Monday, 29 October 2018 00:00

አገር ያለ “ደህንነት” በጤና ውላ አታድርም!

Written by  ከገዙ በቀለ (ዶ/ር
Rate this item
(1 Vote)

     በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት፣ የደህንነቱ መሥሪያ ቤት “የፀጥታው”መሥሪያ ቤት በመባል በአጠቃላይና በጅምላ ይጠራ ነበር፤ የስውር ድርጅቶች  ከአንድ በላይ ነበሩና። በደርግ ዘመን  “የሀገርና የሕዝብ ደኅንነት” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። በኢህአዴግ ዘመን ደግሞ “የብሔራዊ መረጃና የደኅንነት አገልግሎት” ተባለ። የደኅንነቱን መሥሪያ ቤት በሁለት ዓብይ ዋና ዋና ከፍሎች ከፍሎ ማየት ይቻላል። አንደኛው የአገር ውስጥ የስለላ ከፍል ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ በውጭ አገር ላይ ያተኮረው የስለላ ከፍል ነው። የወታደር ደኅንነቱም በውስጥና በውጭ ተከፍሎ ሥራውን ያከናውናል። በእነዚህ ሁለት ዓብይ ከፍሎች ሥር ልዩ ልዩ የሥራ ዘርፎችና መምሪያዎች መኖራቸው ታሳቢ ተደርጓል።  በተለይ በደርግ ዘመን ሁሉንም  በአንድ ማዕከል፣ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ሥር ለማዋቀር የተደረገው ጥረት ስኬታማ ቢመስልም፣ በአሠራር ደረጃ ግን ውጤታማነቱ ሲፈተሽ እንከን አዘል ነበር። በኰሎኔል  ተስፋዬ ወ/ሥላሴ እና በኋላም በአቶ ጌታቸው አሰፋ የተመራው የመረጃና የደህንነቱ መ/ቤት ዋና ዋና መምርያዎችን በአንድ የዕዝ ሰንሰለት አዋቅሮ ነበር።
ሙያውንና ሙያተኞቹን በተመለከተ ሕዝባችን ጆሮ ጠቢዎች፣ ሰላዮች፣ የፀጥታ ሠራተኞች ይላቸዋል። ሙያው በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ ነው ወይ ብሎ  መጠየቁ  አሉታዊ ምላሽ ስለሚያስከትልብኝ፣ ለጊዜው ትቼዋለሁ፡፡ ሙያው ለአገራችን  ያስፈልግ ይሆን? ያለዚህ ሙያ፤ አገርና ሕዝብ በሰላም መኖር ይችሉ ይሆን? ከዚህ ሙያ ፋይዳ ማግኘት ይቻላልን? ለእነዚህ ጥያቄዎች ሙሉ ለሙሉ  መልስ መስጠት ባይቻለኝም፣ በጥቂቱም ቢሆን መልስ ለመስጠት ግን እሞክራለሁ።
ከሳምንታት ማመንታት በኋላ ጽሑፌን  በአጣዳፊ ለማቅረብ የገፋፋኝ፣ መስከረም 30 ቀን ሁለት መቶ ሃምሳ የሚጠጉ ወታደሮች፣ በጦር መሣሪያ በመታገዝ፣ ወደ ቤተ መንግሥት ዘው የማለታቸው ጉዳይ ነው። አድራጎታቸው ቅቡልነት የሌለው ሲሆን  ገቢራቸው ሲታይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነበር። ከዚህ አንጻር የደኅንነቱ መ/ቤት ኃላፊነትና ግዴታውን በቅጡ ተረድቶት ይሆን ያሰኛል፡፡ ይህም ሲባል ወታደራዊውንም ደኅንነት ይመለከታል።
ቀደም ሲል ይኼ ሙያ በሕዝባችን ዘንድ ታዋቂና ተወዳጅ እንዲሆን ካደረጉት መካከል ደራሲና ተርጓሚ ማሞ ውድነህ  ቀዳሚውን ቦታ ይወስዳሉ። ማሞ ውድነህ፤ በተለይ የሞሳድ የስለላ ውጤት የሆኑትን መጻሕፍት ወደ አማርኛ በመመለስ ለአንባቢ አድርሰዋል። በዚህ አኳያ አበጁ ሊባሉ ይገባል፤ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋልና። ጀምስ ቦንድ የተባለው ተከታታይ ፊልም፣ የዓለምን ሕዝብ የዲቴክቲቭና የስለላ ፍላጎት ቀስቅሶት እንደነበር ትዝ ይለኛል። እንዲህ ዓይነቱ ፊልም በእኛም  ሕዝብ ዘንድ፣ ባይበዛም እንኳ የራሱን አሻራ ትቶ ማለፉን መካድ  አይቻልም። አጋታ ክርስቲ የተባለችው ደራሲም  በዓለም ሕብረተሰብ ዘንድ ላቅ ያለ ድርሻ አላት፡፡ እንዳለመታደል ሆነና፣ በዚህ ሙያ አንቱ የተባሉ ሰዎች በአገራችን እንዳሉ ብገምትም፣ ገድላቸው ለድርሳናት ሊበቃ ቀርቶ፣ ስማቸው ከመቃብር በላይ መሆን አልቻለም፤ በህልፈተ ሕይወት የዘነጋናቸውን ሳንጨምር። ነገሩ ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም ይሆን እንዴ?
