጥታ የሚያተኩሩት ማህበራዊ ፍትህ ላይ ነው፡፡
“ማህበራዊ ፍትህ” ሲባል ምን ማለት ነው?
ማህበራዊ ፍትህ ሲባል የሃብት ክፍፍልን ይመለከታል፡፡ ይሄ ፖሊሲ ተሞክሮ ውጤታማ የሆነባቸው የዓለም ሃገሮች አሉ፡፡ ስዊድንን ጨምሮ በርካታ ስኬታማ አውሮፓውያን በዚህ መንገድ  የተራመዱ ናቸው፡፡ እርግጥ የአውሮፓ ማህበረሰብና የኛ ይለያያል፡፡ ይሄንንም ልዩነት አጢነን ነው የምንከተለውን የፖለቲካ መስመር እየመራን ያለነው። ከኛ ጋር ፓርቲ መፍጠር የሚፈልግ አካል፣ በዚህ የሚያምን መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ ኢህአዴግን ብንመለከት፣ ገበሬውን ነው ታሳቢ የማደርገው ይላል። ግን 27 ዓመት ስሙ የሚጠራው ገበሬ፤ እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ አላመጣም፡፡ እኛ ይሄን ክፍተት እንዘጋለን ብለን ነው የምናምነው፡፡ በማህበራዊ ፍትህ ላይ የሚመካ የፖለቲካ ፕሮግራም በተለይ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ፕሮግራም ሲኖረን ነው፣ በማህበረሰቡ መካከል የተፈጠረውን የገቢ ልዩነት ማጥበብ የሚቻለው፡፡ ይሄ ልዩነት ካልጠበበ ወጣቱ፣ በሀገሩ ተስፋ በማጣት፣ የውጪ ተመልካች ወይም ስደተኛ መሆንን ማስቀረት አይቻልም፡፡ ወጣቱን ባጣን ቁጥር የወደፊቱን ሃገራችንን በምን እንደምንገነባ አናውቅም፡፡
እኔ ከአዲስ አበባ የለቀቅሁት ከ24 ዓመት በፊት ነው፡፡ ድሮ የማውቀው ለማኝ በአብዛኛው አካል ጉዳተኛ ነበር፡፡ ዛሬ ከ24 ዓመት በኋላ ተመልሼ ሳየው ግን ጤነኛ እጅ እግር ያለው ለማኝ በየመንገዱ ይታያል፡፡ ህፃናት ለማኞች በዝተዋል። ይሄ ኢ-ፍትሃዊ  የገቢ ክፍፍል ውጤት ነው፡፡ ፓርቲያችን ሲመሰረት በዋናነት ይሄን የሀገሪቱን ችግር በመገንዘብ ነው። አሁን ስም አልጠቅስም፤ በዚህ መርህ መሰረት ከአንዳንድ ፓርቲዎች ጋርም አብረን እየሰራን ነው። እነሱም ያላቸውን የፓርቲ መዋቅር በዚህ መልኩ ሲያጠናከሩ፣ የተሻለ የፓርቲ ቁመናዎች ይፈጠራሉ፡፡ እነዚያ ፓርቲዎች ከወረዳ ጀምረው ራሳቸውን እንደገና እያጠናከሩ ከመጡ በኋላ ኮንግረስ ወደ መፍጠሩ ልንሄድ እንችላለን፡፡ ኮንግረሱ አንድ ጠንካራ ፓርቲ ይመሰርታል፡፡ ያን ጊዜ  አርበኞች ግንቦት 7 በይፋ ይከስማል፡፡
የምትከተሉት ርዕዮተ ዓለም ሶሻል ዲሞክራሲ  ነው ማለት ነው?
ሶሻል ዲሞክራሲን፣ ለኢትዮጵያ በሚመች መልኩ ነው፡፡ ያ ማለት ማህበራዊ ፍትህ ነው። ሶሻል ዲሞክራሲ በእርግጥ የሚያምነው በማህበራዊ ፍትህ ነው፡፡ ስለዚህ ሶሻል ዲሞክራሲን ለኢትዮጵያ በሚያመች መልኩ ስናስቀምጠው፤ “ማህበራዊ ፍትህ” የሚለው ይስማማዋል፡፡ የሶሻል ዲሞክራሲ አካል ነው። ግን የኛን ሃገር ሁኔታ  ከግምት የሚያስገባና የኛ ሀገር እውነታን  አመልካች እንዲሆን ስለምንፈልግ፣ ማህበራዊ ፍትህ ላይ የተመሰረተ ፓርቲ ይሆናል። “ማህበራዊ ፍትህ” የሚለው፤ ፓርቲው የቆመበትን መርህ በግልፅ እንዲያመለክት እንፈልጋለን፡፡
የትኛው የህብረተሰብ ክፍል ነው፣ የፖለቲካ ፕሮግራማችሁ መሠረት?
