Saturday, 27 October 2018 10:39

አለማወቄን ለማወቅ ያነሳኋቸው ጥያቄዎች?!

Written by  ከኮ/ሸዋዬ አድማሱ (ጡ/ፖ)
Rate this item
(2 votes)

(በልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም “የትውልድ አደራ” መጽሐፍ ላይ የቀረበ አስተያየት- ሁለተኛ ክፍል)

 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መነሳት
“ግርማዊነታቸው ወደ ሀገራቸው ለመምጣት እንቅስቃሴ ጀመሩ፤ እንግሊዞች በሱዳንና በኤርትራ በኩል አድርገው ወደ ኢትዮጵያ በሚመጡበት ጊዜ እኛ አድዋ ነበርን፡፡ እንግሊዞች ልኡል ራስ ሥዩምን እዚያ መጡና ተገናኝተው፣ እኛ የመጣነው ወራሪውን ፋሽዝምን ለማጥፋት ብዙ መሳሪያ ይዘን ነው፡፡ ግን የሰው ኃይል የለንም ካሏቸው በኋላ፣ ሕዝቡን አስተባብረው፣ ለሀገርህ ነፃነት ክንድህን አንሳ ብለው እንዲያውጁ መመሪያ ተሰጣቸው፡፡ እሳቸውም ሕዝቡን አስተባብረው 74,000 (ሰባ አራት ሺህ) ሠራዊት አሰልፈው አምባላጌ የመሸገውን የዱካዲ አውስታን ጦር ከእንግሊዝ የጦር ጀኔራል ጋር በመሆን ወግተው ድል አድርገው፣ ዱካዲ አውስታ እጁን ሰጥቶ ጦርነቱ ቆመ። ከዚህ በኋላ እንግሊዞች ልዑል ራስን ወደ አስመራ ወሰዱአቸውና በኢጣልያ የግዛት ክፍፍል መሠረት፣ አንተ የሰሜኑን ክፍል አስተዳደር ቢሉአቸው፣ አገር አልከፋፍልም በማለት ጥያቄውን ባለመቀበል ወደ አድዋ ተመለሱ” ብለዋል፡፡ (ክፍል 3፤ ከገጽ 32 - 36)
 አስተያየት
አቀራረቡ ልዑል ራስ ሥዩም ከጣልያን ባለሟልነት ወይም ከምርኮኝነት ወጥተው ወደ አርበኝነት መመለሳቸውን ለማጠየቅ ይመስላል፡፡ ግን አምስት ዓመት ሙሉ ከእነ ቤተሰባቸው ተንከባክቦ የያዛቸው የጣልያን መንግስት በምን ሁኔታ ለቋቸው፣ አድዋ ሄደው ከእንግሊዞች ጋር ተገናኙ? አምባላጌ የመሸገውን የጣልያን ጦር ለማስወጣት የኢትዮጵያ ጦር በልዑል ራስ ሥዩም መሪነት መሆኑን ተድላ ዘዩሐንስም ጽፈውታል፡፡  
የተድላ ዘዩሐንስ የታሪክ መጽሐፍ በገጽ 255 ስለ አምባላጌው ጦርነት ሲተርክ፡- አምባላጌ ወጥቶ የመሸገው የጣልያን ጦር በዱካዲ አውስታን በጀኔራል ፍሩስኪ የሚመራ እንደነበረ፣ የኢትዮጵያ ጦር በልዑል ራስ ስዩምና በምክትላቸው በደጃዝማች አባይ ካሳ መሆኑን ጠቁሞ፤ የጦርነቱን ከባድነት እንደሚከተለው ይገልጸዋል፡-
“ሚያዝያ 10 ቀን 1933 ተኩስ ተከፈተ፤ ጦርነቱ ከባድ ሆነ፡፡ ለኢጣልያኖች በ1933 ዓ.ም ይህን ተራራ መልቀቅ በ1928 ዓ.ም የመያዙን ያህል ቀላል አልነበረም። ከማለቅ ወይም ከመማረክ በቀር ሌላ ምርጫ አልነበራቸውም፤ ስለዚህ የቻሉትን ያህል በርትተው ተዋጉ፡፡ ጦርነቱ እስከ ሚያዝያ 30 ቀን ሳያቋርጥ ቀንና ሌሊት ተካሄደ። ግንቦት 1 ቀን 1933 ዓ.