ወርቅነህ ገበየሁ የተባሉ የንጉሡ የፀጥታ መሥሪያ ቤት ሹም፣ ከለውጥ ፈላጊዎች ማለትም ከመንግሥቱና ከግርማሜ ንዋይ ጋር በ1953 መሰለፋቸው፤ በስለላ ዘርፍ የተሰማሩ ሁሉ ፀረ ሕዝብ አለመሆናቸውን አስመስክሯል። ስለሆነም ሙያውን ሰው ሁሉ በደፈናው እንዳይጠላው እገዛ አድርጓል 2 እላለሁ። በደርግ ዘመንም ፀረ አብዮተኛ  ናችሁ በመባል የተሰደዱ፣ በዐይነ ቁራኛ የታዩ፣የታሰሩ፣ የተገረፉ ብሎም የተገደሉ የዚህ ሙያ ባልደረቦች አሉ። ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታትም በጣት የሚቆጠሩ እንዳሉ ይታወቃል።                                                                                            
ይኼው ስውር መሥርያ ቤት፣ የስለላ ድርጅት፤ ኢንተለጀንስ ኮሚኒቲ ወይም ኤጀንሲ፤ የምስጢር ወይም  የስውር ኤጀንሲ አገልግሎት፤ ሴኩሪቲ፤ መረጃ መ/ቤት በሚሉ ልዩ ልዩ መጠሪያዎች ይታወቃል፡፡                                                                                  
 ባለሙያዎቹ፤ የመረጃ መኮንን ወይም ኢንተለጀንስ ኦፊሰር በመባል ይጠራሉ። በዚህ ሙያ ቀዳሚነት ያላቸው አገራት የመኖራቸውን ያህል፣ ታዳጊ አገሮችንም በዚህ ዘርፍ  ይደግፋሉ። ሻእቢያ፣ ህወሓት እና ሌሎች አማጽያን ኃይሎችም የየራሳቸው  የስለላ መረቦች እንደነበራቸው በሚገባ ይታወቃል። በዚህ አኳያ ሻእቢያና ህወሓት፤ በደርግ የደኅንነት ድርጅት ውስጥ የየራሳቸውን ወኪሎች አሰርገው፣ አስገብተው እንደነበር የትላንት እውነት ነው፤ ከደኅንነት ሠራተኞች  መካከል ተባባሪ እንደመለመሉም አይዘነጋም። በተለይ የሕዝብ ድጋፍ የሌለው መንግሥት፣ ለሰርጎ ገቦች መቼም ቢሆን የተጋለጠ ነው።
በኢኮኖሚ መስክ እንኳ ሙያው የሚያስገኘው ጥቅም በእድገት አኳያ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። የእንዱስትሪ ስለላ በመባል በሚታወቀው የስለላ ዘዴ በመጠቀም፣ አንዱ አገር ያገኘውን                                                                                                   አዲስ የቴክኖሎጂ ግኝት፣ ሌላው በስለላ በመታገዝ ከዘረፈ በኋላ  አቻና በላጭ ሆኖ ለመገኘት ይሞክራል። በዚህ ረገድ የበለጸጉ አገሮች የመረጃ መረባቸውን በሰፊው ዘርግተው ይጠቀሙበታል።