በጥቅሉ ካየነው የገበሬውና የሰራተኛውን መደብ ነው፡፡ በዚህ ስር ወጣት ገበሬ፣ ወጣት ገበሬ ሴት ይኖራሉ፡፡ በጥቅሉ ግን ገበሬውና ሰራተኛው ነው፣ የኛ የፖለቲካ መሰረት የሚሆነው። በአጠቃላይ የገበሬውና የሰራተኛው መደብ በኛ ሃገር ሁኔታ ሲታይ፣ ከ85 እስከ 90 በመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያን ህዝብ ክፍል ይወክላል። ከዚያ ውጭ ያለው ልሂቁ ነው፡፡ ልሂቁንም ይመለከታል፤ ነገር ግን አብዛኛው ትኩረቱ በገበሬውና ሰራተኛው ላይ ነው፡፡ የገበሬውን ገቢ ማሳደግ በተቻለ ቁጥር የሰራተኛው ቁጥርና አቅምም እያደገ ይሄዳል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የግብርናውን ዘርፍ እስካልለወጥን ድረስ ኢንዱስትሪ አሳድጋለሁ ማለት አስቸጋሪ ነው። የሚመሰረቱት ኢንዱስትሪዎች ጥሬ እቃቸውንና የሰው ኃይላቸውን ከሃገር ውስጥ እንዲጠቀሙ ነው የሚፈለገው፡፡ ስለዚህ ግብርናውን ማሳደግ አማራጭ የሌለው ነገር ነው፡፡ ለዚህ ነው ትልቁ ትኩረታችንን  ገበሬውና ሰራተኛው ላይ ያደረግነው፡፡
አሁን በሀገሪቱ ላይ የገነነው በማንነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አካሄድ ነው፡፡ እናንተ ደግሞ በዜግነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካን ነው እውን እናደርጋለን የምትሉት፡፡ በአሁኑ ተጨባጭ ሁኔታ የሚሳካላችሁ ይመስላችኋል?
የዜግነት ፖለቲካ ኢትዮጵያ ውስጥ አማራጭ የለውም ብለን እናምናለን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን የተለያዩ የፖለቲካ መስመሮች አሉ፡፡ ነገር ግን ሁሉንም ብንመረምራቸው በሁለት ጎራ ብቻ የቆሙ ናቸው። በማንት ላይ የተመሰረተው አንደኛው ጎራ ነው፡፡ ሌላኛው በዜግነት ላይ እምነት ያለው ነው። እነዚህ ሁለት ጎራዎች ናቸው ያሉት በተጨባጭ። ከእነዚህ ጎራዎች ደግሞ ብዙ ኃይል ያሰባሰበው የማንነት ፖለቲካ ነው፡፡ አሁን ሃገሪቱ ውስጥ የምናየው የእነዚህን ሁለት ጎራዎች ግጭት ነው። የወደፊቷ ኢትዮጵያም ከእነዚህ ሁለት ጎራዎች የድርድር ውጤት ውጪ ልትሆን አትችልም። የወደፊቷ ብሩህ ኢትዮጵያን የምንፈልግ ከሆነ፣ ከነዚህ ሁለት ኃይሎች ድርድር የሚመጣው ውጤት ወሳኝ ነው፡፡ እኛ የምንፈልገውን የዜግነት ፖለቲካ በሌሎች ላይ በኃይል መጫን አንፈልግም። እነሱም የማንነት ፖለቲካን በእኛ ላይ እንዲጭኑብን አንፈልግም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሁለት ኃይሎች ወደዱም ጠሉም ተደራድረው የወደፊቷን ኢትዮጵያ መፍጠር አለባቸው፡፡ ከእነዚህ ሁለት ኃይሎች ውጪ የወደፊቷን ኢትዮጵያ መፍጠር የሚችሉ ኃይሎች በፖለቲካ መድረኩ ላይ አናይም። ያሉት ሁለቱ ብቻ ናቸው፡፡ ስለዚህ የወደፊቷን በሩህ ኢትዮጵያ ማግኘት የምንችለው በእነዚህ ሁለት ጎራ ልሂቃን ድርድር ነው፡፡ ሁለታችን ተደራድረን መሃል ላይ ተገናኝተን የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ እንፈጥራለን ብዬ አምናለሁ፡፡ መሃል ላይ ተገናኝተን የምንፈጥራትን ኢትዮጵያ ደግሞ አናፈርሳትም፤ በፍቅር ነው የሰራናት ማለት ነው። እኔ አብዛኛውን እድሜዬን የኖርኩት በአሜሪካ ነው፡፡ አሜሪካኖች ሊበራሊዝም ላይ የተመሰረተ ግለሰብ ላይ ያተኮረ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ነው የሚከተሉት፡፡ በእርግጥ ሊበራሊዝም የቡድን መብትን አይመለከትም፡፡ እኛ ደግሞ የዜግነት ፖለቲካን ስናራምድ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ብዝሃነት ያለው በሃይማኖት፣ በብሄርና በማንነት ፖለቲካ የተከፋፈለ መሆኑን አገናዝበን ነው፡፡ እርግጥ ሊበራሊዝምን በዚህ በተከፋፈለ ማህበረሰብ ውስጥ ዝም ብለን ብናመጣው አስቸጋሪ ነው። ዲሞክራሲን ሊያሰፍን ይችላል፤ ግን 27 ዓመት የተሰበሰበውን የቡድን ፖለቲካ በቀላሉ አይሰብረውም፡፡ ስለዚህ የግለሰብ መብትን ከቡድን መብት ጋር እኩል ማክበር የተሻለው አማራጭ ነው፡፡ ማንነት ዛሬ ከምግብ በላይ ተፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህ ይሄን ማክበር የሚችል ሃሳብ መምጣት አለበት፡፡ የግለሰብ መብት እስከተከበረ ድረስ የቡድን መብት ይከበራል የሚለው አባባል አሁን የሚሰራ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ሊበራሊዝምን ለኢትዮጵያ ስናስብ፣ ማንነትን ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆን አለበት፡፡
