Sunday, 18 November 2018 00:00

የታገሷት “ጥቂት ቀናት” ደስታን ትፈጥራለች!!

Written by  ከወንድወሰን ተሾመ (የማህበራዊ ሳይንስና የስነልቦና ባለሙያ)
Rate this item
(2 votes)

እ.ኤ.አ. ኦገስት 3, 1492 ከፓሎዝ ወደብ (ስፔን) የተነሱት ኒና፣ ፒንታ እና ሳንታ ማሪያ የተባሉት መርከቦች ከያዟቸው ሰዎች መካከል አንድ ራዕይ ያለው ሰው ይገኙበት ነበር፡፡ ይህም ሰው በመርከቦቹ ውስጥ ያሉትን ሰዎች የሚመራ ነበር፡፡ ይህ ሰው አንድ ነገር ያያል - ከባህር ጉዞው ባሻገር የሚገኝን አዲስ አገር!
ከሁለት ወራት የባህር ላይ ጉዞ በኋላ አብረውት የሚጓዙት ሰዎች ጉዞው ሰለቻቸው፣ ኑሮ ተመሳሳይ ሆነባቸው፤ ቅዝቃዜውና ነፋሱ አገረጣቸው፣ ምድርንም ማየት ስላልቻሉ በዚህ  መሪ ላይ ተስፋ ቆረጡና “አጉረመረሙ”፡፡ ይህ ሰው ግን በወጀብ ውስጥ የሚታገስ፣ እሞታለሁ ብሎ የማይፈራ፣ ስለሚያርፍበት ቦታ እርግጠኝነት የሚሰማው አይነት ሰው ነበር፡፡ ማጉረምረማቸውን ሲሰማ በዚያን ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “ጥቂት ቀናት ብቻ ታገሱኝ፤ በእነዚህ ጥቂት ቀናት ምድርን ካላየን በሰይፍ አንገቴን ቁረጡት ከዚያም እናንተ ተመለሱ” አላቸው፡፡ በዚህ ተስማምተው ጥቂት ቀናት እንደተጓዙ ደረቅ ምድር ላይ ደረሱ፡፡  እናም ለወራት ከተቀመጡባቸው መርከቦች ወርደው ወደ አዲሲቷ ምድር ገቡ - ደስታ ሆነ!! ይህ ሰው በአይነ ህሊናው ምድሪቱን አስቀድሞ አይቷት ነበር፤ አብረውት የሚጓዙት ሰዎች ግን በግልጽ በልቦናቸው ስላላዩ ሰለቹ፣ መታገስ አቅቷቸው አጉረመረሙ፡፡ አብረው የጀመሩትን ጉዞ በመሃል ማቋረጥ ፈለጉ፡፡ ይህ ሲመራቸው የነበረው ሰው ክሪስቶፈር ኮሎምበስ ነው፡፡ ዓለም - አሜሪካን አገኘ ብላ እውቅና የሰጠችው፣ እኛም “Christopher Columbus Discovered America” እያልን በታሪክ ትምህርት የምናውቀው ሰው!!
አሁን ያቺ አገር የሁሉም አገር ሆናለች። ከመላው ዓለም የተጓዙ ዜጎች በእኩልነት የሚኖሩባት፣ ከመምረጥ አልፈው ተመርጠው ነጩንም ጥቁሩንም የሚያገለግሉባት፤ በዘርና በትውልድ ቦታ ጦር የማይማዘዙባት፤ በወሰን የማይጋጩባት፤ ቀን ተሌት ከሰው ጋር ሳይሆን ከስራ ጋር እየታገሉ የሚኖሩባት - ክሪስቶፈር ኮሎምበስ ያገኛት አገር!
ባለፈው ህዳር 2 እና 3 (ሰኞ እና ማክሰኞ ዕለት) የሰማናቸው ሰበር ዜናዎች፣ ለብዙ ኢትዮጵያውያን ደስታን የፈጠሩ ነበሩ፡፡ ደስታው የመነጨው በዜጎችና በአገር ላይ ግፍ የፈፀሙ ሰዎች በስልጣናቸው ከፍታ፣ በገንዘባቸው ብዛትና በዘረጉት የክፋት መረብ ተከልለው፣ ከህግና ከፍትህ እንደማያመልጡ የሚያበስሩ ሰበር ዜናዎች ስለነበሩ ነው፡፡ ይህ ቀን እንደሚመጣ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶ/ር ዐቢይና  የለውጡ መሪዎች ያውቁት ነበር - ህልም አላቸውና! ነገር ግን በርካታ ዜጎች መታገስ አቅቷቸው የለውጡን መሪዎች ሲነቅፉና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ውስጥ ሲገቡ ታዝበናል፡፡ ከዶ/ር ዐቢይ አመራር ጋር የጀመሩትን ጉዞ እዚህና እዚያ በሚፈነዱ “ያረጁ አቁማዳዎች” (ከዚህ ቀደም በአዲስ አድማስ ላይ በፃፍኩት ጽሁፍ ያገኙታል) ምክንያት ሊያቋርጡ ዳር ዳር ብለው ነበር፡፡
