Print this page
Saturday, 03 November 2018 15:54

የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ውሳኔዎች!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

 • ከስኳር ፕሮጀክቶች ማጥ የባሰ ረመጥ? (የነፋስ፣ የፀሐይ፣ የእንፋሎት የኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶች)!
  • መንግስትን ከአክሳሪ የብክነት ፕሮጀክቶች አመል ማላቀቅ!
  • ከመንግስት የተትረፈረፈ የስራ እድል? አይገኝም። የስራ እድል ምንጭስ የግል ኢንቨስትመንት!
  • የብር ሕትመት፣ የዋጋ ንረት፣ የደነዘዘ ኤክስፖርትና የተናጋ ሕይወት፣... ከእንግዲህ አይደገምም?
  • ሕግን ማስተካከል ወይስ ማስከበር፣ ስርዓትን ማቃናት ወይስ መጠበቅ?
     
    ባለፉት ዓመታት፣ መንግስት ከገባባቸው በርካታ የብክነትና የኪሳራ ፕሮጀክቶች መካከል፣ አንድ ምሳሌ ብቻ መጥቀስ በቂ ነው።
የውጭ ምንዛሬ እጥረት መከራ የሆነበትና መፈናፈኛ ያጣው የኢትዮጵያ መንግስት፣ በዓመት 150 ሚሊዮን ዶላር ድጎማ ለመስጠት ለአውሮፓ የኤሌክትሪክ ኩባንያ ተዋውሏል። ከአውሮፓ ኩባንያ ዶላር ለመቀበል ሳይሆን፣ የዶላር ድጎማ በየዓመቱ ለመስጠት ነው የተፈራረመው። ግራ ያጋባል? “እንዴት ሊሆን ይችላል?” ያስብላል። “የሆነ አንዳች ጥቅም ቢኖረው ይሆን?” ያሰኛል። ግን፣ አንድም የኢትዮጵያ ባለስልጣን፣... “አንዳች ጥቅም ያስገኛል” ብሎ እስካሁን አላስረዳም፣ ወደፊትም ሊያስረዳ አይችልም። ምክንያቱም፣ የዶላር ድጎማው፣... እርቃኑን የወጣ ኪሳራ፣... ከንቱ ወጪ ብቻ ነው።
የአውሮፓው የኤሌክትሪክ ኩባንያ፣ በዓመት እስከ 8ሺ GWH የኤሌክትሪክ ሃይል እያመነጨ በዶላር ለመሸጥ ነው እቅዱ - በ550 ሚሊዮን ዶላር ገደማ (ግማሽ ቢሊዮን ዶላር መሆኑ ነው)። ግን ችግር የለም።... ለኬንያ፣ ለጂቡቲ በዶላር መሸጥ ይቻላል። ከኬንያና ከጂቡቲ ሊገኝ የሚችለው ክፍያ ግን፣ ከ400 ሚሊዮን ዶላር በታች ነው። ኬንያና ጂቡቲ ኤሌክትሪኩን ይጠቀማሉ። ኢትዮጵያስ? በባዶ ትከስራለች - ቀሪውን 150 ሚሊዮን ዶላር ለኩባንያው ታሟላለች። የአውሮፓውን ኩባንያ ትደጉማለች ማለት ነው። የዚህን ያህል እርቃኑን የቀረ ሌጣ ኪሳራ ስለሆነ ነው፣ በየትኛውም ማብራሪያ የውሸት ለማቆንጀት መሞከር፣ ከንቱ ልፋት የሚሆነው።
ይሄንን እርቃኑን የቀረ ኪሳራ ገና ካሁኑ፣ ቀጭቶ ማስቀረት ያስፈልጋል። የግድ ነው - ተስፋ ያላት አገር እንድትኖረን ከፈለግን። ግን ይሄንን ብቻ ማስቀረት በቂ አይደለም። በርካታ ተመሳሳይ የኪሳራ ውሎችና የብክነት ስምምነቶች እየተዘጋጁና እየተፈረሙ ናቸው። በፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ የሚያመነጩ ናቸው ተብለው ከሳምንት በፊት በገንዘብ ሚኒስቴር የተዘረዘሩ 8 ፕሮጀክቶችን መጥቀስ ይቻላል። የ1.2 ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክቶች ናቸው (ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ)።
