Saturday, 03 November 2018 16:15

አብዮት- ተስፋ የቆረጡ ሰዎች ሥራ! - (ወግ)

Written by  ከቃል ኪዳን
Rate this item
(2 votes)

   አብዮት ተስፋ የቆረጡ ሰዎች ሥራ ነው፡፡ ሰዎች ተስፋ ሲቆርጡ አብዮትን እንደ ፊኛ ያፈነዳሉ። አብዮተኞች ከሀዲዎች ናቸው፡፡ ፈጣሪን ክደው ከሰይጣን  ይወግናሉ፤ ከሰይጣን የገቡትን የደም ውል አፍርሰው፣ ወደ ፈጣሪ ይጠጋሉ፤ ነፍጥ አንስተው ተበላሽቷል ያሉትን መንግስት አንቀው ሲያበቁ፣ ከመሬት ይፈጠፍጣሉ፤ የወረደን መንግስት ለመመለስ እግራቸውን ይቸክላሉ፤ መልክ ብቻ ሆና ከሀሜት በቀር ሙያ ከጎረቤት መቅሰም ያልቻለች ሚስትን ወጥ ከእነ ድስቱ ይገለብጣሉ - አብዮተኞች ገልባጮች ናቸው፡፡
አብዮት ድመት ናት፡፡ ትፋቷን የምትበላ፤ ሂሷን መልሳ የምትውጥ፤ አብዮት ውሻም ናት፡፡ አብዮተኞች ደግሞ ድመታዊነትንና ውሻዊነትን በአንድ የያዙ ደም ፍላታሞች ናቸው - ቆርጦ መጣል እንጂ የቆሰለውን አጥቦ ማሠር የማይችሉ - ቆራጮች ናቸው፤ አብዮተኞች፡፡
ያኔ ክረምትና ጨለማ ሆኖብኝ ሳለ፤ መሬቱን በእግሬ እየዳበስሁ ለስደት ዳር፣ ዳር ስል፤ መኖሯን እንኳ የማላውቃት አብዮት በውስጤ እየተንተከተከች፤ ክዳኔን ከፍ፣ ከፍ እያደረገች አስቸገረችኝ - ልትገነፍልና በግንፍሏ ልታጨማልቀኝ፡፡ ደርሼ ‹ፈሪ ለእናቱ ነዉ!› የሚለውን የሰላሙ ጊዜ እንጉርጉሮዬን ትቼ፣ ‹የወንድ ልጅ እናት ታጠቂ በገመድ…› እያልኩ ሱሪዬን መታጠቅና የጫማ ማሠርያዬን ማጠባበቁን ተያያዝኩት፡፡
ትጥቄን ታጥቄና አጥብቄ ስጨርስ፣ እርዳታ ፍለጋ ዞር  ዞር ብዬ ተመለከትኩ፡፡ በዙርያዬ ያሉት በጋና ብርሃን ሆኖላቸዉ፤ ያኔ በደጉ ጊዜ የነሱን እሮሮ፤ ‹ጆሮ ዳባ ልበስ› ብዬ እንዳለፍኩት ዝም አሉኝ፡፡ ጥቃትህ ጥቃቴ ነው ብሎ መሳርያውን የሚወለውል፤ ፈረሱን የሚጭን ባልንጀራ አጣሁ። እናቴ ሞታብኝ ሳለቅስ፤ እናቱ ገበያ ሄዳበት የሚያለቅስና የሚያላቅሰኝ እንኳን ጠፋ፡፡ ሁሌም እንደዚህ ነን፡፡ ሀዘናችንና ደስታችን አይገጥምም፡፡ አንድ የሚያመሳስለን ነገር ቢኖር፣ ከደጃፋችን የጣልነው ዳስ ብቻ ነው፡፡ እኔ ውስጥ ይለቀሳል፤ እነሱ ጋ  ዳንኪራ ይረገጣል፡፡
አቃባሪ አጣሁ ብሎ ማን በድን ታቅፎ ይኖራል? አብዮት ጀማሪን ብቻ ነው የምትፈልገው፡፡ ገሚሱ ‹በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል?› ብሎ አንድ፣ አንድ እያለ መምጣቱ አይቀርም። የተቀረው (በሌላ ወገን ያለውም ቢሆን) ‹ልታሸንፋቸው ካልቻልክ ተቀላቀላቸው› ብሎ ማተቡን በጥሶ ይመጣል፡፡ ደግሞ ጊዜ ጨረቃ ናት፡፡ ዛሬ ብትሞላ ነገ ትጎድላለች፡፡ ቆይ፣ ቆይ ጊዜ በጨረቃ ዑደት የምትለካው ጨረቃ ሞላ፣ ጎደል/ተለዋዋጭ ስለሆነች ይሆን እንዴ?