ሰላዮቻቸውን በማሰረግ ጭምር መረጃ ለማግኘት ይጥራሉ። በውጭ ፖሊሲ ቀረጻ በኩል የስለላ ድርጅቱ የሚያቀርበው ትንታኔና ግምጋሜ፣ ለአንድ አገር የውጭ ፖሊሲ አውጪ ወገኖች፤ ፋይዳው ቀላል አይደለም። በወታደራዊ ረድፍም  ያለው ስለላ የተጧጧፈ ነው። የአንድ አገር ሠራዊት ብዛት፣ የብርጌዶች ቁጥር፣ የጦር መሣርያ ዓይነትና ብዛት ብሎም የውጊያ ሥልጠናና ብቃት በየጊዜው ገምግሞ ለየአገሩ መንግሥት ያሳውቃል፣ መደረገም ያለበትንም እርምጃ በጥናት አስደግፎ  ያቀርባል። ከቅርብ ጊዜያት በፊት አሜሪካና እስራኤል የሩሲያን ኤስ 300 ፀረ አውሮፕላን ምስጢር ለማወቅና  ብልጫ ያለውን የጦር አውሮፕላን ለማዘጋጀት ወደ ዩክሬን አቅንተው ነበር። ዩክሬን ቀደም ሲል ከሩሲያ ጋር በነበራት ወዳጅነት፣ የድሮ ኤስ 300 ሞዴል እንዳላት ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ኤስ 400 እና ኤስ 500 የሚባሉ ዘመናዊ ፀረ አውሮፕላን መሣርያ ሩሲያ እንዳላት ይታወቃል። ሩሲያን ከአሜሪካ ጎን በወታደራዊ የጦር መሣሪያ ተፎካካሪ  ያደረጋት የኬጂቢ የመረጃ አሰባሰብ ልቀት እንደሆነ  በወታደራዊ ኢንተለጀንስ ዘርፍ የተሰማሩ ሊቃውንት ይገልጻሉ። ኬጂቢ የአሜሪካና የኔቶ ኃይሎች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በመከታተል ጠቃሚ መረጃ ለመንግሥት ያቀብል ነበር። በሌላ በኩል ኬጂቢ በኮሚኒዝም ተቃዋሚዎች ላይ ያደረሰውን በደልና ጉዳት ቤቱ ይቁጠረው።
በዓለማችን ተፎካካሪና ተቀናቃኝ ከሚባሉት የስለላ ድርጅቶች መካከል የእስራኤሉ ሞሳድ እና ሺን ቤት፣ የእንግሊዙ ኤም አይ 5 እና 6፣ የአሜሪካው ሲአይኤ እና ኤፍቢአይ፣ የሩሲያው ኬጂቢ (አሁን ኤፍኤስቢ) ኤስኺአር በተለይም የሚሊተሪ ኢንተለጀንሱ ጂአርዩ፣ የግብጹ ኤስኤስአይኤስ፣ የቻይናው ኤምኤስኤስ፣ የካናዳ ሲኤስአይኤስ እና የጀርመኑ ቢኤንዲ በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው። በተለይ የውጭ የስለላ ድርጅቶቻቸው አመርቂ ውጤት በማስገኘት ደረጃ የአሜሪካው ሲአይኤ፣ የእስራኤሉ ሞሳድ እና የሩሲያው ኤስኺአር እና ጂአርዩ በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱ ናቸው። ዛሬ ዛሬ ደግሞ በሳይበር ሲስተም የሚካሄደው የኤሌትሮኒክ የመረጃ አሰባሰብ  ሙያውን ትንግርታዊና አስደማሚ  አድርጎታል። በስልክ ጠለፋ፣ በኢ-ሜል፣ በሞባይል፣ በሸንጎ የሚደረጉ የጽሑፍ ልውውጦችና 3 ንግግሮችን ማወቁና መቅረጹ ዓይነተኛ የስለላ መንገድ ሆኗል። በዚህ ረገድ የፓርላማ ውይይቶች፣ የባለሥልጣን ስብሰባዎች፣ ሞባይሎች ለዚህ የስለላ ተግባር ሰለባዎች ናቸው። በዚህ አኳያ የአሜሪካ፣ የቻይናና የሩሲያ የስለላ ድርጅቶች ተቀዳሚ ስፍራውን ይወስዳሉ። በማህበራዊ ድረ ገጾች የሚቀርቡት መረጃዎች ከማን እንደሆኑ  እንኳ ለማወቅ አስቸግሯል፤ የስለላ ድርጅቶችም ይህንኑ ዘዴ መጠቀም ጀምረዋልና።