“የጥቂት ቀናት” ትዕግስት ለተጓዦች አዲስ ጸጋን ያጎናፅፋል፤ ብስራትን ይዞ ብቅ ይላል!! ለመሪውም ህልሙን እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ጥቂት ቀናት ስንት ናቸው? የተጀመሩ ስራዎች እየቀጠሉ መሄዳቸው ከታወቀ ስራዎቹ እስከሚያልቁ ድረስ ያሉትን የተሰሉ ጊዜያት ጥቂት ቀናት ልንላቸው እንችላለን፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ለለውጡ የሚበጅ ነገር ማድረግ ይቻላል፤ የተጀመሩ ሪፎርሞች እንዲፋጠኑ ማገዝ፣ መጨረሻቸው እንዲያምር ሁሉም የበኩሉን አስተዋፅኦ በማበርከት ከሰሪዎቹ ጋር አብሮ መሰለፍ ይጠበቅበታል። ለውጥ ቅፅበት አይደለም፤ ለውጥ ሂደት ነው። በተለይ ውስብስብ በሆነው የኢትዮጵያ ችግር መካከል  መፍትሄዎችን  በአጭር ጊዜ ውስጥ ቁጭ ቁጭ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ማሰብ የአገራችንን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተጨባጭ ሁኔታ ከግንዛቤ ካለማስገባት የሚመነጭ እንደሆነ አስባለሁ፡፡ ይህም ሆኖ የለውጥ መሪዎችና ተጽእኖ ፈጣሪዎች፤ ለውጡን ለማፋጠን ቀን ከሌት መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይ መንግስት ሚስጥራዊ ያልሆኑና በህዝቡ ዘንድ የሚጠበቁ ወሳኝ የሆኑ ለውጦችን (በሁሉም ዘርፎች) የሚጠናቀቁበትን ጊዜ አስቀድሞ ዕቅዱን ቢያሳውቅ፣ለክትትልና ለመረጋጋት ይጠቅማል እላለሁ፡፡
ኢትዮጵያ በጉዞ ላይ ናት፤እኛም እየተጓዝን ነው፡፡ አሁንም የሚያስፈልገው ጥቂት ነገር ነው - “ጥቂት ቀናት” መታገስ፤ የለውጡን ሂደት መደገፍና መሪዎቻችንን ማበረታታት! ከዚያም ጠቅላይ ሚኒስትራችን “አያታለሁ” ያሏትን ዲሞክራሲና ፍትህ የነገሰባት፣ ሁሉም ዜጎች በእኩልነት የሚዳኙባት፣ ህግ የሚከበርባት፣ ከመላው አለም የሚመጡ ዜጎች ምንም ስጋት ሳያድርባቸው በቆዳ ስፋቷ ልክ የሚንቀሳቀሱባት፣ የአፍሪካውያን ኩራትና መገናኛ፤ ሰላሟ ከራሷ አልፎ ለጎረቤቶቿ የሚበቃ፤ በብዙ ነገሯ ምሳሌ የምትሆነዋን አዲሲቷን ኢትዮጵያ አብሮ ማየት! “ድልድዩን” ተሻግሮ “አረንጓዴው መስክ” ላይ እኛና ልጆቻችን እጅ ለእጅ ተያይዘን እፎይ ማለት! - ያኔ የብሔር ፖለቲካ የለም፤ ያኔ ጥልቅ ድህነት የለም፣ ያኔ የተደራጀ ሌብነት የለም፤ ያኔ መከፋፈል የለም፤ ያኔ የማንም ወሮበላ በኢትዮጵያ ምድር “መጤ” እያለ ጎረቤቱን አያፈናቅልም---ያ ቀን ያጓጓል! አረንጓዴው መስክ ላይ ለማረፍ አሁንም እንታገስ፤ ጥቃቅን በሆኑና ራስ ወዳድነት በሚታይባቸው ዘረኛ አስተሳሰቦች ታጥረን እንቅፋት አንፍጠር:: ለዓላማቸው የጨከኑ መሪዎች አሉን፤ ለመሪዎቻችን እድል እንስጣቸው፣ የታገሷት “ጥቂት ቀናት” ደስታን ትፈጥራለች! በጠቅላይ አቃቤ ህግ መግለጫና በሰሞኑ የመንግስት እርምጃ በርካታ ዜጎች የሰርጋቸውን ቀን ያህል ተደስተዋል ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ በነገራችን ላይ ሰሞኑን በተነገሩን የዘረፋ መጠኖች ብቻ እንኳን አገሪቷ አገር ሆና እስከ ዛሬ መቀጠሏ አስገራሚ ነው፡፡ እንታገስ እንጂ ሌሎችም ጉዶች መስማታችን አይቀርም! ቸር እንሰንብት!!
***    
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው የአዲስ አድማስ መጣጥፍ አቅራቢ ሲሆኑ በኢ-ሜይል አድራሻቸው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1402 times