Sunday, 18 November 2018 00:00

ጠ/ሚኒስትሩ፤ ወንጀለኞችን የማደንና ለህግ የማቅረቡ ሂደት ይቀጥላል አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(34 votes)

“ኢትዮጵያ ወንጀለኞች በኩራት የሚኖሩባት አገር መሆን የለባትም”
   በከፍተኛ የሙስና እና የሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው የተያዙ ግለሰቦች ቁጥር 70 የደረሰ ሲሆን፤ ፖሊስ አሁንም ቀሪ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የተጠርጣሪዎችና የተጠርጣሪ ቤተሰቦችን ጨምሮ የ206 ግለሰቦች የባንክ ሂሣብ መታገዱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በቁጥጥር ስር የዋሉት የሜቴክ ከፍተኛ አመራሮችና የደህንነትና የፖሊስ ሃላፊዎች ከማክሠኞ ህዳር 4 ጀምሮ እስከ ትናንት ድረስ በተከታታይ ፍ/ቤት ቀርበው፣ ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የጠየቀባቸው ሲሆን፤ አቃቤ ህግ የተጠርጣሪዎችን ንብረትና የባንክ ሂሣብ በማሳገድ ሥራ ተጠምዶ ሰንብቷል፡፡
ጠቅላይ አቃቤ ህግ ባለፉት 6 ወራት ከሙስናና የሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ በስኳር ኮርፖሬሽን፣ በብረታ ብረት ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ብኢኮ)፣ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሣ) እንዲሁም በደህንነትና የፀጥታ ተቋማት፤ ማረሚያ ቤቶች ላይ ምርመራ ሲያካሂድ እንደቆየ ተጠቁሟል፡፡
እስከ ትናንት ድረስ በቁጥጥር ስር ከዋሉት የቀድሞ የሜቴክ ከፍተኛ አመራሮች፣ የደህንነትና የፀጥታ ተቋማት ሃላፊዎችና ባልደረቦች በተጨማሪ በቀጣይ የስኳር ኮርፖሬሽንና የኢንሣ የቀድሞ የስራ ኃላፊዎችን ለህግ የማቅረብ ስራ እንደሚከናወን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ከሜቴክ ጋር ህገወጥ የስራ ግንኙነት አላቸው ተብለው በተጠረጠሩ ኩባንያዎችና የንግድ ተቋማትም ላይ ምርመራ እየተጣራ መሆኑን ምንጮች አክለው ጠቁመዋል፡፡
ከሜቴክ ምዝበራና ሌብነት ጋር በተያያዘ የዋነኛ ተጠርጣሪ ሆነው ፍ/ቤት የቀረቡት ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው፤ “የጡረታ ደሞዜ 4ሺህ ብር ብቻ ነው፤ ጠበቃ በግል ለማቆም አቅም የለኝም ቢሉም፣ አቃቤ ህግ “ሃብት አላቸው” ሲል ማስረጃ ማቅረቡን ተከትሎ፣ ፍ/ቤቱ በራሣቸው ጠበቃ አቁመው እንዲከራከሩ በይኗል፡፡
ተጠርጣሪው ለፌደራል ፀረ ሙስና ስነምግባር ኮሚሽን ያስመዘገቡት ሃብት 800ሺህ ብር የሚያወጣ ተሽከርካሪና ቢሾፍቱ ከተማ ላይ መኖሪያ ቤት  እንደዚሁም የተለያዩ የአክሲዮን ድርሻዎች እንዳላቸው በማስረጃነት በመርማሪ ፖሊስ ቀርቦባቸዋል፡፡ በተጨማሪም በ15 ቀናት ውስጥ ከባንክ 100ሺህ ብር ማውጣታቸውን ያመላከተው ፖሊስ፤ ግለሰቡ ሃብታቸውን ለማሸሽ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበረም አስታውቋል፡፡