በዓለም ላይ የተካሄዱ ጦርነቶች በአብዛኛው የተቆሰቆሱት የግል ዓላማቸውን (በብዛት የመጥፎ ሰዎች ዓላማ) ለማሳካት በሚጥሩ ሰዎች ነው፡፡ በዴሞክራሲ ስም ታላላቅ ፈላጭ ቆራጮች ተነስተዋል - አብዮተኞች ነን ባዮች፡፡ በርዕዮተ ዓለማት ሳቢያ ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሏል፡፡ ጥቁር አፈር በደም ቀልቷል። ምናልባት ከአብዮተኞች መፈጠር በኋላ ይሆናል ቀይ አፈር የሚባለው ነገር የመጣው፡፡
እኔ ብቸኛው፤ ራሴን ነጻ ላወጣ ሁሉም በእስር ላይ እንዳለ መስበክ ጀመርኩ፡፡ ለህዝብ ጥቅም ቅድምያ እንደምሰጥ፤ እራሴን ለመስዋዕትነት እንዳዘጋጀውና  እኔና አንድ ጥይት እስክንቀር ድረስ  እንደምፋለም አወጅኩኝ፡፡ ለጥቄም እራሴን እንኳን በሚያርበደብድ ድምጽ……
‹‹አንዳንዴ ወንድ ይውጣኝ እንጂ! ወተት ብቻ እኮ ነው ሲገፉት የሚወድ!›› ስል ፉከራውንም አስከተልኩ። ውስጤ ግን ፉከራዬን አልወደደውም፡፡
‹‹ቆይ ወተት ሲገፉት እንደሚወድ በምን አረጋገጥህ? ወተቱ ሲገፋ በደስታ ፈገግ ሲል አይተኸው ነበር እንዴ? ይልቅ ሌላ የሚመስል ፉከራ ካለህ ወዲህ በል!›› አለኝ፡፡
ውስጤ እውነቱን ነው፡፡ የሰው ልጅ በተፈጥሮው ሊያውቀውና  ሊደርስበት የተሳነውን ነገር ማገወዝ (ግዑዝ ማድረግ) ይቀለዋል፡፡ አንድ ጊዜ ስለ መረጃ ልውውጥ (መረጃ ከአንዱ ወደ ሌላው ሲተላለፍ እንዴት ቅርጹንና ይዘቱን እየቀየረ እንደሚመጣ) በዝንጀሮዎች ላይ የተደረገ ጥናት ተመልክቼ ነበር። በጥናቱ ላይ ስድስት የሚደርሱ ዝንጀሮዎች በአንድ ክፍል ውስጥ ታጉረው ይታያሉ፡፡ ክፍሉ ወስጥ ጣራው ጋ የሚያደርስ መሰላል ቆሟል፡፡ መሰላሉ አናት ላይ፤ ጣራው ላይ ብዙ ዘለላዎች ያሉት ሙዝ ተሰቅሏል። ዝንጀሮዎቹ በመስገብገብ ሙዙን ሊያወርዱ እየተሸቀዳደሙ መሰላሉ ላይ ወጡ (መቼም እነሱ የሙዝ ነገር አይሆንላቸዉም)፡፡ የመሰላሉ ጫፍ ላይ ሲደርሱ ግን ቀዝቃዛ ውሃ ተርከፈከፈባቸው፡፡ ሁሉም እየደነገጡ ወረዱ፡፡ እንደገና ሲሞክሩም ተመሳሳይ ነገር አጋጠማቸው፡፡
