Saturday, 17 November 2018 10:52

በደቡብ የክልልነት ጥያቄዎች ተበራክተዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(10 votes)

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ውስጥ “ራሳችንን ችለን ክልል እንሁን” የሚሉ ጥያቄዎች  እየተበራከቱ መምጣታቸው ታውቋል፡፡
በ13 ዞኖች በ8 ልዩ ወረዳዎችና በ22 የከተማ አስተዳደሮች የተደራጀውና 56 ብሔር ብሔረሰቦችን በያዘው በዚህ ክልል ውስጥ እስካሁን የሲዳማ፣ የወላይታና የከፋ ክልል የመሆን ጥያቄዎችና የውሳኔ ሃሳቦች ቀርበዋል፡፡
የከንባታ ጠንባሮ ዞንም “የክልል ጥያቄ” ማቅረቡን የጠቆሙ ምንጮች፤ በሌላ በኩል በዚሁ በከንባታ ጠንባሮ ዞን ውስጥ “ጠንባሮ ለብቻው ዞን ይሁን” የሚል ጥያቄም መቅረቡን አመልክተዋል፡፡  
የሲዳማ ክልል የመሆን ጥያቄ በሲዳማ ዞን ም/ቤት በሙሉ ድምፅ ከፀደቀ በኋላ ለክልሉ ም/ቤት ቀርቦ ተቀባይነት ማግኘቱ የታወቀ ሲሆን ከሰሞኑ የወላይታ “ክልል እንሁን” ጥያቄም በወላይታ ዞን ም/ቤት ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ የከፋ ዞን ም/ቤትም “ከፋ ራሱን ችሎ ክልል መሆን አለበት” የሚለውን የውሳኔ ሃሳብ ከትናንት በስቲያ ሐሙስ አፅድቋል፡፡
የከንባታ ጠንባሮ ዞን ም/ቤትም በዞኑ “ክልል ልሁን” ጥያቄ ላይ የውሳኔ ሃሳብ አቅርቦ ለመወያየት ማቀዱን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በቅርቡ በክልሉ የዞን፣ የልዩ ወረዳና የወረዳ አወቃቀር ላይ የህዝቡን ጥያቄ በሚመልስ መልኩ ተዘጋጅቷል የተባለው ጥናት፤ ለክልሉ ም/ቤት ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበት ይታወሳል፡፡

Read 4266 times