Saturday, 10 November 2018 13:32

CYST… (ሲስት) ምንድነው?

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(3 votes)

ጡቴን ልመረመር ወደ አንድ ሆስፒታል ሄጄ ጡትሽ ካንሰር የለውም፡፡ ነገር ግን CYST (ሲስት) አለው የሚል መልስ ነበር የተነገረኝ፡፡ ይህ CYST  (ሲስት) የተባለ ነገር ምንድነው?
ከጋዜጣው አንባቢ በስልክ የተጠቆመ ወይንም የቀረበ ጥያቄ ነው ከላይ ያነበባችሁት፡፡ CYST (ሲስት) ምንድነው ?የጡት ካንሰርና ሲስት ልዩነታቸው ምንድነው? የሚለውን ማዮ ክሊኒክ ለንባብ ያበቃውን ታነቡ ዘንድ እነሆ፡፡

በጡት ውስጥ የሚከሰት CYST (ሲስት)፤
ከላይ በስእሉ እንደምትመለከቱት በጡት ውስጥ የሚገኝ CYST (ሲስት የተባለ ነገር በውሀ የተሞላ እንደ ፊኛ ወይንም ከረጢት ያለ አበጥ ብሎ የሚሰማ ነገር ነው፡፡ ሲስት በቁጥር አንድ ብቻ ሆኖ የሚታይ ሳይሆን ቁጥሩ ሊጨምርም የሚችል ነው፡፡ በጡት ውስጥ ይከሰታል ሲባልም በአንዱ ወይንም በሁለቱም ጡት ውስጥ ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም ይህ CYST (ሲስት) የተባለ ነገር ከካንሰር ጋር የሚያያዝ አይደለም፡፡ ልክ ውሀ እንደተሞላ ፊኛ የሚቆጠር ነው። በጡት ውስጥ የሚገኘው CYST (ሲስት) የተባለ ውሀ የያዘ ከረጢት የህክምና እርዳታ የሚያስፈልገው አይደለም ቢባልም ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ በመጠኑ ከፍ ያለ እና የህመም ወይንም ምቾት የመንሳት ባህርይ ሲኖረው ሐኪምን መጎብኘት ግድ የሚሆንበት ጊዜ ይኖራል፡፡
CYST (ሲስት) በጡት ውስጥ ሊከሰት የሚችለው ብዙ ጊዜ የወር አበባ ከማረጥ በፊት ሲሆን ሴቶች በእድሜያቸው ከ35-50/ ሲደርሱ የሚታይ ይሆናል። ይህ ማለት ግን በማኝኛውም እድሜ ላይ ባሉ ሴቶች ጡት ውስጥ አይከሰትም ማለት አይደለም፡፡
የ CYST (ሲስት) ምልክቶች፤
CYST (ሲስት) በጡት ውስጥ ሲኖር የማይጎረብጥ ነገር ግን ጡትን ሲዳስሱ ወይንም ሲነካኩት የሚንቀሳቀስ የሚመስል፤
በጡት ጫፍ በኩል ንጹህ ፈሳሽ ወይንም ብጫ ፤አረንጉዋዴ መሰል ወይንም ጥቁር ቡናማ የሆነ ፈሳሽ ሊታይ ይችላል፡፡
በጡት ላይ ሕመም ወይንም በትንሽ ምክንያት ጡት ሲነካካ የአለመመቸት ስሜት ሊኖር ይችላል፡፡
የወር አበባ በሚመጣበት ወቅት የጡት መጠን መጨመር እና የህመም ስሜት ሊኖረው ይችላል።
የወር አበባ ካለፈ በሁዋላ የጡት መጠኑም ሆነ የሚሰሙት ሌሎች የህመም ስሜቶች ይቀንሳል፡፡
በጡት ላይ CYST (ሲስት) መኖሩ በምንም ምክንያት በካንሰር ለመያዝ ምክንያት አይሆንም። ነገር ግን ጡት ውስጥ CYST ካለ በጡት ውስጥ የሚፈጠሩ ሌሎች የጤና ለውጦችን በቀላሉ ፈትሾ ለማግኘት ሊያስቸግር እንደሚችል መዘናጋት አይገባም። ስለሆነም ከጤና ባለሙያ ምክር ወይንም ምርመራ ጋር መራራቅ አይመከርም፡፡ በተጨማሪም ማንኛዋም ሴት የጡትዋን ሁኔታ በመረዳት በኩል ትክክለኛው ግንዛቤ እና እውቀት ሊኖራት ይገባል፡፡  
