Saturday, 03 November 2018 16:09

አዋሽ ኢንሹራንስ ያልተጣራ 140 ሚ ብር ማትረፉን ገለፀ

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)


     አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ ሰኔ 30 ቀን 2018 በተጠናቀቀው በጀት ዓመት፣ ከታክስ በፊት ያልተጣራ 140 ሚሊዮን ብር ማትረፉን ያስታወቀ ሲሆን አምና የተገኘው የተጣራ ትርፍ ካቻምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር፣ የ46 በመቶ ብልጫ በማሳየት፣ 128 ሚሊዮን ብር እንደነበር ታውቋል፡፡
ኢንሹራንስ ኩባንያው የዛሬ ሳምንት በሂልተን ሆቴል ባካሄደው 24ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤና 9ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ፣ የኩባንያውን ዓመታዊ እንቅስቃሴ ሪፖርት ያቀረቡት የዲሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ሃምዲሳ ዋቅወያ፤ ጠቅላላ መድን ሥራ ካቻምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር 11 በመቶ ዕድገት በማሳየት ከ604.6 ሚሊዮን ብር በላይ አረቦን መሰብሰቡን፣ በሕይወት መድን ዋስትናም ካቻምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር የ27 በመቶ ብልጫ በማሳየት፣ 69.5 ሚሊዮን ብር በማግኘት፣ በሁለቱም የሥራ ዘርፎች 674.1 ሚሊዮን ብር አረቦን ገቢ በመሰብሰብ፣ 12.5 በመቶ ዕድገት መቀዳጀቱን ገልፀዋል፡፡
ኩባንያው በጠቅላላ መድን የሥራ ዘርፍ ብቻ 246.66 የካሳ ክፍያ አጋጥሞት በገባው ውል መሠረት በብቃት በመወጣት ለደንበኞቹ አለኝታነቱን አረጋግጧል ያሉት አቶ  ሃምዲስ፤  ከዚህ ውስጥ 74 በመቶ ወይም 233.97 ሚሊዮን ብር በሞተር የሥራ ዘርፍ የተከፈለ መሆኑንና ይህም የካሳ ክፍያ በመቶኛ ሲሰላ 57 በመቶ መሆኑ ተስፋ ሰጪና አበረታች ነው ብለዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኩባንያው ሁለት አዳዲስ ቅርንጫፎችና አራት አገናኝ ቢሮዎች በመክፈት፣ የቅርንጫፎቹን ብዛት አንድ የሕይወት ዓቢይ ቅርንጫፍን ጨምሮ 46 መድረሳቸውንና ከአራት አገናኝ ቢሮዎች ጋር የአገልግሎት መስጫዎቹ ብዛት 50 መድረሱን ተናግረዋል፡፡
ኩባንያው በኢንቨስትመንት መስኮች በመሰማራት በቦሌ ክ/ከተማ በመገንባት ላይ ያለ ባለ 4 ፎቅ ጅምር ሕንፃ በ51 ሚሊዮን ብር፣ በልደታ ክፍለ ከተማ ለቢሮ አገልግሎት የሚውል በ3 ሚሊዮን ብር መግዛቱን፣ 1.6 ሚሊዮን ብር ኢንቨስት በማድረግ ከሁለት ተቋማት አክሲዮን መግዛቱን፣ በ4.7 ሚሊዮን ብር ሶፍትዌር በመግዛት የአቶሜሽን ፕሮጀክቱን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገሩን፣ በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ከ60.3 ሚሊዮን በላይ ኢንቨስት ማድረጉን ገልፀዋል፡፡
አጠቃላይ የኢንሹራንስ ኢንፎርሜሽን ሲስተሙን ውጤታማ ለማድረግ በመዲናዋና በመላ አገሪቱ የሚገኙትን ቅርንጫፎችና ዋና መ/ቤትን በመረጃ መረብ በማስተሳሰር፣ በሁሉም ቅርንጫፎች ቢሮዎችና አገናኝ ጽ/ቤቶች በ514 ቋሚ ሠራተኞች (ከዚህ ውስጥ 52.2 በመቶ ወይም 258ቱ ሴቶች ናቸው) የተቀናጀና ቀልጣፋ አገልግሎት ለተጠቃሚው እየሰጠ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ከ24 ዓመት በፊት በ1987 ዓ.ም በ456 ባለ አክሲዮኖች የተመሠረተው አዋሽ ኢንሹራንስ፤ በአሁኑ ወቅት 1,285 ባለ አክሲዮኖች ሲኖሩት፣ ሰኔ 30 ቀን 2018 የኩባንያው የተከፈለ ካፒታል 277.13 ሚሊዮን ብር መድረሱን የኩባንያው አጠቃላይ ሀብት ከ2.2 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑን አቶ ሃምዲሳ ዋቅወያ አስታውቀዋል፡፡

Read 1824 times