በነዚህ ፕሮጀክቶች አማካኝነት ሊመነጭ የሚችለውን የኤሌክትሪክ መጠን ለማነፃፀር ከፈለጋችሁ፣... በግልገል ጊቤ 2 እና በጣና በለስ  የሚመነጨው የኤሌክትሪክ መጠን ወደ አምስት እጥፍ ገደማ ነው። ወጪያቸውስ? የግልገል ጊቢ2 እና የጣና በለስ ወጪ ቢደመር፣ 1.2 ቢሊዮን ዶላር አይደርስም። ማለትም፣... “የፀሐይ ኃይል...” ምናምን እያሉ የድሃ አገር ሃብትን ለኪሳራ ከመዳረግና ለአውሮፓ ኩባንያዎች የዶላር ድጎማ ከማባከን ይልቅ፣ በተመሳሳይ ወጪ፣ አምስት እጥፍ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት ይቻላል።
በሌላ አገላለፅ፣... በስምንቱ የፀሐይ ኃይል ፕሮጀክቶች የሚመነጨውን የኤሌክትሪክ ሃይል፣... በአማካይ 400 ሚሊዮን ዶላር በማይፈጅ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ አማካኝነት መተካት ይቻላል። 800 ሚሊዮን ዶላር ከከንቱ ብክነት ወይም የአውሮፓ ኩባንያዎችን ከመደጎም ይድናል። ወይስ እንደ ዘበት ከድሃ አገር አምራች ዜጎች በታክስ የሚሰበሰበውን ሃብት ማባከን ይሻላል? 800 ሚሊዮን ዶላር ብክነት ቀላል አይደለም - ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ነው።
እነዚህንና ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን በሙሉ ማስወገድና የተፈረሙ ውሎችን ማቋረጥ፣ የጠ/ሚ ዐቢይ አይቀሬ ሃላፊነት ነው። ባለፉት 10 ዓመታት እንደተለመደው በድሃ አገር ሃብት እየተጫወቱ ማባከንና እየቀለዱ መቀጠል የሚፈልጉ ባለስልጣናትን በፍጥነት ማባረርም እንዲሁ።
መንግስትን እና አክሳሪ የብክነት ፕሮጀክቶች አመልን ማላቀቅ!
ብዙ ብክነት ያደረሱ እና እያስከተሉ የሚገኙ የስኳር ፕሮጀክቶችን፣ ወደ  ግል ይዞታ በማዛወር የማያዳግም ሁነኛ መፍትሄ ለመስጠት መወሰናቸውን በመግለፅ ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ቃል ገብተዋል። በእርግጥ የፕሮጀክቶቹ ብክነትና ኪሳራ ወደ ምርታማነትና ትርፋማነት መለወጥ የሚቻለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው - የስኳር ፕሮጀክቶችን ወደ ግል ይዞታ ማዛወርና፣... የግል ኢንቨስትመንትን የሚያሰናክሉ የመንግስትም ሆነ የ”ሕዝብ” ስርዓት አልበኝነትንና ሕግ አልበኝነትን በማስወገድ።
ብዙ ሰው በዚህ ተስፋ ሲደሰትና ሲያጨበጭብ ባይታይም፣ ዶ/ር ዐቢይ ቃላቸውን በፍጥነትና በጥንቃቄ በመተግበር፣ ምስጋና ባያስገኝላቸውም እንኳ ለአገር ትልቅ ውለታ እንደሚሰሩ ተስፋ አደርጋለሁ። በትክክለኛ ሃሳብ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ ነው እየተራመዱ ያሉት። ምናለ የዛሬ ሰባት እና ስምንት ዓመት፣... እንዲህ አይነት ትክክለኛ ሃሳብ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ በተደጋጋሚ ሲቀርብ ሰሚ በተገኘ። ከብዙ ጥፋት እንድን ነበር። አሁንም ግን፣ “ተመስጌን” ነው። ከተጨማሪ ጥፋት ለመዳን ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ስኬት የመጓዝ እድልን የሚከፍት ጉዞ ነው - የስኳር ፕሮጀክቶችን ወደ ግል የማዛወር ውሳኔ።
ከስኳር ፕሮጀክቶች ማጥ የባሰ ረመጥ? (የነፋስ፣ የፀሐይ፣ የእንፋሎት፣ የኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶች)!