ም በእንግሊዞችና በጣልያኖች መካከል ንግግር ተደረገ። ድርድሩ ጣልያኖች ከእነ መሳሪያቸው ለእንግሊዝ እጅ ሊሰጡ ሆነ፡፡ ይህ በምሥጢር የተደረገ ስምምነት በአርበኞች ዘንድ ሲሰማ ቁጣ አስነሳ፡፡ ጦርነቱ ቀጥሎ የጣልያኑ ጄኔራል ከእነ ተከታዮቹ ተገደለ፡፡ ጦርነቱ አልበርድ ስላለ የእንግሊዙ የጦር አዛዥ ራስ ሥዩምን ማነጋገር ግድ ሆነበት፤ ስለ ውጊያውና ስለ ምርኮው ከደጃዝማች ዐባይ ከሳ ጋር እንዲነጋገር ስምምነት ተደረሰ፡፡ የኢትዮጵያ የአርበኞች አለቆችና የእንግሊዝ የጦር መኮንኖች  ተነጋግረው፣ ጣልያኖች እጃቸውን ሰጥተው፣ ለጥበቃ ወደ እንግሊዞች እንዲተላለፉ መኪናዎችና መድፎችን እንግሊዞች እንዲረከቡ፣ መትረየስና ቀላል መሳሪያ በማራኪዎች በኢትዮጵያውን እጅ እንዲሆን ስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡ ውጊያው በዚህ ስምምነት መሰረት ቆሞ ዱካ ዲ.አውስታና ጄኔራል ፍሩስኪ እጅ ሰጥተው፣ የአምባላጌ ውጊያ ከፍፃሜ ደረሰ፡፡”
ከላይ እንዳየነው የአምባላጌው ጦርነት በኢትዮጵያ በኩል በራስ ሥዩም የጦር መሪነት በደጃዝማች አባይ ካሳ ምክትልነት ነው የተደረገው፡፡  ራስ ሥዩምና ደጃዝማች ዐባይ ካሳ በ1929 ዓ.ም በምን ሁኔታ እንደተለያዩ አንብበናል፡፡ አሁን ከአራት ዓመታት በኋላ አንዱ ከእልፈኝ ወጥቶ፣ አንዱ ከጫካ ወጥቶ አዛዥና ታዛዥ ሆነው ለአንድ አላማ መሰለፋቸው ተአምር ሊባል የሚችል ነው፡፡
መቸም የእርቅ ድርድር ሳይደረግ ሁለቱ ተገናኙ ማለት ይከብዳል፡፡ ስለሆነም ራስ ሥዩም አምስት ዓመት ተንከባክቦ ካስቀመጣቸው ከጣልያን ጋር ግንኙነታቸው በምን ሁኔታ እንደተቋረጠ፣ ከእንግሊዞች ጋር በምን ሁኔታ ተማምነው ሕዝብ ቀስቃሽ እንዳደረጓቸው፣ ራስ ሥዩም አምስቱን ዓመት ከጣልያን ጋር ማሳለፋቸውን የሚያውቀው የትግራይ ሕዝብ እንዴት አምኖ እንደተከተላቸው፣ ከአርበኞቹ ከእነ ደጃዝማች ዐባይ ጋር እንዴት ሊቀራረቡ እንደቻሉ በዝርዝር መገለጥ ነበረበት፡፡ ይህ ባለመሆኑ ታሪኩን ጎደሎ አድርጎታል እላለሁ፡፡
ደጃዝማች ካሳ ሥዩም
ደራሲው በገጽ ሃያ በመጨረሻው አንቀጽ ላይ “በዚህ አጋጣሚ ከልዑል አባቴ የበኩር ልጅ ከደጃዝማች ካሳ ሥዩም ጋር የተያያዘ ነገር ልግለጽ--” በማለት የሚከተለውን ጽፈዋል፡-
“ደጃዝማች ካሳ አባታችን ልዑል ጌታዬ አቤቱ ኢያሱን ከንግስተ ነገሥታት ዘውዲቱ ጋር ለማስታረቅ ሞክረዋል በሚል አዲስ አበባ በደጅ ጠኝነት እንዲቀመጡ መደረጋቸው ያስቆጣቸው ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአገራቸው ጉዳይ በተለይም በኤርትራ የቅኝ አገዛዝ ስር መውደቅ ክፉኛ ይቆጡ ነበር፡፡ ራማ ተራራ ላይ ሆነው በመነፅር ሲመለከቱ የኢጣልያ መድፎች ወደ ኢትዮጵያ ተነጣጥረው ይመለከታሉ፡፡ ጭፍሮቻቸውን ወደ ጦር ሠፈሩ በመላክ ወደ ኢትዮጵያ አቅጣጫ የተደገኑ መድፎችህን አዙር፤ አለዚያ መጣሁልህ የሚል መልእክት ያስተላልፋሉ፡፡ አዛዡ ለበላዮቹ በማስታወቁ፣ አስታግሱልን የሚል መልእክት ለኢትዮጵያ መንግስት ይላካል፡፡ ሁኔታው ያሳሰባቸው አልጋ ወራሽ ለአባታችን ስለ ጉዳዩ ገልጠው ደጃዝማች ወደ አዲስ አበባ እንዲላኩ ያዛሉ፡፡ ደጃዝማች ካሳ ተገስጸው አክስታቸው ወ/ሮ አስቴር መንገሻ ቤት በቁም እስር ይቀመጣሉ፤ ግዞቱ ያበሳጫቸው ስለነበር አንድ ሌሊት ሊያመልጡ ሲሄዱ፣ ሱሉልታ ላይ እንደደረሱ አገሬው ታዝዞ ስለከበባቸው፣ እጅ ላለመስጠት ተታኩሰው ሞቱ፡፡” በሚል ደምድመውታል፡፡ (ክፍል4)
