Saturday, 03 November 2018 15:53

“ዳዲ ‘ኔቨር’ አለ”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(7 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
“የሆነ ቦታ የማውቅህ ይመስለኛል፡፡”
“እኔ አንደውም  የረሳኸኝ መስሎኝ ነበር፡፡“
“ሌት ሚ ሲ፣…ዲሲ ነው የማውቅህ?”
“ዲሲ!” (ሰውዬዋ በጠዋቱ በድራጓ ተሳፍሮ ነው እንዴ!)
“ሶሪ ሶሪ ዲሲ አይደለም…” (ጎሽ፤ ጭራሽ ከመጥፋት መለስ ማለቱ ሸጋ!)
“አሁን አስታወስክ?”
“የስ፣ ኢት ካንት ቢ ዲሲ፡፡ ዲሲ ሙቭ ያደረግሁት ሪሰንትሊ ነው፡፡ አይ ጌት… ኢት፣ ቦስተን፡፡ ያ…ኢት መስት ቢ ቦስተን!” (ከዲሲ ጋር ዜማ ፈጥሮ ቤት የሚመታ ጥሩ የአማርኛ ስድብ ትዝ ቢላችሁ ኖሮ፣ እስከ ዶቃ ማሰሪያው መንገር ነበር! እንግዲህ አሱ ካመጣው ምን ይደረጋል... “ለምን ይዋሻል!” ማለት ሳያስፈልግ እውነት፣ እውነቷን መናገር ነው፡፡)
“ስማ እኔ አይደለም አውሮፕላን ላይ ወጥቼ ቦስተን ልሄድ፣ጣና አቅራቢያ ባለው ቦስተን  ዴይ ስፓ በራፍ ካለፍኩ፣ የካቲት ሲመጣ አምስት ዓመት ከሰባት ወር ይሞላኛል፡፡”
“ሀ!...ሀ!...ሀ!...ዩ አር ፈኒ…ድሮም እንዲህ ነበርክ እንዴ!” (ቆይ፣ ቆይማ…‘ፈኒ’ ያለው እኔን ነው ኑሮዬን? ፈረንጅ አገር ቅኔ ባያውቁ ስላቅ አያቅታቸውማ…ያውም ከዚህ ለሄደ የአገር ልጅ! እኛ ዘንድ… አለ አይደል… የሰው ‘ፈኒ’ እየቀነሰ፣ የኑሮ ‘ፈኒ’ እየጨመረ መሆኑን የሆነ ‘ዶላር የጠማው’ አሳብቆብን ይሆናል)
“እኔ እንኳን እንደዛ አይደለሁም፡፡”
“ካም ኦን! ባክ ሂር ስታንድ አፕ ኮሜዲ የለም? ማለት… ዩ ኩድ ትራይ!” (ይሄ ሰውዬ፤ “ደሙን አፍላው” ተብሎ ተልኮ ነው እንዴ! ይቺ ተንተክትካ ያለቀች ደም… የቀረችውን ጭራሽ ሊያሟጥጣት ነው እንዴ! አብዮቴን የግድ ከመከላከል ወደ ማጥቃት ለማሸጋገር እገደዳለሁ፡፡)
“የምንተዋወቅበትን ቦታ አስታወስከው!” (‘ፈኒ’ ምናምን ብለኸኝማ ትንሽ ‘ሳልሞጫጭርህ’ እንዲሁ መለያየት የለም!)
“አላስታወስኩትም፣ ዲድ ዩ?”
“እንዴት አታስታውስም! የነስሩን ፓስቲ እንኳን እየሰረቅን ስንቀምስ የነበረውን ኩርኩም እንዴት ትረሳዋለህ!”
ይሄኔ ነው ዓለም በአፍጢሟ የምትደፋው፡፡ ያ ሁሉ ዋሺንግተን፣ ቦስተን ምናምን ላይ ሲተረክ የነበረው ታሪክ ፉርሽ ይሆናል፡፡
“ይገርማችኋል፤ እኛ ቤት ከኬክ በስተቀር ኖ ዋን ኢትስ ብሬድ፡፡”
“አንድ ቀን እንኳን ፓስቲ ቤት ገብታችሁ አታውቁም?”
“ሁዋት! አር ዩ ኪዲንግ ሚ! ዳድን ብዙ ጊዜ ፓስቲ ቤት ምን እንደሚመስል በበራፉ ድራይቭ እያደረግን አሳየን ስንለው፣ ዩ ኖው ኋት ሂ ሴይስ…ኔቨር!”
