Saturday, 03 November 2018 15:32

“ራይድ” የታክሲ አገልግሎት ድርጅት በደል እየደረሰብኝ ነው ሲል አማረረ

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

  ሃይብሪድ ዲዛይንስ (ራይድ) የታክሲ አገልግሎት ድርጅት፤ ሕጋዊና ዓለምአቀፍ የጥራት ደረጃ ያለው አገልግሎት እየሰጠሁ ቢሆንም የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ሕገ-ወጥ ናችሁ በሚል በደል እያደረሰብኝ ነው ሲል አማረረ፡፡
ድርጅቱ ትናንት በሸራተን አዲስ ሆቴል ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፤  “የትራንስፖርት መጥሪያ ቴክኖሎጂ አገልግሎት ለመስጠት ሕጋዊ ፈቃድ ያለን ብንሆንም የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አብረውን ለኅብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጡ ያሉትን ከ900 በላይ ኮድ 3 የኪራይ መኪኖች ሕገ-ወጥ ናችሁ እያለ በሞተር እያሳደደ፣ በብጣሽ ወረቀት እየከሰሰና መኪኖችን እያሰረ ነው” ብሏል።
“ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸውና ግብር እየከፈሉ በግልጽ አገልግሎት እየሰጡ ያሉትን ኮድ 3 የኪራይ መኪኖች ሕገ -ወጥ ናቸው በማለት ለ10ሩም ክፍለ ከተሞች ደብዳቤ መጻፉና በሚዲያ ማስነገሩ ትክክል አይደለም” ያለው ድርጅቱ፤ “በዚህ አገልግሎት አሰጣጥ ክልከላ ላይ ጥቅማቸው የተነካ ቡድኖች ከጀርባው ያሉ ይመስለናል” ብሏል፡፡
“እኛ ሕጋዊ ፈቃድ ያለን በቴክኖሎጂ አገልግሎት በመስጠት በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየውን የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል፣ ኮድ 3 መኪኖች ካላቸው ወጣቶች ጋር እየሠራን ነው” ያለችው የሃይብሪድ ዲዛይንስ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሳምራዊት ፍቅሩ፤ “አባሎቻችን በብጣሽ ወረቀት ይከሰሳሉ፣ መኪናቸው ይታሰራል፣ ኮንትሮባንድ ነጋዴ ነህ… እየተባሉ የተለያዩ ቅጣቶች ይደርስባቸዋል” በማለት ችግራቸውን ገልፃለች፡፡
ለወጣቶች የሥራ ዕድል እየፈጠርን በመሆኑ ከአገር ተሰደው የነበሩ ሴቶች እየተመለሱ መኪና ገዝተው ከእኛ ጋር ጥሩ እየሠሩ ነው፤ ትራንስፖርቱን እያሳለጥን ከመሆኑም በላይ የሰዎችን ሕይወት እየለወጥን ነው ያለችው ሳምራዊት፤ “ከእኛ ጋር ለሚሠሩት ስለ አገልግሎት አሰጣጡ ሥልጠና እንሰጣለቸዋን፤ አሁን ሕገ-ወጥ ናችሁ እየተባሉ የሚዋከቡና በአገራቸው መሥራት የማይችሉ ከሆነ ግን ተበሳጭተው ወደ ስደት እንዲሄዱ መግፋት ይሆናል” ብላለች፡፡
የተጻፈው የእግድ ደብዳቤ ራሱ ሕገ ወጥ ነው ያሉት የድርጅቱ የሕግ አማካሪ አቶ ቶሎሳ ደሚ፤ የኮድ 3 መኪኖች ሊብሬያቸው ላይ የመኪና ኪራይ አገልግሎት እንዲሰጡ ፈቃድ አላቸው፡፡ የንግድ ሥራ ፈቃድም ያላቸው ናቸው፡፡ ሁለቱን አጣምሮ ወደ ሥራ መግባት ይቻላል፡፡ ስለዚህ እኛ ፈቃድ የመጠየቅ ሕጋዊ ግዴታ የለብንም” ብለዋል፡፡
“ያለ ሕግ መሠረት በብጣሽ ወረቀት መክሰስ ራሱ ሕገ -ወጥ ነው፤ ምክንያቱም ትራፊክ ፖሊስ ሲከስስ የሚሰጠው ፓድ፣ ቁጥርና የክሱን ምክንያት የሚገልጽ ነው” ሲሉ አስረድተዋል - የህግ አማካሪው፡፡

Read 3642 times