ይህን ታሪክ መርስዔ ሀዘን ወልደ ቂርቆስ “የሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ” በሚለው መጽሐፋቸው  ተቃራኒ በሆነ መንገድ ጽፈውታል፡፡ አሳጥሬ ላቅርበው፡-
“የትግሬ ገዥ ራስ ስዩም መንገሻ ባለፈው ዓመት (1909 መሆኑ ነው) በሚያዝያ ወር ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ልጃቸው ደጃዝማች ካሳ የአድዋ ገዥ ሆኖ ቀርቶ ነበር፡፡ አባቱ አዲስ አበባ መክረማቸውን ባወቀ ጊዜ ግዛት ለመደረብ ፈልጎ ሸፈተና የሌላውን አገር ይወጋ ጀመር፡፤ የትግሬ ወጣቶች ተከተሉትና ኃይል ተሰማው፤ የተምቤን ገዥ .. (አጎቱን) ወግቶ አገሩን በእጁ አደረገ፤ ሽሬንም ያዘ ….. ወደ መቀሌ ሄዶ ያባቱን እንደራሴ ወግቶ ከተማውን ያዘ፡፡ ይህ ነገር አዲስ አበባ ሲሰማ ራስ ስዩም ወደ መቀሌ ሄደው እንዲያረጋጉ ስለተወሰነ ከራስ ጉግሳ አርአያ ጋር ወደ ትግሬ ተጓዙ… ማይጨው ሲገቡ ህዝቡ በደስታ ተቀበላቸው፡፡ ደጃዝማች ካሳ መቀሌን ለቅቆ አድዋ ገባ፡፡ መቀሌ ገብተው ና ብለው ቢልኩበት አልመጣም ብሎ አድዋንና ሽሬን ይዞ አስቸገረ፡፡” (ገፅ 215 230 እና 234)
ከላይ የተጠቀሰው መጽሐፍ አተራረክ ድርጊቱ የተፈጸመበትን ዘመን ተከትሎ ስለሆነ በ1912 የተፈጸመውን በገጽ 230 በመቀጠል፡-
“ደጃዝማች በግዛቱ በአድዋ ብቻ ሳይሆን በሌላውም በትግሬ ክፍል ሹም ሽር እያደረገ ቀጠለ። አባቱ ቢዘምቱበትም ስፍራውን ለቅቆ ይሸሽና ሲመለሱ አሽከሮቻቸውን እየወጋ አወከ… ራስ ሥዩም ከአልጋ ወራሽ ጋር በጋብቻ ለማቀራረብ ሞክረው አልተቀበለም። ከዚህ በኋላ ደጃዝማች ማሩና ደጃዝማች ገብረ መድህን እንደዚሁም እናቱ ማልደው እጁን ለአባቱ ሰጠ.. አባትዬውም እንዳባትነታቸው ገርፈው ከቀጡት በኋላ አቆራኝተው …… ወደ አዲስ አበባ ላኩት፡፡ አልጋ ወራሽ ዘንድ ቀርቦ አክስቱ ወ/ሮ አስቴር መንገሻ ዘንድ በቁም እሥረኛነት ተቀመጠ--፡፡” ዘመኑ ወደ 1913 ተሸጋግሮ፣ ታሪኩ ይቀጥላል፡፡
“ደጃዝማች ካሳ ሥዩም ካሁን በፊት እንደተነገረው… በእሥረኛነት ተቀምጦ ነበር፡፡ በዚህ ዓመት በየካቲት 2 ቀን ከታሠረበት አምልጦ ሲሄድ ሜታ አድአበርጋ ላይ ከባላገር ጋር ተታኩሶ መሞቱ ተሰማ…”
ታሪኩ ስለ አማሟቱ ሰፋ አድርጎ ይተነትናል። የታሪኩ ፍሬ ነገር እስከዚህ ያለው ስለሆነ ዝርዝሩን ትቸዋለሁ፡፡
አስተያየት
ስለ ደጃዝማች ካሳ ስዩም በሁለቱ መጻሕፍት የተጻፈውን ስናነብ ተቃራኒነቱ ግልጽ ነው፡፡ ምናልባት ልዑል ራስ መንገሻ፣ በመርስዔ ሀዘን መጽሐፍ ስለ ወንድማቸው የተጻፈውን አላነበቡት ይሆናል፡፡ ግን የመጽሐፋቸውን ረቂቅ የገመገሙና ያረሙ ሊቃውንት ያነበቡት መሆኑን አልጠራጠርም፡፡ ታዲያ ልዑል ስለ ወንድማቸው የጻፉት ትክክለኛ ታሪክ ከሆነ፣ በመርስዔ ሃዘን የተተረከውን እያስተባበሉ እንዲጽፉ ለምን አላደረጉም? ያ የማይቻል ከሆነም “በአጋጣሚ ልንገራችሁ” ብለው በቁንጽል የወንድማቸውን ማንነት የገለጡበት ጽሁፍ ተአማኒነቱን የማያረጋግጥ ከሆነ ቢሰረዝ ምን ያጎድል ነበር፡፡
እነዚህ ምሁራን በዚህ ጉዳይ የሁለቱም መጻሕፍት ትረካ እውነት ነው ማለታቸው ይሆን? መጽሐፍ መገምገም ማረም፣ ሚዛን አሟልቷል ብሎ መመስከር እንደዚህ መሆኑ ነውን? በዚህ መነሻ አንባቢ ለካስ የምሁራኑ ስም በየመጽሐፉ የሚለጠፍ ለማሻሻጫነት ነው ብሎ ቢተች ተሳስቷል ይባል ይሆን? ሰሚ ጆሮ ይስጠን፡፡