እናላችሁ… ሁለት ሰው ስለነበረበት የፓስቲ መንታፊ ‘ክሪሚናል ጋንግ’ እውነቷን የሚያወራ ሲመጣ… ነገር ተበላሸ ማለት ነው፡፡
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እንዲህ አይነት “ዳዲ ‘ኔቨር’ አለ” የሚል ግለ ታሪክ እንደ ልብ ነው፡፡ ያለፉት ወራት ቦተሊካችን እንዳለ ሆኖ...መአት “እሱ ነው አክቲቪስት!”  “እሱ ነው ፖለቲከኛ!” ስንል ነው የከረምነው። አሀ...ምን እናድርግ…“ዳዲ ‘ኔቨር’ አለ” አይነት ነገር በዛብና! ይህች… “ስደት ለወሬ ይመቻል…” የምትለዋ አባባል እንዴት አሪፍ መሰለቻችሁ! አንድ ሰሞን ‘ማዘሮች’ እንኳን መንፈቅ ያህል ቆይተው ሲመለሱ… “እትዬ እንትና እንደምን አደሩ?” ሲሏቸው… አለ አይደል…“ሁዋትስ አፕ?” አይነት ይሞክራቸው ነበር፡፡
የምር ግን…ዘንድሮ ‘ፖሊተከኛ’ ያልሆነ፣ ዘንድሮ…“ታዝዬም ቢሆን በአምስቱ ዓመት የጣልያን ወረራ ጊዜ ዘምቻለሁ…” አይነት ነገር ያላለ፣ ሚዲያ ላይ ቀርቦ… “ላለፉት አራት አስርት ዓመታት ‘ስላመለጡን እድሎች’ ያልተናገረ፣ በቃ…የታሪክ ቀላል ባቡር አመለጠው ማለት ነው፡፡ ብዙዎቻችን አንድ ማንም ሊወስድብን የማይችለው ችሎታ አለን… እውነት እውነቷን ተናግረን ከማሳመን ይልቅ በ‘ፊክሽን’ የማሳመን ችሎታ፡፡ እናማ… “ዳዲ ‘ኔቨር’ አለ” የሚሏት አቀራረብ ዋጋዋ ከፍ ያለው ለዚሁ ነው፡፡
የሚዲያ ሰዎቻችን ጠንከር ለማለት መሞከራቸው አሪፍ ነው፡፡ (በእርግጥ አንዳንዴ ጠንከር ያሉ ናቸው እየተባሉ የሚቀርቡ ‘ጥያቄዎች’ …አለ አይደል… ቃለ መጠይቅ እየቀረበለት ያለውን እንግዳ ሰብአዊ ክብር የሚነኩ ቢመስሉም፡፡ ማፋጠጡ ጥሩ ሆኖ ሳለ “ቆይ በተመልካች ፊት ባላሳጣው!” አይነት አቀራረብ ለተመልካችም ይከብዳል፡፡ ይታረምልንማ!)
ግን ደግሞ አንዳንዴ “ባለፉት ሀያ ሰባት ዓመታት…” (እንደ ጆከርነት የምታገለግል አባባል እየመሰለች ስለመጣች ነው፡፡) በውጪ ሀገራት ሲያደርጉ ስለቆዩት ‘ትግል’ ምናምን ሲያወሩ… “እስቲ ይሄን የሚያረጋግጡ ተጨባጭ የሆኑ ምሳሌዎች ይስጡን…” ወይንም “ስለዚህ ሊያረጋግጡልን የሚችሉ የትግል አጋሮችዎን ቢጠቁሙን…” ማለት ያስፈልጋል፡፡ … ያኔ ነዋ “የነስሩን ፓስቲ እየሰረቅን ስንቀምስ የነበረው ኩርኩም…” ነገር የምትመጣው። አለበለዛ ዘመዶቹ እንኳን “ይሄ ሰውዬ አሁንም በህይወት አለ! እኔ አኮ፣ መቼም እግዜሀር ይቅር ይበለኝ፣ …የሞተ መስሎኝ ነበር…” እያሉት የምን “ታዝዬም ቢሆን ዘምቻለሁ…” ብሎ ነገር ነው!