በዚሁ የምርመራ መዝገብ የተካተተችው ጋዜጠኛ ፍፁም የሺጥላ፤ “ፍፁም ኢንተርቴይመንት” ለተባለ ድርጅት ባልተገባ ስፖንሰርሺፕ 954ሺህ 770 ብር ከሜቴክ እንደወሰደችና ይህን ገንዘብ ተጠቅማ ሃብት ማፍራቷን ፖሊስ ገልጿል፡፡
ተጠርጣሪዋ በበኩሏ፤ “በስፖንሰርሺፕ ያገኘሁት ህጋዊ ገንዘብ ነው፤ በወንጀል አያስጠይቀኝም፤ ገና አራስ በመሆኔም ጉዳዩን ውጭ ሆኜ እንድከታተል ይፈቀድልኝ” ስትል ጠይቃለች፡፡ ይሁን እንጂ የዋስትና ጥያቄው ተቀባይነት አላገኘም፡፡
ሌላኛዋ ተጠርጣሪ ወ/ት ትዕግሥት ታደሰ ደግሞ የህብረት ማኑፋክቸሪንግ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ሃላፊ (ያልተያዙ) ጋር በመመሳጠር ያልተገባ ጥቅም አግኝተዋል፤ ገንዘብ ተቀብለው ተሠውረዋል፤ በምርመራ ወቅትም ከተጠርጣሪዋ መኖሪያ ቤት የመኪና ሊብሬና የቤት ካርታ ተገኝቷል ብሏል - ፖሊስ።
ተጠርጣሪዋ በበኩሏ፤ “ከግለሰቡ ጋር በሚባለው ልክ ግንኙነት የለንም፤ የሠወርኩት ንብረትም የለም፤ ተማሪ ነኝ፤ ዋስትና ይፈቀድልኝ” ብትልም የዋስትና ጥያቄው በፍ/ቤቱ ተቀባይነት አላገኘም፡፡
በብ/ጀነራል ክንፈ ዳኘውና በእነዚህ ተጠርጣሪዎች ላይ ፍ/ቤቱ ተጨማሪ የ10 ቀን የምርመራ ጊዜም ፈቅዷል፡፡
ከዚሁ የሙስና እና የሠብአዊ መብት ጥሰት ወንጀል ተጠርጣሪዎች ጋር በተያያዘ በእነሱ ስም ያለን ጨምሮ በማንኛውም ባንክ ያለ የቤተሰቦቻቸው የባንክ ሂሣብ መታገዱ ታውቋል፡፡
በሠብአዊ መብት ጥሰትና በሙስና የተጠረጠሩት የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ ምክትላቸው አቶ ያሬድ ዘሪሁን፣ ዶ/ር ሃሺም ቶፊቅ፣ ደርበው ደመላሽ፤ ጐሃ አጽብሃን ጨምሮ የሌሎች የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አመራር የነበሩ ግለሰቦች በስማቸውና በቤተሰቦቻቸው የተከፈቱ የባንክ ሂሳቦችም መታገዳቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የደህንነት ኃላፊው አቶ ጌታቸው  አሠፋና የልጃቸው ልዕልቲ ጌታቸው እንዲሁም የምክትል ኃላፊው አቶ ያሬድ ዘሪሁንና በባለቤታቸው ስም ማለትም አዳነች ተሠማ እና ሃዊ ተሠማ በሚባሉ ሁለት ስሞች የተከፈቱ የባንክ አካውንቶችም ታግደዋል፡፡ በተጨማሪም የአቶ ያሬድ ዘሪሁን አራት እህቶች፣ በአራት የባለቤታቸው ወንድሞችና በአራት ልጆቻቸው ስም የተከፈቱ 15 አካውንቶችም ታግደዋል ተብሏል፡፡
በአቶ ጐሃ አጽብሃ፣ በባለቤታቸው ዮርዳኖስ ገ/ማርያምና በሶስት ልጆቻቸው ያሉ አካውንቶች እንዲሁ እንዲታገዱ ታዟል፡፡ በአቶ ደርበው ደመላሽና በባለቤታቸው ወይንሸት ፋቱይና በአምስት ልጆቻቸው ስም የተከፈተ አካውንትም እንዲታገድ ታዟል፡፡ በአጠቃላይ የተጠርጣሪዎቹና የቤተሰቦቻቸው በማንኛውም የሀገሪቱ ባንክ የሚገኝ ሂሣብ እንዳይንቀሳቀስ ታዟል፡፡
ፖሊስ የእግድ ትዕዛዙን ለሚመለከታቸው ሁሉም የሃገሪቱ ባንኮች ባስተላለፈበት ደብዳቤው፤ ስማቸው የተዘረዘረው ግለሰቦች የባንኩ ደንበኛ መሆን አለመሆናቸውን፤ ከባንኩ ጋር ያላቸው ግንኙነት ከመቼ ጀምሮ እንደሆነ፤ በግልም ሆነ በጋራ ወይም በውክልና እና በስም ካልተጠቀሙ በሌሎች ሰዎች ጋር በከፈቱት የቁጠባና ተንቀሳቃሽ ሂሣብ ውስጥ በአሁኑ ሰአት ያለውን የአገር ውስጥ ገንዘብ፣ የከበሩ ማዕድናትና የውጭ ሀገር ገንዘብ እንዲሁም በባንኩ ያላቸውን የሼር መጠን (መኖሩ ከተረጋገጠ) እንዲታገድ እንጠይቃለን ብሏል፡፡
ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር አውሎ ለህግ የማቅረብ የመንግስት እርምጃን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ሰሞኑን “ካንሠርን በጋራ እንከላከል” በሚል ርዕስ መግለጫ አውጥተዋል፡፡
መንግስት ለህዝቡ ቃል በገባው መሰረት፤ በሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ሀገርን በመዝረፍና የሀገሪቱን መፃኢ ተስፋ ለማጨለም የሚንቀሳቀሱ አካላትን እንዲሁም የሰኔ 16 የቦምብ ፍንዳታን ጨምሮ የተለያዩ ወንጀሎችን በማቀነባበር የተጠረጠሩትን ተከታትሎ ለህግ ለማቅረብ ተግቶ እየሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዐቢይ አህመድ አስታውቀዋል፡፡
መንግስት ይህንን እያደረገ ያለው በአንድ በኩል ባለፉት ዘመናት ህዝቡ በግልፅ ሲጠይቃቸው የነበሩ የፍትህ ጥያቄዎች በመሆናቸውና በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት ይህንን ለማድረግ ግዴታ ስላለበትም ነው ብለዋል - ጠ/ሚኒስትሩ ከትላንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ፡፡ በአንድ ሀገር ውስጥ የመንግስት መኖርን የግዴታ ከሚያደርጉት መሰረታዊ ምክንያቶች አንዱ ፍትህን ማረጋገጥ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ፍትህ የሚረጋገጠውም ንጹሃን በኩራት ቀና ብለው የሚሄዱበትና ወንጀለኞች ደግሞ የትም የማይደበቁበት ስርዓት መፍጠር ስንችል ነው ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ንፁሃን ዜጎች እንጂ ወንጀለኞች በኩራት የሚኖሩባት ሀገር መሆን የለባትም ብለዋል፡፡
“ወንጀል የፈፀሙት እንዲቀጡበት፣ ሊፈፅሙ ያሰቡት እንዲጠነቀቁበት፣ እነርሱን ሊከተሉ የሚከጅሉት እንዲማሩበት ሲባል ወንጀለኞችን የማደንና ለህግ የማቅረቡ ሂደት ገና ይቀጥላል፤ ተጀመረ እንጂ አልተፈፀመም፤ ዓላማውም በአራቱም አቅጣጫ ሀገሪቱን ከወንጀለኞች ነፃ ማድረግ ነው” ብለዋል፤ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ፡፡ ወንጀለኞች ጥቅም እስካገኙ ድረስ ወገኔ ለሚሉት አይራሩም ወንጀለኛ ወገንም ብሄርም፣ ዘርም፣ ሞራልም የለውም ብለዋል፡፡
 “ወንጀልና ካንሰር አንድ ናቸው” ያሉት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ፤ “ካንሰርን በልምምጥ፣ በልመናና በአማላጅ ማዳን አይቻልም፤ ካንሰርን በዝምታ መመልከትም ሞትን በእያንዳንዷ ቀን በዝምታ እንደ መጋበዝ ነው” ሲሉ በመግለጫቸው አብራርተዋል፡፡
“አሁን የተጀመረው ስራ ሀገር የገደሉ ወንጀለኞችን፣ እነርሱ ለሌላው በነፈጉት ፍትህ ፊት የማቅረብ ስራ ነው፤የተያዙ ሰዎችም በተገቢ ደረጃና አያያዝ የሚገባቸውን ፍትህ እንዲያገኙ ይደረጋልም” ብለዋል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ አክለውም፤ “የወንጀለኞች መኖሪያ መሆን ያለባቸው ማረሚያ ቤቶች እንጂ ብሄሮች ብሄረሰቦች አይደሉም” ሲሉ ገልፀዋል፡፡ በመጨረሻም የቅጣቱ ዋና ዓላማ አጥፊዎችን መቅጣትና ድርጊቱን መኮነን ብቻ ሳይሆን ዳግም እንዳይከሰት መከላከልም ጭምር ነው ብለዋል፤ ጠ/ሚኒስትሩ በመግለጫቸው፡፡