እንደ አውሮጳ አቆጣጠር ከ1989  በፊት የምስራቅ ጀርመኑ ኤምኤፍኤስ ወይም እስታዚ በመባል የሚታወቀው የስለላ ድርጅት ገናና እና አስፈሪ የስለላ ድርጀት እንደነበር ይነገርለታል። የእስታዚ የውጭ የስለላ ክፍል ኤችኺአይ በሚል ምህጻረ ቃል ይታወቃል።  የምዕራብ ጀርመን ቻንስለር የነበሩቱን የዊልያም ብራንት ቢሮ ሳይቀር አሰርጎ በማስገባት መረጃ እንዳስወሰደ በይፋ ይታወቃል። ምንም እንኳን  የእስታዚ ድርጀት በምስራቁ ሕዝብ ላይ ያደረሰው ጥፋት በሰፊው ተወግዞ፣ የተኮነነ  ቢሆንም፣ በውጭ የተሰማሩትን ሰላዮች ግን የምዕራቡ ክፍል የስለላ ድርጀት ብዙዎችን መውሰዱ ይታመናል።
የብዙ አገር የስለላ ድርጅቶች መሪዎች በይፋ ቢታወቁም፣ አባሎቻቸው ግን በስውር ይንቀሳቀሳሉ።በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የሚሠማሩት በልዩ ልዩ ሽፋን ነው። በተለይ በውጭ አገር ቱሪስት፣ ጋዜጠኛ፣ ዲፕሎማት፣ ነጋዴ፣ ረዳት አማካሪ፣ የእርዳታ ሠራተኛ --- በሚል ሽፋን ሥራቸውን ያከናውናሉ። በዚህ ሙያ ዘላለማዊ ወዳጅና  ዘላለማዊ ጠላት የሚባል ነገር የለም፤ የቀድሞ ጠላት የዛሬ ወዳጅ ሊሆን ይችላል። የአሁን ወዳጅ፣ ለወደፊቱ ጠላት የመሆን ምክንያት ሊገጥመው ይችላል። ስለዚህም  ባይበዛም፣ ጥቂት ነገር  ዛሬ ስለ ወዳጅ ቃርሞ፤ በኮሮጆ ማኖር የተለመደ ነው። ድንገት የሚባል መኖር ስለሌለበት!!
ለአፍታ፣ ድርሳናትን ስንፈትሽ፤ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1300 የእስራኤል ሕዝብ መሪ ሙሴ፤ አሥራ ሁለት ሰላዮችን ወደ ተስፋይቷ የከንዓንን ምድር መላኩን እንረዳለን። መጽሐፍ ቅዱስ ሁኔታውን በዚህ መልክ ገልጾታል፣ “እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፥ ለእስራኤል ልጆች የምሰጣትን የከንዓንን ምድር ይሰልሉ ዘንድ ሰዎችን ላክ፤ ከአባቶች ነገድ ሁሉ እያንዳንዱ በመካከላቸው አለቃ የሆነ አንድ ሰው ትልካላችሁ። ሙሴም እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ ከፋራን ምድረ በዳ ላካቸው፤ እነርሱም ሁሉ የእስራኤል ልጆች አለቆች ነበሩ።” (ዘኁልቁ 13፥1-3)
ከአርባ ቀን የስለላ ቆይታ በኋላ አሥሩ ሰላዮች ከንዓን ለመውረስ እስራኤሎች የሚያደርጉት ጉዞ ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል ለሙሴ ነገሩት። ከሰላዮቹ መካከል ኢያሱና ካሌብ ይህን ሲሰሙ ግን ልብሳቸውን ቀደዱ።
“ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ፥ ዞረን የሰለልናት ምድር እጅግ መልካም ናት። እግዚአብሔርስ ከወደደን ወተትና ማር ወደምታፈሰው ወደዚች ምድር ያገባናል፣ እርስዋንም ይሰጠናል። ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ አታምፁ፤ እንደ እንጀራ ይሆኑልናልና የምድሪቱንም ሰዎች አትፍሩ፤ ጥላቸው ከላያቸው ተገፍፎአልና፥ እግዚአብሔርም ከእኛ ጋር ነው።” ዘኁ. 14፥7-9 4 ከሞላ ጎደለ ተመሳሳይ የሆነ ትረካ በቁራንም አለ ይባላል።  