የስኳር ፕሮጀክቶች፣... በመንግስት ስር የሚቀጥሉ ከሆነ፣ መፍትሄ እንደማይኖራቸውና የውድቀት መዘዛቸውም አይቀሬ እንደሆነ፣... ገና ከጅምሩ በእውነተኛ መረጃና በትክክለኛ ትንታኔ የሚያስረዳ መካሪ፣ የዛሬ 6 ዓመት እና ከዚያ በፊት ብዙ አልነበረም። በአዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ በቀዳሚነትና ጎላ ብለው የሚጠቀሱ ሰፋፊ ዘገባዎችና ትንታኔዎች መቅረባቸው ግን ሊዘነጋ አይችልም። ሰሚ ቢገኝና፣ ያኔውኑ ብዙ ብክነትና ኪሳራ ሳይደርስ በፊት፣... የስኳር ፕሮጀክቶችን ወደ ግል የማዛወር ሁነኛ መፍትሄ ቢፈጠር ኖሮ አስቡት።
አሳዛኙ ነገር፣... ከስኳር ፕሮጀክቶች የባሱ፣... ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚበራከቱ፣ ባለብዙ መዘዝ የኪሳራና የጥፋት ፕሮጀክቶች መኖራቸው ነው? አዎ፣ ላለፉት 8 ዓመታት፣... የስኳር ፕሮጀክቶች፣ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ፣ “ክፉ በሽታ” ሆነዋል። ግን፣ “የኢኮኖሚ ክፉ በሽታ” የሚለውን መጠሪያ የሚነጥቁ ሌሎች የጥፋት ፕሮጀክቶችም መኖራቸው አይገርምም? ከላይ ምሳሌዎችን በመጥቀስ ለማሳየት እንደሞከርኩት፣... ካለፉት ዓመታትም በላይ በመጪዎቹ ዓመታት፣ ለከፋ መከራ የሚዳርጉ፣ ከብክነትና ከኪሳራ ማጥ ወደ ባሰ ረመጥ ላለመግባት፣... ጊዜው ሳይረፍድ መቁረጥና መወሰን ነው የሚያዋጣው።
ከመንግስት የተትረፈረፈ የስራ እድል? አይ! ከግል ኢንቨስትመንት!
እንደተለመደው፣ በየዓመቱ “ለሁለት ወይም ለሦስት ሚሊዮን የከተማ ነዋሪዎች አዳዲስ የስራ እድሎችን ፈጥሬያለሁ” እያለ ራሱንና ዜጎችን ለማታለል የሚሞክር መንግስት፤ ብዙ መራመድ እንደማይችል በመገንዘብም ይመስላል፣ ዋነኛው የስራ እድል ምንጭ የግል ኢንቨስትመንት እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ የተናገሩት።
የከተማ ልማት (የኮንስትራክሽን) ሚኒስቴር፣ ባለፉት 8 ዓመታት፣... በኢትዮጵያ ከተሞች ከ16 ሚሊዮን በላይ የስራ እድሎች በመንግስት ጥረት እንደተፈጠረ በየጊዜው እየደጋገመ አብስሮናል። ገሚሱ ቋሚ፣ ገሚሱ ጊዜያዊ የስራ እድል መሆኑ ነው። 8 ሚሊዮን ጊዜያዊ የስራ እድል፣ 8 ሚሊዮን ቋሚ አዳዲስ የስራ እድል በኢትዮጵያ ከተሞች?