የሚያሰጋው ምን መሰላችሁ… ወጣቱ ቀና ብሎ እንደ ምሳሌ (አይዶል) የሚያየው ማጣቱ! ደግሞ የዘንድሮን ወጣት በ“ዳዲ ‘ኔቨር’ አለ” አይነት ለማሞኘት መሞከር… አለ አይደል… ‘ዝሆን ሰርቆ አጎንብሶ’ አይነት ነገር ነው የሚሆነው፡፡
እናማ… ደመናው በጠቆረ ሰዓት ጭጭ፣ እረጭ ያለው ሰፈር ሁሉ ደመናው ገለጥ ሲል  ድንኳን ሰባሪው መአት ነው፡፡ ስደት ለወሬ ይመቻላ!
ከዚህ በፊት ያወራናትን ስሙኛማ…ሰውየው ስለ ጤናው ከጓደኛው ጋር እያወራ ነው፡፡
“ከሁለት ዓመት በፊት ዶክተር ለመኖር የቀረህ ስድስት ወር ብቻ ነው ብሎኝ ነበር፡፡ ስድስት ወሩ ሲያልቅም ተመልሼ ስሄድ ስድስት ወር ጨመረልኝ” አለ፡፡
“እና ሁለት ዓመት ሙሉ እንዴት ቆየህ?”
“ሀኪሙ ዘንድ በየስድስት ወሩ እየሄድኩ ያራዝምልኛል፡፡”
ታዲያላችሁ… እኛም ዘንድ ብዙ ፖለቲከኝነታቸውን በየምርጫ ዓመቱ ወይም ደመናው ‘ለቀቅ ያለ፣’ በሚመስልበት ጊዜ ብቅ እያሉ የሚያሳድሱ እየመሰለን ያለው ለምንድነው! “እሱ ሰውዬ አንደኛውን ሳይመንን አልቀረም” ያልነው ሁሉ ከሆነ ካርታ ላይ ከሌለ ዋሻ ወይም ጉድጓድ ብቅ እያለ… ‘ፖለቲካዊ ሰርፕራይዝ’ ወርወር ሲያደርግብን ግራ እንጋባለን፡፡ ነገርዬውማ ያው… “ዳዲ ‘ኔቨር’ አለ” አይነት ነች፡፡
እናማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ስንት ዓመት ሙሉ ሠራተኛውን “ቼ ፈረሴ!” ሲል ከርሞ የነፋሱ አቅጣጫ ለወጥ ሲል… በአንድ ሌሊት የሆነ ‘ተሀድሶ’ ነገር ውስጥ እስከ ራስ ጸጉሩ ይጠልቃል፡፡ እናላችሁ…በየመድረኩ ላይ… “የተጀመረውን እድገት አጠናክሮ ለማስቀጠል…” “ድርጅቱ ሀላፊነቱን ለመወጣት በቁርጠኝነት…” ምናምን ማለት ያበዛል፡፡ ከዛም ይህንን ድርጅት ትርፋማ ለማድረግ ከፍተኛ ትግል ስናካሂድ ቢሮክራሲው አላሠራ እያለን…” ምናምን እያለ ያቺ የተለመደችዋን ‘ያኛውን ወገን የማስጠቆር’ ካርድ ይመዛል፡፡ የምር እኮ…አለ አይደል… “የዳይኖሶሮቹ እጣ በደረሰውና ትንሽ ተንፈስ ባልን…” እያልን የምንማረርበት ቢሮክራሲ የሚባለው ‘ነገር’ እኮ ሰውየውን ራሱን ይፈራው ነበር! (ቂ…ቂ…ቂ…) ስደት ለወሬ ይመቻላ!
ታሪኮችና አፈ-ታሪኮች እየተደበላለቁ፣ እየተተረማመሱላችሁ ነው፡፡ እንቁራሪቷ የሰው ስጋ የለበሰች ልዕልት የምትሆንበት የህጻናት አፈ-ታሪክ አይነት የሬድዮ መጽሀፍ ትረካን ሊያስንቁ ምንም በማይቀራቸው ፖለቲካዊ (‘የትግል’ የሚለው በታሳቢነት ይቆይልንማ!) እየተምነሸነሽን ነው። እናላችሁ…ቀን በቀን ፋኖስ አብርቶ ገበያ ሲዞር፤ “ሰው እየፈለግሁ ነው” አለ እንደሚሉት ፈላስፋ እኛም ግራ ስንጋባ (ፋኖስ ውድ ስለሆነ ባንይዝም) ‘እውነተኛ ፖለቲከኛ ፍለጋ ላይ ነን…” ልንል ምንም አልቀረን፡፡
“የነስሩን ፓስቲ እንኳን እየሰረቅን ስንቀምስ የነበረውን ኩርኩም እንዴት ይረሳል?”  ለሚመለከታቸው ብቻ የቀረበ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 6735 times