ህገ መንግስቱ መሻሻል አለበት የሚሉ ወገኖች አሉ። የእናንተስ አቋም በዚህ ላይ ምንድን ነው?
አንዳንድ በፍጥነት መሻሻል ያለባቸው ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች አሉ፡፡ የዜግነት ፖለቲካን ለማራመድ አስቸጋሪ ነው - ህገ መንግስቱ፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክን የመሰረቱት ብሔር ብሔረሰቦቿ ህዝቦቿ ተስማምተው ነው ይላል፡፡ ይሄ ምን ማለት ነው? የፌደራሊዝም ፍልስፍናን በደንብ የተረዳ ሰው፤ ለዚህ የህገ መንግስቱ ድንጋጌ ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ አሁን ያለችው ኢትዮጵያ ቀደም ሲል የራሳቸው ሉአላዊ ሃገሮች የነበሩ ሃገሮች ተሰባስበው የፈጠሯት አድርጎ ነው የሚያስቀምጠው፡፡ ይሄ እውነት አይደለም። የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ስርአት የተመሰረተው እርስ በእርስ በመጠራራት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ከ2 ሺህ አመታት በላይ ሉአላዊ የነበረች ሃገር ነች፡፡ ሕገ መንግስቱ ግን በ1983 የተለያዩ ሉአላዊ ሃገሮች ወደ አንድ የጋራ መድረክ መጥተው ተስማምተው እንደመሰረቷት አድርጎ ነው ያስቀመጠው፡፡ “ተስማምተው ፈጠሯት” ይላል፤ ህገ መንግስቱ፡፡ አንቀፅ 39 ደግሞ ያልተስማማ መገንጠል ይችላል ይላል፡፡ ይሄ ማለት የሰራነውን ቤት በፈለግነው ጊዜ ልናፈርሰው የምንችለው ነው ማለት ነው። ሃገር እንደዚህ ሊኖር አይችልም፡፡ የጀርመን ህገ መንግስት፤ ፓርላማው የፌደራል ስርአቱን ለማፍረስ መወያየት እንኳ አይችልም ይላል፡፡ የኛ ግን የማፍረሻ መንገዱን በዝርዝር ያስቀምጣል። እኛ ከዚህ ህገ መንግስት ጋር አብረን መኖር አንችልም። ለመንግስትም ይሄን አሳውቀናል፡፡ ስለዚህ ህገ መንግስቱ መሻሻል አለበት። የፌደራል ስርአት አፈጣጠሩ ላይም እንደገና መነጋገር ያስፈልገናል። እኛ የፌደራል ስርአትን እንፈልጋለን፤ ነገር ግን አሁን ያለው አይነት አይደለም፡፡
አሁን ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል
በጣም ጤናማ የሆነ ግንኙነት ነው ያለን። እኛ ኢትዮጵያ ውስጥ መረጋጋት መፈጠር አለበት የሚል አቋም አለን፡፡ ያንን በተመለከተ ከመንግስት ጋር ተቀራረብን እየተነጋገርን ነው፡፡ ምን ብናደርግ ነው ከእነዚህ ችግሮች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የምንወጣው በሚለው ላይ እየተመካከርን ነው። ሌላው ከፊታችን ያለው የአገራዊ ምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ ምርጫው እንደከዚህ ቀደሙ የቀልድ መሆን የለበትም። ይሄ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው። የመንግስትን ስልጣን የጨበጠው አካል ተፅዕኖ የማያደርግበት ምርጫ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲካሄድ ማየት እንፈልጋለን። ተቋማት ነፃ እንዲሆኑ እንሻለን፡፡ የጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ መንግስት ቀና ነው፡፡ ነገር ግን ቀናነቱ ወደ ተቋማት መመንዘር አለበት፡፡ አሁን የሽግግር ወቅት ላይ ነን፡፡ አንድ ፓርቲ ብቻውን መርቶ ደግሞ ሽግግር ሊኖር አይችልም፡፡ ስለዚህ አሁን ያለው ሽግግር ውስጥ አርበኞች ግንቦት 7 በተለያዩ አግባቦች ይሳተፋል። ሃገርን በማረጋጋት ድርሻውን እየተወጣ ነው፡፡
በቀጣይ የሃገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ያላችሁ ትንተና ምን ይመስላል?
