Saturday, 19 May 2012 11:20

ጄ. ሎ የሌዲ ጋጋ የዝነኝነት ደረጃ ቀማች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ጄኒፈር ሎፔዝ ባለፈው ዓመት በሌዲ ጋጋ ተይዞ የነበረውን የፎርብስ 100 የዝነኛ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የደረጃ ሰንጠረዥ የአንደኛነት ደረጃን እንደነጠቀች ፎርብስ አስታወቀ፡፡ 42ኛ ዓመቷን የያዘችው ድምፃዊት፤ ተዋናይትና ዳንሰኛ ጄኒፈር ሎፔዝ በገቢ ምንጮቿ መስፋት፤ በሚዲያ ሽፋኗ እና በሶሻል ሚዲያ መድረኮች በጨመረችው ዝና አምና ከነበረችበት ደረጃ በአስደናቂ ሁኔታ 50 እርከኖችን አሻሽላለች፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት 52 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያደረገችው አርቲስቷ፤ በአሜሪካን አይዶል በዳኝነት መስራቷ ወደ ነበረችበት ክብርና ዝና እንድትመለስ አስችሏታል ያለው ፎርብስ፤ “ኮህል” በተባለ የዘመናዊ ፋሽን ልብሶች ምርቷና በታዋቂ ሽቶዋ ተፈላጊነት፣ እንዲሁም በትዊተር እና ፌስ ቡክ ሚሊዮኖችን ወዳጅ በማድረግ እንደተሳካላት ጠቁሟል፡፡ ጄኒፈር ሎፔዝ ከታዋቂው የላቲን ድምፃዊ ኤነሪክ ኢግላስያስ ጋር ዓለምን የምትዞርበት ኮንሰርት ለማድረግ መወሰኗ በ2012 የምታገኘውን ገቢ ከፍ እንደሚያደርግላት ተገምቷል፡፡

ዘንድሮ በከፈተችው የራሷ የቴሌቪዥን ጣቢያ እምብዛም ያልተሳካላት ኦፕራ ዊንፍሬይ በበኩሏ  ባለፈው አንድ ዓመት ከ165 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያገኘች ሲሆን ከሎፔዝ በመቀጠል የሁለተኛነት ደረጃውን እንደያዘች ፎርብስ አስታውቋል፡፡ የ18 ዓመቱ ጀስቲን ቢበር ባለፈው አንድ ዓመት 55 ሚሊዮን ዶላር የሰበሰበ ሲሆን በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው እየፈጠረ ባለው ተፅእኖ ሦስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተመልክቷል፡፡ ፎርብስ እንደገለፀው ሪሃና በዚሁ የደረጃ ሰንጠረዥ ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ የገባች ሲሆን ባለፈው ዓመት ለገበያ ባቀረበችው አልበሞች የሞቀ ገበያ የተነሳ እንዲሁም “ኒቬያ” እና “ቪታ ኮኮ” በተባሉ ግዙፍ ኩባንያዎች በገባችው የንግድ ውል አራተኛነት ባገኘችው ገቢ አምና መሪ የነበረችው ሌዲ ጋጋ በአራት ደረጃዎች በመውረድ አምስተኛ ስትሆን ሰሞኑን በ”ኤክስ ፋክተር” የታለንት ውድድር በዳኝነት ለመስራት የተዋዋለችው ብሪትኒ ስፒርስ ደግሞ ስድስተኛ ሆናለች፡፡ ሁለቱ አርቲስቶች 52 እና 58 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንዳገኙ ፎርብስ ጠቁሟል፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት በ18 ሚሊዮን ዶላር ዝቅተኛውን ገቢ ያስመዘገበችው ኪም ካርዴይሺያን፤ ዘንድሮ አግብታ በአጭር ግዜ ፍቺ በመፈፀሟ ባገኘችው የሚዲያ ሽፋን ሰባተኛ ደረጃ ስትወስድ፣ በፖፕ ሙዚቃዋ አሜሪካን የማረከችው ኬቲ ፔሪ ስምንተኛ ደረጃ ተሰጥቷታል፡፡ ‹ሚሽን ኢምፖሲብል ፣ ዘ ጎስት ፕሮቶኮል› በተባለው ፊልሙ በመላው ዓለም 700 ሚሊዮን ዶላር ያስገኘው ቶም ክሩዝ፤ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ሲሆን በቲቪ እና በሲኒማ ኢንዱስትሪው በትጋት ተሳትፎ ከ130 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያገኘው ስፒልበርግ በ10ኛ ደረጃ ላይ እንደተቀመጠ የፎርብስ መረጃ ያመለክታል፡፡

 

 

 

Read 1190 times Last modified on Saturday, 19 May 2012 11:22