ክፍል አምስት  ገጽ 35-50
ልዑል ራስ ሥዩም ከአስመራ ወደ አድዋ እንደተመለሱ ንጉሰ ነገስቱ አቶ ሎሬንዞ ታእዛዝን እንጠብቅዎታለንና ወደ እኛ ይምጡ የሚል መልእክት አሲዘው ላኩባቸው፡፡ ልዑልም ጥሪውን አክብረው አዲስ አበባ መጡና ከንጉሰ ነገሥቱ ጋር ተገናኙ። ቀጥሎም የትግራይ አስተዳደር በእሳቸው ስም እንዲሆን ተደረገና እሳቸው አዲስ አበባ እንዲቀመጡ ሆነ፡፡ ለጠቅላይ ግዛቱ አስተዳደር በዲሬክተርነት ከመሀል አገር ሰው ተሾመበት፡፡ ደጃዝማች መንገሻ ሥዩም የቀድሞውን ግዛታቸውን እንዲያስተዳድሩና በተጨማሪም በጦርነቱ ጊዜ ለተዋጉ ለቆሰሉና ለሙት ቤተሰቦች ተገቢው ካሳ እንዲከፈል ዝርዝር ስለተዘጋጀ ጉዳዩን ለዳይሬክተሩ እያቀረቡ እንዲያስፈጽሙ ከልኡል አባታቸው ትዕዛዝ ተሰጣቸው፡፡ (የትግራይ አስተዳደር በዚህ ሁኔታ እንዲመራ ተደረገ ማለት ነው።)
የቅሬታ እርሾዎች
ደጃዝማች በተሰጣቸው መመሪያ መሰረት ሥራቸውን ጀምረው የውለታ ተከፋዮችን ዝርዝር ለዲሬክተሩ አቀረቡ፡፡ ዲሬክተሩ ግን “ጥሩ ነው ቅድሚያ የሚሰጥ ግን ለመንግስት አሽከሮች ነው” የሚል መልስ ሰጧቸው፡፡ ይህን ሲሰሙ ደጃዝማች “እኛስ የማን አሽከር ነን? ልዑል ጌታዬስ የማን ናቸው?” በሚል ቂም ቋጠሩ፡፡
በሕዝቡም በኩል፡-
ልዑል ራስ ስዩም አዲስ አበባ ተጠርተው እዚያው ተቀማጭ መሆናቸው፤
የትግራይንና የሕዝቡን ማንነት የማያውቁ፣ የራሳቸውም ማንነት የማይታወቅ ከመሀል አገር እየተሾሙ እየመጡ የአስተዳደር በደል ማድረሳቸው፤
 በ1928 ዓ.ም ጣልያን ኢትዮጵያን ሲወር የልዑል ራስ ስዩም ማዕረግ ማርሻል ደረጃ የነበረ ሲሆን አሁን ወደ ሜጀር ጄኔራልነት መውረዱ፤
ሰባት ወር ሙሉ ጠላትን መክተው የተዋጉ፣ ጃንሆይ ወደ መሀል አገር ሲመለሱ ጠላት ተከታትሎ እንዳያጠቃቸው ልዑል ራስ ብቻቸውን ቀርተው እንዲከላከሉ በሚል ለጠላት መጋለጣቸው፤
የትግራይ ሕዝብ በልዑል ራስ ሥዩም መሪነት አምባላጌ መሽጎ የነበረውን በዱካዲ.አውስታ የሚመራውን አርባ ሺህ ጦር ድል አድርጎ ውለታ ቢስ መሆኑ፤
ሕዝቡ ከዚህ በላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ተመሳሳይ ምክንያቶች እየተወያየ እሮሮ ማስማት ቀጠለ፡፡ ለእሮሮው ደጃዝማችም ተካፋይ መሆናቸውን ከማንፀባረቅ አልተቆጠቡም፡፡   
ዋጅራት
የትግራይ ሕዝብ በመንግስት ላይ እንደቆዘመ የዋጅራት ጉዳይ ተከሰተ፡፡ የዋጅራት ሕዝብ በአዳሎች ላይ ዘምቶ ግድያና ዝርፊያ ፈጽሞ ይኸው በአዳሎች በኩል ለንጉሰ ነገስቱ ክስ ቀርቦ ንጉሱም በዋጅራቶች ላይ መቀጫ ጥለው ቅጣቱን እንዲያስፈጽሙ ለትግራይ ጠ/ግዛት ዳይሬክተርና ለደጃዝማች መንገሻ በስም ደብዳቤ ተጻፈላቸው፡፡ ደብዳቤው እንደደረሰ ትዕዛዙ ሁለቱንም የሚመለከት ሲሆን ዳይሬክተሩ “እኔ አሞኛል አንተ ሄደህ አስፈጽም” ብለው ደጃዝማችን አዘዙአቸው። ደጃዝማችም ብቻቸውን ላለመሄድ ቢከራከሩም ተቀባይ ስላጡ ከተመደቡላቸው መኳንንት ጋር ተመካክረው ትዕዛዙን ለማስፈጸም ወደ ዋጅራት ሄዱ። ዋጅራት ደርሰው ህዝቡን ሰብስበው አዋጅ አስነግረው፣ ሕዝቡ በሰላም የተጣለበትን መቀጫ እየከፈለ፣ የተዘረፈ ከብትና ሃብት መመለስ ጀመረ፡፡ በዚህ ሥራ ላይ ሳምንት ያህል እንደቆዩ ሽማግሌዎች መጥተው ደጃዝማች አባይ ካህሳይ፣ ሕዝቡን አስተባብሮ ዋጅራትን ሊወጋ እየመጣ ነው ይሉአቸዋል፡፡ እሳቸው እኔ ተልኬ የንጉሰ ነገሥቱን ትዕዛዝ በማስፈፀም ላይ እያለሁ በላዬ ላይ እንዴት ጦር ይታዘዛል ብለው ወደ መቀሌ ተመልሰው፣ ዳይሬክተሩን፤ “እንዴ ራስዎ ልከውኝ ጦር እንዴት ይልኩብኛል?” ይሉአቸዋል፡፡
