Saturday, 27 October 2018 09:59

የሰላም- ዘውዷ- ሣህለ ወርቅ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(13 votes)

“ሰላምና ኢትዮጵያ አንድና ያው እስኪኾኑ መሥራት ይገባናል”

ከትናንት በስቲያ ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው በለቀቁት የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ምትክ አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ የመጀመሪያዋ የአገሪቱ ሴት ርዕሰ ብሔር ሆነው ተሾመዋል፡፡ ይሄ ደግሞ ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋን ሴት ፕሬዚዳንት በመሾም በምስራቅ አፍሪካ ፈር ቀዳጅ ያደርጋታል፡፡  
በአዲስ አበባ ከተማ ተወልደው ያደጉት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሊሴ ገብረማሪያም የተከታተሉ ሲሆን፤ በ17 ዓመት ዕድሜያቸው ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝተው ወደ ፈረንሳይ በማቅናት፣ በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሞንቸፔለየር፣ በተፈጥሮ ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡
በአገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በአምባሳደርነት ከተሾሙት ዮዲት እምሩ ቀጥሎ የአምባሳደርነት ሹመት ያገኙት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመደቡትም በሴኔጋል ሲሆን፤ የአምባሳደርነት ስልጣናቸው ማሊን፣ ኬፕቨርዲን፣ ጊኒቢሳዎን፣ ጋምቢያንና ጊኒን የሚያቃጠልል ነበር፡፡ ከዚያም በጅቡቲ፣ ቱኒዚያ፣ ሞሮኮና ፈንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከአምባሳደርነታቸው በተጨማሪም በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ፣ በዩኔስኮ የኢትዮጵያ ተወካይ፣ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና በአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ተወካይ፣ በውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር፣ በተባበሩት መንግስታት ስር የነበረው የተቀናጀ የሰላም አስከባሪ ኃይል ተወካይ ሆነውም አገልግለዋል፡፡ እ.ኤ.አ ከ2011 ጀምሮ ደግሞ ኬኒያ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በረዳት ዋና ፀሐፊ ማዕረግ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሰርተዋል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ህብረት ልዩ መልዕክተኛም ነበሩ፡፡
አዲሷ ፕሬዚዳንት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ በበዓለ ሲመታቸው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “ስልጣንን በቃኝ በማለት ለተተኪ ማስረከብ በአገራችን እየተለመደ የመጣ ባህል መሆኑ ይበል የሚያሰኝ ነው፤ ዶ/ር ሙላቱ፤ ከስልጣን በፊትም ሆነ ከስልጣን በኋላ ህይወት እንደሚቀጥል አሳይቷል፤ ሌሎችም የእሱን ፈለግ እንዲከተሉና ለለውጥ ዝግጁ እንዲሆኑ እጠይቃለሁ” ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በአገሪቱ እየታየ ያለው ለውጥ እጅግ ተስፋ ሰጪ መሆኑን የገለፁት አዲሷ ፕሬዚዳንት፤ “በአገራችን ታሪክ ባልታየና ባልተለመደ መልኩ ከካቢኔ አባላት መካከል 50 በመቶ ያህሉን ሴቶች እንዲይዙት ከማድረግም ባሻገር የአገሪቱን የርዕሰ ብሔርነት ስልጣን ለሴት በመስጠት ያከበሩንን ጠ/ሚኒስትር እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ” ብለዋል፡፡
ከሃያ ዓመታት በላይ በተለያዩ አለም አቀፋዊ ድርጀቶች የኢትዮጵያ አምባሳደርና ተጠሪ ሆነው ያገለገሉት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድን) የተቀላቀሉት እ.ኤ.አ በ2009 ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 በወቅቱ የተመድ ጠቅላይ ፀሐፊ በነበሩት ባንኪሙን ተመርጠው፣ ድርጅቱ በናይሮቢ ላቋቋመው አዲስ ጽ/ቤት የመጀመሪያዋ ሴት ኃላፊ ሆነው በመሾም፣ ለሰባት ዓመታት አገልግለዋል፡፡
ባለትዳርና የሁለት ወንድ ልጆች እናት የሆኑት አዲሷ ፕሬዚዳንት፤ በስልጣን ዘመናቸው በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍንና ዜጎች በእኩልነትና ያለ አድልዎ የሚኖሩባትን አገር ለመገንባት በሚደረገው ርብርብ የበኩላቸውን ድርሻ ለማበርከት ዝግጁነታቸውን ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ዛሬ በእጅጉ የናፈቃቸው ሰላም መሆኑን በቅጡ የተረዱት አምባሳደሯ፤ ስለ ሰላም ተናግረዋል፡፡ በአገሪቱ ከዳር እስከ ዳር ሰላም ይሰፍን ዘንድም በብርቱ ተመኝተዋል። ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባለፈው ሳምንት 50 በመቶ ካቢኔያቸውን በሴቶች ያዋቀሩበትን ምክንያት ሲያስረዱ፤ ሴቶች ሰላም በማስፈን ረገድ ያላቸውን ተፈጥሮአዊ ብቃትና አቅም ጠቅሰዋል። የመከላከያ ሚኒስትሯ እንዲሁም፣ የሰላም ሚኒስትሯ አሁን ደግሞ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሴቶች መሆናቸውም ከዚህ ዓላማ ጋር ይገናኛል፡፡ የዶ/ር ዐቢይ እምነትና ምኞት ከሰመረ፣ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ለዓመታት የናፈቁትን ሰላምና መረጋጋት ይቀዳጃሉ፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያዋ ርዕሰ ብሄር የነበሩት ንግስት ዘውዲቱ ስልጣን የያዙት መስከረም 18 ቀን 1908 ዓ.ም እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ታሪክ ግን አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ የአገሪቱ የመጀመሪያዋ ሴት ርዕሰ ብሔር ሆነዋል፡፡ በኢትዮጵያም በምስራቅ አፍሪካም ሴት ፕሬዚዳንት በመሾም ፈርቀዳጅ ለመሆን በቅታለች፡፡


Read 8408 times