Saturday, 24 November 2018 12:09

ሰመጉ በመንግሥት የታገደበት 9 ሚ. ብር ገደማ እንዲለቀቅለት ለጠ/ሚኒስትሩ አቤቱታ አቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

መንግስታዊ ያልሆነው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም፣ “የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ” ከ10 ዓመት በፊት በመንግሥት የታገደበት 9 ሚሊዮን ብር ገደማ ገንዘብ እንዲለቀቅለት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በፃፈው ደብዳቤ ጠይቋል፡፡
ላለፉት 27 አመታት በሀገሪቱ ይፈፀማሉ የሚባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመንግስት በሚደርስበት ተጽእኖ ምክንያት በውስን አቅም ሲመረምር መቆየቱን የጠቆመው ሰመጉ፤ በ2001 ዓ.ም የበጐ አድራጐት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅ መታወጁን ተከትሎ፣ በንብ ባንክ፣ በአዋሽ ባንክ፣ በህብረት ባንክና በአቢሲኒያ ባንክ ውስጥ ተቀማጭ የነበረ በድምሩ ስምንት ሚሊዮን ሰባት መቶ ዘጠና ሰባት ሺህ አንድ መቶ ሰማንያ አራት ብር (8,797,184.28) በመንግስት እንደታገደበት ይገልፃል - በደብዳቤው፡፡
በወቅቱ የታገደበትን ገንዘብ ለማስለቀቅ ክስ መስርቶ እንደነበረ አስታውሶ፤ “በዳኝነት ነፃነት እጦት ምክንያት” እንዳልተሳካለት ሰመጉ ጠቁሟል፡፡
በዚህም የተነሳ ተቋሙ ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ችግር በመዳረጉ፣ በ13 ከተሞች ላይ ከነበሩት ጽ/ቤቶች አስሩን ለመዝጋት መገደዱንና ከ80 በመቶ በላይ ሠራተኞቹን ማሰናበቱን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በፃፈው አቤቱታ ጠቁሟል፡፡
እስካሁንም በፋይናንስ እጦት ሳቢያ የተዘጉ ቢሮዎቹን መልሶ መክፈትና ሠራተኞቹን መተካት እንዳልቻለ የጠቀሰው ሰመጉ፤ አሁን ላሉት ከ20 ለማይበልጡ ሠራተኞቹም የወር ደመወዝ ለመክፈል መቸገሩን ገልጿል፡፡
ላለፉት ዘጠኝ አመታት በዚህ መልኩ በከፍተኛ የገንዘብ እጥረት እየተዳከመ ጠቁሞ በአሁኑ ወቅት ህልውናው ጥያቄ ውስጥ መውደቁን በፃፈው በደብዳቤ ገልጿል፡፡
የተቋሙን ህልውና ለማቆየት ያለ አግባብ የታገደበት ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ እንዲለቀቅ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በፃፈው ደብዳቤ የጠየቀ ሲሆን፤ በሀገሪቱ ባለፉት 7 ወራት የሰብአዊ መብትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች የሚበረታቱ እንደሆኑ ገልፆ ቀጣይነት፤ እንዲኖራቸው ሠመጉን የመሳሰሉ ተቋማት መልሰው መጠናከራቸው ወሳኝ ነው ብሏል፡፡
በአንጋፋው ፖለቲከኛና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያምና አጋሮቻቸው ከ27 አመት በፊት የተመሠረተው ሠመጉ፤ እስካሁን ከ150 ጊዜያት በላይ ልዩ ልዩ የመብት ጥሰት የምርመራ ሪፖርቶችን ይፋ አድርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሰመጉ ሊቀ መንበር የህግ ባለሙያውና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አቶ አመሃ መኮንን መሆናቸው ይታወቃል፡፡

Read 7355 times