ዳይሬክተሩም “እኔ የማውቀው ነገር የለም፤ ደጃዝማች ዐባይ በራሳቸው ፈቃድ ነው የሚዘምቱ” ይሏቸዋል፡፡ ይህ ከሆነ ደጃዝማች አባይን እናነጋግር ብለው ደጃዝማች ወደ አሉበት ተያይዘው ሄደው፣ ሕዝቡ ያለበትን ሰላማዊ ሁኔታና ቅጣቱንም እየከፈለ መሆኑን ገለጡላቸው፡፡ ደጃዝማች ዐባይ ግን የሚመለሱ አልሆኑም፡፡ በዘመቻው ገፉበትና ከዋጅራት ሕዝብ ጋር ተኩስ ከፍተው ብዙ ተከታዮቻቸውን አስገድለው፣ ራሳቸውም ከሶስት ረዳቶቻቸው ጋር በዋጅራቶች ምርኮኛ ሆነው አረፉት፡፡
የልዑል አልጋ ወራሽ መዝመት
የዋጅራት ግጭትና ውጤቱ በንጉሰ ነገስቱ ዘንድ እንደተሰማ ልዑል መርድ አዝማች ለአስፋ ወሰን የወሎን ጦር አዝምተው አገሩን እንዲያረጋጉ ታዘዙ፡፡ ልኡል አልጋ ወራሽ በትዕዛዙ መሰረት ጦር መርተው፣ መቀሌ ደርሰው ሁኔታውን ከዳሬክተሩም ከደጃዝማች መንገሻም ተረዱ፡፡ ምን ይደረግ በሚለው ሲመካከሩ፣ የመጀመሪያው እርምጃ ምርኮኞችን ማስለቀቅ ስለሆነ እኛ ብንሄድ ህዝቡ ጦር ተላከብን ብሎ ተኩስ ስለሚከፍት፣ አንተን ሕዝቡ ስለሚያውቅህ ሥራውንም በሰላም የጀመርከው ስለሆነ፣ አንተ ሄደህ ሕዝቡን አሳምነህ ምርኮኞችን አስለቅቅ፣ የሚል ትዕዛዝ ለደጃዝማች ተሰጠ፡፡ ደጃዝማች መንገሻ ትዕዛዙን ተቀብለው ወደ ዋጅራት ሄደው ከሕዝቡ ጋር ተገናኝተው፣ የፈፀሙት የበሰለና ያላሰለሰ ተግባር ምንም እንኳ ታሪኩን በራሳቸው ስም ቢገልጡትም፣ የበሰሉ መኳንንት ወይም የሀገር ሽማግሌዎች ምክር እንዳለበት አያጠራጥርም፡፡
ደጃዝማች ቀንቷቸው ያለምንም ችግር ሦስቱን ምርኮኞች ተረክበው አምጥተው፣ ለልዑል አልጋ ወራሽ አስረከቡ፡፡ ልኡል አልጋ ወራሽም ምርኮኞችን ተረክበው ደጃዝማችን አመስግነው፣ አንተ እዚሁ ሁን ብለው ተመለሱ፡፡ የሀገሩም ፀጥታ የተረጋጋ መሰለ፡፡
ትግራይ ወየነ
ልዑል አልጋ ወራሽ እነ ደጃዝማች ዐባይን ይዘው ወደ ሸዋ መመለሳቸው ሊደርስ የነበረውን ደም መፋሰስ ያስቀረ ቢሆንም፣ አስተዳደሩ የፈጠረውን ችግርና ቅሬታ አልሻረውም። ከላይ የተዘረዘሩት የሕዝብ ብሶቶች እየከረሩ መጡ፡፡ ደጃዝማች መረር ያለውን ብሶት በድጋሚ ሲገልጡ፤ “ልዑል ጌታዬ ራስ ሥዩም በ1928 ዓ.ም ክብራቸው በማርሻልነት ደረጃ ነበር፤ አሁን ባልታወቀ ምክንያት ደረጃቸው ወርዶ ወደ ሜጀር ጀኔራልነት ዝቅ ብሏል፡፡ ይህም በህዝቡ ዘንድ አንድ ዓይነት መሻከር ፈጥሯል፤ በራሳቸውም በሁላችንም፡፡ በእኔም ጭምር ምንም ሕፃን ብሆን” የሚለውን አሥምረውበታል፡፡
ሕዝቡ ለአመጽ እየተባበረ መሄዱን ሲገልጡ፤ “የነበረው ችግር ህዝቡን አነቃንቆታል፤ ብዙ እብሪተኞች ደግሞ በየቦታው ሊኖሩ ይችላሉና እነሱ የሚሰጡትን አመራር እየተከተለ ክንድህን ለማንሳት ምን ያስፈራሃል መንግስት እኮ የለም፣ እኛን የሞትነውን  ስንት የሆንነውን ተመልሶ እንኳ አላየንም፣ እናንተ ባለውለታ ናችሁ ብሎ ላፈሰስነው ደማችን አልካሰንም፤ የኢትዮጵያ ጋሻ የሆነውን ሕዝብና አገር ማን ከጉዳይ ቆጠረው፤ ዘላለም እንደተጠቃን የምንኖር ነን” ብለዋል።