የሚኒስቴሩ መስሪያ ቤት በየዓመቱ በሪፖርትና በመግለጫ የሚያቀርብልን የስራ እድል መረጃ፣ ጨርሶ እውነተኛ መረጃ የመሆን እድል የሌለው መረጃ እንደሆነ ጠፍቶት ነው? በነባር 3 ሚሊዮን የስራ እድል ላይ 8 ሚሊዮን አዳዲስ ቋሚ የስራ እድሎች ቢጨመሩ ኖሮ... በዚያ ላይ በርካታ ሚሊዮን ጊዜያዊ የስራ እድሎች ሲታከሉበት አስቡት... በከተሞች ብቻ 16 ሚሊዮን ነባርም ሆኑ አዳዲስ የስራ እድሎች... እንዲያው ከሕፃናትና ከተማሪዎች ውጭ፣ ለስራ የሚፈቅድ እድሜና ጤና ያለው የከተማ ነዋሪ በሙሉ ይቆጠር ቢባል፣ 10 ሚሊዮን አይሞላማ። በሚሊዮን የሚቆጠሩ የውጭ አገር ሰራተኞችን አስመጥተናል ካልተባለ፣ በኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ፣ ያንን ሁሉ የተትረፈረፈ የስራ እድል የሚመጥን በቂ የነዋሪ ቁጥር የለም።
እንዲህ አይነት የቁጥርንና የስሌትን ትልቅ ክብር የሚያራክስ ቀሽም ጨዋታ፣ አላዛለቀም። ከኪሳራ ውጭ ትርፍ አያስገኝም። ትርፍ ተገኘ ከተባለም፣ በየከተማው የአገሪቱን ቀውስ የሚያባብስና ለአቀጣጣዮች የሚመች የስራ አጥነት ጭድ እየተቆለለ፣ የችግር ክምር እየበረከተ መሄዱ ብቻ ነው።
ለዚህም ነው፣... የስራ እድል ምንጭ የግል ኢንቨስትመንት እንደሆነ የገለፁት ዶ/ር ዐቢይ፣ ይህን በተመለከተም የመንግስት ዋና ሃላፊነት፣ ኢንቨስትመንትን የሚያሰናክሉ፣ የሚያደናቅፉና የሚፃረሩ ነገሮችን ማስወገድና ማስተካከል እንደሆነ መግለጻቸው ትልቅ ትርጉም የሚኖረው።
እንደ ቀድሞው፣ ዛሬም፣... መንግስት የስራ እድል ይፈጥርላችኋል እያን ለመቀጠል ብንሞክር፣... የስራ እጦት ችግር፣... ምን ያህል የሕልውና አደጋ እንደሆነ አለመገንዘብ ይሆናል። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ይህንን እውነታ ጠቅሰውታል። ጠ/ሚ ዐቢይ ደግሞ፣ ከዚያ በፊትም በኋላም በተደጋጋሚ በአፅንኦት አስረድተዋል። ስራ አጥነት፣... በዛሬው ዘመን፣ አገርን ለሚያተራምሱ ቀውሶች የሚያጋልጥና የሚመች አደጋ በመሆኑም ነው፣... “መንግስት፣... የስራ እድል ይፈጥርላችኋል” የሚለውን ከንቱ አባባል መተውና፣ ትክክለኛውና ሁነኛው የስራ እድል ምንጭን... ማለትም የግል ኢንቨስትመንትን ከማጥላላት መፅዳት፣ ከአደናቃፊ ጠማማ ፖሊሲዎችና ህጎች መገላገል፣ ከአሰናካይ ውሳኔዎችና ድርጊቶች መራቅ የሕልውና ጉዳይ የሚሆነው። በእርግጥ ይሄኛው አቋም፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙ ጭብጨባና ምስጋና ያስገኝላቸዋል ብዬ አልጠብቅም። ግን፣ ለአገር ሕልውና፣... ማለትም ሰርተው መኖር ለሚፈልጉ ዜጎች ትልቅ ውለታ ነው (ትክክለኛ አቋም፣... በጥንቃቄና በፅናት እየተተገበረ ሲሄድ)።
የብር ሕትመት፣ የዋጋ ንረት፣ የደነዘዘ ኤክስፖርትና የተናጋ ሕይወት
በዋጋ ንረትና በኑሮ ውድነት የዜጎችን የእለት ተእለት ሕይወት ላለማናጋትና የኢንቨስተትመንት ውጥኖችንና ጅምሮችን የሚያሰናክል፣ ከዚህም ጋር ብር እየረከሰ የዶላር ምንዛሬ ቁጥጥርን ጨምድዶ ለመዝለቅ በሚደረግ ከንቱ ሙከራ ኤክስፖርትን አደንዝዞ የሚያስቀር ስህተትም እንደማይደገም ጠቁመዋል። ለዚህም ሌላ ሁነኛና መሰረታዊ ዘዴ የለም። ገንዘብን ከሚያረክስ መረን የለቀቀ የብር ኖት ህትመት መቆጠብ ብቻ ነው መፍትሄው። ዶ/ር ዐቢይ ይህንንም ቃል ገብተዋል።
ሕግን ማስተካከል ወይስ ማስከበር፣ ስርዓትን ማቃናት ወይስ መጠበቅ?