ቀጥሎ አጥኚዎቹ፤ አንዱን ዝንጀሮ አስወጡና ሌላ አዲስ ዝንጀሮ አስገቡ፡፡ አዲሱ ዝንጀሮ ገብቶ ክፍሉን ሲቃኝ፣ ጣራው ላይ ምን የመሰለ ሙዝ ተሰቅሎ ተመለከተ፡፡ ደግሞ ፈጣሪ ሲረዳው መሰላልም አለ። ዝንጀሮው እሮጦ መሰላሉ ላይ ሲወጣ፣ የተቀሩት በጩኸትና በንክሻ አስወረዱት፡፡ አጥኚዎቹ አንድ፣ አንድ እያሉ ነባሩን እያስወጡ፤ መሰላሉ ላይ ሲወጡ ቀዝቃዛ ውሃ የተርከፈከፈባቸውን ዝንጀሮዎች በሙሉ በአዲስና ውሃውን ባላዩት ቀየሯቸው፡፡ ከዛ ከአዲሶቹ መሀል አንዱን አስወጡትና ሌላ ሶስተኛ ትውልድ ዝንጀሮ አስገቡ፡፡ እሱም ሌሎቹ እንዳደረጉት፣ ሙዙን ለማውረድ ዘሎ ከመሰላሉ ላይ ተሰቀለ፡፡ ይሄኔ የተቀሩት ዝንጀሮዎች ተጯጩኸዉ አስወረዱት፡፡
እንግዲህ ዝንጀሮውን መሰላሉ ላይ ከመውጣት ያገዱት፤ ምኑንም ያላዩት ዝንጀሮዎች ናቸዉ፡፡ አጥኚዎቹ ጥናቱን ሲያጠቃልሉ፤ ዝንጀሮዎቹ ምንኑንም ሳያውቁ ቅድም የነበሩት ዝንጀሮዎች ተከትለው መጮኻቸውን ሰዎች በቃል ብቻ የሚያውቁትን፤ ከጥንት ሲተላለፍላቸው የነበሩትን ነገሮች ተቀብለው ከማስጋባታቸዉ ጋር አያያዙት፡፡
ይህ በዝንጀሮዎች ላይ የተደረገ ጥናት፣ እንደዚህ ዓይነት ድምዳሜ ላይ ሊያደርሰን ይችላል ወይ? እዚህ ጋ መስማት ስለማንችል ብቻ እንስሳት መናገር አይችሉም የምንል እኛ ማን ነን? ዝንጀሮዎቹስ አዲስ የሚመጣውን ዝንጀሮ በዝንጀሮኛ……
‹‹እባካህ አሁን እነዚህን ነጫጩባዎች አምነህ ነው እዚህ የብረት ዛፍ ላይ የምትሰቀለው? ይልቅ ሙዙን ለማውረድ ብለህ ቀዝቃዛ ዝናብ እንዳታዘንብብንና ብርድ እንድታስመታን!›› ብለውት ቢሆንስ? እንደውም አንዱ እያሳለ፤
‹‹ኧረ እኔ እንደውም እዚህ ከመምጣቴ በፊት ሾላ ዛፍ ላይ ፈሽ ብዬ ተቀምጬ ሳለ፤ አብዮተኞች መጥተው ሾላውን በድንጋይ ሊያወርዱ ሲሉ፤ ደንግጬ ከሾላው ዛፍ ላይ ወደ ኮምጣጤ ዛፍ ስዘል፣ ጎኔን ብርድ መቶኝ፣ ስንት ነገር አድርጌ መሰላችሁ የተወኝ›› ብሎስ ቢሆን፡፡