በከፍተኛ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው እስከ ትናንት ድረስ በቁጥጥር ስር የዋሉት ዋነኛ ተጠርጣሪውን የሜቴክ የቀድሞ ስራ አሥኪያጅ ብ/ጀነራል ክንፈ ዳኛውን ጨምሮ 31 ግለሰቦች መሆናቸው ታውቋል፡፡ በዚሁ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የተያዙትም የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የማርኬቲንግ ኃላፊ ብ/ጀነራል ጠና ቁርንዴ፣ የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ኦዲትና ኢንስፔክሽን ሃላፊ ብ/ጀነራል ብርሃነ በየነ፤ የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኮርፖሬት ሎጀስቲክ ሰፕላይ ሃላፊ ብ/ጀነራል ሃድጉ ገብረጊዎርጊስ፤ የኮርፖሬሽኑ ም/ዋና ዳይሬክተርና የወታደራዊ ምርቶች ኦፕሬሽን ሃላፊ ኮሎኔል ሸጋው ሙሉጌታ፤ የኮርፖሬሽኑ ም/ዋና ዳይሬክተርና የኒው ቢዝነስ ደቨሎፕመንት ሃላፊ ኮሎኔል ሙሉ ወልደገብርኤል፤ የኮርፖሬሽኑ ሎጀስቲክና ሰፕላይ የትራንስፖርት ኃላፊ ኮሎኔል አለሙ ሽመልስ፤ የኮርፖሬሽኑ የኒው ቢዝነስ ደቨሎፕመንት ፕሮጀክት ኃላፊ ኮ/ል ያሬድ ሃይሉ፣ በየኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኒው ቢዝነስ ደቨሎፕመንት ሃላፊ የነበሩት ኮ/ል ተከስተ ኃ/ማርያም፤ የኮርፖሬሽኑ የሽያጭና ማርኬቲንግ ኃላፊ ኮ/ል አዜብ ታደሰ፤ የኮርፖሬሽኑ የደጀን አቪዬሽን የኢንዱስትሪ ኦፕሬሽን ኃላፊ ሻለቃ ሰመረ ሃይሌ፤ በኮርፖሬሽኑ የማርኬቲንግና ሽያጭ ፕሮሞሽን ኃላፊ ሻምበል ይኩኖ አምላክ ተስፋዬ፤ የኮርፖሬሽኑ የአዳማ እርሻ ስራዎች ኢንዱስትሪ ስራ አስኪያጅ ኮ/ል ደሴ ዘለቀ፤ በኮርፖሬሽኑ በብረታ ብረት ፋብሪኬሽን የኢንዱስትሪና ፋይናንስ ኃላፊ ሌተናል ኮሎኔል ሰለሞን በርሄ፤ በኮርፖሬሽኑ የህብረት ማሽን ቢዩልዲንግ ኢንዱስትሪ የፋይናንስ ኃላፊ ሻለቃ ይርጋ አብርሃ፤ በኮርፖሬሽኑ ሎጀስቲክስና ሰፕላይ የንብረት አስተዳደር ኃላፊ ኮ/ል ግርማይ ታረቀኝ፤ በኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ትራንስፎርሜሽን የአቅም ግንባታ ማዕከል ኃላፊ ሻምበል ገብረስላሴ ገብረ ጊዮርጊስ፤ በኮርፖሬሽኑ የትራንስፎርሜሽን የስልጠና ኃላፊ ሻምበል ሰለሞን አብርሃ፤ በኮርፖሬሽኑ የደን ምንጣሮ ክትትል ኃላፊ ሻለቃ ጌታቸው ገ/ስላሴ፤ በኮርፖሬሽኑ የኮሜርሻልና ሲቪል ምርቶች ኦፕሬሽን የፕላኒንግ ኮንትሮል ሃላፊ ሌተናል ኮሎኔል ይስሃቅ ሃይለ ማርያም፤ በኮርፖሬሽኑ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች የፋይናንስ ሃላፊ ሻለቃ ክንደያ ግርማይ፤ በኮርፖሬሽኑ ሎጀስቲክስና ሰፕላይ የንብረት ክፍል ሃላፊ ሌተናል ኮሎኔል አዳነ አገርነው፤ በኮርፖሬሽኑ የማሽነሪ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ክፍል ሃላፊ ሻለቃ ጌታቸው አፅብሃ፤ የጋፋት አርማመንት ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ተወካይ ሃላፊ የነበሩት ሌ/ኮሎኔል አስመረት ኪዳኔ፤ የመከላከያ ጤና ኮሌጅ ሠራተኛ የሆኑት ኮሎኔል ዙፋን በርሄ እንዲሁም ከኮርፖሬሽኑ የስራ ሃላፊዎች ጋር የጥቅም ግንኙነት ነበራቸው የተባሉት የዋይቲኦ ኩባንያ ባለቤት አቶ ቸርነት ዳና (በድለላም ይሠራሉ ተብሏል) የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ባልደረባ ጋዜጠኛ ፍፁም የሺጥላ እንዲሁም የሜ/ጀነራል ክንፈ ዳኘው ወንድም (በኢትዮ ቴሌኮም የሚሠሩ) ኢሣያስ ዳኛው ናቸው፡፡ ከጋፋት አርማመንት አመራር ጋር ያልተገባ ጥቅም ተቋድሰዋል የተባሉት ወ/ት ትዕግሥት ታደሠ፡፡
በዚሁ የተጠርጣሪዎች መዝገብ ስር መረጃ ሊያጠፉ ሙከራ አድርገዋል የተባሉ አያልነሽ መኮንን የተባሉ ግለሰብ እና አቃቤ ህግ የጀመረውን ምርመራ እንዲያቋርጥ ማስፈራሪያና ዛቻ ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩት ኮ/ል ጉደታ ኦላና ይገኙበታል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ሠራተኛ የሆኑት የብ/ጀነራል ክንፈ ዳኛው ወንድም አቶ ኢሣያስ ዳኘው፤ የመንግስትን የግዥ ስርአት በጣሰ መልኩ ሜቴክ ጨረታ እንዲያሸንፍ በማድረግ ወንጀል ነው የተጠረጠሩት፡፡
የሰብአዊ መብት ጥሠት ተጠርጣሪዎች (አንዳንዶቹ በሌብነትም የተጠረጠሩ ናቸው)
የሰብአዊ መብት ጥሰት በመፈፀም ተጠርጥረው የታሰሩት ደግሞ የቀድሞ የብሔራዊ ደህንነት፣ የፌደራል ፖሊስ እና የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች የነበሩ መሆናቸው ታውቋል፡፡
ከብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት ተጠርጣሪዎች
እነዚህም የቀድሞ የብሔራዊ ደህንነት ምክትል ኃላፊ በኋላም ለ1 ወር ያህል የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩትና ወደ ኬንያ ለማምለጥ ሲሉ ዱከም ላይ በቁጥጥር ስር የዋሉት አቶ ያሬድ ዘሪሁን (በተጨማሪም በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ)፤ የአዲስ አበባ ደህንነት ኃላፊ አቶ ጉሃ አፅበሃ፤ የሃገር ውስጥ ደህንነት ጥበቃ ዋና መምሪያ ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል ኪሮስ፤ የውስጥ ደህንነት ም/ዋና ዳይሬክተር የነበሩና የኢኮኖሚ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ደርበው ደመላሽ፤ የውስጥ ደህንነት ጥናትና የወንጀል ምርመራ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ገ/ፃድቅ፤ በዋናነት የግንቦት “7” ጉዳይን የሚከታተሉት አቶ ቢኒያም ማሙሸት፤ የአማራ ክልል የደህንነት ኃላፊ የነበሩና የጥበቃ ዋና መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ኃይሌ፤ የኦሮሚያ ክልል ደህንነት ኃላፊ አቶ አዲሱ በዳሳ፤ የውጭ መረጃ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ወይም ገ/እግዚአብሔር ውበት፤ በፀረ ሽብር