Saturday, 27 October 2018 10:09

ግማሽ ልጩ፣ ግማሽ ጎፈሬ

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ! 
እኔ የምለው... እንደ ሰሞኑ አይነት ከበድ ያለ ነፋስ ምኑን ምናምኑን ሲያንኳኳው “የሆነ ግንድ ሊወድቅ ነው…” ምናምን እንል ነበር፡፡ ዘንድሮ ነፋስ ሳያስፈልግም ብዙ ነገር እያየን ነው፡፡ የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እዚች ከተማ ውስጥ እያየነው ያለው የእለት ከእለት የስርአት ጉድለት “መድረሻችን የት ይሆን?” የሚያሰኙ ሆነዋል፡፡ ከቁጥራችን መብዛት ጋር ለስርአትና ለማህበራዊ ህጎች ያለን እውቀት አናሳነት ወይም ንቀትና “ማን ምን ያመጣል!” አይነት ነገሮች ለከተማዋ ነዋሪዎች አስቸጋሪ እንቅፋቶች እየሆኑ ነው፡፡
እናማ…ህግና ስርአት አክብረው ለመንቀሳቀስ ወይም መብታቸውን ለማስከበር የሚሞክሩ ሰዎች የሚጨበጨብላቸው አልሆኑም፡፡ ሚኒባሰ ታክሲ ውስጥ ተቀምጣችኋል፡፡ ተሳፋሪው በወንበር ልክ ገብቶ ታክሲዋ ሞልታለች፡፡ ከዛም ረዳቱ ለሁለት ሰው በተዘጋጀው ወንበር ላይ ሦስተኛ ‘በትርፍነት የሚያዝ’ ተሳፋሪ ለመጨመር…
“ጋሼ እዚች’ጋ ጠጋ በሉ…”
ተሳፋሪው ነቅነቅ አይልም፡፡ ለምን ብሎ! አራት ብር ከሀምሳ የከፈለበት ወንበር ነው፡፡ እስኪወርድ ድረስም ወንበሩ ላይ የመወሰን መብቱ የእሱ ነው። ረዳቱ አልፎ፣ አልፎ እንደምናያቸው ‘ጉርምስናው የፈላበት’ አይነት ከሆነ…
“የራሱ ታክሲ መሰለው እንዴ!” ምናምን አይነት ነገር ይወረውራል፡፡ ጸያፍ ቃላትም ሊወረውር ይችላል፡፡ (ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ… ‘በትርፍነት የሚያዘው’ ተሳፋሪ “ጠጋ በል!” በሚል አይነት በመቀመጫው ትከሻችሁን መግፋት ጀምሮ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሄኔ እኮ እሱም “በትርፍነት መጫን መብቴ ነው!” ብሎ ያስብ ይሆናል!) እናንተ ተጨማሪ የስድብ ናዳ እንዳይወርድባችሁ ዝም ትላላችሁ፡፡ ይሄኔ ማን ጣልቃ ቢገባ ጥሩ ነው… ሌላ ተሳፋሪ፡፡ ወደ ዜሮ ማርሽ ሊወርድ የነበረውን ነገር፣ በአንድ ጊዜ ወደ አምስተኛ  ማርሽ ያስፈነጥረዋል፡፡
“ምናለበት ጠጋ ብትልለት?” ይላል፡፡
የዘላለም ችግራችን….በሌላው ምጣድ ላይ የራሳችንን እንጀራ መጋገር! ምን አገባው! ረዳቱ ራሱ እንኳን አራት ዓረፍተ ነገር ወርውሮ አምስተኛው ላይ ነገሩን ትቶታል፡፡ እና ይህኛው ተሳፋሪ የምን ‘ሳይጠሩት አቤት፣ ሳይልኩት ወዴት’ ነው! ከዛ ረዳቱ ለራሱም ‘ረዳት’ ስላገኘ ያገረሽበታል፡፡ እናላችሁ… እዛ ስፍራ ላይ የደግነትና የክፋት ጉዳይ ሳይሆን ህግና ስርአት የማክበርና ያለማክበር ጉዳይ ነው፡፡
የ‘ከተሜነት’ ነገሩንማ ተዉት! ‘ከተሜነት’ ማለት የሚብልጨለጩ ሞሎችና ሚጢጢ ጨርቅ ሰውነታቸው ላይ ‘ጣል’ ያደረጉ ‘ሚጢጢ’ እንትናዬዎች መብዛት የሚመስለን በዝተናል፡፡ (ህጻናቱ ሁሉ ‘ከተሜ’ ለመሆን ጨርቃቸውን ሁሉ ጥለው፣ ጥለው…አለ አይደል… ወጣትነትን በአቋራጭ አልፈው እድሜ አንዱ መለኪያ ያልሆነበት ‘አቅመ ሄዋንነት’ ላይ እየደረሱ ነው፡፡)  ‘ከተሜነት’ ማለት “መደበኛ ምናምን መቶ ብር፣  ቪአይፒ ምናምን ሺህ ብር” ብር የሚባልላቸው ኮንሰርቶች የሚመስለን የበዛን ነው የሚመስለው፡፡
የሚጠጣ ውሀ ሲጠየቁ የጄኔራል አልቤርቶኒ አገልጋይ ረስቷት የሄደች በምትመስል ብርጭቆ ይዞላችሁ ብቅ ሲል የምር ቀሺም ነው፡፡
በነገራችን ላይ ዘንድሮ ተገረሙ ሲለን የማይገጥመን ነገር የለም፡፡
“የእኔ እመቤት ውሃ ትሰጪኛለሽ?”