ንክሻቸውም አናምንም/አንሰማም ያሉትን ለማሳመን የተደረገ ስላለመሆኑ ምን ማረጋገጫ ማቅረብ እንችላለን። ለማንኛውም ወተቱ ሲናጥ ደስ አለውም፣ አላለውም፤ ውስጤን ችላ ብዬ፤ ወጌን ለማሳመር ያህል ‹ወተት ብቻ እኮ ነው መገፋት የሚወድ› ብዬ አብዮቴን ቀጠልኩ፡፡ መፈክርስ ለምን ይቀርበኛል? ግራም፣ ቀኝም እጄን እያወናጨፍሁ፤
‹‹እኔ ስደቴ በጨለማና በክረምት ሆኖ፤ እነሱ ደስ ያላቸው ይውደሙ!›› አልኩ፡፡ በቅርቤ ያገኘሁትን ሁሉ ልወረውር እያሟሟቅሁ፤ የሚወረወርበትን ጥበቃ ገባሁ፡፡
ድንገት ታሪክ ተለወጠ፡፡ አብዮቴ ሳይፈነዳ፤ መከራንና መከፋትን የቋጠረው እባጬ ፈነዳ፡፡ ቤቴ በር ላይ ድንጋይ ብቻ ከነበረው የከረጭ ድንጋይ ውስጥ የነበረው አንበሳ በቀራጺው ተፈልፍሎ ወጣ፡፡ የጎደለው ማጀቴ ሞላ፡፡ የአስቤዛዎቹ ትንፋሽ ቤቴን አሞቀው። አልጋዬም ተጋሪ አገኘና መኝታዬ አንድም በተጋሪዬ ሙቀት፤ ሌላም በመዋጮው በተገኘው ሙቀት፤ እጥፍ ድርብ ሞቀ፡፡ መጀመርያ ከቤቴ ወደ ደጅ መውጣት አስጠላኝ፡፡ ቀጥሎም ከመኝታዬ ወደ ቤቴ መውጣት አስጠላኝ። ከዚያም ከፍቅረኛዬ ዕቅፍ ወደ መኝታዬ መውጣት አስጠላኝ፡፡
የፍቅረኛዬን ችቦ የሚሞላ ወገብ እንዳቀፍኩ ለመኖር ስል፤ ለመፈክር ሰቅየዉ የነበረውን እጄን አወረድኩ፤ በሌላ እጄ ይዠው የነበረውን ነፍጥ አሽቀንጥሬ ወረወርኩት፡፡ በእንጭጭ የነበረችውን አብዮቴን እራሴ ቀጥፌ በላኋት፡፡
‹‹ጥያቄዬ ምን እንደነበረ እስካሁን ባይገባኝም አሁን ጥያቄዬ አንጀት አርስ መልስ አግኝቷል!›› አልኩት ለራሴ፡፡
ደግሞስ ስሜት ለማይሰጥ ጥያቄ፤ ስሜት የሚሰጥ መልስ አነሰው እንዴ? ሌሎቹም ጋ ቀጥ ብዬ ሄጄ፤ ለጥ ብዬ እጅ ነሳሁና ‹‹ጥያቄአችሁ በኔ ሆድ መሙላት ተመልሷል!፡፡›› አልኳቸው፡፡
“ደንታህ ነው!” ሲሉ ወደኔ ያልመለሱትን ፊታቸውን ነሱኝ።
 “ደንታዬ ነው!” ስል ተውኳቸው፡፡
“ላለው ይጨመርለታል፡፡” ያለው ደስተኛ ነው። ‹ተመስገን› ማለት አይጠበቅበትም፡፡ ፊቱ ላይ የሚነበበው ደስታና ፈገግታ እራሱ ምስጋና ነው፡፡ ፊትን አጨፍግጎ በፍርሃት እየራዱ ተመስገን ማለት ምን የሚሉት ‹ኩመካ› ነው?
ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ፊቷን ወደኔ አዞረች፡፡ የኔን ደስታ ወዳዋለች፡፡ እደጃፌ ከጣራዬ በላይ የምሰቅለው የራሴን ጸሐይና ጨረቃን ገጸ-በረከት አድርጋ ሰጠችኝ፡፡ ለቤቴ ፍቅረኛዬ አለች!፡፡ እሳት እንኳን የምናያይዘዉ ከጸሐይቱ ነዉ፡፡ ከፍቅሬ ጋር ፍቅር ማዉራት ስንፈልግ ጸሐይቱን ገልል አድረገን ጨረቃን እንጎትታታለን፡፡ ከፍቅር ጋር ፍቅር ማዉራት እንዴት ደስ ይላል መሰላችሁ፡፡ በአይበሉባዬ ገለል ያደርግኋት ጸሐይ እራሱ ይሄን ነገር ስለምትወደዉ እስራችን ተቀምጣ ምን እንደምናወራ እየሰማች ሀሴት ስታደርግ ትዉላለች፡፡
ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ፊቷን ወደኛ ስታዞር፤ ሌሎቹን ፊት ነሳቻቸዉ፡፡ አይሆንም ብለዉ ወጡ፡፡ እንድቀላቀላቸዉ አዩኝ
‹‹ሥራ አጣን፣ እራበን፣ ታረዝን›› አሉኝ፡፡
‹‹ለምን ሥራ ስታጡ፣ ስትራቡና ስትታረዙ ብቻ ሥራ አጣን፣ እራበን እና ታረዝን ትላላችሁ?›› አልኋቸዉ፡፡
‹‹እና ሥራ ካለን፣ ከጠገብንና ከለበስን ለምን ሥራ አጣን፣ እራበንና ታረዝን እንበል?›› ሲሉ አፈጠጡብኝ።
‹‹እኔንጃ!›› አልኋቸዉ፡፡ መልሼም
‹‹ቆይ በሁሉ አመስግኑ ይል አይደለም ወይ?›› ስል ጠየቅኋቸዉ፡፡
‹‹አዎ እርግጥ ነዉ ይላል!፡፡›› ሲሉ መለሱልኝ፡፡
‹‹ታድያ በሁሉ ብታማሩ ምን ክፋት አለዉ?›› ስል ጠየቅኋቸዉ፡፡
ወንድሜ አንዲት ድቡልቡል ደንጋይ አነሳና ከሰልፈኞቹ ፊት ወጣ፡፡ ሰልፈኞቹ በእጃቸዉ ምንም አልያዙም፡፡ ምንም ባልያዙ አብዮተኞች መሀል ድቡልቡል ድንጋይ እንኳሱ በትረ መንግሥት ሆና መሪ ታደርጋለች፡፡ ወንድሜ የመሪነቱን ቦታ ሲይዝ ከላይ እስከታች ገላመጠኝ፡፡ አስተያየቱ ‹አሁን እኔና አንተ የመደብ ትግል ላይ ነዉ ያለነዉ፡፡ ታማኝነቴ ለመደቤ ነዉ!› የሚል ድብቅ መልዕክት አለዉ፡፡
‹‹አሁን አንተ ደግሞ ምን ሆንኩ ብለህ ነዉ? ሥራ ከፈታህ ገና ሁለት ዓመትህም አይደል? ምንድ ነዉ እንዲህ በአንዴ ተስፋ መቁረጥ?›› አልሁት፡፡ አይቶኝ ተንገሽግሾ ሲያበቃ ምራቁን ጢቅ አለ፡፡
