Sunday, 18 November 2018 00:00

ከተሜነት ‘ዳገት’ ሲሆን--

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)


          “--የ ‘ዘ ዳ ቪንቺ ኮድ’ ደራሲ ዳን ብራውን በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር… “ከጥቂት አስርት ዓመታት በኋላ መኪና መንዳት ለሰዎች ተክልክሎ ማሽኖች ብቻ
ሊያሽከረክሯቸው ይችላሉ” ያ ኔ መኪና አምራቾቹ “እንዲህ መገላገል እያለ!…” ብለው መኪኖቹን ከሁሉም ቀድመው ለእኛ ሳይልኳቸው አይቀሩም፡፡--”
   

     እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሰውየው አዲስ ባርኔጣ አድርጓል፡፡ እናላችሁ… አንድ የሚያውቀው ሰው መንገድ ላይ ያገኘዋል፡፡
“በጣም ደስ የሚል ባርኔጣ ነው፡፡ የሚገርምህ ባርኔጣ ስታደርግ እኮ ከእድሜህ ከአስር ዓመት በላይ  የቀነስልህ ነው የምትመስለው”
“እውነት፤ይሄን ያህል ይለውጠኛል!”
“በጣም እንጂ! በነገራችን ላይ፣ አሁን እድሜህ ስንት ነው?”
“አሁን ሠላሳ ስምንት ዓመቴ ነው”
“ማለቴ ባርኔጣ ሳታደርግ እድሜህ ስንት ነው?” አለውና አረፈው፡፡ (እድሜውን በ‘ኮላተራል’ ያስያዘ አስመሰለው እኮ!)
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ባርኔጣ ማድረግ የከተሜነት ምልክት ሆነ እንዴ? የምናደርግ ሰዎች በዛን ብዬ እኮ ነው፡፡ እንግዲህ በሌላ በኩል ያልቻልንበትን ባርኔጣ በመድፋት ማካካስ ከተቻለ እሰየው ነው፡፡ እናላችሁ… እንደ ከተሜ መኖር  ለብዙዎቻችን እያስቸገረን ያለ ነው የሚመስለው፡፡
ለምሳሌ ለዓይን ደስ የሚሉ መኪናዎች በዝተዋል፡፡  ለዓይን ደስ የማይሉ የአሽከርካሪዎች የስነ ምግባር ጥሰቶችም በዝተዋል፡፡ በአገር ደረጃ “ለመኪና ብቁ ናቸው አይደሉም” የሚባል ‘የብቃት ማረጋገጫ’ ምናምን የሚባል ነገር ቢኖር፣ ለእኛ የሚፈቀድልን ከማስጠንቀቂያ ጋር ባይሆን ነው!
እኔ የምለው… ሳናውቃቸው የተለወጡ የትራፊክ ህጎች አሉ እንዴ! “ቀይ መብራት ከበራ በኋላ ለአራት፣ አምስት ሴኮንዶች ፈጠን ብሎ ማለፍ ይቻላል” የሚል ‘የህግ ማሻሻያ’ ወጥቷል እንዴ?! ግራ የሚገባ ነው እኮ! ያለ አሽከርካሪ በራሳቸው የሚሽከረከሩ መኪኖች በተፈበረኩበት ዘመን…አለ አይደል… እኛ ከመሪ ኋላ ሆነን በስርአት ማንቀሳቀስ ያቅተን! ግራ የሚገባ ነው፡፡ የ ‘ዘ ዳ ቪንቺ ኮድ’ ደራሲ ዳን ብራውን በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር… “ከጥቂት አስርት ዓመታት በኋላ መኪና መንዳት ለሰዎች ተክልክሎ ማሽኖች ብቻ ሊያሽከረክሯቸው ይችላሉ” ያኔ መኪና አምራቾቹ “እንዲህ መገላገል እያለ!…” ብለው መኪኖቹን ከሁሉም ቀድመው ለእኛ ሳይልኳቸው አይቀሩም፡፡
መስመር ይዞ መቆም ብርቅ እየሆነ ነው። በነገራችን ላይ… የዓለምን ከተሞች ጎን ለጎን ቢደረድሯቸው ከአየር ላይ ሆኖ አዲስ አበባን ለመለየት አያስቸግርም፡፡ ልከ ነዋ… በየትራፊክ መብራቶች ላይ የመኪናዎቹን አቋቋም ማየት ይበቃል፡፡ እኛም ከተሜዎች መሆን እያቃተን፣ ከተማዋም መዘመን እያቃታት ነው፡፡ ድህነታችን ላይ ውሀ ሲነካው ሙልጭ የሚል ‘ኩል እንደመቀባት’ አይነት የሆኑት ባለ ብዙ ሚሊዮን ብር መኪኖችን “የእኔን እዩልኝ፣ የእኔን” አይነት ፉክክር ውስጥ ያሉ ነው የሚመስለው፡፡ ሰዋችን በመኪና መደነቅ ማቆሙን አላወቁ!