ብዙ ጊዜ በሃገራችን የለውጥ ታሪክ ውስጥ የምናየው ተስፋ ሲጨልም ነው፡፡ በዚህ ንቅናቄ ውስጥ ያለን ሰዎች፤ ይሄን አዙሪት እንዴት እናቆማለን የሚል ጥያቄን ያነገብን ነን፡፡ የዚህ የቀውስ አዙሪት መቆም እኛ በምርጫ ከምናገኘው ስልጣን በላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የነፃ ምርጫ መሰረት መጣል አለበት ብለን እናምናለን፡፡ ነፃ የዲሞክራሲ ተቋማት እውን ሆኖ ማየት ትልቁ ዓላማችን ነው፡፡ ሃገሪቱ የፕሬዚዳንታዊ ስርአት ነው የሚያስፈልጋት ወይስ አሁን ያለው? አሁን ያለው የፓርላማ ስርአት ጠቃሚ ነው? ይሄ ውይይት የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው፡፡ ሁሉም ህዝብ ያልመረጠው ሰው ነው ጠ/ሚኒስትር የሚሆነው፡፡ ለምን ይሄ ይሆናል? ፕሬዚዳንታዊ ስርአት ይሻለን ይሆን? ፕሬዚዳንታዊ ስርአት ለአምባገነንነት ያጋልጠን ይሆን? የሚሉት ውይይት ያስፈልጋቸዋል፡፡ እንደ ፈረንሳይ ቅይጥ የሆነ ማለትም ጠ/ሚኒስትሩ እና ፕሬዚዳንቱ እኩል ስልጣን የሚከፋፈሉበት እንዲሁም ፓርላማው ጠ/ሚኒስትሩን ካልወደደው ከእነ ካቢኔው ማባረር የሚችልበት ሥርዓት ይበጀን ይሆን? የሚለው በአንክሮ መጠናት አለበት፡፡ የምርጫ ስርአቱ አሁን አብላጫ ድምፅ ነው፡፡ ይሄ ለኛ ምን ጠቀመን? ለምሳሌ እኔ አርሲ ውስጥ ሰርቻለሁ፡፡ አርሲ ውስጥ ሁለተኛው ትልቅ ህዝብ አማራ ነው፡፡ ይሄ ህዝብ አሁን ባለው ፓርላማ ውስጥ የራሱ ድምፅ የለውም፡፡ ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ስርአት ቢሆን ግን የእነዚህ ወገኖች ድምፅ የሚሰማበትን ሂደት ያበጃል፡፡ እነዚህን ጉዳዮች ኢትዮጵያውያን ምሁራን በቅጡ አጥንተው ሊመረምሩት ይገባል፡፡ ዛሬ በባንዲራ ጉዳይ ላይ እንኳን አልተስማማንም። ይሄ ለምን ሆነ? ከላይ ወደ ታች ስለተጫነ ነው፡፡ ለምን በህዝበ ውሳኔ አይፈታም? ይሄ ህዝበ ውሳኔ የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው፡፡  
መቼ ነው የፓርቲያችሁ ምስረታ እውን የሚሆነው?
በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ውስጥ በኢትዮጵያ ጠንካራ ፓርቲ እውን እናደርጋለን፡፡    





Read 2396 times