CYST (ሲስት) የመፈጠሩ ምክንያት፤
በሙያው የተካኑት ሰዎች በትክክለኛው መንገድ CYST (ሲስት) ለመፈጠሩ ምክንያቱ ይህ ነው ብለው መናገር እስከአሁን አልቻሉም፡፡ ነገር ግን በሆርሞን ሁኔታ መለዋወጥ እና በየወሩ በሚከሰተው የወር አበባ ምክንያት ሊፈጠር ይችል ይሆናል የሚሉት ነገር ሊኖራቸው ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከመጠን ያለፈ ኢስትሮጂን በሰውነት ውስጥ ሲኖር ለ CYST (ሲስት) መፈጠር ምክንያተ ሊሆን ይችላል የሚል ግምትም አለ፡፡  
በጡት ውስጥ የሚከሰቱት CYST (ሲስት) የተባሉት ነገሮች በመጠናቸው የተለያየ ስያሜ ይኖራቸዋል፡፡
Microcysts-፡ ማይክሮሲስትስ የሚባሉት መጠናቸው በጣም ትናንሽ ሲሆኑ ጡትን በመዳሰስ ብቻ መኖራቸውን ለማወቅም አስቸጋሪ ነው፡፡ እነዚህ ሊታዩ የሚችሉት ጡት በ ultrasound እና በ mammography ሲመረመር ብቻ ይሆናል፡፡
Macrocysts -፡ማክሮሲስትስ በመባል የሚለዩት መጠናቸው ትልቅ የሚባሉ ሲሆን ከ2.5-5/ሴንቲ ሜትር ድረስ ያደጉ ናቸው፡፡ እነዚህኞቹ በንክኪ ወቅት በጡት ውስጥ የሕመም ስሜትን የሚፈጥሩ እና ምቾት የሚነሱ ናቸው፡፡   
ጠያቂያችን ያቀረቡት በጡት ውስጥ የሚፈጠር የCYST (ሲስት) ምንነት ከላይ እንዳነበባችሁት ሲሆን ከጡት ካንሰር ጋር ምንም የማይገናኝ መሆኑን ባለሙያዎች መስክረዋል፡፡  
የጡት ካንሰር፡
የጡት ካንሰር በአለም አቀፍ ደረጃ በሴቶች ላይ በብዛት የሚታይ እና በገዳይነቱም በሁለተኛነት ደረጃ የተፈረጀ ነው፡፡ የጡት ካንሰር በሴቶች ላይ ብቻም ሳይሆን በወንዶች ላይም በመጠኑም ቢሆን እንደሚታይ እሙን ነው፡፡ ወደ 90% የሚሆነው የጡት ካንሰር የሚፈጠረው ወተት በሚፈጠርበት ወይንም ወተቱን ወደመጥቢያው በሚወስደው መስመር ላይ ነው፡፡ የጡት ካንሰርን በጊዜው ማለትም ሳይስፋፋ በምርመራ ከተገኘ ማዳን ይቻላል፡፡ ነገር ግን ጊዜ ወስዶ ተስፋፍቶ ከተገኘ አደጋው ከፍ ያለ ይሆናል፡፡
ለጡት ካንሰር በምክንያትነት የሚጠቀሱ፤
እድሜ፡-
ሴቶች በእድሜያቸው ከ50/ አመት በላይ ከሆኑ ለሕመሙ ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡
በጡት ካንሰር ምርመራ የግል ታሪክ፤
አንዲት ሴት ቀደም ብላ አንዱን ጡትዋን በካንሰር ምክንያት ታክማ ከነበረ እና እርዳታ ከተደረገላት ጊዜ ወስዶ ሕመሙ እንደገና በሁለተኛው ጡት ላይ ሊከሰት እንደሚችል ይታመናል፡፡
የጡት ካንሰር በቤተሰብ ውስጥ፤
በቤተሰብ ውስጥ የጡት ካንሰር ሕመም ከነበረ ሕመሙ በዘር እንደሚተላለፍ እሙን ነው፡፡
ኢስትሮጂን የተባለ ሆርሞን፤
ሴቶች ኢስትሮጂን የተባለው ሆርሞን መጠናቸው በሚያድግበት ወቅት በጡት ካንሰር ለመያዝ ሁኔታዎች ሊመቻቹ ይችላሉ፡፡
የአኑዋኑዋር ዘዴዎች፤
ከመጠን በላይ ውፍረት…የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ …አልኮሆል መጠጣት …ከፍተኛ ለሆነ የአየር ብክለት መጋለጥ የመሳሰሉት ለጡት ካንሰር መንገድ ሊከፍቱ ይችላሉ፡፡


Read 1279 times