ነገሬ ካላችሁ ሞባይል እየተጠቀሙ የሚሄዱ አሽከርካሪዎች በዝተዋል፡፡ እንደውም “ትራፊክ አየኝ፣ አላየኝ” ማለቱ ሁሉ እየቀረ ያለ ነው የሚመስለው፡፡ እኔ ካልቀደምኩ የሚል አሽከርካሪ መአት ነው፡፡ ችግሩ ደግሞ እነዚህ የባህሪይ ችግር የሚታይባቸው ደግሞ እንደ ድሮ የታክሲ አሽከርካሪ፣ የመንግሥት መኪና ሾፌር ብቻ አለመሆናቸው ነው፡፡ የአገርና የትውልድ ተምሳሌት ሊሆኑ የሚገባቸው ‘ጉምቱ’ ምናምን የሚባሉ ዜጎች፤ ሰፈር እንደሚያምስ ጎረምሳ አይነት ሲያደርጋቸው ማየቱ የተለመደ ነው፡፡
እናም…እኛም ከተሜ መሆኑ፣ ከተማዋም መዘመን ያቃታት ነው የሚመስለው፡፡ ለምሳሌ በአደባባይ ምራቅ መትፋት (ቃሉን መጥራት ደስ ባይልም) አንገት ማስደፋቱ ቀርቷል፡፡ እንዲህ አይነት ባህሪይ ጸያፍ መሆኑን ለማወቅ አኮ ከተሜነት ምናምን መሆን አያስፈልግም… ሰብአዊ ፍጡር መሆን ይበቃል፡፡ የምር እኮ…አንዳንዱ ለሆነ የኦሎምፒክ ውድድር የሚዘጋጅ ይመስል አምስት ኪሎ ላይ ቆሞ አራት ኪሎ ድረስ ‘ሊወረውር’ የሚሞክር ነው የሚመስለው፡፡
በዚህ ላይ “ይቅርታ” ማለት የለ፣ “ሳላውቅ ነው” ብሎ ነገር የለ፣ ጭራሽ ገፍትሮ ነው የሚሄደው። እናም… ይቺን ከተማ ከህንጻዎቿ ሌላ ዘመናዊ የሚያሰኟት ነገሮች እየቀነሱ ይመስላል፡፡
ስሙኛማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ቦሌ አካባቢ አንድ ግዙፍ ግንባታ በሚካሄድበት በር አካባቢ ነው፡፡ “አጭር ነው ይሉታል፣ በአጭር ያስቀራቸው…” የሚባሉ አይነት ጎልማሶች ቻይናውያን ቆመው ያወራሉ፡፡ (“የቻይና ጎልማሳ በምን ይለያል አንዳትሉኝማ!) የሆነች ልጅ ‘ለአካባቢው በሚመጥን አረማመድ’ (ቂ…ቂ…ቂ…) በአጠገባቸው እያለፈች ነው፡፡ ምን ቢያደርጉ ጥሩ ነው…አንደኛው አፏጨ፡፡ የምር…ልክ እንደ እንትን ሰፈር ማይክ ታይሰኖች አፏጨ! (ሦስተኛዋ ሴት ልጁ እኮ አቅመ ማፏጨት ካለፈች ከራርማለች!) ሌላኛው ደግሞ ጮክ ብሎ ‘በቋንቋው’ የሆነ ነገር ተናገረና፣ መርካቶ ቻይኖቹ ሞባይል እስከሚጠግኑባት ሱቅ የሚደርስ ሳቅ ሳቁ፡፡
“ነብር አየኝ በይ!” ብሎ ይሁን…
“አማረብኝ ብለሽ አትበይ ደንበር ገተር…” ብሎ ይሁን…
“ይቺንማ በሁለት ሳምንት ጠብ ካላደረግሁ የሻንጋይ አድባር ድርቅ ያድርገኝ!” ብሎ ይሁን እግዜር ይወቀው፡፡
