Saturday, 03 November 2018 15:36

ሰማያዊ ፓርቲ የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ለዲፕሎማቶች አብራራ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

 የፖለቲካ ፕሮግራሙንና ህገ ደንቡን እንደሚያሻሽል ጠቁሟል

    በጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የተጀመሩ የፖለቲካ ለውጦች አበረታች መሆናቸውን መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶች ማብራራቱን የገለጸው  ሰማያዊ ፓርቲ፤ ከለውጡ ጋር አብሮ ለመጓዝ የፖለቲካ ፕሮግራሙንና ህገ ደንቡን እንደሚያሻሽል ጠቁሟል፡፡  
ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በሀገሪቱ አያሌ አበረታች የፖለቲካ ለውጦች መካሄዳቸውን  ያብራራው ፓርቲው፤ በተለይ የፖለቲካ እስረኞች መፈታታቸው፣ ትጥቅ አንስተው ሲታገሉ የነበሩ ተቃዋሚ ኃይሎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ሃገር ቤት መመለሳቸው፣ በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዘንድ አንድነትና ህብረት መፈጠሩ እንዲሁም ለ20 ዓመታት  በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የዘለቀው ግጭት ተወግዶ፣ እርቅ መፈፀሙ፣ ትልቁ የለውጡ ስኬት መሆኑን ለዲፕሎማቶቹ አስረድቷል፡፡  
የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዛወር መወሰኑ፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲታረቁ መደረጉ፣ ሴቶች ወደ ከፍተኛ ስልጣን መምጣታቸው እንዲሁም የፀረ ሽብር ህጉን ጨምሮ አፋኝ ህጎችን ለማሻሻል ሥራ መጀመሩም  የለውጡ ትሩፋት መሆኑን ፓርቲው አብራርቷል፡፡  የዶ/ር ዐቢይ አመራር በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖ የሀገሪቱን የለውጥ ጉዞ እየመራ እንደሚገኝ የገለፀው ፓርቲው፤ አሁንም በብሄር ላይ የተመሰረተው ፌደራሊዝም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን በማውሳት፣ ስርአቱ መቀየር አለበት ብሎ እንደሚያምን ጠቁሟል፡፡
በደቦ ፍርድ ዜጎች እየተገደሉ መሆኑና በርካቶች መፈናቀላቸው የለውጡ ፈተናዎች እንደሆኑ የጠቆመው ሰማያዊ ፓርቲ፤ የፍትህና የዲሞክራሲ ተቋማትን ገለልተኛ አድርጎ በማዋቀር፣ የህግ የበላይነት ማስከበር እንደሚያስፈልግ አስረድቷል፡፡   
በሌላ በኩል፤ ፓርቲው ከለውጡ ጋር አብሮ ለመጓዝ  የፖለቲካ ፕሮግራሙንና ህገ ደንቡን ለማሻሻል  በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ይህን እውን ለማድረግም ከወዲሁ ከተለያዩ  ምሁራንና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር እየተወያየ መሆኑን ጠቁሞ፤አንድ ሃገር አቀፍ ግዙፍ ፓርቲ ለመመስረትም ከአርበኞች ግንቦት 7 እና ከሙስሊሙ ማህበረሰብ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ጋር  ምክክር መጀመሩን አስታውቋል፡፡   
በ2012 ለሚካሄደው አገራዊ  ምርጫም ከመላ ሀገሪቱ ክልሎች፣ ዞኖችና ወረዳዎች ተወካዮችን በመመልመል ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የገለጸው  ፓርቲው፤ በ547 የምርጫ ጣቢያዎች እጩዎችን ለማቅረብ ከወዲሁ እቅድ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

Read 7115 times