“ያም ሆነ ይህ ሕዝቡ ይህን በመሰለው ብሶት ተገፋፍቶ የወያኔ ግጭት  ተከሰተ፡፡ ሻለቃ ኢሳያስ ገ/ሥላሴ ጦርነቱን መርተው፣ ከሕዝብ ጋር ተጋጭተው ብዙ ውጊያ ተደረገ፡፡ በእኛ መንግስት በኩልም ስብሰባ ተደርጎ እንዴት አድርገን ወያኔን እንከላለከል ተብሎ ተመከረና “አንተ እቤተ መንግስት ሁንና መቀሌ ከተማን ጠብቅ፤ እኛ እንዳኢየሱስ ሄደን የሚያስፈልገውን እናደርጋለን” በሚል ተወሰነ፡፡ እኔ መቀሌ ቤተ መንግስት በምጠብቅበት ጊዜ ሕዝቡ ጠቅላላው እኔን ከአደጋ ለመከላከል ቤተ መንግስት ገባ፡፡ ከኩይሐ ድል የሆነውን የመንግስት ጦር አዝማች መኮንኖችን እነ ሻለቃ ኢሳያስን ተቀብዬ የቆሰሉትንም ራሴ አስታመምኩ፤ በበኩሌ በመከላከል ላይ እያለሁ እነሱ ተነስተው ወደ ሸዋ ሄዱ። እኔ ለብቻዬ ቀረሁ፤ ያንን የባላገር ኃይል ምንም መመከት ባለመቻሉ ተነስቼ ወደ ተምቤን ሄድኩ፡፡
“እኔ ተምቤን እያለሁ የመከላከያ ሚኒስትሩ ራስ አበበ አረጋይ፣ የእንግሊዝ ጦር መኮንኖችን ይዘው መጥተው አምባላጌ ላይ ተዋጉ፡፡ ብዙ ችግርና መከራ ደረሰ፡፡ ባላገሩ የማይበገር ሆነ፡፡ አንድ የእንግሊዝ መኮንን ተገደለ፡፡ ከዚህ በኋላ በገበያ ቀን መቀሌ ላይ አይሮፕላን ተልኮ ቦምብ ጣለና ብዙ ሰው አለቀ። በሕዝቡ በኩል ሰፊ ድንጋጤና ፍርሃት ተፈጠረ፡፡ ሕዝቡ ተደናግጦ ሲበተን በድል አድራጊነት መቀሌ ገቡ፡፡ ኮሎኔል ክፍሌና አቡነ ዮሐንስ የተባሉ ጳጳስ ከግርማዊነታቸው ተልከው እኔ ዘንድ ተምቤን መጡና “አንተ ስትከላከል የቆየህ ነህ፤ አሁንም ይኸው መቀሌ ራስ አበበ ገብተዋልና እንድትመጣ” የሚል ትዕዛዝ ደረሰኝ፡፡ እኔም ከታላቅ እህቴና ከሌሎችም አባረውኝ ከነበሩ መኳንንት ጋር መቀሌ ገባሁ፡፡
“እነ ብላታ ኃይለማርያም እንደ ወያኔ መሪነት ሲያዙ “ዋናው እማ እሱ አይደለም እንዴ በዱለታው ውስጥ የልዑል ራስ ሥዩም መኳንንት ያሉበት ነው” እየተባለ ይወራ ጀመር፡፡ አንድ አስር ቀን ከቆየሁ በኋላ ራስ አበበ ዘንድ ማታ ተጠርቼ፣ በግርማዊነታቸው ትዕዛዝ መሰረት አዲስ አበባ እንድትላክ ስለታዘዘ ነገ ጠዋት አብረኸን ትሄዳለህ፤ አሁን እጅህ ተይዞ እዚህ እንድታድር ተባልኩ፡፡ እስራት ሳይደርስብኝ ከእሳቸው ጋር አደርኩ፡፡  በማግስቱ ወደ አርባ የሚሆኑ የልዑል ጌታዬ መኳንንት፣ በአሥር ትሬንታ ኳትሮ የጭነት መኪና መቶ መቶ ወታደር በተጫነ፣ እኛ ግንባር ላይ (ጋቢና) ተሳፍረን ወደ ደሴ ተጓዝን፡፡   በአንድ ከባድ መኪና መቶ መቶ ወታደር ሆኖ በጠቅላላው በ1000 ጦር ታጅበን ነበር ማለት ነው፡፡
“አጃቢው ከደሴ ተመለሰ፡፡ ደሴ አዳር ሆኖ በማግስቱ በአንድ ትልቅ አውቶቡስና በአንድ ትንሽ መኪና ተሳፍረን አዲስ አበባ ገባን፡፡  አዲስ አበባ ገብተን፣ አንድ ቀን ገነተ ልዑል ቤተ መንግስት አድረን በማግስቱ ደጃዝማች ከበደ ተሰማ ተረክበው ወስደው  በመኖሪያ ቤታቸው አስቀመጡኝ። ግቢው በአንድ ሻምበል ጦር ዙሪያ ጥበቃ እየተደረገለት ለሰባት ወራት ተቀመጥን። በዚህ ጊዜ ውስጥ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብሳቢነት ሚኒስትሮች ሁሉ እየተሰበሰቡ ይመረምሩኝ ነበር።” በማለት የትግራይ ህዝብ አመጽ ማለትም መወየኑ በዚህ ሁኔታ ፍጻሜ ማግኘቱን በሰፊው ገልጠውታል፡፡