ካሌብና ኢያሱ የተባሉት ግን በእግዚአብሔር ላይ ታምነው፣ የተስፋይቷን ምድር መውረስ የሚችሉ  መሆናቸውን ተናገሩ። ሙሴን የተካው ኢያሱም ሁለት ሰላዮችን በስውር  ልኮ ኢያርኮን አሰለለ። ረዓብ የተባለች የኢያሪኮ ሴት ከእነዚህ ሰላዮች ጋር ተባብራ፤ በቂ መረጃ እንዲሰበስቡ አስደረገች። በወቅቱ የኢያሪኮ ንጉሥ ሰላዮች አገሩ መግባታቸውንና በስለላ ላይ እንዳሉ መረጃ ደርሶት ነበር። ረዓብ  ግን እግዚአብሔር በሰጣት ብልሃት ሰላዮቹን እንዳስመለጠቻቸው በመጽሐፈ ኢያሱ ምዕራፍ ሁለት ተጠቅሷል።
እውቅ የሆኑት ሞሳድ እና ሺን ቤት ዛሬም የሚመሩት ከብሉይ ኪዳን ወይም ከታናኽ በተወሰዱ ጥቅሶች ናቸው። ለአብነት መዝሙር 121፣ ምሳሌ 11፥14፤ 24፥6 መጥቀስ ይቻላል።
ሰላይ የሚለውን ቃል ለመጀመርያ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ የምናየው፤ በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ አርባ ሁለት ነው። ቃሉንም የተናገረው ዮሴፍ የተባለው ከአሥራ ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች አንዱ ነው።ግብጾችም በፈሮዖን ዘመን በመረጃ አሰባሰብ በኩል ሰፊ እውቀት እንደነበራቸው ከ“አምራና ደብዳቤዎች” መረዳት ይቻላል። ስለ ትሮይ ጦርነት ያነበበ ሁሉ የግሪክና የዙርያው ገዥዎች በስለላ በኩል ቅድመ እውቅት እንደነበራቸው መገንዘብ ይቻላል። ሐኒባል የተባለው የሰሜን አፍሪካ  የጦር ሰው የመረጃ አስፈላጊነቱን በመረዳቱና ጥቅም ላይ በማዋሉ፣ የሮም መንግሥትን በተደጋጋሚ አሸንፎታል፤ አደጋ ላይም ጥሎት ነበር።
በቻይናና በሕንድ የኢንተለጀንስ ሙያ የቆየ መሆኑን “የጦርነት ዘዴ” እና “አርታሀስትራ”  የሚባሉት መዛግብት ፍንትው አድርገው ይነግሩናል። በተለይም “የጦርነት ዘዴ” የተባለው ሰነድ ወኪሎችን ማሰማራት ለጦርነት ድል  ማግኘት ፍቱን ዘዴ መሆኑን ያበስራል። “ጠላትህንና እራስህን እወቅ፤ በመቶ በሚቆጠሩ ጦርነቶች ላይ ተሸናፊ አትሆንም” የሚለው ቁልፍ ቃል፤ በዘመኑ የስለላ ሙያ መጎልበቱን ያሳያል። ይሁን እንጂ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ዊንስተን ቸርችል ፥”ጥሩ ኢንተለጀንስ የጠላትን ድንገተኛ ጥቃት ይቀንስ እንደሆነ እንጂ፣ ጠላትን ለማሸነፍ ዋስትና አይሆንም” ብለዋል። ምክንያቱም ለማሸነፍም ሆነ ለመሸነፍ ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች አሉ።
