Saturday, 27 October 2018 10:38

በቡና ምርት ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሄደ

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

“ኢትዮጵያ ከቡና ተገቢውን ጥቅም አላገኘችም”

 ኢትዮጵያ፣ የአረቢካ ቡና መገኛ ብቻ ሳትሆን፣ ለቡና ተስማሚ የሆነ ሰፊ መሬት፣ ምቹ ሥነ ምህዳር፣ በቂ የሰው ጉልበት፣ በልዩ ጣዕማቸውና የንጥረ ነገር ይዘታቸው በዓለም ተወዳጅ የሆኑ የቡና ዝርያዎች ባለቤት ብትሆንም ተገቢውን ጥቅም እያገኘች አይደለም ተባለ፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ዓለም አቀፋዊ “ተወዳዳሪነት፣ ዕድሎች፣ ተግዳሮቶችና የመፍትሄ ምክረ ሀሳብ” በሚል ርዕስ አቤጋ ማኔጅመንትና የቡናና ሻይ ባለስልጣን ባዘጋጁት ትናንት በሸራተን አዲስ ሆቴል በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ የቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳኒ ረዲ አህመድ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ ለቡና ልማት የተመቸ 5.47 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ቢኖራትም እስካሁን የለማው 1.1 ሚሊዮን ሄክታር ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።
ለቡና ምርት ከደረሰው 725,961 ሄክታር መሬት በአማካይ ከ6.2 ኩንታል፣ ጠቅላላ ምርቱም 449.229.8 ቶን አልበለጠም ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በዓለም የቡና ኤክስፖርት ድርሻችን ከ3-4 በመቶ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ቡና የምናመርተው ለዓለም ገበያ ብቻ ሳይሆን ወደ 62 ቡና ሸማች ሀገራት በመላክ ሰፉ የገበያ ዕድል ቢኖረንም፣ እስካሁን ከምናመርተው ከ238 ሺህ ቶን በላይ ወደ ውጭ መላክ እንደተሳነንና የሚገኘው የውጭ ምንዛሬም 1 ቢሊዮን ዶላር መድረስ እንደተሳነው አስታውቀዋል፡፡
መንግስት፣ የቡናውን ዘርፍ በማዘመን፣ ምርትና የምርት ጥራት እንዲሻሻል፣ ህጋዊና ፍትሐዊ የግብይት ስርዓት ለመዘርጋት፣ እሴት የሚጨምሩ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ፣ የአምራቹና የተዋኒያኑ ገቢና የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የሚያስችል ሪፎርም እያደረገ ነው ያሉት አቶ ረዱ፣ የቡናና ሻይ ባለስልጣንም ዳግም እንዲደራጅና የቡና ግብይትና ቁጥጥር አዋጅና ማስፈጸሚያ ደንብ ባለድርሻ አካላት ፀድቆ ሥራ መጀመሩን ገልፀዋል ዋና ዳይሬክተሩ፡፡

Read 1865 times