Saturday, 19 May 2012 11:16

በቢልቦርድ አዋርድ ለዓመቱ ምርጥ አርቲስት ከባድ ፉክክር አለ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

በነገው እለት ላስቬጋስ ውስጥ በሚገኘው የኤምጂኤም ግራንድ ጋርደን አዳራሽ የ2012 የቢልቦርድ የሙዚቃ አዋርድ ሲካሄድ የዓመቱ አርቲስት ለመባል በአዴሌ፤ሪሃና፤ ብሪትኒ ስፒርስና ክሪስ ብራውን መካከል ከባድ ፉክክር እንደሚኖር ይጠበቃል፡፡ በምሽቱ ክሪስ ብራውን ታላቅ የሙዚቃ ድግስ እንደሚኖረው የጠቆመው የቢልቦርድ ዘገባ፤ የዓመቱ ምርጥ ወንድ አርቲስትን ጨምሮ በአራት የተለያዩ ዘርፎች መታጨቱንና ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ የግራሚ ሽልማትን “ፌም” በተባለ አልበሙ እንዳሸነፈ አስታውሷል፡፡ በኤቢሲ ቻናል የቀጥታ ስርጭት በሚኖረው የቢልቦርድ አዋርድ ላይ ጀስቲን ቢበር፤ ኬሪ አንደርውድና ኤልኤምኤፍኤኦ ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ተጋባዦች ይሆናሉ ተብሏል፡፡ በ2012 ለገበያ ከቀረቡ አልበሞች ውስጥ 90 ሚሊዮን ቅጂዎች መሸጣቸውን ያመለከተው ሚውዚክዊክ፤ ከኢንተርኔት በመጫን የሚገዙ ነጠላ ዜማዎች ገበያ መድራቱን አመልክቷል - 416.6 ሚሊዮን ነጠላ አልበሞች መሸጣቸውን በመጥቀስ፡፡

በነገው የቢልቦርድ ሚዩዚክ አዋርድ ለሁለተኛ ጊዜ “አይኮን አዋርድ” ተብሎ የሚሰጠውን የክብር ሽልማት ስቲቪ ወንደር እንደሚሸለምም ታውቋል፡፡ በ2012 የቢልቦርድ ሙዚቃ አዋርድ ላይ በፍፃሜ ተፋላሚነት በብዙ ዘርፎች በመታጨት “የአመቱ ምርጥ አርቲስት” እና “የዓመቱ ምርጥ ሴት አርቲስት”ን ጨምሮ በ18 ዘርፎች የታጨችው እንግሊዛዊቷ አዴሌ እና በ17 የሽልማት ዘርፎች የታጨው የኤሌክትሮ ፖፕ ሙዚቃ ቡድን ኤልኤምኤፍኤኦ ይመራሉ፡፡ ባለፈው ዓመት በከፍተኛ ዘርፎች ታጭታ ግንባር ቀደም የነበረችው ሪሃና በ13 የሽልማት ዘርፎች ስትከተል፤ ሌዲ ጋጋ እና ሊል ዋይኔ በእኩል 10 የሽልማት ዘርፎች እጩ ሆነው ቀርበዋል፡፡ የዓመቱ ምርጥ ሴት አርቲስት በሚለው የውድድር ዘርፍ ፉክክሩ በአዴሌና ሪሃና መካከል ሲሆን በዓመቱ ምርጥ አዲስ አርቲስት ደግሞ ኬቲ ፔሪና ዊዝ ካሊፋ ይፎካከራሉ ተብሏል፡፡ አርቲስቶቹ በዓመቱ ምርጥ አርቲስት ሽልማት ከፍተኛ ፉክክር ላይ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡  አምና የዓመቱ ምርጥ አርቲስት ተብሎ ከፍተኛውን ሽልማት የወሰደው ራፕሩ ኤሚነም ነበር፡፡

 

 

Read 1183 times Last modified on Saturday, 19 May 2012 11:19