Tuesday, 06 November 2018 00:00

ማይክል ጃክሰን ከሞቱ የአለማችን ዝነኞች ለ6ኛ ጊዜ በገቢ መሪነቱን ይዟል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 በህይወት ከሌሉ የአለማችን ዝነኞች ከፍተኛውን ገቢ በማግኘት ላለፉት አምስት አመታት በመሪነት የዘለቀው የፖፕ ሙዚቃ ንጉስ ማይክል ጃክሰን ዘንድሮም በ313 ሚሊዮን ፓውንድ አመታዊ ገቢ በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጡ ተዘግቧል፡፡
ማይክል ጃክሰን ከኤሚ ሚዩዚክ ፐብሊሺንግ በተባለው አሳታሚ ኩባንያ ውስጥ ካለው የአክስዮን ድርሻና በህይወት ሳለ የሰራቸውን ሙዚቃዎች ለማሳተም ከኩባንያዎች ጋር የተደረጉ ስምምነቶችን ጨምሮ በድምሩ 313 ሚሊዮን ፓውንድ ማግኘቱን የዘገበው ፎርብስ መጽሄት፤ ድምጻዊው ከዚህ አለም በሞት ከተለየበት እ.ኤ.አ 2009 በኋላ ባሉት አመታት በድምሩ 1.8 ቢሊዮን ፓውንድ ገቢ ማግኘቱን የጠቆመው ዘገባው፣ በህይወት ከሌሉ የአለማችን ዝነኞች በገቢ የሁለተኛነት ደረጃን የያዘው ሌላው ዘመን አይሽሬ ድምጻዊ ኤልቪስ ፕሪስሊ ሲሆን፣ ኤልቪስ ባለፉት 12 ወራት ጊዜ ውስጥ 31 ሚሊዮን ፓውንድ ገቢ ማግኘቱን አመልክቷል፡፡
በተወለደ በ42 አመቱ እ.ኤ.አ በ1977 ከዚህ አለም በሞት የተለየው ኤልቪስ ፕሪስሊ ባለፉት 12 ወራት የተጠቀሰውን ገቢ ያገኘው ከቀድሞ ሙዚቃዎቹ ሽያጭና ከሌሎች ገቢዎች እንደሆነ ተነግሯል፡፡
ዝነኛው የጎልፍ ተጫዋች አርኖልድ ፓልመር በ27 ሚሊዮን ፓውንድ የሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ፣ ታዋቂው ካርቱኒስት ቻርለስ ሹልዝ በ26 ሚሊዮን ፓውንድ አራተኛ፣ የሬጌው ሙዚቃ ንጉስ ቦብ ማርሌ ደግሞ በ18 ሚሊዮን ፓውንድ አምስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
በፎርብስ መጽሄት የዘንድሮ የአለማችን ሟች ዝነኞች ገቢ ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት ሌሎች ዝነኞች መካከል እውቋ የፊልም ተዋናይ ማርሊን ሞንሮ የምትጠቀስ ሲሆን፣ በ11 ሚሊዮን ፓውንድ የ11ኛ ደረጃን ይዛለች፡፡


Read 5304 times