በአንድ በኩል፤ ሕግን ማስከበርና ስርዓትን ማስጠበቅ ማለት፣ የዘፈቀደ ስርዓትንና የተጣመመ ሕግን በጭፍን ታቅፎ መቀጠል ማለት አይደለም። በሌላ በኩል፣ ስርዓትን ማስተካከልና ሕግን ማረም ማለት ደግሞ፣ ሕገ ቢስነትና ስርዓት አልበኝነት ማለት አይደለም። በአንድ በኩል ተገቢ የመንግስት ስራዎችን በትክክል ማከናወን፣ በሌላ በኩልም መንግስት ያለ ስራው ቢዝነስ ውስጥ ገብቶ የብክነትና የኪሳራ ማጥ እንዳያቦካ መቆጠብ ይከብዳል? አዎ ከባድ ሃላፊነት ነው። እንኳንስ፣ እንደ ኢትዮጵያ የስልጣኔ ጉዟቸው ተቋርጦ ወደ ኋላ ለቀሩ አገራት ይቅርና፣ በስልጣኔ ጎዳና ደህና ለተራመዱት የአሜሪካና የአውሮፓ አገራትም እንኳ፣ ከባድ ሃላፊነት ሆኖባቸዋል። ቢሆንም ግን፣ የተሳሳተውን እያረሙ፣ የተጣመመውን እያቃኑ ሕግን ከማስከበርና ስርዓትን ከመጠበቅ ውጭ፣... በስኬት ለመራመድ ይቅርና፣... “አገር አለኝ” የሚለው ተስፋም ተሸርሽሮ ከእጅ ሲያመልጥና ሲፋጅ በአለም ዙሪያ እያየን ነው። ስለዚህ የግድ ያስፈልጋል - ምን?
ኢኮኖሚን በተመለከተ፣... “መንግስት ያለ ስራው ቢዝነስ ውስጥ ገብቶ የብክነትና የኪሳራ ማጥ እንዳያቦካ መቆጠብ፣ ተገቢ የመንግስት ስራዎችን ደግሞ በትክክል ለማከናወን መትጋት ያስፈልጋል። በዘንድሮው የመንግስት እቅድ፣... የግል ኢንቨስትመንትን የሚያደናቅፉ አላስፈላጊና አጥፊ የመንግስት ቁጥጥሮችንና ክልከላዎችን ማስወገድ አንድ ትልቅ ስራ እንደሆነ ተገልጾ የለ?
በአጠቃላይ ግን፣ የተሳሳተውን እያረሙ ሕግን ለማስከበርና የተጣመመውን እያቃኑ ስርዓትን ለመጠበቅ መትጋት ያስፈልጋል።
ሕግን ማስከበርና ስርዓት አልበኝነትን መከላከል የሕልውና ጉዳይ መሆኑንም የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ለፓርላማ ተናግረው የለ?
ፅሁፌን ጨርሻለሁ።
(ከርዕሰ ብሔር የሚጠበቀው የስክነትና የእርጋታ መንፈስ ሳይለያቸው ለቆዩባቸው የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው ምስጋና ይገባቸዋል። ወደፊት የፕሬዚዳንት ስልጣን፣ ቀስ በቀስ ሰፋ እና ደርጀት እያለ ቢሄድም እንኳ፣ ከወቅታዊ የፖለቲካ ዘመቻና ቅስቀሳ ይልቅ፣ /ለምሳሌ፣ “ሁሉም ሴቶች እና ሰላም ወዳድ ወንዶች” ከሚል የ”አክቲቪዝም” አገላለፅ በመቆጠብ/፣ ለማንኛውም ቀና ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያዊት ሁሉ፣ የስክነትና የእርጋታ አርአያ የመሆን ብቃትና ትጋት፣ ዋነኛ የፕሬዚዳንት ሃላፊነት ሆኖ ቢቀጥል ይበጃል። በዚህ አጋጣሚ፤ ለአዲሷ ፕሬዚዳንት መልካም የስራ ዘመን ይሁንላቸው!!)

Read 6021 times