 እናማ… እንደ ጎረምሳ አፏጩሏት! እሷዬዋ ግን ኮስተር ብላ ከመጤፍ ሳትቆጥራቸው መንገዷን ቀጠለች፡፡ በሆዷ “እኔ ኒውዮርክና ላስ ቬጋስን እያሰብኩ፣ ጭራሽ ቤይጂንግ!” ሳትል አልቀረችም። እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ ይቺ ከተማ አኮ የሆነች የሶዶምና ገሞራ አይነት ነገር ሆናለች ነው የሚባለው። የተቋማትን ዩኒፎርም የለበሱ ሰዎች ሁሉ በአስራዎቹ መጀመሪያ ያሉና ከአቅመ ሔዋንነት በብዙ እርቀት ያሉትን ህጻናት በቃላትና በድርጊት ሲጎነታትሉ እናያለን። ዝግ ብላ የምትራመድ ሴት... አለ አይደል… ልክ ‘የሆነ ነገር’ የፈለገች ይመስል የመኪናውን ፍጥነት እየቀነሰ ወደ እግረኛ መንገድ ጠርዝ ጠጋ የሚል መአት ነው… የመኪና መሪ እንዴት መያዝ እንደቻለ ግራ ከሚያጋባው ታዳጊ ቢጤ… መኪና ለስምንተኛ ጊዜ ለውጠው መሪ ጀርባ መቀመጥ ስልችት እስካላቸው ‘ቬተራን’ ድረስ፡፡ (የማንም ይሁን የማን ብቻ የተከፈተ የመኪና በር ካዩ ዘለው ለመግባት ወደ ኋላ አይሉም የሚባሉ አንዳንድ አህቶቻችን አሉ እየተባለ ‘እንደሚታማ’ ለመጠቆም ያህል ነው። እኔ የምለው…የሆነች ሴት ሸለል ብላ ስትታይ “እንዲህ የምትዘንጠው ሠርታ መሰላችሁ! አጅሪት ማታ፣ ማታ ሥራዋ ከመኪና መኪና መዝለል  ነው አሉ…” ምናምን የሚባለው ለዚህ ነው እንዴ?)
እናማ…
ፎቅና መርሴዲስ ስሜት አይሰጡኝም
እኔን ፍቅር እንጂ ሀብት አያሞኘኝም
የሚባል ዘፈን ነበር፡፡ አሁን “ሀብት አያሞኘኝም፣” ምናምን ብሎ መዝፈን ጎጂ ልማድ ነገር የሆነ ይመስላል፡፡
አትመልከች ሱፍ አትዪ መኪና
እኔም አገዛለሁ ዕድሌ ሲቃና
የምትል ዘፈን ነበረች፡፡ ዘንድሮ… “ዕድሌ ሲቃና…” ብሎ ዘፈን ‘ጎጂ ልማድ’ እየሆነ ነው የሚመስለው፡፡ ስንትና ስንት አስፈንጥሮ እላይ የሚያስቀምጥ አቋራጭ እያለ የምን የአምስት ዓመት ምናምን ፕሮጀከት ፕሮፖዛል ነው፡፡
ስሙኛማ…ይህ ‘መለካከፍ’ የሚሉት ነገር፣ ‘እንደምንሰማው’ ከሆነ መንገድ ላይ ሳይሆን… ዘንድሮ በተለይ የእኛ ቢጤ ምስኪኖች ድርሽ በማንልባቸው የመዝናኛ ስፍራዎች እንትናዬዎቹም ከእንትናዎቹ በተቀራረበ መልኩ ‘ይላከፋሉ’ ይባላል፡፡  እኔ የምለው… ወላ ታዳጊው፣ ወላ ሩጫውን ለማገባደድ ‘መጨረሻው እሩብ’ ላይ የደረሰውም ሁሉም ሰው ሴቶችን መተናኮል የለመደበት ግሎባላይዜሽን የሚሉት ነገር መሆኑ ነው! ግራ ቢገባን ነው፡፡ ሰለጠኑ የምንላቸው አገሮች ውስጥ “የዛሬ ሠላሳ ዓመት ያለፈቃዴ ዳሌዬን ዳብሷል” በሚል የፍርድ ቤት ፋይል በሚያስከፍቱበት ዘመን፣ እኛ ዘንድ እንዲህ ‘እንደልብ’ ነገር ሲኮን የምር ቀሺም ነው፡፡
ከተሜ መሆን ያቃተን ከተሜዎች፣ ከህንጻዎቿ ባለፈ በባህሪይ መዘመን ያቃታት ከተማ! የተሻለውን ጊዜ ያምጣልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5382 times