የኢንተለጀንስ ሙያ በአገራችን፣ ይህ ሙያ በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን፣ ዘመናዊ አሠራርን ተከትሎ የተጀመረ ቢሆንም፣ ከዚያ ቀደም ሲልም ይስራበት እንደነበር ልዩ ልዩ ድርሳናት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ይነግሩናል። ሙያው ከጣልያን ጋር ለነበረን ጦርነቶች ያበረከተው አስተዋጽኦ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። ከሶማሌና ከሱዳን ጋር ለነበሩን ችግሮች የደኅንነቱ መሥሪያ ቤት የፈጸመው ታሪካዊ ድርሻ ከቶውንም ለመካድ የሚቻል አይመስለኝም። ሙያውን በጥልቀት የሚያውቁት አምባሳደር ዘመነ ካሳዬ እና አምባሳደር ሞገስ ሀብተ ማርያም ሳይዘገይ ብዕራቸውን ከፍ ቢያደርጉ ደስታዬ እጥፍ ድርብ ይሆናል። በአገር ውስጥ በደረሰው በደልና ጭቆና የተነሳ በደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ መኖሩን ከቶም አልዘነጋም። ዲሞክራሲ በሌለበት አገር ውስጥ፣ ልክ እንደ ሌሎቹ የፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች፤የስለላ ድርጅቱም አምባገነን መሪዎችን ከሚገባው በላይ  ማገዙ፣ መርዳቱና መሣሪያ መሆኑን ለአፍታም አይዘነጋኝም። በዚህ ጉዳይም ላይ አንድ ሁለት ብዬ ነቅሼ መሞገት አልችልም። እውነት ከእኔ ጎን አትቆምምና! ይኼ ማለት ግን የደኅንነቱ ሙያተኞች ሁሉ ዘወትር የሚያቀርቡት ሪፖርት ፀረ-ሕዝብ ነው ብሎ መደምድሙ ደግሞ ስለ ሙያው በቂ እውቀት ያለ መኖሩን ያሳያል። ደኅንነቱ ሥራውን 5 በተገቢ መልክ እንዲወጣ ለማድረግ ከተፈለገ አገሪቷ በዲሞክራሲ የዳበረች  ልትሆን ይገባል። ያኔ ነው ደኅንነቱ በሕግና በደንብ የሚተዳደረው። ይኼ ከሆነ፣ የደኅንነቱ መሥርያ ቤት፣ የሕዝቡን ደኅንነት ይጠብቃል፣ ሕገ መግሥቱን ያስከብራል፤ የአገሪቷን ልዑላነት በማስጠበቅ ረገድ የሙያ ግዴታውን ይወጣል። በእንዱስትሪና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ይከታተላል፤ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸውን መሪዎች ይጠብቃል። የሽብርተኞችን ሴራ በተመለከተ ለመንግሥት በፍጥነት ሪፖርት ያቀርባል። በአገር ውስጥ የሚደረግ የጠላት የመረጃ አሰባሰብን እንቅስቃሴ ይከታተላል፤ ለመንግሥት መረጃ ያቀርባል፤ ያስመክናል። ከላይ በገለጽኳቸው ምክንያቶች ደኅንነቱ ለዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ያለ ጥርጥር አስፈላጊ ነው።
የኢንተለጀንስ  ሙያተኞች የማንኛውም ፓርቲ አባል ሳይሆኑ ሥራቸውን ማከናወን አለባቸው። ለዚህ ሙያ የሚታጩት ሁሉ እንደ ሙያው አስፈላጊነት የላቀ እውቀትና ብቃት ያላቸው ሊሆኑ ይገባል።በዘመድ አዝማድ፣ በብሔር ኮታ፣ እንዲሁም ሌላ ሥራ ከማጣት የተነሳ ወደዚህ ሙያ የሚቀላቀሉ ከሆነ ሙያው የበለጠ ይናቃል፤ ይዋረዳል፡፡ የዘራፊዎችና የቀማኞች ዋሻ ሊሆንም አይገባውም። ኢንተለጀንስ ሙያው ካደገ፣ አገር  የምትለማበትን ዘዴ ይፈልጋል፤ ሰላም የሚጠበቅበትን መንገድ ይቀይሳል፡፡ ለግጭቶች መፍትሔዎችን  ይጠቁማል የሚል ግምት አለኝ።
 በቸር ይግጠመን!!




Read 5286 times