መምሪያ የኦነግና ኦብነግ ክፍል ዋና ኃላፊ አቶ ተመስገን በርሄ፤ የግንቦት 7 ክትትል ምክትል መምሪያ ኃላፊ አቶ ሸዊት በላይ፤ የአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ደህንነት አስተባባሪ አቶ አሸናፊ ተስፋሁን፤ በውጪ መረጃ የአማራ ክልል ክትትል አቶ ደርሶ አያና፤ የደቡብ ክልል ክትትል ኦፊሰር አቶ ሰይፉ በላይ፤ የደቡብ ክልል ደህንነት ኃላፊ አቶ ኢዮብ ተወልደ፤ የኦሮሚያ ክልል የደህንነት ክትትል ም/ኃላፊ አቶ አህመድ ገዳ ናቸው፡፡
ከፌደራል ፖሊስ ተጠርጣሪዎች
ከፌደራል ፖሊስ ደግሞ የቀድሞ የፌደራል ፖሊስ የሽብር ወንጀል ምርመራ ም/ዳይሬክተርና በኋላ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ም/ኮማንደር አለማየሁ ኃይሉ፤ የሽብር ወንጀል መርማሪዎቹ ም/ኢንስፔክተር የሱፍ ያሲን፣ ም/ሳጅን እቴነሽ አረፋይኔ፣ ኢንስፔክተር ፈይሳ ደሜ፣ ም/ኢንስፔክተር ምንላርግልህ ጥላሁን፣ ዋ/ሳጅን ርዕሶም ክህሽን መሆናቸው ታውቋል፡፡
ከማረሚያ ቤቶች ተጠርጣሪዎች
ከማረሚያ ቤቶች በሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የተፈቀደባቸው ደግሞ ኦፊሰር ገ/ማርያም ወልዳይ፣ ኦፊሰር አስገለ ወ/ጊዮርጊስ ዋና ሱፐር ኢንተንደንት አሰፋ ኪዳኔ እንዲሁም የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የጥበቃና ደህንነት ኃላፊ ዋና ሱፐር ኢንተንዳንት ገብረ እግዚአብሔር ገብረሃዋርያት፤ የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሰራተኛ የሆኑት ሌላኛው ዋና ሱፐር ኢንተንዳንት ተክላይ ኃይሉ፤ የሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት ኃላፊ የነበሩ ዋ/ሱ/ ኢንተንዳንት አቡ ግርማ፤ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ከፍተኛ የደህንነት ባለሙያ ዋ/ሱ/ኢ ተስፋ ሚካኤል አስጋለ፤ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሰራተኛ ዋ/ሱ/ኢንተንዳንት አዳነ ሃጎስ፤ የዝዋይ ማረሚያ ቤት የጥበቃ ደህንነት ኃላፊ የነበሩት ዋ/ሱ/ኢንተንዳንት ገብራት መኮንን መሆናቸው ታውቋል፡፡
ከአዲስ አበባ ፖሊስ ተጠርጣሪዎች
ከአዲስ አበባ ፖሊስ ደግሞ የወንጀል መርማሪ የሆኑት ረ/ኢንስፔክተር አለማየሁ ሃይሉ፣ ረ/ኢንስፔክተር መንግስቱ ታደሰ እንዲሁም አዳነች ወይም ሃዊ ተሰማ፣ ጌታሁን አሰፋና ሙሉ ፍሰሃ ናቸው፡፡ አቶ ያሬድ ዘሪሁንን ጨምሮ በዚህ ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ፍ/ቤት ቀርበው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
በከፍተኛ ሙስና እና በሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ከመጪው ሐሙስ ህዳር 13 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በተከታታይ ባሉ ቀናት ጉዳያቸው ልደታ በሚገኘው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት መታየት ይጀምራል፡፡  




Read 9246 times