አስተያየት
በዚህ በክፍል አምስት ማለትም ልዑል ራስ ሥዩም ወደ አዲስ አበባ ተጠርተው አዲስ አበባ ነዋሪ እንዲሆኑ ከተደረገበት ጊዜ ተነስቶ እስከ ወያኔ አነሳስና ፍጻሜ ድረስ የተተረከው በትግራይ ውስጥ የተካሄደው የሕዝብ አመፅ ነው፡፡ አመጽ በመንግስት በኩል ወንጀል ሲሆን በአመጸኛው በኩል ደግሞ መብትን የማስጠበቅ ትግል ሊባል ይችላል፡፡
መንግስት በሚያስተዳድረው ግዛት ውስጥ ሰላም ሲደፈርስ የችግሩን ምንጭ እውቆ ተገቢውን መፍትሄ የመውሰድ ግዴታ አለበት፡፡ በትግራይ ውስጥ ለተነሳው አመጽ የንጉሰ ነገስቱ መንግስት ሰላምን ለመፍጠር ምን እርምጃ እንደወሰደ አልተገለጸም። ይህን ታሪክ የሚተርኩት የመንግስት አካል የሆኑት የያኔው ደጃዝማች መንገሻ የዛሬው ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም፣ የሕዝቡን እሮሮ እየዘረዘሩ ከመግለጥና እሳቸውም የብሶቱ ተካፋይ መሆናቸውን ከማሳወቅ በስተቀር መንግስት ችግሩን ተረድቶ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ምን ሙከራ እንዳደረገ በአንድ አረፍተ ነገር እንኳ አልነገሩንም፤ ምክንያቱን ከራሳቸው በቀር የሚያውቅ ይኖር ይሆን?
እኔ ከላይ እንደተመለከታችሁት፣ በሌሎች ጉዳዮች ላይ በድርጊቶች እየተመራሁ የመሰሉኝን አስተያየቶች እየሰጠሁ መጥቻለሁ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ግን ምንም እንኳ  መንግስት የወሰደውን የሀይል እርምጃ  በተለይም ለገበያ በተሰበሰበ ህዝብ ላይ የተደረገውን የአውሮፕላን ጭፍጨፋ ባልደግፍም፣ መንግስት ታጋሽ መሆን አለበት ብዬ ስለማምን ትእግስቱን አሟጦ ጨርሶ ለዚህ ደረጃ የደረሰበት ምክንያት እስከ አልታወቀ ድረስ ሚዛናዊ አስተያየት መስጠት ያስቸግራል፡፡ ስለሆነም አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቤ የታሪኩን ሂደት ብቻ  በማሳወቅ አልፌዋለሁ፡፡
ማጠቃለያ
በዚህ ጽሁፌ መግቢያ እንደገለጽኩት፤ አስተያየት ለመስጠት የተነሳሁት ያነበብኩት ታሪክ በእድሜዬ ከሰማሁትና ካነበብኩት ጋር ሳጋጨው አንዳንዱ አጠራጣሪ፣ አንዳንዱ አጠያያቂ፣ አንዳንዱ አከራካሪ  እየሆነብኝ ስለመጣ ነው፡፡ ይህንን ግጭት የፈጠሩብኝ ምእራፍ አንድ፣ ሁለት፣ ሶስትና አራት ብቻ ናቸው። በእነዚህ ምእራፎች ሀተታ ላይ የመጽሀፉን ይዘት እየጠቀስኩ፣ በኔ በኩል ታሪኩ የተጋጨበትን ምክንያት በመሰለኝ እየተነተንኩ፣ ያገኘሁትንም ማስረጃ እየጠቀስኩ የምለውን ብዬ አጠቃልያለሁ፡፡
ልዑል ራስ መንገሻ እስከ ምእራፍ አምስት የተረኩት ታሪክ፣ ከልደታቸው እስከ ዙፋን ችሎት ያለውን ነው፡፡ ልዑሉ የተወለዱ በ 1919 ዓ.ም ሲሆን ዙፋን ችሎት ተከሰው የቀረቡት በ1936 ዓ.ም ነው፡፡ ይህ ሲቀናነስ 1936-1919=17 አንድ ሰው አካለ መጠን ደርሷል የሚባል 18 አመት ሲሞላው መሆኑ ልማዳዊም ህጋዊም ይመስለኛል፡፡ በትምህርትም በኩል በአብነት ትምህርት ዳዊት ከመድገም ያለፉ አይመስለኝም፡፡ በውጭ ትምህርት ሮማ በነበሩ ጊዜ እቤት ውስጥ እማር ነበር አሉ እንጂ ምን እንደተማሩ አልገለጡም፡፡