“ባለ አንድ ሊትሩን ነው?”
“አይ፣ በብርጭቆ ብትሰጪኝ…”
“በብርጭቆ ውሀ አይሰጥም፡፡”
“ለምን?”
“ባለቤቶቹ ከልክለዋል፡፡”
ይህ አንድ ከተማችን ‘አሪፍ’ የሚባል ካፌ ውስጥ የሆነ ነው፡፡ ‘አሪፍ ካፌ’ ማለት የማኪያቶው ዋጋ የሀያ ምናምን ብር በርን የሚያንኳኳበት ካፌ ማለት ነው። እናላችሁ… ተራዋና ‘ሚጢጢዋ’ ፓስቲ ቤት እንኳን፣ አይደለም ተገልጋይ ሆናችሁ ጠምቷችሁ እግረ መንገዳችሁን  ጎራ ብትሉ እንደልባችሁ የምታገኙትን ‘የእግዜር ውሀ’… አለ አይደል… ‘ዘመናዊው’ ካፌ ይከለክሏችኋል፡፡ ስለዚህ ጉሮሮ ለማራስ አንድ ብርጭቆም፣ አንድ ስኒም ውሀ የፈለገ ሰው የግዱን ሊትሩን ምናምን መግዛት ሊኖርበት ነው፡፡ እኔ የምለው… ይሄ እኮ የንግድ ስትራቴጂ ሳይሆን  እጅ እንደ መጠምዘዝ ነው፡፡ (ስንቱ ‘እጃችንን እየጠመዘዘን’ እንደምንዘልቀው አንድዬ ይወቀው፡፡)
ህብረት ሱቅ ይባል በነበረው ኮታውን እህል፣ ስኳር ምናምን ሲገዛ የማይፈልጋቸውን ነገሮች አብሮ እንዲወስድ ይገደድ ነበር፡፡ ብቻ እዚች አንዳንዶች ከሰዶምና ገሞራ ጋር እያመሳሰሏት ባለች ከተማችን ውስጥ የምናያቸውና የምንሰማቸው ለከተሜነትና ‘ስልጡንነት’ ባይተዋር የሆኑ ነገሮች በዝተውበናል፡፡
እግረ መንገድ…“እንኳን ደህና መጣችሁ…”
“መልካም ምግብ ይሁንላችሁ…”
“ምን የጎደለ ነገር አለ?” የሚሉ ሲገጥሙን ደንገጥ የምንለው ወደን አይደለም፡፡ እንደ ላስቬጋስ ቁማር ቤቶች ተብለጭልጨው የምናያቸው አገልግሎት መስጫ ሁሉ መስተንግዶአቸው እንደዛው ነው ማለት ስላልሆነ ነው፡፡
ስሙኛማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው፡፡ ሰዎቹ በቤት እቃ ጉዳይ የሆነ ክርክር ቢጤ ገጥመው ነው፡፡ አንደኛው “ሰዉ ፈረንጅ ሶፋና ምንጣፍ  ላይ ገንዘቡን ከሚያባክን ለምን ቤቱን በባህላዊ እቃዎች አይሞላም!”  እያለ የቀሺም ፖለቲከኛ (እጥረት የሌለብን ‘ምርት’ ቂ…ቂ…ቂ…) አይነት ዲስኩር ይሰጣል፡፡ ነገርዬው ሲሰሙት “እውነቱን ነው…” ምናምን የሚያሰኝ ነው፡፡ ችግሩ ምን መሰላችሁ… የእሱ ቤት የተሞላው እነኚህ በቴሌቪዥን ማስታወቂያ ላይ ‘እንቁልልጭ’ በሚሉን አይነት እቃዎች ነው!  (ቤቱ ውስጥ የአገር ውስጥ ምርት ቢኖር እኮ እሱ፣ ራሱ ብቻ ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…)         