ሰዉን ሲጠየፍ ጢቅ የሚለዉ ምራቅ ያለዉ ሰዉ እንዴት እንደዚህ ተስፋ ይቆርጣል? ሥራስ ጥቅሙ ሥራ የሌላቸዉን ለመናቅና እነሱ ላይ ለመኮፈስ አይደል እንዴ? ታናሼን እንዴት እንደማረጋጋዉ ሳወጣና ሳወርድ ግራ ተጋባሁና የራሴ መረጋጋት ጠፋ፡፡ ካጽናናዉና ካጸናዉ በሚል ‹‹ታዉቃለህ እኔም ቢሆን የያዝሁትና የምሠራዉ የማልፈልገዉን ሥራ ነዉ፡፡ አንተም ቢሆን ፈልገህ ያጣኸዉ የማትፈልገዉን ሥራ ነዉ፡፡ ታድያ እኔ እና አንተን ምን ለየን? ስለዚህ አርፈህ ተቀመጥ!›› አልሁት።
‹‹እሱንና አንተን የሚለያችሁ ከሌለ ለምን አትቀላቀለንም?›› አለኝ አንድ አብሮ አደጋችን፡፡ ድሮ ልዉደደዉ አልዉደደዉ ባላዉቅም ይህን በማለቱ ግን አብሮ አደጌን ጠላሁት፡፡
‹‹ተዉት እሱን!፡፡ አሁን እሱ ባለጊዜ ነዉ፡፡ አታዩትም ከደጃፉ የሰቀላቸዉን የግሉን ጸሐይና ጨረቃ? ፍቅሩ እራሱ እንዴት እንደምታበራ ተመልከቷት፡፡ አሁን እሱ ጌታ ሆኗል!። ችግራችን አይታየዉም!›› አላቸዉ ከኔ በላይ እሱን ጠንቅቆ የሚያዉቀዉ የለም በሚል ትምክህት ደረቱን ነፍቶ፡፡ ሁሉም በመስማማት አጉረመረመ፡፡
‹‹አሁን እኛ እንሂድና ነገርየዉን እንደሾላ ቢያቅተን እንደኮምጣጤ በድንጋይ እናወርደዋለን፡፡›› ሁሉም በፉጨትና በጩኸት ድጋፍ ሰጡት፡፡
ልጅ እያለን እኔና ይሄ ወንድሜ፤ ግማሽ አካሉ ተንዥርግጎ ከአጥር ዉጪ ያለዉን የጎረቤታችንን ኮምጣጤ ተደብቀን በድንጋይ እናወረድ ስንታገል ነበር የምንዉለዉ። ከምንወረዉራቸዉ ድንጋዮች አብዛኛዎቹ የኮምጣጤዉን ዛፍ ስተዉ የጎረቤታችንን ጣራ ይወግሩ ነበር፡፡ ጣራቸዉ በድንጋይ ሲወቀር የሰሙት ጎረቤቶቻችን ተሯሩጠዉ ቢወጡም እኔና ወንድሜን ስለማያገኙን እናታችንን በአንደርቢ ቤቴን እያስወገርሽ ነዉ ሲሉ ይጨቃጨቋት እንደነበር አስታዉሳለዉ። አንድ ቀን እኔና ወንድሜ እናታችንን
‹‹አንደርቢ ግን ማነዉ?›› ስንል ጠየቅናት፡፡
‹‹ሾላ ግን ምንድነዉ?›› ሲል መሪዉ ወንድሜ ዞሮ ተመሪዎቹን ጠየቃቸዉ፡፡
ሁሉም እርስ በርስ ተያይተዉ ፍንጭ ስላጡ ሆ እያሉ የሚወረወር ድንጋይ ፍለጋ መሬት ቧጠጡ። አብዮቱ ጥቅሙ ዞሮ፣ ዞሮ ለእናንተዉ ነዉ በሚል የድሃዉን የእንጨት አጥር ነቀነቁ፡፡ ጣራቸዉን ነፋስ ነቅሎ እንዳይወስድባቸዉ ያስያዙበትን ድንጋይ ተንጠራርተዉ አወረዱ፡፡ አብዮተኞቹ ጊዜን በጉልበት ወደራሳቸዉ ሊያዞሩ ተሰናዱ፡፡
‹‹እንሂድባቸዉ! እንሂድባቸዉ!......ምንም አያመጡም እንሂድባቸዉ!›› ተባባሉ፡፡