ወደ አዲስ አበባ ከተመለሱም በኋላ በጣሊያኖች ት/ቤት ገብተው በጥሩ ሁኔታ ይማሩ እንደነበረ ገለጹ  እንጂ የትምህርቱን አይነትና ደረጃ አልጻፉትም። እንግዲህ በዚህ እድሜና እውቀት የነበሩበትን ጊዜ ነው ወደ ኋላ 85 አመት ተመልሰው ሰነድ ሳያገላብጡ በቃል አስታውሰው የተረኩልን። በሰነድ ያላስደገፉበት ምክንያት ከልጅነት እስከ እውቀት ያሰባሰቡት ሰነድ በሞላ በደርግ ስለተወሰደባቸው መሆኑን በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ገልጠውታል፡፡
በዚህ ሁኔታ የቀረበ ጽሁፍ ግድፈትም ስህተትም ተቃርኖም ቢገኝበት አያስደንቅም፡፡ ደራሲው ግን ረቂቁን ለእርምት አቅርበውታል፡፡ በመግቢያቸውም ላይ እንደገለጡት፤ ለመጽሀፉ ይዘትና ጥራት በብዙ መልኩ የተባበሯቸውን አያሌ ምሁራን ከእነ ሙያቸውና አስተዋጽኦዋቸው ስማቸውን በዝርዝር በመግለጽ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ይህ በተቃራኒው ሲታይ ምናልባት ስህተት ቢገኝ እናንተም ተሳታፊ ናችሁ ማለት ሊሆን ይችላል፡፡ ስህተቱ ቅጣት የማያስከትል ቢሆንም ትዝብት ያስከትላል፡፡ ትዝብቱም ደግሞ ከመጽሐፉ ጋር እየኖረ ዘላለማዊ ትዝብት የሚሆን ይመስለኛል፡፡
ትዝብቱን እኔ ልጀምረው
ቀዳሚ ቃሉን የጻፉት ምሁር ስለ መጽሀፉ ይዘት ሲተነትኑ፤ “አንዳንዱን የህይወታቸውን ምእራፍ ሰፋ አድርገው ያቀርባሉ፡፡ አንዳንዱን አነስ አድርገው ያቀርባሉ። ሳሳ ብለው የቀረቡትን ትውስታዎች ስናነብ፤ ምነው ከዚህ ሰፋ ብሎ በተጻፈ የሚል ስሜት ያድርብናል፡፡” ካሉ በኋላ “በተከታታይ ገጽ ትውስታቸው ሰፋ ቢል እንወድ ነበር፤ ግን ያለውን ተቀብለን ንባባችንን ስንቀጥል--” ብለው ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡  በእውነት እንነጋገር ከተባለ ይህ አስተያየት ምኞት ሆኖ መቅረት ነበረበትን? ልዑል ራስ መንገሻ እኮ በህይወት አሉ፤ ከዚያም በላይ በመጽሐፌ ላይ አስተያየት ስጡልኝ ብለው በሆነ መንገድ ተገናኝታችኋል፤ ታዲያ የሳሳው እንዲወፍር ያጠረው እንዲረዝም ተወያይታችሁ ምኞት ወደ ተግባር እንዲለወጥ ለምን ሙከራ አልተደረገም? ሙከራ ተደርጎ ከደራሲው አሉታዊ መልስ ተገኝቶ ከሆነ በጎደሎ ታሪክ ላይ ውዳሴ አዘል ምስክርነት መስጠት ተገቢ ነውን? የንግድ ማስታወቂያ ቢመስልስ?
ትዝብቴ  ይህ ብቻ አይደለም፤ ሙሉ ጽሁፌ ትዝብት አዘል ሆኖ ይታየኛል፡፡ ማንን እንደታዘብኩ ለመፍረድ የሁሉም አንባቢ መብት እንደተጠበቀ ነው፡፡
ልኡል ራስ መንገሻ ከመጽሐፉ እንደተረዳሁት፣ ብዙ ጉዳዮች ነካ ነካ እያደረጉ አልፈዋል፡፡ ስለሆነም ከቤተሰብም ሆነ ከውጭ ፍላጎትና ሙያ ያለው ሰው ቃለ መጠይቅ እያደረገ ቢያወያያቸው ኖሮ ብዙ ጉዳዮች ተዘለው ሳያልፉ ለትውልድ ይተላለፉ ነበር እላለሁ፡፡ በተረፈ ቀሪ ህይወታቸውን በሰላም እንዲኖሩ እየተመኘሁ፣ የባለቤታቸውን ነፍስም አምላክ በገነት ያኑራት እላለሁ፡፡


Read 1366 times