ዘንድሮ በከፈተችው የራሷ የቴሌቪዥን ጣቢያ እምብዛም ያልተሳካላት ኦፕራ ዊንፍሬይ በበኩሏ ባለፈው አንድ ዓመት ከ165 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያገኘች ሲሆን ከሎፔዝ በመቀጠል የሁለተኛነት ደረጃውን እንደያዘች ፎርብስ አስታውቋል፡፡ የ18 ዓመቱ ጀስቲን ቢበር ባለፈው አንድ ዓመት 55 ሚሊዮን ዶላር የሰበሰበ ሲሆን በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው እየፈጠረ ባለው ተፅእኖ ሦስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተመልክቷል፡፡ ፎርብስ እንደገለፀው ሪሃና በዚሁ የደረጃ ሰንጠረዥ ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ የገባች ሲሆን ባለፈው ዓመት ለገበያ ባቀረበችው አልበሞች የሞቀ ገበያ የተነሳ እንዲሁም “ኒቬያ” እና “ቪታ ኮኮ” በተባሉ ግዙፍ ኩባንያዎች በገባችው የንግድ ውል አራተኛነት ባገኘችው ገቢ አምና መሪ የነበረችው ሌዲ ጋጋ በአራት ደረጃዎች በመውረድ አምስተኛ ስትሆን ሰሞኑን በ”ኤክስ ፋክተር” የታለንት ውድድር በዳኝነት ለመስራት የተዋዋለችው ብሪትኒ ስፒርስ ደግሞ ስድስተኛ ሆናለች፡፡ ሁለቱ አርቲስቶች 52 እና 58 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንዳገኙ ፎርብስ ጠቁሟል፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት በ18 ሚሊዮን ዶላር ዝቅተኛውን ገቢ ያስመዘገበችው ኪም ካርዴይሺያን፤ ዘንድሮ አግብታ በአጭር ግዜ ፍቺ በመፈፀሟ ባገኘችው የሚዲያ ሽፋን ሰባተኛ ደረጃ ስትወስድ፣ በፖፕ ሙዚቃዋ አሜሪካን የማረከችው ኬቲ ፔሪ ስምንተኛ ደረጃ ተሰጥቷታል፡፡ ‹ሚሽን ኢምፖሲብል ፣ ዘ ጎስት ፕሮቶኮል› በተባለው ፊልሙ በመላው ዓለም 700 ሚሊዮን ዶላር ያስገኘው ቶም ክሩዝ፤ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ሲሆን በቲቪ እና በሲኒማ ኢንዱስትሪው በትጋት ተሳትፎ ከ130 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያገኘው ስፒልበርግ በ10ኛ ደረጃ ላይ እንደተቀመጠ የፎርብስ መረጃ ያመለክታል፡፡