ነፋስ ከምስራቅ ወደምዕራብ እየነፈሰ ‹‹መከራ ሊመጣ ነዉ! መከራ ሊመጣ ነዉ!›› እያለ አስጠነቀቀ። ጥቁሩ ደመና ከመጠን እላፊ ደም መፋሰስ ቢመጣ አጥቂዉንና ተከላካዩን በዉሃ ሊበትን በተጠንቀቅ ቆመ።
የቻሉት የባሰ ቢመጣ አገራቸዉን ሊለቁ፤ የአየር ትኬታቸዉን ቆርጠዉ፤ ቦሌ ኤርፖርት አካባቢ ድንኳኖቻቸዉን ተከሉ፡፡ ያልቻሉት ግርግሩ እስኪያባራ ጊዜ የሚገፉበትን አስቤዛ መርካቶ ሄደዉ ገዝተዉ፤ መኪናቸዉን ሞልተዉ በደሃዉ አፍንጫ ሥር አለፉ፡፡ ድሃዉ ምጎ አፍንጫዉ ዉስጥ እንዳይከታቸዉ፤ መኪኖቹ ፍጥነታቸዉ ከሚግ ይበልጣል፡፡ አስቤዛዉ ማጀታቸዉን መሙላቱን፤ ‹ዳዲ› እና ‹ማሚ› የገዙት ዘይት ከወጥ መሥርያነት አልፎ ለቺብስ እና ለፈንዲሻ እንደሚተርፍ ያረጋገጡት ልጆች፤ እቤት መቀመጡ እንዳይሰለቻቸዉ ወጥተዉ እቅፍ ሙሉ ፊልም ተከራዩ፤ ‹ፍላሽ ዲስኮቻቸዉ› እስኪያብጡ ድረስ ፊልም አስጫኑ፡፡
ዉሃ ስንቁ ደሃዎች እቤት ቁጭ ብዬ ከማዛጋ በሚል አብዮተኞቹን ተቀላቀሉ፡፡ እኔ እና እሷ ግን ከደጃፋችን ያለችዉን ጸሐይ አጥፈተን፤ ጨረቃችንን አድምቀን ከበለሱ ዛፍ ስር የ‹ፐርዢያ› ምንጣፍ አነጠፍንና ተቃቅፈን ቁጭ አልን፡፡ ኦማር ካያም ያስተረፈዉን ወይን አንስተን ጽዋችንን ሞላን፡፡ ወይኑን ተጎንጭቼ፤ የፍቅሬን ዓይኖች በፍቅር እያየሁ የመጀመርያዋን ሩብያት በቃሌ ወጣሁላት፡፡ ድንገት ወንድሜ የመጀመርያዋን ድንጋይ ወረወረ፡፡ የወንድሜን የመጀመርያ ዉርወራ ተከትለዉ ሊሰዉ(የፈለገ ያጥብቀዉ ያሻዉ ያላለዉ) አብዮተኞች በጆሮዎቻችን ክፈፍ ላይ እንዳየወድቁ እየተጠነቀቁ፤ እየጨፈሩ ሲያልፉ ሰማን፡፡
‹‹እሺ ፍቅሬ!...›› አልኳት ስለአብዮተኞቹ እንዳታስብና ጭንቀት ዉስጥ እንዳትገባ በመስጋት፡፡ ፍቅሬ አንድ የበለስ ፍሬ ቆርጣ ዘረጋችልኝ፡፡
‹‹ትዝ ይልህ እንደሆነ የባለፈዉን ጀምረህ አልጨረስከዉም›› አለችኝ ማንቁርቴን በስሱ እየነካካች፡፡
‹‹አውቃለሁ! የዛኔ መች አወቅሁሽ፡፡ አንቺ ካልሺኝ አሁን የሰጠሺኝን እንክት አድርጌ ከበላሁ በኋላ ጉሮሮዬ ላይ የተቀረቀረዉንም እንደ ምንም እዉጠዋለሁ፡፡›› አልኳትና ግንባሯን ሳምኳት፡፡ ድንገት ከርቀት አንድ ግምባር በአንዳች ነገር ሲበረቀስ ሰማን፡፡ የማን ግምባር ይሁን? በምን ተበርቅሶ ይሆን?


Read 1278 times