Sunday, 18 November 2018 00:00

እባብ ቆዳው ለሰለሰ ብለህ ቀበቶ አርገህ አትታጠቀውም

Written by 
Rate this item
(10 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ጉደኛ ትንሽ ልጅ ነበረ፡፡ ይህ ልጅ የደምብ ልብሱን በንፅሕና ይይዛል፡፡ በሰዓቱ ወደ ትምህርት ቤት ይሄዳል፡፡ በሰዓቱ ይመለሳል፡፡ ገና ትንሽ ልጅ ነው፡፡

ሆኖም አስተዋይ ነው፡፡
አንድ ቀን ሳያስበው አንድ ብርጭቆ ሰበረ፡፡ ታላቅ ወንድሙ መጥቶ በጣም ተቆጣውና ገሰፀው፡፡
“እየውልህ አንድ ነገር ከማድረግህ በፊት አስብ፡፡ ብታስብ ኖሮ ይሄን ብርጭቆ አትሰብርም ነበር፡፡ ስለዚህ
1ኛ/ አስብ
2ኛ/ አስብ
3ኛ/ አስብ” አለው፡፡
ልጁም
“እሺ በቃ፡፡ ከዛሬ ጀምሮ አስባለሁ” አለ፡፡
ከቀናት በኋላ ልጁ ታላቅ ወንድሙን፤
“ወንድም ጋሻ እፈልግሃለሁ” አለው፡፡
“እሺ ምን ልርዳህ ታናሼ” አለና ጠየቀው፡፡
“ወንድም ጋሻ አንድ ጥያቄ ብጠይቅህ ቅር ይልሃል?”
“በጭራሽ! የፈለከውን ጠይቀኝ”
“ወንድም ጋሻ፤ ማሰብ አስተምረኝ?”
ወንድም ጋሼ አይኑ ፈጠጠ፡፡ ለካ ማሰብን ማስተማር አይቻልም፡፡
ሌላ ቀን፤ ይሄው ጉደኛ ልጅ ከትምህርት ቤት ተመልሶ ይመጣል፡፡ እያለቀሰ ነው የመጣው፡፡
እናቱ፤
“ምን ሆነህ ነው የምታለቅሰው ልጄ?”
“የኔታ ገረፉኝ!”
“ለምን ልጄ? ምን አጥፍተህ ነው?”
“ምንም”
“ምንም ሳታጠፋማ አይመቱህም፡፡ ዕውነቱን ንገረኝ?”
“ `ሀ` በል አሉኝ፡፡ አልልም፤ አልኳቸው፡፡ ከዛ ገረፉኝ፡፡”
እናትየውም፤
“የሞትክ! ሀ ማለት አቅቶህ ትገረፋለህ?” አለችው፡፡
ልጁም፤
“አይ እማዬ፤ የየኔታ ጉዳቸው መች ያልቃል?
“ሀ” ስል “ሁ” በል ይሉኛል፡፡ “ሁ” ስል “ሂ” በል ይሉኛል፡፡ “ሂ” ስል “ሃ” በል ይሉኛል፡፡ እንዲህ እያሉ እስከ “ፐ”  ድረስ ሊያስለፉኝ እኮ ነው” አላት፡፡
*   *   *
የልጆችን ጭንቅላት አለመናቅ ትውልድን መንከባከብ ነው፡፡ ትውልድን መንከባከብ ህብረተሰብን ከማናቸውም ችግር ማዳን ነው፡፡ ሁሉም ነገር ከቤታችን ይጀምራል፡፡ ልጅ ከቤት ሳይገራ

ውጪ ከወጣ በኋላ እናርምህ ብንለው ከንቱ ድካም ነው፡፡ የሀገራችንም የፖለቲካ ተዋንያን ከመሠረቱ ሳይስተካከሉ ደጅ ከወጡ በኋላ፣ አደባባይ ከወጡ በኋላ፣ ሥልጣን ላይ ከወጡ

በኋላ ማረቂያ አይኖራቸውም፡፡ ዐይን ያወጣ ሌብነት ሰለባ የሆንነው ለዚህ ነው፡፡ የትልቁ አሳና የትንሹ አሳ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር የባለተራ ደወል አይቀሬ ነው… For whom

the bell tolls እን
ዳለው ነው ሔሚንግዌይ! ተረኛ ጊዜውን ጠብቆ መግባቱ ግድ ነው፡፡ አገር ዘርፎ፣ አገር መዝብሮ እንቅልፍ የለም፡፡ ሼክስፒር እንደሚለው፤ “ከእንግዲህ እንቅልፍ የለችም
የእረፍት አድባር አጣች መቅኖ
ማክቤዝ እንቅልፍን ገደላት
በእኩለ - ሌሊት አፍኖ” … ለማለት የምንደፍርበት ጊዜ ነው፡፡ ዕውር ቢሸፍት ከጓሮ አያመልጥም እንደሚባለው፣ መርከብ ቢሸፍትም ከውሃው አይወጣም፡፡ ዛሬም፤ They

shout at most, against the vices they themselves are guilty of እንላለን፡፡ “ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮህ” እንደማለት

ነው:: የተነቃ ለታ ሁሉም እጁን ይሰጣል፡፡
“…የእጅ ሰንሠለት እረ አመቻቹ
ለእነ እንዳይበቃኝ ለቀማኞቹ!” መባሉ ለፌዝ አልነበረም፡፡
የኢትዮጵያውያንን መልካም ስም ያጐደፈ፣ ኢትዮጵያዊነትን የዘረፈ ከየትኛውም ባላንጣችን የማይተናነስ ጠላት ነው፡፡
“ገንዘቤን የሰረቀኝ ሰው ወሰደ እንበል ከንቱ ነገር
የእኔም የሱም የሷም ነበር
ግና ስሜን የሰረቀኝ የማያከብረውን ወስዶ እኔን በግልጽ አደኸየኝ” ማለት ይሄኔ ነው!
እስከ ዛሬ አያሌ ዘራፊዎችን፣ መዝባሪዎችን፣ የአየር - በአየር ሌቦችን ተሸክመን እዚህ ደርሰናል፡፡ አንዳንድ ተቋማት አይነኬ በመሆናቸው “እናውቃለን፤ ብንናገር እናልቃለን” በሚል

የፍርሃት መርህ፤ ስንበዘበዝ ከርመናል፡፡ መከላከያ አይነካም፡፡
ደህንነት አይጠቀስም፡፡ እገሌ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወንድም ስለሆነ አይደፈርም፡፡ እገሌ የእነ እገሌ ዘር ስለሆነ ባናስቀይመው ይሻላል ወዘተ እያልን፣ እያየናቸው በህዝብ ገንዘብና ንብረት

ሲላሲሎ ሲጫወቱ በዝምታ ተቀበልናቸው፡፡ አሁን መሸባቸው፡፡ እኛ ግን ዛሬም ገና አልነጋልንም፡፡ ቀጥለን ምን እናድርግ? አልተባባልንም፡፡ ነገን እንደፈራን፣ ነገን እንደሰጋን ነን፡፡ ይሄን

መሻር አለብን፡፡ አሁንም እየተለሳለሱ፣መፈክር እያሰገሩ የሚኖሩ ብዙ ጨዋ መሳይ “ታጋዮች” አሉ፡፡
“እባብ ቆዳው ለሰለሰ ብለህ ቀበቶ አድርገህ አትታጠቀውም” የሚባለው እኒህን እኩያን ዐይናችንን ገልጠን እንድናይና እነሱ ላይ ማነጣጠር እንድንችል ነው፡፡ እናነጣጥር፤ ግን ሳናልም

አንተኩስ!

Read 8015 times