እናላችሁ… የቆዳ ጫማቸውን ግጥም አድርገው ስለ እንስሳት መብት ‘የሚከራከሩ’ አይነት ሰዎች አይገርሟችሁም! አሀ…ጫማውስ! በሬው እኮ “ከፍላጎቴ ውጭ ቆዳዬን ገፈውኝ የሠሩት ጫማ ነው” ብሎ ምስክርነት መሥጠት አያስፈልገውም፡፡ ደግሞላችሁ…ይሄን ያህል የእንስሳት መብት ተቆርቋሪ ከሆኑ ለምን ‘ቬጂቴርያን ጫማ’ ምናምን አይፈጥሩም! (ቂ…ቂ…ቂ…) ልክ እኮ እኛ ዘንድ መስታወት የመሰለ የስፔይን ጫማውን ግጥም አድርጎ የሆነ መድረክ ላይ…“ህብረተሰቡ አገር ውስጥ የሚመረቱ ጫማዎችን እስካልገዛ ድረስ የጫማ ኢንዱስትሪው ማደግ አይችልም!” እንደሚለው የካሜራ ፊት ‘ፓትሪየት’ አይነት ነው፡፡
ዳኛው ተከሳሹን እድሜውን ይጠይቁታል፡፡ መልስ አይሠጣቸውም፡፡ ይናደዱና…
“አንተ ለምንድነው እድሜህን ስትጠየቅ መልስ የማትሰጠው?” ይሉታል
“እኔ እድሜዬን ለመናገር ፈቃደኛ አይደለሁም፡፡”
“ይሄ እኮ ፍርድ ቤት ነው፡፡ ለምንድነው የማትናገረው?”
ይሄኔ ተከሳሹ ምን ቢል ጥሩ ነው…
“እርሶ ግን  የእኔ እድሜ ይህን ያህል የሚያስጨንቀዎት ለምንድነው! የልደት ስጦታ አያመጡልኝ!” አለና አረፈው፡፡
“አንቺ…ይሄ ጥልፍ ሹራብሽ ደስ ሲል! የእጅ ሥራ ነው፣ አይደል!”
«ምን!... ሰውየው ጤና የለውም እንዴ…ከአሜሪካ በስንት መከራ የመጣውን ‘ባለ ፈር’ ሹራብ የእጅ ሥራ ይላል እንዴ!”
“ስማ ያቺ አዲሷ ገርልህ እንዴት ነች?”
“ተዋት እባክሀ እሷን፡፡”
“ምነው፣ ያቺን የመሰለች ልጅ ተውኳት እንዳትል!”
“የሆነች ኮንሰርቫቲቭ ቢጤ ነች፡፡ ለኪሶሎጂ እንኳን ስንት ስቴፕ አለው መሰለህ!”
“አንተ ሰውዬ ገና ሳምንት እንኳን መች ሞላችሁ! ትከሻ ከማጋጨት አልፈህ ከንፈር ላይ ምን አዘለልህ!”
“እና እዛ ለመድረስ ፕሮጀክት ፕሮፖዛል መጻፍ አለብኝ!”
ኸረ ምን በወጣህ!  ያውም በዚህ የፍጥነት ዘመን! የምር ግን ብዙ እንደ ሰልጣኔ እየታዩ ያሉ ነገሮች ትውልድ ላይ የሚኖራቸው ተጽእኖ ቀላል አይሆንም። እያየናቸው ያሉ ነገሮች የሚመሰክሩት ይህንኑ ነው፡፡ መጠጥ ፋብሪካው ሁሉ “ከአስራ ስምንት ዓመት በታች የተከለከለ” በሚልበት ዘመን የአስራ ሁለትና አስራ ሶስት ዓመት ልጆች በጠራራ ፀሀይ ጥምብዝ ብለው ሰክረው የምናይባት ከተማ ነች፡፡ ከተለመዱት ርእሶች ባለፈ ከስርአት ማክበርና ማስከበር፣ ከህግ የበላይነት፣ ከትውልድ ቀረጻና ከመሳሰሉት ጋር የተያያዙ ብዙ፣ እጅግ ብዙ ችግሮች የተሸከመች ከተማ ነች፡፡ መሪዎቿም ይህንን የሚገነዘቡ መሆን አለባቸው…ነገሮች ግማሽ ልጩ፣ ግማሽ ጎፈሬ እንዳይሆኑ ብለን ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኛማ!

Read 5504 times